Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርመፍትሔ ለአዲስ አበባ ትራንስፖርት ችግሮች

መፍትሔ ለአዲስ አበባ ትራንስፖርት ችግሮች

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ችግር በተደጋጋሚ የተነሳና ተጨባጭ መፍትሔ ያልተገኘለት በሽታ መሆኑ ቀጥሏል፡፡ ነገር ግን በመንግሥት በኩል ባሁኑ ወቅት በመፋጠን ላይ ያለው የቀላል ባቡር መንገድ ሥራ መጀመር ከፍተኛ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የሚታየውን የትራንስፖርት ችግር ጥልቀት በአኃዝ አስደግፎ በአገር ኢኮኖሚና ዕድገት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት የመግለጽ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፣ ችግሩ ለማናችንም ግልጽ ከሆነ ሰንብቷል፡፡ ከሰሞኑ ያነበብኩት አንድ መጽሔት በሰጠው አኃዛዊ ትንታኔ የችግሩን ጥልቀትና ስፋት ይበልጥ አሳይቷል፡፡ መጽሔቱ እንዳስቀመጠው ከሆነ፣ አንድ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ በአማካይ በቀን ሁለት ሰዓታትን ያለአግባብ በመንገድ ላይ ትራንስፖርት በመጠበቅ ያባክናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ባለሥልጣን መረጃ መሠረት እ.ኤ.አ በ2008፣ 4.678 ሚሊዮን መንገደኞች በየቀኑ እንደሚጓጓዙ፣ ከእነዚህ ውስጥም 38.2 በመቶው በግል ሥራ የሚተዳደሩ ተጓዦች ናቸው፡፡ በመሆኑም የትኛው የኅብረተሰብ ክፍል ቅድሚያና ማግኘት እንደሚያሻውና ትኩረት እንደሚፈልግ ለመገመት ይቻላል፡፡ በዓለም ባንክ ሪፖርት መሠረት እ.ኤ.አ. 2014 ይኖራል ተብሎ የተገመተውን 9,400 ብር የነፍሰ ወከፍ ገቢን መሠረት በማድረግና ከላይ ከተጠቀሱ ቁጥሮች ጋር በማጣመር ቢሰላ፣ በአንድ ቀን ውስጥ በአዲስ አበባ መንገዶች ላይ በአማካይ 37,424,000 ብር፣ በዓመት 9.7 ቢሊዮን ብር እንደሚባክን፤ ከዚህም ውስጥ ከሥራ ግብር መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ከፍተኛ ገንዘብ እንደሚያጣ ያመላክታል፡፡

ከላይ የተመለከተውን ሐሳብ ስለጉዳዩ ለአንባቢያን መሠረታዊ መረጃ ለመስጠት ቀለል አድርጌ ላስቀምጥ እንጂ፣ የዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ ዓላማ ከትራንስፖርት ችግር ጋር በተያያዘ በአገር ሀብት ላይ እየደረሰ ያለውን ብክነት ለማስቀረት ወይም ለመቀነስ የሚያስችሉ ሐሳቦችን ለመጠቆም ነው፡፡ በመንግሥት በኩል ተጨማሪ የትራንስፖርት አማራጮች መቅረብ አለባቸው ተብሎ በተደጋጋሚ የሚጠቀሰው ጉዳይ ተገቢነቱ ባያጠያይቅም፣ ምን ዓይነት አማራጮች አሉን? የትኛው የመንግሥት አካል የመፍትሔ ዕርምጃውን መውሰድ ይጠበቅበታል? እንዴትና በምን መንገድ ዕርምጃውን መውሰድ ይቻላል? የሚሉ ጥያቄዎችን ጠለቅ ብሎ መመልከት ተገቢ ስለሆነ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ የመፍትሔ አስተያየት ለመስጠት ጭምር ነው፡፡

