Tuesday, October 3, 2023

ሠልፍና ተቃውሞ አልተገናኝቶም?

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኬንያ ውስጥ ለየት ባለ ሰላማዊ ሠልፉ የሚታወቀው የፓዋ 254 መሥራች በአፋስ ምዋንጊ ሰላማዊ ሠልፉን በመጠቀም ምን ያህል ተፅዕኖ መፍጠር እንደሚችል አሳይቷል፡፡ የጉዳዩ መነሻ የኬንያ የፓርላማ አባላት የደመወዝ ጭማሪ ነው፡፡ ይኼንንም ጉዳይ በመቃወም የሰብዓዊ መብት አቀንቃኝ የሆነው በአፋስ፣ ሰዎችን በማሰባሰብ ሰላማዊ ሠልፍ ይወጣሉ፡፡ የዚህ ሰላማዊ ሠልፍ አስገራሚው ጉዳይ በአፋስ አሳማዎችን ወደ ፓርላማ መውሰዱ ነበር፡፡ የበርካታ ሚዲያዎችን ቀልብ መሳብ የቻለው ይኼ ጉዳይ ለዘለቄታውም ፓርላማ አባላትን ‹‹ፒግ›› (አሳማ) የሚል መጠሪያ እንዲኖራቸው አድርጓቸዋል፡፡ የሠልፉ ተሳታፊዎች በወቅቱ የአሳማ ደም ያፈሰሱ ሲሆን፣ ፖሊሶችም በሚጠጓቸው ጊዜ እጃቸውን ወደ ላይ በማውጣት ‹ሰላማዊ ነን!› በማለትም ይገልጹ ነበር፡፡ ሠልፈኞቹ በፖሊሶች ይኼ ነው የሚባል ጥቃት ሳይደርስባቸው ሠልፉ ተጠናቀቀ፡፡ የበርካታ ሚዲያዎችን ትኩረት ማግኘቱ ለሰላማዊ ሠልፉ እንደ አንድ ዘዴ የተጠቀሙበት ሲሆን፣ በውጤቱም ለፓርላማ አባላት የደመወዝ ጭማሪው እንዳይደረግ በማሳሰብ ተጠናቋል፡፡

‹‹በሒትለርም ጊዜ የተቃውሞ ሠልፍ ነበር፤›› አሉ ስለሠልፍ ታሪክ ዓላማና ግብ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ዕውቅ የሕግ ባለሙያ፡፡ አንድን መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ከሚያስብሉት መሥፈርቶች አንዱ ለመጻፍ፣ ለመናገርና ለመደራጀት መብቶች ከለላ የሚሰጥ የሕግ ማዕቀፍ ማደራጀቱ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ እነዚህ ሕጎች በተግባራዊነታቸው ላይ እንከን እንዳይገጥማቸውና ተግባራዊ እንዲሆኑ ማድረግ መቻሉም ይጠበቃል፡፡

ሐሳብን ከመግለጽ ባሻገር በመንግሥት ላይ ተቃውሞ ማሰማትና ከተቻለም ጫና በመፍጠር በአንድ ጉዳይ ላይ ሐሳቡን እንዲለወጥ፣ አልያም አንድ ችላ ያለውን ጉዳይ አጀንዳ አድርጎ መፍትሔ እንዲሰጥ ለማስገደድ ብዙ ቦታ ላይ ጥቅም ከዋሉ ዘዴዎች አንዱ ሰላማዊ ሠልፍ ነው፡፡ በዓለማችን በተለያዩ አጋጣሚዎች ተጠቃሽ ሰላማዊ ሠልፎች የተደረጉ ሲሆን፣ ‹‹ሰላማዊ›› በመባል የሚታወቀውና ታዋቂው ማርቲን ሉተር ኪንግ ለጥቁሮች መብት ዘመን ተሻጋሪ ንግግር ያደረገበት የተቃውሞ ሠልፍ የሚጠቀስ ነው፡፡

እንዲሁም ቅኝ ገዢዋ እንግሊዝ ህንድን ለቃ እንድትወጣ ያስገደደ በዓለም ተጠቃሹ ተቃውሞ የማህተመ ጋንዲ ‹‹ሰላማዊ አለመታዘዝ›› ዘዴም እጅግ ተጠቃሽ ነው፡፡ በተቃውሞ ሠልፍና በሰላማዊ ሠልፍ መካከል ግን ልዩነት አለ፡፡

