Sunday, May 26, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የትምህርት ጥራት መጓደል እያስከተላቸው ያሉ ተግዳሮቶችና መዘዛቸው እስከ መፍትሔው

በተሰማ አያሌው አስረስ

ትምህርት የአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ (ምጣኔ ሀብታዊ)፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ዕድገትና ብልፅግና ኅብለ ሰረሰር ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከሌሎች አገሮች በተለየ ሁኔታ የትምህርት ጥራት መጓደል በኢትዮጵያ የመንግሥት ትኩረትና ጉዳይ አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት በአገራችን የትምህርት ጥራት ከድጡ ወደ ማጡ እያሽቆለቆለ ነው፡፡  ‹‹ጥራት›› የሚለው ቃል ብቻ ነው ያለው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ትልቅ ትኩረትና ሽፋን አግኝተው የቆዩት ብዛትና ተደራሽነት ናቸው፡፡ ሁለቱም አስፈላጊ በመሆናቸው ትኩረት ማግኘታቸው ተገቢ ነው፡፡ ሁለቱንም ማሳካት የተቻለ ይመስለኛል፡፡ ይህችን ጽሑፍ መጻፍ ያስፈለገው የትኩረት አቅጣጫ ወደ ጥራት ቢደረግ ከማለት ባለፈ ተግባራዊ እንቅስቃሴው ላይ መበርታት እንደሚኖርብን ለማሳሰብ ነው፡፡ ተግባራዊ እንቅስቃሴው የተሳካ እንዲሆን በቅድሚያ ትምህርት በኢትዮጵያ በፀና ሕመም ላይ መሆኑን ማመንና መቀበል ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ጽሑፍ በምክረ ሐሳብነት የተዘረዘሩት በመፈወሻ መድኃኒትነት ሊያገለግሉ ይችላሉ፡፡

የአንድ አገር የትምህርት ሥርዓት ጠንካራ ኢንዱስትሪና ጤናማ ኢኮኖሚ ማደራጀትና መምራት የሚችሉ በከፍተኛ ደረጃ የሠለጠኑ ልምድ ያላቸውን ባለሙያዎች በየሙያ መስኩ መፍጠር የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህም ሲሆን የትምህርት ሥርዓቱ ጥራትን አስጠብቋል ሊባል ይቻላል፡፡

‹‹አሁን ላይ በአገሪቱ ያሉ የማሠልጠኛ ተቋማት አጫጭር ሥልጠናዎችን እንደ አሽከርካሪነት ሥልጠና ከሚሰጡት እስከ ዩኒቨርሲቲዎች ያሉ ተቋማት በየትምህርት ዘርፉ በጣም የሠለጠኑ የገባቸውንና የበቁ ሥነ ምግባር ያላቸውና የሠለጠኑበት ሙያ የሚጠይቀውን ሥነ ምግባር የተላበሱ ምሩቃንን ነው እያፈሩ ያሉት?›› የሚለው ጥያቄ ምላሽ ነው የትምህርት ጥራት ተጠብቋል? ወይም አልተጠበቀም? ለማለት የሚያስችለው፡፡

በየሥራ መስኩ የባለሙያዎች እጥረት እንዳለ የሚታወቅ ነው፡፡ ምናልባት ‹‹በፍፁም የምን እጥረት አመጣህ?›› የሚሉ ካሉ ሠራተኛ ተብሎ የተቀጠረውን፣ ከየማሠልጠኛ ተቋማት የተመረቀውን፣ የትምህርት ማስረጃ ሰርተፍኬት/ዲፕሎማ/ መንጃ ፈቃድ ያለውን ሁሉ ባለሙያ አድርገው ተረድተውት ሊሆን ይችላል፡፡

ባለሙያና ሠራተኛ ከፍተኛ የሆነ የትርጉም ልዩነት አላቸው፡፡ ምሩቁን ሁሉ በተመረቀበት የትምህርት መስክ ባለሙያ ብሎ መፈረጅ ይከብዳል፡፡ ለዚህም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከምረቃ በኋላ መውጫ ፈተና እና/ወይም የብቃት ማረጋገጫ ሰርቲፍኬት (ሲኦሲ) ማግኘት ያስፈልጋል በሚል ጅምር እንቅስቃሴ ይታያል፡፡