- Advertisement -

የጊዜ ብክነት የሚያስከትለው ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳት የሚያያዘው ከትራንስፖርት ስምሪትና ሥርጭት ወይም ከትራንስፖርት አስተዳደር ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከኤሌክትሪክ ኃይል መጥፋት ወይም መቆራረጥ፣ ከኔትወርክ መቆራረጥ፣ ከውኃ አቅርቦት መቋረጥና ከመሳሰሉት ጋር በተያያዘ ስለሚደርሰው ብክነትም ጥናት በማድረግ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥበትን መንገድ መጠቆም ተገቢ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ በዚህ ረገድ በተለያዩ አካላት እየተደረጉ ያሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎች ምሥጋና እንደሚገባቸውም ማውሳት እፈልጋለሁ፡፡

ወደተነሳሁበት ጉዳይ ልመለስ፡፡ የተለያዩ አካላት የተለያዩ የመፍትሔ ዕርምጃዎችን መንግሥት መውሰድ እንዳለበት ሲጠቁሙ ከሚደመጡት ውስጥ ሌሎች የትራንስፖርት አማራጮችን ሥራ ላይ ማዋል የሚለው ተደጋግሞ ይነሳል፡፡ ነገር ግን ሌሎቹ የትራንስፖርት አማራጮች የትኞቹ ናቸው? ለየትኛው የኅብረተሰብ ክፍል ትኩረት ሊሰጠው ይችላል? የትኛው የመንግሥት ተቋም ኃላፊነቱን ሊወስድ ይገባል? እንዴት መተግበር ይቻላል? የሚሉና ሌሎች ጥያቄዎችን መመለሱ ለመንግሥትም ሆነ ለኅብረተሰቡ መልካም ይሆናል ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለሆነም ከላይ የተጠቀሱ መረጃዎችን ተጠቅሜ ከላይ ያነሳኋቸውን መሠረታዊ ጥያቄዎች ቀጥሎ ባለው መልክ ለመመለስ ወደድኩት፡፡

ለየትኛው የኅብረተሰብ ክፍል ቅድሚያና ትኩረት ይሰጥ?

ይኼንን በተመለከተ ራሱን የቻለ ሳይንሳዊ ጥናት ማድረግ አስፈላጊነቱ የሚታመን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከአጠቃላይ ነባራዊ ሁኔታዎች ተነስተን ለማየት እንደምንችለው ከሆነ፣ አስገዳጅ የመንገድ ላይ ጉዞ የሚያደርገው የመንግሥት ሠራተኛውና በግሉ ዘርፍ የተሠማራው ኅብረተሰብ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡ ከሰሞኑ ባነበብኩት መጽሔትም ይኼው እውነታ ተነስቷል፡፡ በግሉ ዘርፍ ከተሰማሩትም የንግዱ ማኅበረሰብ ቁጥር የመጀመርያውን ድርሻ እንደሚይዝ መገመትም ይቻላል፡፡

በእርግጥ የንግዱ ማኅበረሰብ  ወደ አገልግሎት ሰጪ የመንግሥት ተቋማት ብቻ ሳይሆን፣ ሸቀጦችን ለደንበኞቻቸው ለማድረስና ወደ ገበያ ለማመላለስ ወይም ተያያዥ ለሆኑ ጉዳዮች እንቅስቃሴ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ እንደዚህ ያለው እንቅስቃሴ በባህሪው ውሱን ጊዜና ፈጣን እንቅስቃሴን የሚጠይቅ እንደመሆኑ ትልቁን የጊዜ ድርሻ ይወስዳል ተብሎ ላይሰብ ይችላል፡፡ ይልቁንም በየሩብ ዓመት ውስጥ ጥናት ቢደረግ፣ እጅግ የሚበዛው የንግዱ ማኅበረሰብ እንቅስቃሴ እንደሚያደርግ ሊረጋገጥ ይችል ይሆናል፡፡ በተጨማሪም ሰፊውን ጊዜ ወደ መንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንደሚመላለሱም ማየት ይቻላል፡፡