ሠልፍና የመቃወም መብት

የኢትዮጵያን የፖለቲካ ታሪክ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ጀምሮ የተከታተሉት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት እኚሁ የሕግ ምሁርና የፖለቲካ ተንታኝ፣ ‹‹በሒትለርም ጊዜ ሰላማዊ ሠልፍ ነበር፤›› ያሉበትን ምክንያት ያብራራሉ፡፡ በዓለም በአምባገነንነትና በገዳይነቱ ወደር የማይገኝለት በጀርመኑ ሒትለር ጊዜ ሠልፍ የሚደረገው በዋናነት ለድጋፍ ሳይሆን፣ ተቃውሞን ለመግለጽ መሆኑን የሚጠቁም እንደሆነም ገልጸዋል፡፡ ሐሳብን በጽሑፍና በቃል ከመግለጽ ባሻገር በተባበረ፣ በተደራጀና ግፊት ሊፈጥር በሚችል መንገድ ሐሳብን ለመግለጽ በመንግሥት ላይ፣ በኅብረተሰቡ ላይ ወይም ደግሞ በሃይማኖት ተቋም ላይ ጫና ለመፍጠር ዋነኛው መንገድ ሰላማዊ ሠልፍ መሆኑንም አስረግጠዋል፡፡ “The Right to Protest” [የመቃወም መብት] የሚሉትን የሠልፍ ዋነኛ መገለጫ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡

‹‹ሕጋዊና ሰላማዊ›› የሚሉ አገላለጾች ዋነኛ መገለጫቸው ‹‹ተቃውሞ እስከምን መሄድ ይችላል?›› ለሚለው ጥያቄ ምላሽ እንደሚሰጥ የሞከሩት ባለሙያው፣ ‹‹በምን ዓይነት መንግሥት?›› የሚለው ጥያቄ ግን አከራካሪ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በእርግጥ›› በማለት ይጀምሩና ‹‹በሕግ በሚመራ መንግሥትም ሆነ በጉልበት በሚገዛ መንግሥት ላይ የሚካሄድ ሠልፍ መጠኑም፣ ውጤቱም ይለያያል፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡ ዋነኛ የሚለየው ግን ተቃውሞ የሚያሰሙ ሠልፈኞች ጉዳይ ሳይሆን፣ ሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሚወስደው ዕርምጃ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

‹‹በእርግጥ ሕጋዊና ሰላማዊ መሆን አለበት›› በማለት መሠረታዊ ቁም ነገር አስቀምጠው፣ ‹‹ባይሆንስ መንግሥት ምን ያህል መታገስ አለበት?›› የሚለውን ጥያቄ ያነሳሉ፡፡ ለጥያቄያቸው ምላሽም፣ ሲጀምር የተወጣው ሠልፍ የተቃውሞ ከሆነ የሚፈለገውን ያህል ሰላማዊ (Non-Violent) እና ሕጋዊ (Legal) ሊሆን አይችልም የሚል ነው፡፡ መንግሥት ግን በተቻለ መጠን ቻይና ትዕግሥተኛ መሆን አለበት ይላሉ፡፡

ማስፈቀድ ወይስ ማሳወቅ?

በዓለም አቀፍ ደረጃ በተለያዩ ከተሞች ሠልፍ የሚወጣባቸው የታወቁ ሥፍራዎች አሉ፡፡ ማሳወቅ እንጂ ማስፈቀድም አያስፈልግም፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክም ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ጀምሮ በሰላማዊ ሠልፍ ተቃውሞ መግለጽ የተለመደበት አካባቢ ‹‹አብዮት አደባባይ›› በአሁኑ ወቅት መስቀል አደባባይ እየተባለ የሚጠራው ነው፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴን በመቃወም ለሠልፍ የወጣው የተቃውሞ ኃይል ሥርዓቱን ለአንዴና ለመጨረሻ የጣለው ሲሆን፣ የደርግ ደግሞ ተቃውሞን መግለጽ የሚቻልበት ጊዜ እንዳልነበረ የታሪክ ድርሳናት ይጠቁማሉ፡፡

