Thursday, December 1, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊምላሽ ያጣው የላብ አደሮች ዕሮሮ

  ምላሽ ያጣው የላብ አደሮች ዕሮሮ

  ቀን:

  የሳሙና ማስቀመጫ በምታህለው ትንሿ ምሳ ዕቃዋ የያዘችውን ቀይስር የተቀላቀለበት አልጫ ምግብ ከጓደኛዋ ጋር የሆድ የሆዳቸውን እያወሩ መብላት ይዘዋል፡፡ አበላላቸው እንደተራቡ ሳይሆን ምግቡ እንደሰለቻቸው ሁሉ ቆንጠር ቆንጠር እያደረጉ ነው፡፡ ለነገሩ አቀማመጣቸውና ያሉበት ቦታ እንኳንስ ምግብ አጣጥሞ ለመጉረስ ለአፍታ ያህል ቆም ለማለትም ከባድ ነው፡፡ በአካባቢው ለሚያልፉ መንገደኞች እንኳ ፈፅሞ አይመችም፡፡

       በወጪና ወራጅ የተሞላው ከቃሊቲ መናኸሪያ ለጥቆ የሚገኘው የኢንዱስትሪ መንደር የውስጥ ለውስጥ መንገድ አስፋልት ቀርቶ የጠጠር መንገድ አያውቅም፡፡ ጥርጊያ መንገድ ለማለት እንኳ አያስደፍርም፡፡ ወጣ ገባ የበዛበት ሲሆን፣ አቧራው እንኳንስ በእግር በመኪና ለማለፍም በጣም ያስቸገራል፡፡

       አካባቢው እንደ ዓለምነሽ ያሉ (ስሟ ተቀይሯል) የፋብሪካ ላብ አደሮች (ሠራተኞች) ግን መዋያ፣ መኖሪያም ጭምር ነው፡፡ አቧራ የበዛበት መንገድ ደግሞ ሠራተኞች ምሳ የሚመገቡበት ግድግዳና ጣሪያ የሌለው፣ መቀመጫ አልባ መመገቢያ አዳራሽ እንደማለት ነው፡፡ ምሳ ሰዓት ሲደርስ ሠራተኞች ከየፋብሪካው ወጥተው መንገዱ ላይ ይኮለኮላሉ፡፡ ቀትር ላይ የሚበረታው ጠራራ ፀሐይ፣ ከባድ የጭነት መኪኖች ባለፉና ባገደሙ ቁጥር አካባቢውን እንደ ጉም የሚሸፍነው አቧራ ዕረፍት የሚነሳ ቢሆንም ተላምደውታል፡፡ ካርቱን ዘርግተው፣ ድንጋይ አመቻችተው በየአጥሩ ጥግ ተቀምጠው እንደ ነገሩ የቋጠሩትን ምሳ ይበላሉ፡፡

       በአንደኛው የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ ውስጥ የሚሠሩት ዓለምነሽና ጓደኛዋም ከሥራው በላይ ከባድ የሆነባቸውና ከጥቅሙ ባልተናነሰ መጠን ጉዳት እያደረሰባቸው የሚገኘውን የምሳ ሰዓት ጠብቀው ከአንደኛው አጥር ጥግ ተሰይመዋል፡፡ አንድ ከቀይ ስሩ አንድ ከአልጫው እያደረጉ ወደአፋቸው የሚልኩትን ጉርሻ ከአቧራ ጋር ያወራርዱታል፡፡ ‹‹እዚህ ቤት ስቀጠር የነበረኝ መልክና አሁን ፈፅሞ አንገናኝም፤›› አለች ገና በ23 ዓመቷ ወደ ሠላሳዎቹ ማብቂያ የመሰለችው ዓለምነሽ፡፡ ጓደኛዋም በመስማማት ዓይነት አንገቷን እየነቀነቀች የሥራውን አድካሚነትና አካባቢው ለሥራ ያልተመቸ መሆኑን እያስተዛዘነች ተናገረች፡፡ ምሳቸውን እየበሉ በጎናቸው ሽው እያሉ የሚያልፉ መኪኖችንና አላፊ አግዳሚውን ይመለከታሉ፣ የሚያውቁትን ሰው ሲያልፍ ሲያዩ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ሰላምታ ይለዋዋጣሉ፣ እያነፈነፈ የሚጠጋቸውን ውሻ ያባርራሉ፡፡  አጠቃላይ ሁኔታቸውን ለተመለከተ የሚሰጣቸው 45 ደቂቃ የምሳ ዕረፍት ዕረፍትነቱ ምኑ ላይ ነው የሚል ጥያቄ ያጭርባቸዋል፡፡

  ዓለምነሽ በዚህ የምሳ መመገቢያ ቦታ እንኳ ማዘጋጀት በተሳነው ድርጅት ተቀጥራ መሥራት ከጀመረች አራት ዓመታት አስቆጥራለች፡፡ ስትቀጠር ይከፈላት የነበረው 655 ብር እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ በየዓመቱ ከ150 እስከ 200 ብር የደሞዝ ጭማሪ እየተደረገላቸው በአሁኑ ወቅት ደሞዟ 1,500 ብር ሊደርስላት መቻሉን ስትገልፅ በኩራት ነው፡፡

       የምትሠራበት ድርጅት የሕፃናትና የአዋቂ አልባሳትን አዘጋጅቶ የተወሰነውን ለአገር ውስጥ ገበያ አብዛኛውን ደግሞ ለውጭ ገበያ ያቀርባል፡፡ የስፌት ሥራ የምትሠራው ዓለምነሽ በቀን ከ400 እስከ 500 ልብሶች ትሰፋለች፡፡ ነገር ግን ከላይ የለበሰችው አረንጓዴ ዩኒፎርም የቅያሪ ያለህ ይላል፡፡ አለመጠን ያረጀ ሲሆን፣ አረንጓዴ ቀለሙም ወደ አመዳምነት ተቀይሯል፡፡ ሠራተኞቹ ጠዋት ሁለት ሰዓት ገብተው ምሽት 11 ሰዓት ላይ የሚወጡ ሲሆን፣ ያላቸው ብቸኛ የዕረፍት ጊዜ አቧራ ላይ የሚያስቀምጣቸው የምሳ ፕሮግራም ነው፡፡

       ከሥራው አድካሚነትና በአንፃሩ ደግሞ የሚከፈላቸው ደሞዝ ዝቅተኛነት ሌላ አማራጭ እንዲፈልጉ የሚያደርግ ነው፡፡ ዓለምነሽም ጥሩ ሊከፍላት የሚችል ቢኖር  ይህንኛውን ድርጅት ለቃ መሄድ ትፈልጋች፡፡ ችግሩ በተመሳሳይ ዘርፍ የተሰማሩ ቀጣሪዎች ክፍያ ተመሳሳይ መሆኑ ነው፡፡ ለዚህም የራሴ የምትለውን ሥራ የመሥራት ፍላጎት አላት፡፡ ነገር ግን በወር የምታገኘው ገንዘብ ከቤት ኪራይና ከተለያዩ ወጪዎች ተርፎ መነሻ የሚሆናትን ተቀማጭ የምታስቀርለት አይደለም፡፡ በዚያ ላይ በሕመም አልያም በሌላ አጋጣሚ አንድ ቀን ከሥራ መቅረት የሁለት ቀን ደመወዝ የሚያስቀጣ ሲሆን፣ በተመሳሳይ አጋጣሚዎች ተቆራርጦና አንሶ የሚደርሳት ደሞዟ ለምንም የማይሆናት ዓይነት እንደሆነም ትናገራለች፡፡

       ‹‹አምስት ዓመት ሲሞላን ጥሩ የሥራ ልምድ ይፃፍልናል፣ የአገልግሎትም ይከፈለናል፡፡ እኔ አምስት ዓመት ሲሞላኝ እስከ 6000 ብር ድረስ የአገልግሎት ላገኝ እችላለሁ፡፡ ይህንንም መነሻ ገንዘብ አድርጎ የመሥራት ፍላጎት ስላለኝ አምስት ዓመት እስኪሞላኝ እየጠበቅኩ ነው፤›› የምትለው ዓለምነሽ፣ ሕይወቴን ይቀይርልኛል ብላ የምትጠብቀውን 6000 ብር መነሻ ገንዘብ ልታደርገው እንዳሰበች ትናገራለች፡፡ እንደ ዓለምነሽ ያሉ አማራጭ የሌላቸው በአገራቸው እንደ ‹‹ሁለተኛ ዜጋ›› ተቆጥረው በዝቅተኛ ክፍያ ጉልበታቸው የሚበዘበዘውማ ሕይወታቸውን የሚቀይርላቸውን 6000 ብር ሲጠባበቁ አምስት ዓመት ሊሞላቸው ወራት ብቻ ቀርቷቸዋል፡፡ 

       የኢትዮጵያን ዕድገት ከሚፈታተኑ ማነቆዎች መካከል አንዱና ዋነኛው ሥራ አጥነት መሆኑ ከማንም የተደበቀ አይደለም፡፡  ስለ ሥራ ያለው አመለካከት እምብዛም ነው እየተባለ የሚታማው ማኅበረሰቡ ያለው የሥራ ዕድል እጥረት አመለካከቱን በመጠኑም ቢሆን የቀየረው ይመስላል፡፡ ዝቅተኛ ተብለው በሚታሰቡ የሥራ መስኮች ለመቀጠር ብዙዎች ክብሬን ይሉ ነበር፡፡ ተላላኪ፣ አልያም የፅዳት ሠራተኛ ሆኖ መሥራትን ያናንቁበት የነበረው ጊዜ ግን አሁን ላይ ተቀይሯል፡፡ ዋናው ነገር ሥራ ማግኘቱ ብቻ ነው፡፡ የልጁ ሥራ የማግኘት ጉዳይ የማያሳስበው ወላጅ፣ የማይጨነቅ ተማሪ የለም፡፡ በአሁኑ ወቅት በጥሩ ውጤት ተመርቆ ከኮሌጅ መውጣት ብቻ ሥራ ለማግኘት ዋስትና አይሆንም፡፡ ሥራ ማግኘት ጥረት ሳይሆን  የዕድል ጉዳይ እስከመሆን የደረሰ አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑም ይወሳል፡፡

       ላለው ጠባብ የሥራ ዕድል አብዛኛውን የሰው ኃይል ቀጥሮ ለማሠራት ዕድል ያለው የግሉ ዘርፍ አለማደግና ሌሎች የተለያዩ ነገሮች በምክንያትነት ይጠቀሳሉ፡፡ ካደጉት አገሮች በተቃራኒ በኢትዮጵያ ብዙኃኑን ቀጥሮ የሚያሠራው መንግሥት ነው፡፡ የግሉ ዘርፍ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ገና ብዙ እንደሚቀረው ግልፅ ነው፡፡ ይህም መሥራት የሚችለው ሰው ኃይል ሥራ ፈቶ እንዲቀመጥ እያደረገው ይገኛል፡፡

       ከፍተኛ የሥራ አጦች ቁጥር ካለባቸው አገሮች ከቀዳሚዎቹ በምትጠቀሰው ኢትዮጵያ ከሁለት አሠርታት በላይ የተመዘገበው የሥራ አጦች ቁጥርም ይህንን እውነታ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ በአገሪቱ ከፍተኛው የሥራ አጥ ቁጥር የተመዘገበው እ.ኤ.አ በ1999 ሲሆን፣ ከጠቅላላ የሰው ኃይል የነበረው ድርሻ 26.4 በመቶ ነበር፡፡ ይህ ቁጥር እ.ኤ.አ በ2014 ወደ 17.4 በመቶ፣ እ.ኤ.አ በ2015 ደግሞ ወደ 16.8 በመቶ መቀነስ መቻሉን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

        የሥራ አጦች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መምጣቱ ይበልታ ቢያስገኝም በሥራ መሰማራት ከሚችለው የሰው ኃይል ውስጥ 16.8 በመቶ የሚሆነው ሥራ አጥ መሆኑ ግን በቀላል የሚታይ አይደለም፡፡ ካለው የሕዝብ ቁጥር አንፃር ሲሰላም ቁጥሩ በአገሪቱ ኢኮኖሚ ውድቀትና መቃናት ላይ የጎላ ሚና እንዳለው መገንዘብ ይቻላል፡፡ ያለው የሥራ ዕድልና የሥራ ፈላጊ ቁጥር አለመመጣጠን ለቀጣሪዎች የተሻለ ዕድል ሲሰጥ እንደ ዓለምነሽ ያሉ ተቀጣሪዎች ደግሞ በዝቅተኛ ደመወዝ እንዲበዘበዙ፣ ባልተመቸ የሥራ ከባቢ እንዲንገላቱ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡

  የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ  

  እንዲህ ያሉ ኢፍትሐዊነቶችን መስመር የሚያስይዙ በአሠሪና ሠራተኛ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያስተዳድሩ የአሠሪና ሠራተኛ ሕጎች በተለያዩ ጊዜ ፀድቀው በሥራ ላይ ውለዋል፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ በመሠረቱ በአሠሪና በሠራተኛ መካከል በሚደረግ  የሥራ ውል ላይ ተመሥርቶ የሚፈጠሩ ግንኙነቶችን የሚመራ፣ የሚቆጣጠር  ነው፡፡ ‹‹የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ ከሌሎች የሕግ ዘርፎች አንጻር ሲታይ የቅርብ ዘመን ታሪክ አላቸው ከሚባሉ ሕጎች የሚመደብ ነው፡፡ ከመነሻው የካፒታሊስቱን ሥርዓት ተከትሎ በሠራተኞች ላይ ይደርስ የነበረውን አስከፊ ብዝበዛና የሥራ ሁኔታ ለማስቀረት ሲባል የተመሠረተ የሕግ ክፍል ነው፤›› ይላል የቀድሞ የፍትሕ ሚኒስቴር የሕግ ጥናትና ማስረፅ ክፍል በማኅበራዊ ድረ ገጹ ስለአሠሪና ሠራተኛ ሕጉን አመጣጥ አስመልክቶ ባቀረበው ማብራሪያ፡፡

       በአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ አዋጅ ቁጥር 377/1996 መሠረት የአሠሪውና የሠራተኛው ጠቅላላ ግዴታዎች በሁለት አንቀጾች ተካተው ይገኛሉ፡፡ አንቀጽ 12 የአሠሪውን፣ አንቀጽ 13 ደግሞ የሠራተኛውን ግዴታዎች ይዘረዝራሉ፡፡ በአንቀጽ 13 ሥር የተዘረዘሩ የሠራተኛው ግዴታዎች ሲሆኑ፣ ሠራተኛው ሥራውን ራሱ የመሥራት፣ በሥራ ቦታ በአካልና በአዕምሮ  ብቁ ሆኖ የመገኘትና ትዕዛዝን የመፈጸም፣ ለሥራ የሚገለገልባቸውን መሣሪያዎችና ዕቃዎችን ሁሉ በጥንቃቄ የመጠበቅ፣ የንብረትና የሕይወት አደጋ እንዳይደርስ ወይም አስጊ ሁኔታ ሲፈጠር ተገቢውን ዕርዳታ የመስጠትና የድርጅቱን ጥቅም የሚነኩ ሌሎች ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ወዲያውኑ ለአሠሪው የማስታወቅ እንዲሁም የአዋጁን፣ የኅብረት ስምምነትን፣ የሥራ ደንብንና በሕግ መሠረት የሚተላለፉ መመሪያዎችንና ትዕዛዞችን የማክበር ግዴታዎች አሉበት፡፡

       የአሠሪውን ግዴታዎች በዝርዝር የሚያስቀምጠው አንቀጽ 12 ደግሞ በዘጠኝ ንዑስ አንቀጾች ተከፋፍሎ ቀርቧል፡፡ አሠሪው ሥራ የመስጠትና ውሉ በሌላ ሁኔታ ካልገለጸ በስተቀር መሣሪያና ጥሬ ዕቃ የማቅረብ ግዴታ፣ ደሞዝና ሌሎች ክፍያዎችን የመፈጸም፣ የሠራተኛውን ሰብአዊ ክብር፣ ከሥራ ጋር የተያያዘ ጤንነትና ደኅንነት የመጠበቅ ግዴታዎች ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡ 

