Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የሳምንቱ ገጠመኝ"የሰው ያለህ!!..."

“የሰው ያለህ!!…”

ቀን:

በግፍ የተገደሉ ሰማዕታት ወንድሞቻችን ቤተሰቦች ድረስ ከተለያዩ አካባቢዎች ሕዝብ ተሞ ለቅሶ ለመድረስ ጨርቆስ ባሉት አምስት ያህል ለቅሶ ቤቶች በመገኘት፣ የራሳችንን ሐዘን አወጣን፡፡ ያገኘሁትን የመንፈስ መረጋጋትና ከሐዘን መጽናናት አስታውሳለሁ።

ዛሬ ምን ያህል ራስ ወዳዶች እንደነበርን ተሰማኝ። በየለቅሶ ቤቶቹ ተገኝተን ራሳችንን ይበልጡን ስናጽናና እንደነበርን፣ የሰማዕታቱ ቤተሰቦች መጽናናታቸውን ገልጸውልን ደስታቸውንም ሰምተን ተሰናብተን ስናበቃ ወደ የሥራችን ወደ የቤታችን ተመለስን።

ዛሬ የተሰማኝን ሐዘን ለመግለጽ፣ ይህ ዓይነት ስሜት ከዚህ ቀደም ተሰምቶኝ ስለማያውቅ የምችልበት አይመስለኝም።

- Advertisement -

የስምንትና የአራት ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሕፃናትን (ኢየሩስ ብርሃኑን እና ዮናታን ብርሃኑን) ለማሳደግ አባት ተሰደደ። እነዚህ የሚያምሩ ሕፃናት አባታቸው ለሥራ ወደ ድሬዳዋ መሄዱን እንጂ አንገቱን ለካራ እንደሰጠ አያውቁም። እንኳን እነሱ እናታቸው ብርቱካን ጌቱ ጭምር አታውቅም ነበር። እንደ ማንም ኢትዮጵያዊ በሰማዕታቱ እጅጉን አዝነው ሲያለቅሱ ቤታቸው መርዶው ከቀናት ወዲህ የሚዘልቅ አልመሰላቸውም ነበር።

ብርሃኑ ጌታነህ “እግዚአብሔር መልካም ነው…” ዓይነት መንፈሳዊና ሥነ ምግባራዊ መልዕክቶች የሚያስተላልፉ የሸክላ ላይ ጽሑፎችን በመጻፍ ይተዳደር ነበር። ቤተሰቦቹንም የሚመግበው እነዚህን የእጁን ውጤቶች በመሸጥ ነበር።

ከሦስት ወራት በፊት ግን ለሚወዳቸው ሕፃናትና ባለቤቱ የተሻለ ሕይወት ተመኘ። “እንዳታስቢ ስልክ የማይሠራበት ቦታ ወደ ድሬዳዋ ሥራ አግኝቻለሁ። ትንሽ ሠርቼ ተመልሼ እመጣለሁ። ልጆቼ ከጠየቁሽም ይመጣል በያቸው፤” ብሎ ሚስቱን አሳምኖ ከቤቱ ወጣ።

ለወራት ድምፁ ቢጠፋም የናፍቆት እንጂ የሥጋት ጭንቀት ፈጽሞ ያልነበራት ባለቤቱ፣ ልጆቹ ሲጠይቁም ይመጣል እያለች ያመነችበትን እየነገረቻቸው ተታልላ ስታታልላቸው፣ በየመሀሉ በወዳጆቹ በኩል መልዕክት እየላከ እንዳይጨነቁ ሲያደርግ ቆይቶ፣ ሱዳንን አልፎ ሊቢያ ላይ ፍፃሜው ሆነ። ባለህልሙ ብርሃኑ ተሰዋ።

ምኑም የማይገባው የአራት ዓመቱ ሕፃን ዮናታን፣ እናቱና ሌሎችም ጎረቤቶች ለአገራቸው ሰማዕታት ሲያለቅሱ አይቶ ግራ ቢጋባም፣ ስምንት ዓመት የሞላት ኢየሩስ ግን ለሰማዕታቱ ከእናቷ ጋር ታለቅስ ነበር። በመላው አገራችን ሐዘኑ ከሳምንት በላይ ሲዘልቅና ሁሉም እየተጽናና ሲመጣ ያልገመቱት መርዶ በእነ ብርቱካን ቤት ገባ።

ሱዳን ነበር የተባለው የብርሃኑ ወዳጅ መሞቱንና ለቅሶ ለመድረስ የብርቱካን አክስት ሲጠሯት የእሷ ባል መሰዋቱን ፈጽሞ አልገመተችም። ቆይቶ ግን ራሷ ኢንተርኔት ቤት ሄዳ የባልዋን ግድያ ቪድዮ አስከፍታ የተሠራውን ግፍ በዓይኗ አይታ፣ ድሬዳዋ ነኝ ያላትን የልጆቿን አባት እስትንፋሱ ስትወጣ አይታ (ጨርቋን ጥላ) የምትይዘው የምትጨብጠው አጥታ በደጋፊ ወደ ቤትዋ ተመለሰች።

ሕፃን ኢየሩስ ዛሬም ቢሆን ታለቅሳለች። ዮናታን ግን ዛሬም ድረስ አባቱ ከድሬዳዋ ይመለሳል እያለ ይጠብቃል።

ይህ በሆነ በአራተኛው ቀን ወደ ለቅሶው ቤት አመራሁ። ሚስት ጠባቧን ወና ቤት ብቻዋን ታቅፋ፣ እንባዋን አሥሬ እየጠረገች፣ ልጆችዋን ትምህር ቤት ሰድዳ፣ ሲመጡ የሚበሉት እንዳያጡ የከሰል ምድጃ ላይ ሽሮ ስታበስል ደረስኩ። ብቻዋን ነች። የጨርቆስ ልጆች ካስቀመጡት አበባና የሰማዕቱ ብርሃኑ ምሥል ውጪ ማንም የለም።

ሐዘን በባዶ ቤት ውስጥ ምን ያህል እንደሚብስ ብዙ የቀበርን እናውቀዋለን። ለካስ ራሳችንን ለማጽናናት ነበር ሳምንቱን ሙሉ በየለቅሶው ቤት የተመላለስነው። እጅጉን አዝኛለሁ። አሁን እንኳን ይህን ስጽፍ ማልቀሴን ማቆም አልቻልኩም።

እባካችሁ ዛሬም ልናጽናናቸው የሚገቡ ብዙ ናቸው። ይህን የሐዘን ጊዜ ሳናልፍ ሌላ ተስፋ የቆረጡ ቤተሰቦችን ሐዘን እንዳንሰማ። ብርቱካን ለልጆቿ ስትል ለመኖር ወስናለች። እንባዋን ብቻዋን እያፈሰሰች፣ ልጆችዋ የሚበሉትን ሽሮ እያበሰለች ነው።

ሁሉም ትችትና ዘለፋውን ጨርሶ ዝም ሲል ትግራይ እንትጮ፣ ጎንደር ትክል ድንጋይና ወልቂጤ ድረስ ሄደህ ቤተሰቦችን ለማጽናናት የሞከርከው ዮሴፍ ገብሬ፣ የሚወራብህን በሙሉ በመቻልህና ዛሬም ድረስ የምትችለውን ለማድረግ በመሞከርህ እግዚአብሔር ይስጥህ። የተባልከው ‘አንተ አትንገረን ሌሎች ያውሩልህ’ መሰለኝ እንጂ፣ ያደረግከው በሙሉ መልካም ነው። አሁንም ቀጥል። እኔም መሰከርኩልህ።

የነብርቱካን ቤት ግን የሰው ያለህ የአጽናኝ ያለህ እያለ ነው። ሕፃናቱም የእኛው ልጆች በመሆናቸው ሄደን አለን እንበል። በቻልነውም አቅም እያደንን ቤተሰቦቻቸውን እናጽናና።

ይህን መልዕክት አንብበው ሲጨርሱ እባክዎን ከቻሉ አቡዋሬ (ኤድና አዲስ ሆቴል ጀርባ) በመሄድ ለቅሶውን ይድረሱ። ካልቻሉ ግን መልዕክቱን ለሌሎች ያድርሱ።

እግዚአብሔር ጽናቱን ይስጥልን።

(ያሬድ ሹመቴ፣ ፌስቡክ ገጹ ላይ ያሠፈረው) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...