ባለሙያ ማለት ቢያንስ በአንድ የሙያ ዘርፍ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመጀመርያ ዲግሪ የተመረቀ/ች ወይም በአንድ ሙያ ከፍተኛ ክህሎትና ልምድ ያለው/ላት ሲሆን ሠራተኛ ማለት ደግሞ ማንኛውንም የጉልበትም ሆነ ሌላ መጠነኛ ክህሎትና ዕውቀት የሚጠይቅ የተለመደና ተደጋጋሚ ሥራ የሚሠራ ነው፡፡

ስለዚህ በዚህ ጽሑፍ ጠቅለል ባለ መልኩ ኢንዱስትሪው ማለትም በየሥራ መስኩ የባለሙያዎች እጥረት በመኖሩ (እያንዳንዱ የሥራ ክፍል/መሥሪያ ቤት) የሚፈልገውን ያህል ብቃት ያላቸው ባለሙያዎች ከገበያው እያገኘ እንዳልሆነና በየሥራ ዘርፉ የባለሙያዎች ዕጥረት የሚያስከትላቸውን ዋና ዋና ችግሮች ለመዘርዘር ተሞክሯል፡፡

1ኛ/ በትምህርት ተቋማት (ከአፀደ ሕፃናት እስከ ዩኒቨርሲቲ)

አሁን አሁን በየትምህርት ቤቶችና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚያስተምሩ መምህራን ሁሉም የተዋጣላቸው የሚያስተምሩትን ትምህርት ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ ያወቁትን በደንብ አደራጅተው ተማሪዎቻቸው ሊረዱት በሚችል መልኩ ማቅረብ የሚችሉ ናቸው ወይ? የሚል ጥያቄ ማንሳትና መመለስ አስፈላጊ ነው፡፡

እኔ ከሠላሳ ሰባት ዓመት በላይ በመምህርነት እያገለገልሁ ያለሁ በመሆኔ የግል ጥልቅ አስተውሎዬን እንደ መረጃ እንዳቀርብ እገደዳለሁ፡፡ አሁን አሁን ‹‹ከመምህሩ ደቀ መዝሙሩ›› የሚለው አባባል እውነት እየሆነ ነው፡፡ ብዙ ማስረጃ ገጠመኞችን መዘርዘር ይቻላል፡፡ አንድ በጣም እየገረመኝ ያለ በትክክል የሆነ ታሪክ አጠር አድርጌ ላካፍላችሁ፡፡

ከአሥር ዓመት በፊት በሒሳብ የመጀመርያ ዲግሪ ትምህርት አጠናቀሀል የተባለ፣ አንድ ሁለት ዓመት ሥራ ሳያገኝ ቆይቶ አዲስ አበባ ከአንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በተመረቀበት የሒሳብ ትምህርት በመምህርነት ይቀጠራል፡፡ የተቀጠረ ሰሞን አግኝቼው መቀጠሩንና እስከሚያስተምርበት ትምህርት ቤት ነገረኝ፡፡