       የሁለቱንም ወገኖች መብትና ግዴታዎች በዝርዝር የሚያስቀምጠው አዋጁ ምን ያህል ተፈፃሚ ነው የሚለው ጉዳይ ግን አጠያያቂ ነው፡፡ በተለይም በአሁኑ ወቅት የሠራተኞች መብት አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱ ሁሉም የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ ግብርና መር የሆነውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ወደ ኢንዱስትሪ ለመቀየር በሚደረገው ጥረት መንግሥት የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንቶችን የሚያበረታቱ ፖሊሲዎች ቀርፆ ባለሀብቶችን እየሳበ ይገኛል፡፡ ጥቂት የማይባሉ ተቋማትም ትልልቅ ፋብሪካዎቻቸውን ኢትዮጵያ ውስጥ እያቋቋሙ ይገኛሉ፡፡ በተለይም በጨርቃ ጨርቅ የተሰማሩ ትልልቅ ተቋማት አገሪቱን መዳረሻቸው እያደረጉ ነው፡፡

       መሰል ተቋማትን ለመሳብ ምቹ የኢንዱስትሪ መንደሮችን ከመገንባት ጀምሮ ጠንካራ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይተዋል፣ እየተሠሩም ይገኛሉ፡፡ ከዚህ ባሻገርም በአገሪቱ ያለው ‹‹ርካሽ የሰው›› ኃይል የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ኢትዮጵያን እንዲመርጡ እያደረገ ይገኛል፡፡ ይህ ለብዙኃኑ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ትልቅ እምነት የተጣለበት ቢሆንም ዜጎችን ለብዝበዛ እያጋለጠ እንደሚገኝ ሲነገር ሰነባብቷል፡፡ ወርኃዊ ደሞዛቸው ዝቅተኛ መሆን ዋናውና አሳሳቢው ጉዳይ ሲሆን፣ ሌሎችም የመብት ጥሰቶች መኖራቸውን ሪፖርተር ቃሊቲ አካባቢ በሚገኘው የኢንዱስትሪ መንደር ተገኝቶ ያረጋገጠው ጉዳይ ነው፡፡

       ‹‹የሠራተኞች መብት እየተረገጠ ያለው ሠራተኞች በማኅበር ተደራጅተው መብታቸውን መጠየቅ ባለመቻላቸው ነው፡፡ በኢንዱስትሪ መንደር ያሉ ሠራተኞችን ማደራጀት በጣም አስቸጋሪ ነው፤›› የሚሉት የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌደሬሽን (ኢሠማኮ) ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች የሠራተኛ ማኅበር መመሥረት ባለመቻላቸው የሚደርስባቸውን የመብት ጥሰት ማስቀረት እንዳልተቻለ ይናገራሉ፡፡

       ‹‹የመደራጀት መብት ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው፡፡ አስፈፃሚው አካል ይህንን ማየት መፈተሸና አሠሪዎችን መጠየቅ አለት፤›› የሚሉት አቶ ካሳሁን፣ አሠሪዎች የሠራተኛ ማኅበር እንዳይመሠረት ሲሉ ‹‹ጊዜ የለንም አሁን አጣዳፊ ሥራ ላይ ነን፤›› በሚል ሰበባሰበብ እየፈጠሩ እንደሚጠፉ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ካሳሁን ገለፃ፣ አሠሪዎች የሠራተኛ ማኅበር እንዳይመሠረት ሲሉ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም፡፡ ‹‹አጣዳፊ ሥራ ላይ ነን›› የሚለውን ምክንያት በተደጋጋሚ የሚጠቀሙበት ቢሆንም፣ ሠራተኞች በዕረፍት ቀናቸው ለመሠረቷቸው ማኅበራት ዕውቅና አይሰጡም፡፡

       ኮንፌደሬሽኑ ዱከም አካባቢ በሚገኙ ኢንዱስትሪዎች የሚሠሩ ሠራተኞችን በብዛት ያደራጀ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ በመበተናቸው የቀሩት ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ የየማኅበሩ አባላት የነበሩትም በሰበብ አስባቡ ከሥራ ገበታቸው ሲፈናቀሉ፣ በተቀሩት ላይ ደግሞ በአሠሪዎች ከፍተኛ ተፅዕኖ እየደረሰባቸው ይገኛሉ፡፡ ይህንን የተመለከቱ አብዛኞችም ማኅበሩን ትተው ተበትነዋል፡፡ ‹‹ለምን ብለን ስናናግራቸው ለራሳቸው ጊዜ አቀላጥፈው የሚናገሩትን ቋንቋ አንችልም የሚሉ የውጭ አገር ባለሀብቶች አሉ፤›› ብለዋል አቶ ካሳሁን፡፡

       በዚህ እልህ አስጨራሽ በሆነው የሠራተኞች ማኅበር የማደራጀት ትግል ውስጥ ኮንፌደሬሽኑ ማኅበራትን ለማደራጀት የሚያደረገውን ጥረት አልተወም፡፡ ‹‹አሁን ቦሌ ለሚ ላይ ለማደራጀት እየሞከርን ነው፡፡ በአንድ ፋብሪካ ውስጥ 4000 አባላት ያሉት አንድ ማኅበር አደራጅተናል፤›› ይላሉ አቶ ካሳሁን፡፡

       ከዚህ ባሻገርም ሠራተኞች የሚከፈላቸው ዝቅተኛ ደሞዝ ለማስተካከል ጥረት ተጀምሯል፡፡ የዓለም የሠራተኞች ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ዋና ጸሐፊ ሻረን ባሮውም ከጥር 9 ቀን 2010 .. ጀምሮ በአዲስ አበባ ለሁለት ቀናት የተካሄደውን የአፍሪካ ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ፎረም በከፈቱበት ወቅት ኢትዮጵያ የሠራተኞች ብዝበዛ የሚደረግባት አገር መሆኗን ገልፀዋል፡፡ ዋና ፀሐፊዋ በከተማው ከሚገኙ ፋብሪካዎች መካከል አንደኛውን በጎበኙበት ወቅት በወር 600 ብር እየተከፈላት የምትሠራ አንዲት እናት አነጋግረው እንደነበር፣ የሚከፈላት ደመወዝም ለኑሮ የማይበቃ መሆኑንና ክፍያው ከጉልበት ብዝበዛ የሚመደብ መሆኑን በወቅቱ ገልፀዋል፡፡ ለዚህም መንግሥት የመሰል ሠራተኞችን ሕይወት ለማሻሻል ዝቅተኛውን የደመወዝ ዕርከን መደንገግ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

       ‹‹ካለፈው የበጀት ዓመት ጀምሮ ስለ ዝቅተኛው የደመወዝ ወለል ጉዳይ አንስተን እየተነጋገርንበት ነው፡፡ ይህንንም እውን ለማድረግ በሚመለከተው አካል ጥናት እያስደረግን እንገኛለን፤›› በማለት አቶ ካሳሁን እንደ ዓለምነሽ ያሉ ሠራተኞችን ከብዝበዛ ያድናል ብለው ያመኑበትን ዝቅተኛውን የደመወዝ ወለል የማውጣት ጉዳይ ቀደም ብሎ መጀመሩን ይናገራሉ፡፡

  spot_img
  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img

  ተዛማጅ ጽሑፎች
  ተዛማጅ

  [በተቋሙ ሠራተኞች የተወከሉ አንድ ባልደረባ ሚኒስትሩን ለማነጋገር ቀጠሮ ይዘው ወደ ቢሯቸው ገቡ]

  ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም ሰላም ... ተቀመጥ! አመሠግናለሁ ክቡር ሚኒስትር!...

  የጉራጌ ዞን ጥያቄና የክላስተር አደረጃጀት የገጠመው ተቃውሞ

  መንግሥት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል አካል የነበሩ ዞኖችንና...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን ወደ 55 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ያስገደደው ምክንያት ምንድን ነው?

  ባለፈው ቅዳሜ ጠቅላላ ጉባዔውን ያካሄደው አዋሽ ባንክ የ43 ቢሊዮን...

  አቢሲኒያ ባንክ ካለፈው ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው ትርፍ በማግኘት አዲስ ታሪክ አስመዘገበ

  አቢሲኒያ ባንክ ከቀደሚ የሒሳብ ዓመት የ127 በመቶ ብልጫ ያለው...