የተጠቀሱት ሁለት ነጥቦች ማለትም ግምት የሚወሰደው በየሩብ ዓመት ማጠቃለያ ቢሆንና የንግዱ ማኅበረሰብ አብዛኛውን ጊዜ ወደ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመመላለስ በተነፃፃሪ ረጅሙን ጊዜ ያጠፋል የሚሉትን መነሻዎች ታሳቢ በማድረግ፣ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ላይ በቀን ከሚመላለሱት ተጓዦች ውስጥ 38.2 ከመቶ የሚሆነው የንግዱ ማኅበረሰብ ነው የሚለውን መነሻ ብንወስደው፣ እጅግ የፈጠነ ትኩረት የሚሻ ነገር ግን በቂ ትኩረት ያላገኘ አለያም የችግሩን ስፋትና ጥልቀት የሚመጥን አቅጣጫ ያልተሰጠው የማኅበረሰብ ክፍል የንግዱ ዘርፍ ላይ የተሠማራው ነው ብሎ ማለት ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል የትራንስፖርት ዘርፉ የመረጃ ዘዴ ቴክኖሎጂዎችን ማካተት ሲገባው፣ ለተሽከርካሪና መንገድ ዘርፍ ብቻ በተነፃፃሪ የተሻለ ትኩረት በመስጠት እንደ ኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ያሉ ትልቅ ፋይዳ ያላቸው ተቋማት ከገበያ የመውጣት አደጋ ተደቅኖባቸዋል፡፡ ይህ ተቋም በሥጋት ውስጥ ከመውደቁም ባሻገር የገንዘብ ተቋማት ተግባር በሆነው ዘርፍ ውስጥ ከመሰማራቱም በተጨማሪ ወደ ውጭ አገር የሚላክ ደረቅ ዕቃ ማስተላለፍ ውስጥ ገብቶ ሲዳክር ማየት ምን ያህል በዕውቀት ላይ ያልተመሠረተ ሥራ እየተሠራ እንደሆነ ያሳያል፡፡ በእርግጥ ሌሎች ሁኔታዎች ባልተቀናጁበት ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ህልውናውን ላለማጣት የፖስታ አገልግሎት የሚያደርገውን ጥረት መኮነን ተገቢ ላይሆን ይችላል፡፡

ምን ይደረግ?

ከላይ በተጠቀሰው መረጃ መሠረት ከ4.678 ሚሊዮን ሕዝብ ውስጥ 38.2 ከመቶው የንግዱ ማኅበረሰብ ወደ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት በመመላለስ በቀን በአማካይ ሁለት ሰዓታትን ያባክናል የሚል ድምዳሜ ላይ የሚያደርሰን ስለሆነ፣ በቀን 7,147,984 ብር በዚሁ የኅብረተሰብ ክፍል ብቻ ከአቅም በላይ በሆነ ምክንያት ያለአግባብ እንደሚባክን ያስረዳል፡፡ ወደየትኞቹ የአገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሊሄዱ ይችላሉ ከተባለ ደግሞ ወደ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን፣ ወደ ንግድ ማደራጃና ማስፋፊያ፣ ወደ ውልና ማስረጃ ተቋማትና ወደ ሌሎችም እንደሚመላለስ መጥቀስ ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል እነዚህ የንግድ ማኅበረሰቡ አባላት የፖስታ አገልግሎት ሳጥን በመከራየት ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚፈልጓቸውን አገልግሎቶች ማግኘት ቢችሉ፣ በመንገድ ላይ ያለአግባብ የሚባክነውን ጊዜ ከማዳን በተጨማሪ በምልልስ የሚደረስባቸውን እንግልትና ድካም በማስወገድ ምርታማነታቸውን ማሻሻል ይቻል ነበር፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን የንግዱ ማኅበረሰብ አብዛኛውን ጊዜ ለሸቀጥ ፍለጋ እንደመርካቶ ያሉ አካባቢዎች ከመንቀሳቀስ ውጭ ሰፊውን ጊዜ በንግድ ሥራ ቦታው ስለሚያሳልፍ፣ በመንገድ ትራንስፖርትና መጓጓዣ ላይ የሚፈጠረውን መጨናነቅ በማስቀረት በመንገድ ትራንስፖርትና መጓጓዣ በየዕለቱ መጠቀም ግዴታ ለሆነባቸው የኅብረተሰብ አካላት ቦታውን በማስለቀቅ እፎይታና ምርታማነት የማሳደግ ሚና እንደሚኖረው ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን የፖስታ አገልግሎቱ በመስፋፋቱ ምክንያት ተጨማሪ በርካታ ሥራ አጥ ወጣቶችን በፖስታ አገልግሎት ዘርፍ በማሰማራት የተሳለጠ የቅብብሎሽ ሥራ በማስፈን የሥራ አጥነት ችግርን ከመፍታትም ባሻገር የህልውና ሥጋቶችንም በአግባቡ ይመልሳል፡፡ በተነፃፃሪ ዘመናዊነትንም ያስፋፋል፡፡