በአጋጣሚ የእኔ ዘመድ ልጆች የሚማሩት ከዚህ ትምህርት ቤት በመሆኑ የሒሳብ አስተማሪያቸው በየክፍለ ጊዜው የሚፈጽማቸውን ስህተቶች፣ እንዲሁም ተማሪዎች እንደሚያርሙትና እስኪ ወጥተህ ሥራው እያለ ተማሪዎችን እየጋበዘ እሱ የሠራውን ስህተት ተማሪዎች እያስተካከሉት እያፈረ ላብ በላብ እየሆነና ላበቱን እየጠረገ ‹‹ተማሪዎች አጨብጭቡለት፤›› ማለቱ በየቀኑ በየክፍለ ከተማ ጊዜው በጣም እያሳቀቀው መሆኑን የሰማሁ ሲሆን፣ በዚያው ዓመት ይህንኑ የቀድሞ ተማሪዬን አግኝቼው እንዴት ነው ማስተማር ብዬ ስጠይቀው፣ ‹‹አይ ቲቸር፣ ተውኩት እኮ ለቀቅሁ፤›› ሲለኝ “እንዴት? ለምን?” ብዬ ለጠየቅሁት ጥያቄ “አይጋሼ ተማሪዎችን አልቻልኳቸውም፤” ነበር ያለኝ፡፡ ዕርግጠኛ ነኝ ይህ ምላሽ “ተማሪዎችን አልቻልኳቸውም፤” በጣም የሚገርምና የችግሩን ጥልቀት፣ ለማስገንዘብ ትልቅ እውነተኛ አጋጣሚ የሚሆን ይመስለኛል፡፡ ይህ አባባል ለእንደ እኔ ዓይነቱ ለብዙ ጊዜ ላስተማረ የሚሰጠው ትርጉም ዩኒቨርሲቲዎች የሚያስመርቋቸው ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ከዚህ በፊት ተምረው ያለፉትን ትምህርት ሁሉ የሚያጠፋ እንደሆነ ነው፡፡

በመማር ማስተማሩ ያለውን ችግር ለማጠቃለል፣ ብዙዎች ‹‹መምህር›› ተብለው የተቀጠሩት ከመማሪያ ወይም ከሌላ ማጣቀሻ መጽሐፍ ወይም ከየ“ድረ ገጹ”  የገለበጡትን/ያወረዱትን ኖት መገልበጥ፣ ማስገልበጥ፣ ፈተና ብለው ለተማሪዎቻቸው የሚሰጡት ስህተት በስህተት፣ ትርጉም የማይሰጡ ጥያቄዎች የሚገኙበት፣ ከተዘረዘሩት አማራጮች ውስጥ መልስ የሌላቸው ወይም ከአንድ በላይ መልስ የሚኖራቸው ጥያቄዎች የሚበዙበት እንደሆነ የአብዛኛዎቻችን ገጠመኝ ሊሆን እንደሚችል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፡፡ አንድ የሥራ ባልደረባዬና ወዳጄ ቢቸግረው “ለምን ልጆቻችንን በየቤታችን እኛው እንድናስተምራቸውና በማዕከል ፈተና እንዲዘጋጅ አይፈቀድም?” ማለቱን አስታውሳለሁ።

አንዳንዶች የሚያስተምሩት ትምህርት ዕውቀት ማነስ ብቻ ሳይሆን ያለባቸው የዕለቱን ትምህርት የማቅረቢያና የማስተማሪያ ዘዴውን በደንብ ያለማወቅ ችግርም አለባቸው፡፡

ሌላው ትልቁ ችግርና ብዙዎች መምህራን ላይ የሚስተዋለው የተሰማሩበትን የማስተማር ሥራ በአብዛኛው ወደውትና ፈልገውት ሳይሆን የግድ የወር ገቢ ለማግኘት ሲሉ ብቻ የተሰማሩበት ሙያ መሆኑ ነው፡፡

“የእኛ ሙሽራ ባለድሪ ወሰዳት አስተማሪ” ተብሎ ለተዜመለት ከፀሐይ በታች እጅግ ክቡር ለሆነው የመምህርነት ሙያ የሚመለመሉ ዕጩ መምህራንና ሙያውን የሚቀላቀሉትበት ሥርዓት ሊፈተሽ ይገባል። ይህን ጽሑፍ አጠናቅቄ ለኅትመት ለመላክ ከቤት ልወጣ ስነሳ በኢብኮ የዜና እወጃ ‹‹ኬንያ ሠላሳ ሁለት ዓመት የቆየ የትምህርት ሥርዓቷን ቀየረች” የሚል ዜና ስሰማ የዚህችን ጽሑፍ አስፈላጊነት አጠናከረልኝ፡፡

2ኛ/ በጤና መስክ

በጤናው መስክ በየሆስፒታሉ፣ በጤና አገልግሎት መስጫ ክሊኒኮች የሚሠሩ ሐኪሞችና ነርሶች ምን ያህል ሙያው የሚፈልገው ብቃትና ሥነ ምግባር አላቸው? የሚለውን ጥያቄ በሚመለከት ብዙ ተብሏል (ለምሳሌ በሬዲዮ ፋና)፣ ተጽፏል (በየጋዜጣው) አሁንም ብዙ ማለት ይቻላል፡፡

