Friday, December 1, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የምርጫው ጥርጊያ ጎዳና ይስተካከል!

የዘንድሮ ጠቅላላ ምርጫ ሊካሄድ የቀሩት ውስን ቀናት ናቸው፡፡ ለአምስተኛ ጊዜ የሚካሄደው ይህ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ፣ የሁሉንም ባለድርሻ አካላትና የመላ አገሪቱን ሕዝብ ርብርብ ይጠይቃል፡፡ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ ሲጠናቀቅ ውጤቱም ሁሉንም ወገን ከሞላ ጎደል የሚያስማማ ይሆናል፡፡ ከዚህ በተቃራኒ ሲሆን ደግሞ የሚያስከትለው ችግር አስከፊ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል ነው የምርጫው ጥርጊያ ጎዳና መስተካከል አለበት የሚባለው፡፡

የምርጫው ጥርጊያ ጎዳና የተስተካከለ እንዲሆን መንግሥትን ጨምሮ በርካታ ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ ሊጫወቱ ይገባል፡፡ ምርጫው ነፃ፣ ግልጽ፣ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ መሆን አለበት ሲባል የበርካታ ባለድርሻ አካላትን ተሳትፎ የግድ ይላል፡፡ አገር የማስተዳደር ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ምርጫው በሚፈለገው መንገድ ከእንከን የፀዳ እንዲሆን ትልቅ ኃላፊነት አለበት፡፡ መንግሥትን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ በዚህ ምርጫ ከሌሎች ተወዳሪ ፓርቲዎች እኩል የሕዝብ ድምፅ ለማግኘት የሚወዳደር ቢሆንም፣ ሌሎቹ ፓርቲዎች ፍትሐዊ በሆነ መንገድ በምርጫው ተፎካካሪ እንዲሆኑ ለምርጫው ዴሞክራሲያዊነት ግንባር ቀደም መሆን ይኖርበታል፡፡

ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ አልጋ በአልጋ እንዳልሆነ አውቀው ሒደቱ የሰመረ እንዲሆን የሚፈለግባቸውን አስተዋጽኦ በፅናት ሊያበረክቱ ይገባል፡፡ ምርጫውን የሚመራው ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ሁኔታ በገለልተኝነት ምርጫውን የመምራት ኃላፊነት መወጣት አለበት፡፡ ምርጫውን የሚታዘቡ ግለሰቦችና የሲቪል ማኅበረሰቦች ኃላፊነታቸውን በብቃትና በታማኝነት ሊወጡ ይገባል፡፡ የመገናኛ ብዙኃን የሙያ ሥነ ምግባር በሚፈቅደው መሠረት በሀቀኝነትና በገለልተኝነት ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡

ይህ የዘንድሮ ምርጫ አገራችን ወደ አንድ ከፍታ የምትሸጋገርበት ይሆን ዘንድ፣ የሚመለከታቸው ባድርሻ አካላት በትጋት ሥራቸውን ሊያከናውኑ ይገባል ሲባል፣ የሕዝቡን የመምረጥ ነፃነት ለማረጋገጥ ሲባል መሆኑን ግንዛቤ መያዝ ተገቢ ነው፡፡ ሕዝቡ ይጠቅመኛል የሚለውን ፓርቲ ወይም ዕጩ በነፃነት እንዲመርጥ የሚፈለግ ከሆነ፣ በተለይ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ሕዝቡ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታው የተሳካ ሆኖ በመረጠው የፖለቲካ ፓርቲ መተዳደር ይፈልጋል ሲባል፣ ምርጫ እንዲያው ዘው ተብሎ የሚገባበት አይደለም፡፡ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ሥራው በምርጫ ወቅት በሚወጣ የጊዜ ሰሌዳ የታጠረ ሳይሆን፣ አምስት ዓመት ሙሉ የሚለፋበት ተግባር ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሕዝቡን ድምፅ ሲፈልጉ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚና በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ያሉዋቸውን አማራጮች በዝርዝር ማቅረብና ሕዝቡን ማሳመን የግድ ይላቸዋል፡፡ የራሳቸውን ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ተንትነው ሳያቀርቡ በምርጫ ወቅት የሚተራመሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በባዶ ሜዳ ቢውረገረጉ ፋይዳ የላቸውም፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አስተዋጽኦም አይኖራቸውም፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በሰላማዊ ትግሉ ውስጥ ፋይዳቸው የሚለካው ገዥው ፓርቲን ወይም መንግሥትን በማብጠልጠላቸው ወይም የሚወጡ ፖሊሲዎችን በመተቸታቸው ሳይሆን፣ አማራጭ አቅርበው ተፎካካሪያቸውን በመብለጣቸው ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ የሠለጠነ የፖለቲካ አካሄድ በርካታ መሰናክሎችና ጥልፍልፎሾች የበዙበት ቢሆንም፣ በፅናት ለመታገል የሚያስችላቸው ዓላማና ፕሮግራም ያስፈልጋቸዋል፡፡ ሕዝብን ለአንድ ዓላማ ከጎን ማሠለፍ የሚቻለው መራር የሆኑ ፈተናዎችን በብቃት መቋቋም ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ምርጫ በደረሰ ቁጥር ግር ብሎ መነሳት አቧራ ከማስነሳት ያለፈ ፋይዳ የለውም፡፡ ለዚህም ነው በዘንድሮ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ኃይሎች ራሳቸውን ለዴሞክራሲና ለሰላማዊ ትግል ያዘጋጁ ቆራጦች መሆን አለባቸው የሚባለው፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ከማገዛቸውም በላይ፣ የመራጩን ሕዝብ ይሁንታ ለማግኘት ይችላሉ፡፡ ተዓማኒነት በመፍጠራቸውም አገር ለመምራት ይታጫሉ፡፡

ምርጫውን ከተቻለ በማምታታት ለማሸነፍ፣ ካልተቻለ ደግሞ ዋጋ በማሳጣት የማይፈለግ ምሥል ለመፍጠር የሚፈልጉ የፖለቲካ ኃይሎች ከጅምሩ ችግር አለባቸው፡፡ በመጀመርያ ከራሳቸው በስተቀር ለሌሎች የፖለቲካ ተዋንያን ዕውቅና አይሰጡም፡፡ ዴሞክራሲያዊው ሒደቱ ተቀልብሶ ሁከትና ግርግር የሚፈጥሩ ተግባራትን ይቀምራሉ፡፡ ሕዝቡ በምርጫው ላይ ጥርጣሬ እንዲኖረውና ለእነሱ የማይመች ውጤት ሲመጣ ደግሞ ለብጥብጥ እንዲነሳሳ ያደርጋሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ፀረ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴ ለአገራችን ሕዝብ አይጠቅመውም፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች ሙሉ ጊዜያቸውን ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በማዋል፣ ሕዝቡ የእነሱን አማራጭ እንዲሸምት ቢያንቀሳቅሱት ይመረጣል፡፡ ‹‹የትም ፍጪው ዱቄቱን አምጪው›› የሚለው የከሰረ የፖለቲካ ሥልት በዚህ ዘመን ፈላጊ ስለሌለው፣ ለዴሞክራሲያዊ ሒደት መረባረቡ ይበጃል፡፡ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አገርን ኪሳራ ውስጥ የሚከት የፖለቲካ ሥልት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አይበጅም፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው በሚያደርጉት ተሳትፎ መሰናክሎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ማወቅ አለባቸው፡፡ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ይሆናል ብለው ሲገቡ፣ ከእነሱ የሚፈለገውን አስተዋጽኦ ካላበረከቱ ከሌላው ምንም መጠበቅ አይችሉም፡፡ በተቃራኒው ወገን ከቆሙ ኃይሎች ጋር በሚያደርጉት ፉክክር ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚበጁ ተግባራትን እያከናወኑ የተሻሉ መሆናቸውን ማሳየት ሲገባቸው፣ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባራት ውስጥ ተዘፍቀው ከተገኙ ግን የምርጫውን ጥርጊያ መንገድ   እያበላሹት መሆኑን መገንዘብ አለባቸው፡፡ ባለፉት አራት ምርጫዎች የታዩት ደካማ ጎኖች በወጉ ተጠንተው የተሻለ ነገር ለማምጣት ጥረት ካልተደረገ፣ የዓመታት ድክመትን እየደገሙ በዚያው ጎዳና ላይ መመላለስ ጥቅም የለውም፡፡ ለዚህም ነው የዘንድሮ ምርጫ ጥርጊያ ጎዳናው የተስተካከለ ይሁን የሚባለው፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ካለፉት አሳዛኝ ስህተቶች በመማር የተሻለ ውጤት ለማግኘት መነሳት አለባቸው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወጣቶች የሚቀረፁባቸው የልቀት ማዕከላትና የዴሞክራሲ ማበልፀጊያ መድረኮች መሆን ሲገባቸው፣ መወዛገቢያ በመሆን ከቀጠሉ ለአገርም አይበጁም፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታም አይረቡም፡፡

የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ አንደኛው አካል የሆነው ምርጫ ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሲፈለግ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሸፍጥ፣ ከአሉባልታና ከፀረ ዴሞክራሲ ተግባራት ሊፀዱ ይገባል፡፡ የፓርቲ ፖለቲካ ሥራው ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ ሐሳብን በነፃነት ለመግለጽ መብት ማበብና ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ አገር እንድትኖር አሳማኝ መሠረት የሚጥል መሆን አለበት፡፡ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲ መሆን አለበት ሲባልም ለአገር ህልውና ጠቃሚ መሆኑ ተገቢው ግንዛቤ ሊያዝበት ይገባል፡፡ በጥላቻና በመፈራረጅ ላይ የተመሠረተው የፖለቲካ ፓርቲዎች አላስፈላጊ ንትርክ የሚወልደው ግትርነትና ጽንፈኝነት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ፈፅሞ ፀር ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ከንቱ አባዜ ደግሞ በምርጫው ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ በሕዝቡ ውስጥ ፍርኃት ያነግሳል፡፡ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዳይኖር ያደርጋል፡፡ የአገር ገጽታን ያበላሻል፡፡ ስለዚህ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ እንዲካሄድ ጥርጊያ መንገዱ በሁሉም ወገኖች ይስተካከል፡፡

ተወደደም ተጠላም ኢትዮጵያ በአፍሪካ በኢኮኖሚ ግስጋሴዋ አንቱ በመባል ላይ ያለች አገር መሆኗን ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እያስተጋቡ ነው፡፡ ይህ ኢኮኖሚያዊ ዕመርታ በፖለቲካውም መስክ መታየት አለበት፡፡ በአፍሪካ ትልቅ ስም ያስገኘው የኢኮኖሚ ዕድገት ተስፋ በፖለቲካው ጭምር ካልታገዘ በአንድ እጅ እንደማጨብጨብ ይቆጠራል፡፡ ኢትዮጵያ ለዘመናት ስትዳክርበት ወደነበረው የድህነት አረንቋ እንዳትመለስና ሰላምና መረጋጋት የሰፈነባት ተምሳሌታዊት አገር እንድትሆን፣ ይህ ምርጫ እንደ መንደርደሪያ እንዲያገለግል የሁሉም ወገኖች ርብርብ መኖር አለበት፡፡ ምርጫው ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ በሰላም እንዲጠናቀቅ ሲፈለግ፣ የጥርጊያ ጎዳናው መመቻቸት ከምንም ነገር በላይ ተፈላጊ ነው፡፡ አመፅና ብጥብጥ ለአገሪቱም ሆነ ለሕዝቧ አይጠቅምም፡፡ ዴሞክራሲ በሁከትና በግርግር አይሰፍንም፡፡ በመሆኑም የአገሪቱን ሕዝብ ፍላጎት እንዲያማክል ለምርጫው ስኬታማነት ርብርብ ይደረግ፡፡ ምርጫውም በተስተካከለ ጥርጊያ ጎዳና ላይ ይከናወን፡፡

በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ሥልጣን የሚያዘው በዴሞክራሲያዊ ምርጫ ነው፡፡ ለምርጫ የሚደረገው ውድድርም በዚህ መርህና ዕምነት ላይ መመሥረት አለበት፡፡ በምርጫው ሒደት የመገናኛ ብዙኃን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ዕጩ ተወዳዳሪዎችና የምርጫ አስፈጻሚ አካላት የምርጫ የሥነ ምግባር ደንቦችን በመከተል አንዱ የሌላውን መብትና ነፃነት ሳይነኩ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መንቀሳቀስ አለባቸው፡፡ ይህም ለምርጫው ሰላማዊነትና ዴሞክራሲያዊነት ይጠቅማል፡፡ ምርጫው ነፃ፣ ግልጽ፣ ፍትሐዊ፣ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን ሲፈለግ የእነዚህ አካላት መናበብ ያስፈልጋል፡፡ የፀጥታና የሕግ አስከባሪ አካላት ገለልተኝነት ሲታከልበት ደግሞ ምርጫው ይናፍቃል፡፡ መራጩ ሕዝብም በነፃነት የፈለገውን ይመርጣል፡፡ የምርጫው ጥርጊያ ጎዳና ይስተካከል የሚባለው ለዚህ ነው!

 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...

ሀብቱንና ትርፉን እያሳደገ የቀጠለው አዋሽ ባንክ

አዋሽ ባንክ በአዲስ አበባ ከተማ አዲስ ዋና መሥሪያ ቤት...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ድጋፍና ተቃውሞ እኩል ይስተናገዱ!

ኢትዮጵያ ውስጥ ለረዥም ዓመታት ለመንግሥት ከሚቀርቡ ጥያቄዎች መካከል አንዱ የመብት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ ዜጎች ተፈጥሯዊም ሆኑ ሕጋዊ መብቶቻቸው እንዲከበሩላቸው ለመንግሥት ጥያቄ ሲያቀርቡ፣ ጥያቄው የቀረበለት...

ፖለቲካዊ ችግሮች ፖለቲካዊ መፍትሔ ይፈለግላቸው!

መንግሥት ከኦነግ ሸኔ ጋር በታንዛኒያ ዳሬሰላም ከተማ ሲያካሂድ የነበረው ንግግር ያለ ውጤት መጠናቀቁን ካስታወቀ በኋላ፣ በኦሮሚያ ክልልም ሆነ በሌሎች ቦታዎች ሰላም ለማስፈን የነበረው ተስፋ...

ኢትዮጵያን ከግጭት ቀጣናነት ማላቀቅ የግድ ነው!

ፍሬ አልባ ፖለቲካዊ ልዩነቶች ወደ ግጭት እያመሩ ለአገርና ለሕዝብ የማያባራ መከራ ሲያቀባብሉ፣ ከትናንት ስህተቶች ለመማር ፈቃደኛ ያልሆኑ ፖለቲከኞችና ተከታዮቻቸው በእሳት ላይ ቤንዚን እያርከፈከፉ ጠማማ...