የፖስታ አገልግሎት ሊሰጥ ከሚችለውና ከላይ ከተገለጸው አገልግሎት በማይተናነስ ሁኔታ የመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂ ማለትም ኢንተርኔት ያሉትን የመገናኛ ዘዴዎች ማስፋፋት ሲቻል ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ሰፊ አገልግሎት የማይሰጥ እንደሆነ ማንሳቱ ተገቢ ይሆናል፡፡ በእርግጥ የንግዱ ኅብረተሰብ ከቴክኖሎጂ ጋር ያላው ቁርኝትና የመጠቀም ዝንባሌ ዝቅተኛ ከመሆኑ ጋር ተግዳሮቶች መግጠማቸው ባይቀርም፣ ችግሩን የምንፈታበት ዘዴዎች ተጠንተው ተግባራዊ መደረግ መቻል አለባቸው፡፡

እንዴት ሊተገበር ይችላል?

የንግዱ ማኅበረሰብ የጊዜ ብክነትን በተመለከተ ትኩረት እንደሚያስፈልገውና በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅትና ቴሌኮሙዩኒኬሽን ዘርፎችን መሠረት ያደረገ ሥራ በመሥራት በመጠንም ሆነ በጥራት ላቅ ያለ ሥራ መሥራት እንደሚቻል ለማንሳት ሞክሬያለሁ፡፡

ከዚህ በመቀጠል አተገባበሩ ላይ የፖስታ አገልግሎት ድርጅት ሚና በዘርፉ እንዲጎለብት ለማድረግና ለውጤታማነቱ ሁሉም የንግዱ ማኅበረሰብ የፖስታ ሳጥን እንዲከራይ ማድረግ ሊያስፈልግ ይቻላል፡፡ ግለሰቦች የፖስታ አገልግሎት ሳጥን መከራየታቸው ብቻውን ውጤታማ ሥራ ላያመጣ ይችላል፡፡ በየዕለቱ የሚሠሩ የፖስታ አገልግሎት ማዕከላትን በተጠና መንገድ ለንግዱ ማኅበረሰብ አመቺና ቅርብ በሆኑ ቦታዎች ማደራጀትን ይጠይቃል፡፡ የፖስታ አገልግሎት ባለሙያዎች እንደ አስፈላጊነታቸው በፖስታ አገልግሎት ማዕከላቱ በመገኘት አልያም ከማዕከላቱ ወደ ግለሰቦቹ አገልግሎቱን የሚያደርሱ ፖስተኞችን በተገቢው ሁኔታ በማደራጀትና በማስተዳደር የመረጃና የአገልግሎት መለዋወጡን ማሳለጥ ይቻላል፡፡ በዚህ ጊዜ ማዕከሉ ስለሚቋቋምበት ቦታ አመቺነትና አንድ ፖስተኛ ሊያገለግል የሚገባውን የተገልጋይ መጠን በተመለከተ በጥናት ላይ በመመሥረት መፈጸም አስፈላጊ ነው፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ የፖስተኞች ጋጋታ በራሱ ችግሩን የሚያባብስ ሊሆን ይችላል፡፡