ቀደም ባሉት ጊዜያት ችግር የሚፈጠረው በቸልተኝነት ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን በዕውቀት፣ በችሎታ ማነስም ዘግናኝ ስህተቶች እየተፈጸሙ እያየን እየሰማንም ነው፡፡

በጣም ጎበዝና በዕውቀታቸው የሚተማመኑ የጤና ባለሙያዎች ያሉትን ያህል ተመሳሳይ የጤና ሳይንስ ትምህርት የተማሩ የማይመስሉ በመሰለኝና በግምት በመመራት እስኪ ይህን ሞክረው/ሪውና ካልተሻለህ/ሽ እቀይርልሀለሁ/ሻለሁ የሚሉትን ባለሙያዎች ብሎ መጥራት እንዴት ይቻላል? በሕይወት ያለ ታካሚን ፎርማሊንን የወጋችውን ምን ትሏታላችሁ? ከዕውቀት ማነስ ሳይሆን ከአንዱ ክሊኒክ ወደ ሌላኛው ለመሄድ በመቻኮል ለወንዱ የምጥ ማፋጠኛ መድኋኒት ያዘዘውንስ ምን ትሉታላችሁ?

አለቃዋ ‹‹ሲስተር ለመሆኑ ምን መድኃኒት ነበር ለሕመምተኛዋ የሰጠሻት?›› ሲላት ‹‹እኔ እንጃ፣ ቆይ ካርቶኑን ላምጣው፤›› በማለት፣ ‹‹ይኸው አንተው አንብበው፤›› የምትለዋንስ ምን እንበላት?

ቀላል የጤና ችግርን ማወቅ ሲከብዳቸው አካብደው ውጭ አገር ሄደህ/ሽ ካልታከምህ/ሽ ተስፋ የለህም/ሽም የሚሉትንስ ምን ትሏቸዋላችሁ?

በጥሩ ሁኔታ ያለን ፅንስ ጊዜው ተጠብቆ በተፈጥሮአዊ አወላለድ መውለድ እየቻለች ገና በስምንተኛው ወር በቀዶ ሕክምና ዛሬውኑ እኔ ከምሠራበት የግል ክሊኒክ ላዋልድሽ የሚሉትንስ ምን እንበላቸው?

የዘመኑ ቴክኖሎጂ ያፈራቸውን የሕክምና መሣሪያዎችና ማሽኖች አጠቃቀምና በትክክል ማንበብ ባለመቻል የተሳሳተና አስደንጋጭ መረጃ ለሕመምተኞች እየሰጡ ብዙዎችን ያስደነገጡትን ምን እንበላቸው? ሁሉንም ገጠመኝን ልዘርዝር ብል አንድ መጽሐፍ ይወጣዋል፡፡ ስለዚህ በዚህ ላብቃ፡፡

3ኛ/ በምሕንድስናና ኮንስትራክሽን ዘርፍ

አሁን አሁን በምሕንድስና ተመርቀው በዚሁ ዘርፍ እየተሠማሩ ካሉት ጥቂቶች አንድ አናፂ ወይም ግንበኛ እንኳ የማይፈጸመውን ስህተት ይፈጽማሉ እየተባሉ እንደሚታሙና እንደሚተቹ መስማት የተለመደ ሆኗል፡፡ ሀሜቱ ተራ ሐሜት እንዳልሆነ እንደ ማሳያ የሚከተሉትን ልጥቀስ፣

ሕንፃዎች ገና ተገንብተው ሳይጠናቀቁ ዘመም የማለትና የመውደቅ ሁኔታ እያየንና እየሰማን ነው፡፡ ለምሳሌ ባለፈው ዓመት አዲስ አበባ ሰሚት አካባቢ ባለ አራት ወለል ሕንፃ ሌሊቱን ወድቆ ማደሩን በመገናኛ ብዙኃን ሰምተናል፣ ድርጊቱን ቦታው ተገኝቼ አይቻለሁ፡፡

