Thursday, July 25, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ካስቴል ለውጭ ገበያ ካቀረበው ወይን ከግማሽ በላዩን ቻይና ገዛች

ተዛማጅ ፅሁፎች

 ካስቴል ወይን በአሥር ሚሊዮን ዩሮ ማስፋፊያ ሊያደርግ ነው

በኢትዮጵያ ሁለተኛው የወይን አምራች በመሆን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ ገበያ የገባው ካስቴል ወይን ለውጭ ገበያ ካቀረበው ምርት ውስጥ ቻይና ከ50 በመቶው በላይ ገዛች፡፡

የካስቴል ወይን ዓመታዊ የወይን ፌስቲቫል ባለፈው ቅዳሜ በዝዋይ በተከበረበት ወቅት እንደተገለጸው፣ ካስቴል ወይን ለውጭ ገበያ ካቀረበው ምርት ውስጥ 50 በመቶውን በላይ የገዛችው ቻይና ነች፡፡ ካስቴል ወይን በአንድ ዓመት ውስጥ ወደ ውጭ ከላከው ከ150 ሺሕ ጠርሙስ በላይ ወይን ውስጥ ቻይና ከግማሽ በላዩን ገዝታለች፡፡ ቻይና የካስቴልን ወይን ብቻ ሳይሆን በኢትዮጵያ የመጀመርያው የወይን አምራች የሆነውና ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ግል ከተዛወረው የአዋሽ ወይን መግዛትም ጀምራለች፡፡  

የካስቴል ወይን ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር የሽያጭና ገበያ ኃላፊ ወ/ሪት ዓለም ፀሐይ በቀለ እንደገለጹት፣ በእስካሁኑ የወይን የወጪ ንግድ ገበያ ቻይና ቀዳሚ በመሆንዋ ከዚህም በኋላ የካስቴል ወይን ዋነኛ የገበያ መዳረሻ ሆና ትቀጥላለች፡፡ ከቻይና ሌላ አውስትራሊያ፣ አሜሪካና የተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የካስቴል ወይን በመሸመት ተጠቅሰዋል፡፡ በአፍሪካ የኩባንያውን ምርት እየገዙ ካሉ አገሮች መካከል ኡጋንዳ፣ ደቡብ ሱዳንና ጂቡቲ ይገኙበታል፡፡ በቅርቡም ወደ ኬንያ የመላክ ዕቅድ ተይዟል ተብሏል፡፡

ካስቴል ወይን ባለፈው ዓመት ወደ ማምረት ሥራ ሲገባ ይፋ አድርጐት የነበረው ግን ከጠቅላላ ዓመታዊ ምርቱ ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ነበር፡፡ አሁን ያስመዘገበው አፈጻጸሙ ግን ካሰበው በታች ነው፡፡ እንደ ወ/ሪት ዓለም ፀሐይ ገለጻ ደግሞ ለውጭ ገበያ ያቀረበው ምርት ከጠቅላላ ምርቱ 15 በመቶ ብቻ የሆነበት የራሱ የሆነ ምክንያት ነበረው፡፡ ኩባንያቸው አሁን ለውጭ ገበያ ካቀረበው በላይ ምርት ወደ ውጭ የመላክ ዕቅዱን እንዳይተገብር ያደረገው፣ በርካታ አገሮች ኢትዮጵያ እንደ ወይን አምራችና ላኪ ያልተመዘገበች በመሆኑዋና ምርቱን ለመሸጥ ያስፈለገው የነበረው ምዝገባ ረጅም ጊዜ በመውሰዱ ነው፡፡

ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ወይን ለመሸጥ የሚያስፈልጋትን ምዝገባ ለማድረግ ብዙ ሒደቶችን ማለፍ ይገባ ስለነበርና ለምዝገባው የሚያስፈልጉትን የተለያዩ ሰነዶች ማዘጋጀቱ ደግሞ ጊዜ በመፍጀቱ የታቀደውን ያህል ምርት ሊላክ አልቻለም፡፡ ለምሳሌ ወደ አሜሪካ ገበያ ለመግባት ምዝገባውን ለሚያካሂደው የፌዴራል መድኃኒት አስተዳደር (ኤፍዲኤ)፣ ካስቴልን ወይን ናሙና ልኮ የጥራት ደረጃውን ለማስፈተሽና ምዝገባውን ለማግኘት ጊዜ መውሰዱን ወ/ሪት ዓለም ፀሐይ ተናግረዋል፡፡ ካስቴል ምርቱን ለመሸጥ የወይን ምርቱን ናሙና በመላክ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን፣ የወይን ተክሉ የሚመረትበት ቦታና አመራረቱ ጭምር ግምገማ ውስጥ ይገባል፡፡ ወደ አውሮፓም ለመግባት ተመሳሳይ ሒደቶችን በማለፍ ምዝገባው እስኪረጋገጥ ጊዜ መውሰዱ፣ በዕቅዳቸው ልክ ወይኑን እንዳይልኩ ማድረጉን ወ/ሪት ዓለም ፀሐይ ገልጸዋል፡፡ ‹‹አሁን ግን ይህንን ምዝገባ በማግኘታችን በዘንድሮው የምርት ዘመን ዕቅዱን ለማሳካት ጥረት እናደርጋለን፤›› ሲሉ ወ/ሪት ዓለም ፀሐይ ተናግረዋል፡፡  

‹‹ወደ ውጭ እንልከዋለን ያልነውን ያህል ወይን መላክ ባንችልም፣ ምርቱን ለአገር ውስጥ ፍጆታ ውሏል፤›› ያሉት ወ/ሪት ዓለም ፀሐይ፣ ይህም ከዚህ ቀደም በከፍተኛ ሁኔታ ከውጭ ይገቡ የነበሩ በተለይ የደቡብ አፍሪካ የወይን ምርቶች እንዲቀንሱ አድርጓል ብለዋል፡፡

‹‹በአገር ውስጥ ገበያ በደንብ በመግባታችን ደግሞ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች እንዲቀንሱ በማድረጋችን የውጭ ምንዛሪ ለማደን አስችሎናል፤›› ይላሉ፡፡ ምን ያህል የውጭ ምንዛሪ ማስገባት እንደቻሉና ከውጭ የሚገባውን ወይን ምን ያህል እንዲቀንስ እንዳስቻሉ ግን በአኃዝ አልገለጹም፡፡ የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ ኢትዮጵያ ደቡብ አፍሪካን ጨምሮ ከተለያዩ አገሮች ለምታስገባው ወይን ከ30 ሚሊዮን ