Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሰፋፊ እርሻዎች ልማት በችግር መተብተቡ ተጠቆመ

የሰፋፊ እርሻዎች ልማት በችግር መተብተቡ ተጠቆመ

ቀን:

–  ለኢንቨስተሮች ከተሰጠው 2.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ሥራ የተጀመረው በ840 ሺሕ ሔክታር ብቻ ነው

በኢትዮጵያ ግብርና ዘርፍ ከፍተኛ ለውጥ ያመጣል ተብሎ ብዙ የተነገረለት የሜካናይዝድ እርሻዎች ልማት በችግሮች መተብተቡ ተገለጸ፡፡ የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ ለኢንቨስተሮች ከሰጠው 2.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ወደ ልማት የገባው 840 ሺሕ ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከክልሎች ሰፋፊ የእርሻ መሬት በውክልና እየተረከበ ለ86 የውጭና የአገር ውስጥ ኩባያዎች 2.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት በዝቅተኛ ሊዝ ክፍያ መስጠቱ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን ኩባንያዎቹ በራሳቸው የውስጥ አቅምና መሬቶቻቸው በሚገኙባቸው ክልሎች ችግር ምክንያት፣ በሚፈለገው መጠን በሚገባ ካለማልማታቸው በተጨማሪ የጀመሩትም በከፍተኛ ችግር ታንቀው እንደሚገኙ ተገልጿል፡፡

የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት ግንቦት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንት መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ በተጠራው ስብሰባ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አበራ ሙላት እንደገለጹት፣ በጋምቤላና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች የመልካም አስተዳደር ችግር፣ ሙስና፣ የመሬት ካርታ መደራረብ፣ ሕገወጥ የመሬት ወረራ፣ ምርት ማቃጠል፣ የፀጥታ ችግርና የለማ መሬት በኃይል መቀማት ዋነኛ ችግሮች ሆነው ተለይተዋል፡፡ አቶ አበራ ጨምረው እንደገለጹት፣ በደቡብ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን ይህ ችግር የሚታይ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ የኦሞ ወንዝ ድልድይ ተገንብቶ ሥራ ባለመጀመሩ በአካባቢው ኢንቨስት ለማድረግ በገቡ ኢንቨስተሮች ላይ ከፍተኛ ችግር ተፈጥሯል፡፡

በአፋር ክልል ያለው ችግር ከዚህ የተለየ መሆኑንና በተለይ የመሬት ፖሊሲ ተግባራዊ ባለመሆኑ ችግር መፈጠሩን አቶ አበራ ገልጸዋል፡፡ ሕገ መንግሥቱ መሬት የሕዝብና የመንግሥት ነው ቢልም በአፋር ክልል ግን በአብዛኛው መሬት በጎሳ መሪዎች የተያዘ በመሆኑ፣ ኢንቨስተሮች መሬት ከመንግሥት ሳይሆን ከጎሳ መሪዎች እንዲከራዩ መገደዳቸውን ጠቅሰዋል፡፡ ይህ ደግሞ ኢንቨስተሮች ከባንኮች ብድር ለማግኘት እንዳይችሉ ከፍተኛ እንቅፋት እየፈጠረ መሆኑ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡

አቶ አበራ የመሬት ፖሊሲውን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችለው መመርያ ለአፋር ክልላዊ መንግሥት ምክር ቤት ቀርቧል ብለዋል፡፡ የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ወንድይራድ በጉባዔው ላይ እንደተናገሩት፣ መንግሥት ሊፈታቸው የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት ዝግጁ ነው፡፡ ባለሀብቶችም በራሳቸው በኩል ያለባቸውን ችግሮች በመፍታት ወደ ሥራ ሊገቡ ይገባል ብለዋል፡፡

በስብሰባው ላይ ተሳታፊ የነበሩ ኢንቨስተሮች አቶ አበራ ካቀረቧቸው በተጨማሪ ሌሎች ችግሮችም እንዳሉ አንስተዋል፡፡ የደቡብ ኦሞ እርሻ አምራቾች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ሐዱሽ ግርማይ፣ በአፋር ክልል ከመሬት ፖሊሲው ባልተናነሰ ከአዋሽ እስከ ገዋኔ ያለው መሬት ጨዋማ መሆን ከፍተኛ ችግር ፈጥሯል ብለዋል፡፡ ሰሜን ሸዋ አካባቢ ዝናብ ዘንቦ የመሬቱን ጨዋማ ክፍል እስካላጠበ ድረስ ልማት ማካሄድ አስቸጋሪ በመሆኑ፣ መንግሥት ወጥ በሆነ መንገድ መሬቱን ማከም ይኖርበታል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

አቶ ሐዱሽ እንደሚሉት የደቡብ ኦሞ እርሻ አምራቾች ማኅበር፣ ወቅቱ የጥጥ ዘር መሸጫ እንደመሆኑ መጠን እስካሁን ድረስ አንድ ሺሕ ኩንታል የጥጥ ዘር መሸጥ ነበረበት፡፡ ነገር ግን ማኅበሩ ሽያጭ ያከናወነው 40 ኩንታል ብቻ በመሆኑ በሚቀጥለው የምርት ዘመን ኢንቨስተሮች የጥጥ ልማት ለማካሄድ እንደማይፈልጉ የሚያሳይ ምልክት ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡ በዚህ ምክንያት በዘርፉ ያለውን ችግር ለመፍታት መንግሥት መንቀሳቀስ እንደሚኖርበት አሳስበዋል፡፡

ከቤንች ማጂ ዞን ጉራ ፈርዳ አካባቢ የመጡ አንድ ኢንቨስተር በበኩላቸው፣ በአካባቢው አስቸጋሪ የቡና በሽታ መግባቱን ገልጸዋል፡፡ ይህንን የቡና በሽታ መንግሥት በተጠናከረ መንገድ መፍታት ካልቻለ  አስቸጋሪ ሁኔታ እንደሚፈጥር አስጠንቅቀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በተለይ ጋምቤላ ክልል ማጀንግ ዞንና አጎራባች በሆነው ሸካ ዞን፣ እንዲሁም የቤንች ማጂ ዞን ኢንቨስተሮች በፀጥታ ችግር ላይ ያላቸውን ሥጋት አንፀባርቀዋል፡፡

አካባቢው ለምና ለሥራ አመቺ ቢሆንም የፀጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየከፋ መምጣቱን ኢንቨስተሮቹ አስገንዝበዋል፡፡ በፀጥታ መደፍረስ ምክንያት የእርሻ ጠባቂዎች እየተገደሉ፣ ለአካል ጉዳት እየተዳረጉና ሠራተኞችም እየሸሹ በመሆናቸው የደረሰ ቡና መሰብሰብ እንዳልቻሉም ጠቁመዋል፡፡ ይህ ለከፍተኛ ችግር ዳርጎናል የሚሉት የአካባቢው ኢንቨስተሮች፣ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው ጠይቀዋል፡፡

በአካባቢው ባሉት የልማት ችግሮችና የፀጥታ ጉዳይ ላይ ለመምከር የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ደሴ ዳልኬ ሰሞኑን ቴፒ ከተማ ተገኝተው ከነዋሪዎች ጋር መክረው ነበር፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች በፀጥታ ጉዳይ ላይ ጠንከር ያሉ አስተያየቶችን መሰንዘራቸውን በስብሰባው የተሳተፉ ምንጮች ገልጸዋል፡፡

አቶ ደሴ ችግሩን ከሕዝቡ ጋር ሆነው ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን በስብሰባው ወቅት መናገራቸውንም ምንጮች አክለው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...