አዲስ አበባ ላፍቶ አካባቢ ለጋራ መኖሪያነት ከተሠሩ ኮንዶሚኒየም ሕንፃዎች ውስጥ ሁለቱ ይሁን ሦስቱ እርግጠኛ አይደለሁም ብቻ ግን “ሊወድቁ ነው” ተብሎ ኑሮአቸውን በእነዚህ ሕንፃዎች አድርገው የነበሩ ሰዎች ወደ ሌላ አካባቢ መዛወራቸውን ከጋዜጣ አንብቤአለሁ፡፡

ሐዋሳ የመብራት ኃይል ዋናው መሥሪያ ቤት ሕንፃ ዋናው በር በጓሮ በኩል መሆኑ አርክቴክቱ ወረቀት ላይ ወይም ኮምፒዩተሩ ላይ በትክክል የሠራውን ዲዛይን ወደ መሬት ያወረደው ‹‹መሐንዲስ›› በትክክል ያልተረዳው መሆኑን ያመለክታል፡፡ የሚገርመው ሕንፃው ቀለም እስኪቀባ ድረስ ስህተቱ አለመታወቁ ነው፡፡

የምሕንድስና ሳይንሱን በሚቃረን ሁኔታ ሕንፃዎችን ያለበቂ መፀዳጃ ቤቶች መሥራት የተለመደ ነው::

የርክክብ ቀን ሕንፃ ጠፋ መባልንም ሰምተናል። እንዲያውም ቀልደኞች አጣፍጠው ከሽነው አሉት የተባለው ፈገግ የሚያደርግ ስለሆነ ላልሰማችሁ ላጋራችሁ። “እስኪ የግቢ ጠባቂዎች ይጠየቁ ተብሎ ሲጠየቁ በእኛ ተራ ቀን አንድም ሕንፃ አልወጣም፤” አሉ ተባለ::

አንዳንዶቻችሁ እነዚህን እኔ የጠቃቀስኳቸውን ስህተቶች እንዳነበባችሁ ይህ ታዲያ ለድምዳሜ የሚያደርስ ነው ወይ ልትሉ እንደምትችሉ እገምታለሁ፡፡ ላስታውሳችሁ የምፈልገው የትምህርት ጥራት መጓደል የሚያስከትላቸው ችግሮች በአንዴ፣ በአጭር ጊዜ የሚከሰቱ ሳይሆን ቀስ ብሎ ወደ ፊት ትልቁ አደጋ እንደማይቀር ነው፡፡ እነዚህ የዘረዘርኋቸው ምልክቶች ናቸው፡፡

በዚህች ጽሑፍ በሦስቱ ትልልቅ የሥራ መስኮች፣ ችግሩ በጣም በፀናባቸው ኢንዱስትሪዎች ላይ በምልክትነት እየታዩ ያሉትን ለመነካካት ሞከርሁ እንጂ ችግሩ በሌሎች ኢንዱስትሪዎች ላይ አልተንፀባረቀም ማለት አይደለም፡፡

ማጠቃለ

የትምህርት ጥራት መጓደል በእያንዳንዱ የሥራ መስክ የሚፈለገው ሥነ ምግባር ያላቸው ባለሙያዎች እጥረት እንዲከሰት የሚያደርግ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ዝቅተኛ የምርት መጠን፣ ሥራ አጥነት፣ ጤናማ ትርፍ ማግኘት ቀርቶ ኮርፖሬሽኖች/ኢንዱስትሪዎች የገንዘብ/መዋለ ንዋይ እጥረት እንዲገጥማቸው እያደረገ ነው፡፡ ከሥራ አጦች ቁጥር መጨመር ጋር ተያይዞ ለማኅበራዊ ደኅንነት ጥበቃ ከፍተኛ ወጪ ይወጣል፣ እንዲሁም ከግብር የሚገኝ ገቢ ይቀንሳል፡፡ ችግሩ በጣም ብዙ ነው፡፡

የትምህርት ጥራት ሲጓደል ትምህርት/ሥልጠና የባህሪ ለውጥ ሊያመጣ ስለማይችል ከፍተኛ የሆኑ ምስቅልቅልሎች ይከሰታሉ፡፡ ለምሳሌ ሙስና እንዲህ ትልቅ ችግር እየሆነ የመጣው ትምህርት የባህሪ ለውጥ ሊያመጣ ባለመቻሉ ነው፡፡ ወጣቱ የውጭ ባህል አራማጅ የሆነውና የተለያዩ ሱሶች ተጠቂ ለመሆንና ለወንጀል መበራከት የትምህርት ጥራት መጓደል አንዱና ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡ ለእሴቶቻችን መሸርሸር ዋናው መነሻ ምክንያት የትምህርት ጥራት መጓደል ነው፡፡

የትምህርት ጥራት መጓደል የሚያስከትላቸው ዋና ዋና ችግሮች

 1. ኢንዱስትሪው የሚፈልጋቸውን ባለሙያዎች እንዳያገኝ ያደርጋል፣
 2. ችግር ፈቺ ሐሳብ አፍላቂ፣ ፈጠራዎች ይጠፋሉ፣
 3. ተቀባይነት ያለው የባህሪ ለውጥ አይመጣም፣
 4. የንባብ ባህል ያሽቆለቁላል፣ ስለዚህም መግባባት ችግር ሆኗል፣
 5. የሥራ አጦች ቁጥር ይጨምራል፣
 6. ከግብር የሚሰበሰብ ገቢ ይቀንሳል፣
 7. ምርትና ምርታማነት ይቀንሳል፣
 8. ወንጀል (ሙስናና የሐሰት የትምህርት ማስረጃ)፣ ሥርዓት አልበኝነት ይበራከታል፣
 9. የአገር ደኅንነትንና ሰላምን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ወጪ ይወጣል፣
 10. የአገር ፍቅርና ብሔራዊ ስሜት ይጠፋል፣
 11. ወጣቱ የኅብረተሰብ ክፍል የአደገኛ ሱሶችና ለውጭ ባህል ወረራ ይጋለጣል፣
 12. ወጣቱ ቴክኖሎጂውን በማይጠቅም ውጤታማ በማያደርግ መልክ አልባሌ ነገሮችን በመጠቀምና በመጠመድ ውድ ጊዜን ያጠፋል፣
 13. የአገር ኢኮኖሚ በእጅጉ ያሽቆለቁላል፡፡

ትምህርት ከሞተ ሁሉም ሞተ!! ምክረ ሐሳብ

በተለያዩ ጥናቶች እንደተረጋገጠው የተዘረዘሩት ችግሮች ምክንያቶች በርካታ ናቸው። የዕውቀትና ክህሎት ማነስ፣ የሚሠሩትን ሥራ ወዶ በፍቅር አለመሥራት፣ ጤናማ ያልሆነ የሀብት ማግኘት ፉክክር፣ ቸልተኝነት በዋና ምክንያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ።

ትምህርት ከሞተ ሁሉም ሞተ ስለሆነ አጠቃላይ የትምህርት ሥርዓቱ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት ተሰጦት የሚከተሉት ምክረ ሐሳቦች ጊዜ ሳይሰጣቸው ተግባራዊ እንዲሆኑ አሁኑኑ እንቅስቃሴ መጀመር አለበት፡፡

በየትምህርት ደረጃው ለሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ሥራና አሠራር የሚያስፈልግና የሚስማማ አዲስ የትምህርት ሥርዓት (ሥርዓተ ትምህርት) ቢዘጋጅ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡ ተማሪዎችን  ወደ ሕክምና፣ ምሕንድስናና መሰል የትምህርት ዘርፎች እየመደቡ የነገዪቱን ኢትዮጵያ ተረካቢዎችን አርሞና ኮትኩቶ የሚያዘጋጀው የመምህርነት ዘርፍን በደካማ ተማሪዎች በማጥለቅለቅ ትምህርትን ለአገራዊ ህዳሴ እንጠቀምበታለን ብሎ ማለም ከንቱ ስለሆነ፤ በየደረጃው ብቃት ያላቸው መምህራንን ማፍራትና ማሠማራት ላይ ልዩ ትኩረት አድርጎ መሥራት፣ ብቃት ያላቸውን መምህራን ማፍራት ከተቻለ በሁሉም ኢንዱስትሪዎች ብቃት ያላቸውን ባለሙያዎች ማፍራት ይቻላል፡፡ ብቃት ያላቸውን መምህራን ለማፍራት ከየሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ10ኛ ክፍል ከአንደኛ እስከ 10ኛ ደረጃ ለሚወጡ ተማሪዎች ልዩ ብሔራዊ ፈተና ተዘጋጅቶ በጣም የተሻለ ውጤት የሚያገኙት በመምህራን ትምህርት የልህቀት ማዕከል ሆነው በተመረጡ ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው ለሁለት ዓመት የዩኒቨርሲቲ መሰናዶ ትምህርታቸውን እንዲማሩ ማመቻቸትና የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ብሔራዊ ፈተናውን ሲያልፉ ከምረቃ በኋላ ቢያንስ ለሁለት ዓመት በመምህርነት ሊያገለግሉ እየፈረሙ ለ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርነት ወደሚሠለጥኑበት የመምህራን ትምህርት ኢንስቲትዩት በቀጥታ እንዲገቡ ቢደረግ፡፡

ለአንደኛና ሁለተኛ ሳይክል ትምህርት ቤቶች ብቃት ያላቸው መምህራንን መመደብ ለመቻል ወደ መሰናዶ ትምህርት ቤት የሚያስገባ ውጤት ማግኘት ላልቻሉት በ10ኛ ክፍል የሁለት ወሰነ ትምህርት አማካይ ውጤት የተሻለ ያላቸው በክልል ደረጃ የተዘጋጀ መግቢያ ፈተና ተፈትነው የተሻለ ውጤት የሚያገኙት በቀጥታ በደረጃ አራት ወይም በዲፕሎማ ወደሚያሠለጥኑ የመምህራን ትምህርት ኮሌጆች እንዲመደቡና ከምረቃ በኋላ ቢያንስ ለሁለት ዓመት በመምህርነት እንዲያገለግሉ ቢደረግ፡፡

‹‹በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ወዳቂ ወይም በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪ መባረር የለበትም ወይም የሚባረሩ ተማሪዎች ቁጥር በእጅጉ መቀነስ አለበት›› የሚለው በይፋ ያልተጻፈ ሕግ ቀርቶ ሙሉ ኃላፊነቱ ለመምህራን ቢሰጥ።

በዩኒቨርሲቲዎች የተሰጣቸውን ተከታታይ ምዘናዎች ማለፊያ ውጤት ማግኘት የማይችሉት እንደገና እንዲፈተኑ የሚፈቅደው ሕግ ወይም አሠራር ቢቀርና ኮርሱን ደግመው እንዲወስዱ ቢደረግ::

“ለተመሳሳይ ሥራ እኩል ክፍያ” የሚለው መርህ ልምድን ዋጋ ያሳጣ በመሆኑ በተለይ መምህራን ላይ ባይተገበር::

በየትምህርት ዘመኑ መጀመርያ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች የመግቢያ ውጤት አወሳሰን በዩኒቨርሲቲዎች የመቀበል አቅም ሳይሆን በብሔራዊ ፈተናው ግማሽና ከግማሽ በላይ ያገኙ በሚል ቢሻሻል፡፡

እያሽቆለቆለ ያለው የንባብ ባህል እንዲያንሰራራ ብሔራዊ ንባብ ዘመቻ አዋጅ ቢታወጅና የአምስት ዓመት ስትራቴጅክ ዕቅድ ተዘጋጅቶ በአስቸኳይ ወደ እንቅስቃሴ ቢገባ።

የሁለተኛ ደረጃ፣ የኮሌጅና የዩኒቨርሲቲ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎች የሳይንስ ፅንሰ ሳቦችን በደንብ መረዳት እንዲችሉ ገር በቀል ቋንቋዎችን በማስተማሪያ ቋንቋነት መጠቀም ቢጀመርና ደት የመማያና ማጣቀሻ ጻሕፍትን በተመረጡ ገር በቀል ቋንቋዎች ማዘጋጀት ቢጀመር። እንደማመጥ!!

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected]. ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles