በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ክለቦች መካከል ሲካሄድ የቆየው የዘንድሮው የጥሎ ማለፍ ዋንጫ ውድድር ለፍጻሜ ግማሽ የሚያልፉት አራት ቡድኖች በግንቦት መገባደጃ እንደሚለዩ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አስታወቀ፡፡
ለከርሞ በአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን የሚወክለውን ክለብ ለመለየት ሲካሄድ የቆየው የጥሎ ማለፍ ውድድር ያፋጠጠው የመጨረሻዎቹን ስምንት ክለቦችን ነው፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለሪፖርተር በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በወጣው ድልድል መሠረት ሐሙስ ግንቦት 27 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአርባ ምንጭ፣ ኢትዮጵያ ቡና ከሐዋሳ ከነማ ሲጋጠሙ፣ በማግስቱ ዓርብ ሲዳማ ቡና ከመከላከያ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ ከወላይታ ድቻ ይጫወታሉ፡፡
የሁለቱ ቀናት አራት አሸናፊዎች በግማሽ ፍጻሜው በሰኔ ወር እንደሚጋጠሙ ታውቋል፡፡
በተያያዘ የፕሪሚየር ሊግ ዜና፣ ሊጠናቀቅ አምስት ጨዋታዎች የሚቀሩት የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮና የአዲስ አበባና የክልል የግንቦት 2 ቀን ግጥሚያዎች ተጠባቂ ሆነዋል፡፡
በተለይ በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚደረጉት ሁለቱ የደደቢትና ሙገር፣ የቅዱስ ጊዮርጊስና ኤሌክትሪክ ግጥሚያዎች በራስጌና በግርጌ ያሉ በመሆናቸው ላለመውረድና ከላይ ያላቸው ደረጃ ላለመልቀቅ የሚከናወን በመሆኑ ተጠባቂ አድርጎታል፡፡
በክልል ከተሞች በወላይታ ሶዶ ከተማ ድቻ ሊጉን በሁለተኛነት ከሚመራው ሲዳማ ቡና ጋር የሚያደርገው ጨዋታ ሌላው አጓጊ ነው፡፡ በወልዲያ ወልዲያ ከነማ ከመከላከያ፣ በሐዋሳ ሐዋሳ ከተማ ከኢትዮጵያ ቡና፣ በአዳማ አዳማ ከነማ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ በአርባ ምንጭ አርባ ምንጭ ከነማ ከዳሽን ቢራ ይጋጠማሉ፡፡
ፕሪሚየር ሊጉን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ42 ነጥብ ሲመራ ሲዳማ ቡና፣ አዳማ ከነማና ደደቢት ከሁለተኛ እስከ አራተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