ከደርግ ውድቀት በኋላ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን ሲመጣና በሽግግሩ መንግሥት የፀደቀው ቻርተር ላይ በሚደንቅና የመንግሥት ባለሥልጣናትን በሚያስደነግጥ ደረጃ ሰላማዊ ሠልፍን መሠረታዊ ‹‹የመቃወም መብት›› ብሎ ትልቅ ሥፍራ ነበር የተሰጠው፡፡ የሕግ ምሁሩ፣ በአሁኑ ሕገ መንግሥት ከተሰጠው ቦታ በላይም ተሰጥቶት እንደነበር ይናገራሉ፡፡

‹‹የዴሞክራሲ ጀማሪ አገር እንደ መሆናችን መጠን የሚወጣው ሠልፍ ለተቃውሞ እንደሚወጣ ይጠበቃል፤›› ያሉት ምሁሩ፣ ‹‹ኢሕአዴግ አልደግፍህም፣ አልወድህም፣ ከሥልጣን ውረድ፤›› ብሎ ለሚወጣ ሕዝብ ምላሹ በትር መሆን እንደሌለበት ያሳስባሉ፡፡ የተቃውሞ ሠልፈኞች ከመነሻው ሠልፍ መውጣት ሲፈልጉ በዓለም አቀፍ ተሞክሮም ሆነ በኢትዮጵያ (በመርህ ደረጃ) ማስፈቀድ አይጠበቅባቸውም፡፡ ማሳወቅ እንጂ፡፡ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም ቢሆን ሠልፍ ለመውጣት የማንም ፈቃድ እንዲጠየቅ አያዝም፡፡ በአዋጁ መሠረት አስቀድሞ ሠልፉ የሚደረግበትን ቦታና ጊዜ ማሳወቅ ብቻ ይጠይቃል፡፡

ከዓላማዎቹ አንደኛው ሠልፈኞች ጉዳት እንዳይደርስባቸው ለመጠበቅ፣ እንዲሁም ድንገት ሠልፈኞቹ በሕዝብና በመንግሥት ንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርሱ ለመከላከልና ለመጠበቅ እንደሆነ ምሁሩ ይናገራሉ፡፡ በተግባር ግን በኢትዮጵያ ሁለቱም አግባቦች ያላግባብ ጥቅም ላይ እያዋሉ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡

መንግሥት በተለይ ተቃዋሚዎች የሚጠሯቸው ሠልፎች ሕጋዊ ቅድመ ሁኔታዎችን እንደማያከብሩ ይከሳል፡፡ በፖሊስና በንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ ስለሚሞክሩ ፖሊሶች ራሳቸውን የመከላከል መብት እንዳላቸው፣ እንዲሁም የመንግሥትን ንብረት ከውድመት የመከላከል ኃላፊነት እንዳለበት በሚወስደው ዕርምጃ ማስተባበያ ይሰጣል፡፡

ተቃዋሚዎች በሚጠሩዋቸው የተቃውሞ ሠልፎች በተደጋጋሚ ድምፃቸውን አሰምተው በሰላም እንደሚመለሱ ይገልጻሉ፡፡ ሚያዝያ 30 ቀን 1997 በቅንጅትና በኅብረት የተጠራውን ሰላማዊ ሠልፍ እንደ ማስረጃ ያቀርባሉ፡፡

ሠልፉ ከመጠናቀቁ በፊት የጣለው በረዶ ያዘለ ከፍተኛ ዝናብ ሠልፈኞችን ባይበትነው ኖሮ እየተመመ ከነበረው ሕዝብ ብዛት አኳያ ነገሮች በሰላም ላይጠናቀቁ ይችሉ ነበር በማለት የሚከራከሩ ተንታኞች አሉ፡፡

ሚያዝያ 30 ቀን 1997 ዓ.ም. በኢትዮጵያ የተቃውሞ ታሪክ ትልቅ የሚለው ሠልፍ ሲሆን፣ ምርጫ 97 መድገም እንዳልተቻለ ሁሉ ይኼንን ዓይነት ሰላማዊ ሠልፍ ማድረግ አልተቻለም፡፡ በተመሠረተ ጊዜ ብዙም ሳይቆይ ግንቦት 25 ቀን 2005 ዓ.ም. ሰላማዊ ሠልፍ የጠራው ሰማያዊ ፓርቲ ኅብረተሰቡ ለሰላማዊ ሠልፍ ዓይኑን እንዲከፍት ማድረጉን የሚናገሩ አሉ፡፡ በእርግጥ ‹‹ድምፃችን ይሰማ›› በሚል ይካሄድ የነበረውን የሙስሊሞች ተቃውሞ አንድ ላይ ማስተናገዱ ሃይማኖትንና ፖለቲካን ያደባለቀ በመሆኑ ተገቢ አልነበረም የሚሉም አሉ፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ፣ ፓርቲያቸው ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ከአራት ጊዜ በላይ ሠልፍ መጥራቱን ይናገራሉ፡፡ መንግሥት በሕግ ማሳወቅ ይበል እንጂ በተግባር ለማስፈቀድ የተቀመጠ ተቋም በዋናነት ለመፍቀድ ሳይሆን ለመከልከል የተቀመጠ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ሠልፍ መውጣት እንዳይቻል ሕገወጥ ነው እየተባለ ሲከለከል ቆይቷል፤›› በማለት በቅርቡ በኢትዮጵያውያን ላይ አረመኔያዊ ግድያ የፈጸመውን አይኤስ የተባለውን ቡድን ለማውገዝ መንግሥት በጠራው ሠልፍ የታየው ብጥብጥ የዚሁ አፈና ውጤት እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ‹‹ቁጭቱን የሚገልጽበት ሌላ መንገድ የለም፡፡ እንዲህ ዓይነቱ አጋጣሚ ሲገኝ ተቃውሞ የከፋ እንደሚሆን ግልጽ ማሳያ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የመድረክ ምክትል ሊቀመንበር ዶ/ር መረራ ጉዲና በበኩላቸው፣ ‹‹መንግሥት አፍኖ ስለያዘው በዓመት አንድ ጊዜ አጋጣሚ ሲገኝ ወደ አመፅ የመቀየር ዕድሉ ይበዛል፤›› በማለት ከአቶ ዮናታን ሐሳብ ጋር ይስማማሉ፡፡

‹‹መንግሥት በሕግ ሠልፉን መከልከል አይችልም፡፡ በተግባር ግን ሕጉን ለመከልከል እየተጠቀመበት ነው፤›› ያሉት ዶ/ር መረራ፣ ለዚህም ምክንያቱ ፍርኃት እንደሆነ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹መንግሥት በሕዝብ ተዓማኒነት እንደሌለው ያውቃል፡፡ ስለዚህ ሠልፍ መፍቀድ ሁሉም ነገር ወደ ቀውስ እንዲያመራ ያደርጋል፤›› የሚል አቋም እንዳለው ይናገራሉ፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ ሕዝቡን፣ ሕዝቡ ደግሞ የኢሕአዴግን ጠመንጃ እየፈሩ ይኖራሉ፤›› ብለዋል፡፡

የሕግ ባለሙያውም፣ ‹‹በተለይ የተቃውሞ ሠልፍ የሚወጣው ሰው ተቃውሞውን ለማሰማትና አቤቱታን ለመግለጽ እንጂ ሰርግ ለማጀብ አይደለም፤›› በማለት መንግሥት በሠልፈኞች ላይ ሁሌም ትዕግሥት ሊኖረው እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡

‹‹እውነት ለመናገር ሕጉን ለመከልከል እየተጠቀመበት ነው፤›› ያሉት ምሁሩ፣ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከነበረው ጋር ያነፃፅሩታል፡፡ እሳቸው እንደሚሉት፣ ‹‹የኢሕአዴግ መንግሥት ከአፄ ኃይለ ሥላሴ የተሻለ አይደለም፡፡ ልዩነቱ በአፄው ጊዜ ሠልፍ መፍቀድም መከልከልም በሕግ ይቻላል፡፡ የአሁኑ በሕግ ይፈቅዳል፡፡ በሕገወጥ መንገድ በቢሮክራሲ ይከለክላል፤›› ብለዋል፡፡ ስለዚህ የኢሕአዴግ መንግሥት በሰላማዊ ሠልፍ ላይ ያለው አቋም በሕግ ደረጃ ሕገወጥ እንደሆነ ተከራክረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው ግን ከተማው በከፍተኛ የልማት እንቅስቃሴ ውስጥ በመሆኑ ተቃዋሚዎች በሚፈልጉት ቦታና ጊዜ አይሁን እንጂ፣ ሠልፍ ለማድረግ የተከለከለበት ጊዜ እንደሌለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ በዓመት ከ40 ጊዜ በላይ ሰላማዊ ሠልፍ መፍቀዱንም ለአብነት ጠቅሰዋል፡፡