የመረጃ መረብና ኢንተርኔት አጠቃቀምን በተመለከተ ሁሉም የንግዱ ባለድርሻ ፈቃድ እንደማውጣቱ ሁሉ የሚሠራ ተቋማዊ ኢሜይልና ድረ ገጽ እንዲከፍቱ በማድረግና የንግዱ ማኅበረሰብም የየዕለት ሁኔታውን የመከታተልና የመጠቀምን ባህሉ እንዲያድግ በማስቻል ውጤት ማምጣት ይቻላል፡፡ ይህ በተነፃፃሪ ከፍ ያለ ኢኮኖሚያዊ አቅም ሊጠይቅ ከመቻሉ የተነሳ፣ ጥልቅ ሙያዊ እገዛ ከመፈለጉም ጋር በተያያዘ ሊተገበር ይችላል ወይ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡ ነገር ግን የኢኮኖሚና የተቋማዊ አቅማቸውን መሠረት በማድረግ ቅደም ተከተል በማውጣት ራሳቸውን አደራጅተው መሔድ ለሚችሉት ተገቢውን ትኩረትና ድጋፍ በመስጠት ወደ ውጤታማ ሥራ እንዲገቡ ማድረግ አንዱ መፍትሔ ነው፡፡ በግላቸው መደራጀትና መተግበር ለማይችሉት የሚሆን የማኅበረሰብ መረጃ ማዕከልን በተጠና ሁኔታ በማቋቋምና ለወጣቶች ስምሪት በመስጠት ተጨማሪ የሥራ ዕድል መፍጠርም ይቻላል፡፡ ከዚህ አኳያ ልክ እንደ ክፍያ መመዝገቢያ ማሽን የየተቋሙን ድረ ገጽና ተያያዥ ጉዳዮችን አጣምሮ የሚሠራ ባለሙያ እንዲኖራቸው በማድረግ ቴክኖሎጂውን ከማስፋፋትም በተጨማሪ በርካታ ቁጥር ያላቸውና በዘርፉ የሰለጠኑ ወጣቶች ወደ ሥራ እንዲገቡ በማድረግ ሥራ አጥነትና ድህነት ሊያመጣ ከሚችለው ጫና መራቅ ይቻላል፡፡

ከላይ የተጠቀሱት ሁለቱ ዘርፎች የሚፈለግባቸውን አገልግሎት ውጤታማ በሆነ መንገድ እንዲተገብሩ፣ በቅርብ ክትትልና ድጋፍ እንዲፈጸም ለማስቻል የሚረዱ የምክክር መድረኮች በቋሚነት የንግዱን ማኅበረሰብና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ማለትም ትራንስፖርት፣ ፖስታ አገልግሎት፣ ቴሌኮሙዩኒኬሽን፣ ገቢዎችና ጉምሩክ፣ ንግድ ሥራ አስተባባሪዎች፣ ውልና ማስረጃና ሌሎችም ላይ አስገዳጅ በሆነ ሕግ ተደግፎ ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የፖስታ፣ የመረጃና ግንኙነት ቴክኖሎጂዎችን በተመለከተ አገልግሎቱ በጥቃቅንና አነስተኛ ሙያ ሠልጠነው በማኅበር ለተደራጁ ወጣቶች ቢሰጥ የተሟላና የተሳለጠ ሊሆን ይችላል፡፡

ከተሽከርካሪ ባለንብረቶችና አሽከርካሪዎች ጋር ተገቢውን ውይይት በማድረግ ለአገር ሰላም፣ መረጋጋትና ዕድገት ያላቸውን አስተዋጽኦ እንዲረዱትና ተገቢውን ሚና እንዲጫወቱ ማስቻል ጠቃሚ ይመስላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ያለውን ሁኔታ ብንመለከት፣ የተሽከርካሪ ባለንብረቶች በቀን ወይም በወር ከሚያስገኝላቸው ገቢ ውጪ የሕዝብ አገልጋይነት መንፈሳቸው የተዳከመ ነው፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጡት ገንዘብ ለማግኘት ብቻ የሆነ ይመስላል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ አሽከርካሪዎችም ቢሆኑ በፈለጉት ሰዓት ወደ ሥራ ከመውጣታቸው በተጨማሪ በፈለጉት ጊዜም መኪናውን ባዶውን ይዘው ተሰልፎ ታክሲ በሚጠበቀው ተጓዥ አጠገብ ሲመላለሱ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ይኼን ሁኔታ መቀየር የባህሪይ ለውጥ ማምጣት የሚፈልግ ቢሆንም፣ የመንግሥት ሠራተኛው በሰዓቱ ገብቶ በሰዓቱ እንደሚወጣ ሁሉ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችም በቀን ውስጥ ዝቅተኛው የአገልግሎት መስጫ ጊዜ ገደብ ወጥቶላቸው በሕግ አስገዳጅነትና በዕውቀት ላይ ተመሥርቶ የሚተገበር ሥርዓት መፍጠር ግድ ይለናል፡፡ ይህ ባልሆነበት ወቅት የፈለገውን ያህል የትራንስፖርት መጠን ቢያድግና ዘመናዊነት ቢስፋፋ ችግሩ በሚፈለገው ደረጃ ላይፈታ ይችላል፡፡

(ዮናታን ዳሪ፣ ከአዲስ አበባ)

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኝት ይቻላል፡፡

*****

 ያላነሳኋቸው ሐሳቦች ይታረሙ

በሪፖርተር የሚያዝያ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. ዕትም በቢዝነስና ኢኮኖሚ ዓምድ ሥር ‹‹የአገሪቱ የሥጋ ኤክስፖርት ትኩረት እንዲሰጠው ተጠየቀ›› በሚል ርዕስ የተስተናገደው ዘገባ ላይ አንዳንድ ስህተቶች በማየቴ እንዲስተካከሉ በማለት ይህችን ደብዳቤ ለሪፖርተር ዝግጅት ክፍል ልኬያለሁ፡፡

ባቀረብሁት ጥናት ላይ ከ2001 ዓ.ም. በፊት ተብሎ የተጠቀሰው የእኔን አኃዝ የማይወክል በመሆኑ፣ ከ2001 ዓ.ም. ጀምሮ ተብሎ እንዲስተካከል እጠይቃለሁ፡፡ ከዘርፉ 500 ሚሊዮን ዶላር ይጠበቃል ተብሎ የተገለጸው፣ ባቀረብኩት ጽሑፍ ያልቀረበ በመሆኑ እኔ እንዳቀረብኩት መጠቀሱ አግባብ አይደለም፡፡ ሞጆ ቄራ ብቻ የጥራት ማረጋገጫ አግኝቷል ተብሎ የተገለጸውም ስህተት በመሆኑ እንዲታረም፣ ወደ አገር ውስጥ የገባው የሥጋ መጠንም 3.7 ሚሊዮን ዶላር ተብሎ እንዲጠቀስ ስል በትህትና እጠይቃለሁ፡፡

(ሔኖክ አባዲ፣ የፕራይም ሚት ኢትዮጵያ ኩባንያ የፕሮጀክት ኃላፊ)

ከአዘጋጁ፡- አቶ ሔኖክ ያቀረቡት ጽሑፍ ላይ በእሳቸው ያልተገለጹ ነጥቦች መካተታቸው መረጃን አዳብሮና ሌሎች ግብዓቶችን አካቶ ማቅረብ የጋዜጠኝነት ሙያ የሚጠይቀው የሙያ ግዴታ በመሆኑ ከእኔ ሐሳብ ውጪ መካተቱ ስህተት ነው እንደማይሉ ተስፋ እያደረግን፣ እርስዎ እንዳቀረቡ ተደርገው በቀረቡት አኃዞች ላይ ለተፈጠረው ስህተት የዝግጅት ክፍሉ ይቅርታ ይጠይቃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...