የመቃወም ባህል

ከጥቂት ዓመታት በፊት በቱኒዝያና በግብፅ ለመንግሥት ለውጥ ምክንያት የሆኑት የተቃውሞ ሠልፎች ተጠቃሽ ሲሆኑ፣ በቅርቡ በአሜሪካ ባልቲሞርና በእስራኤል ዘረኝነትን በመቃወም የተደረጉ ተቃውሞዎችም ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በተለያዩ አካባቢዎች የሚደረጉ የተቃውሞ ሠልፎች በሁለት መንገድ እንደሚታዩም የሕግ ባለሙያው ይናገራሉ፡፡ እነዚህም የተደራጀና ቅጽበታዊ (ግብታዊ) እንደሚባሉ አስገንዝበዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የተቃወሞ ሠልፎች የተጠሩ ቢሆንም፣ አብዛኞቹ ወደ አመፅና ወደ ነውጥ አምርተዋል ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ አንዳንዶች በሰላማዊ መንገድ ተቃውሞ የማሰማት ልምድና ባህል በኢትዮጵያ እንደሌለ ያስረዳሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ዶ/ር መረራ ጉዲና፣ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ በሠልፍ ተቃውሞን የማሰማትና የመግለጽ ሁኔታን አልለመደም፡፡ የቅርብ ጊዜ ሙከራ ነው፡፡ ለዚህም ነው ከፍተኛ ትዕግሥት ማድረግ ከመንግሥት የሚጠበቀው፤›› ብለዋል፡፡

አቶ ዮናታን ተስፋዬም፣ ‹‹በእርግጥ የተጠራው ሠልፍ በሙሉ ሕግን ተከትሎ ሙሉ ለሙሉ ይከናወናል ማለት አይደለም፡፡ የታፈነ ሲመስለው ግን ወደ ግጭት የማምራት ዕድሉ ይሰፋል፤›› ብለዋል፡፡ በቅርቡ በመንግሥት በተጠራው ሠልፍ ላይ የተከሰተውን ጉዳይ በተመለከተ ይህ ሊሆን ቢችልም፣ ‹‹በባህላችን ውስጥ ግን የመጋጨትና ነውጠኛ የመሆን አጋጣሚ የለም፤›› ሲሉ ሁኔታው ሁልጊዜም መገለጫ እንዳልሆነ አስተባብለዋል፡፡

ቀደም ሲል ሰማያዊ ፓርቲ የጠራቸው ሰላማዊ ሠልፎች ሕዝቡ አንድም ተቃውሞ በሰላማዊ መንገድ ማሰማት እንዲለምድ፣ በዋናነት ግን ሕዝቡ ፍርኃት እንዲያስወግድ መሆኑን የሚናገሩ አቶ ዮናታን፣ ‹‹መንግሥት እንደ መልካም ዕድል ቀደም ብሎ ቢጠቀምበት ጥሩ ነበር፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡

በ1997 ዓ.ም. ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል በተለይ ቅንጅት በጠራው ተቃውሞ ለበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፍና ለንብረት መውደም ምክንያት በመሆኑ፣ በአሁኑ ወቅት በድኅረ ምርጫ እንደዚህ ዓይነት ያጋጥማል የሚል እምነት እንደሌለ አቶ ዮናታን ይናገራሉ፡፡

‹‹ብዙም ካርድ የወሰደ መራጭ የለም፡፡ አሁን ነው የሰማያዊ ፓርቲ ቅስቀሳ አይቶ የሚንቀሳቀስ ሰው የበዛው፡፡ ብዙ ሰው አይመርጥም፡፡ ተጭበረበረ በሚል ወደ አላስፈላጊ ቀውስ ለመግባት ፍላጎቱም ዓላማውም የለንም፡፡ በስትራቴጂያችን ውስጥም የለም፤›› ሲሉ የድኅረ ምርጫ 97 ተመሳሳይ ነገር ውስጥ ፓርቲያቸው የመግባት ዕቅድ እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -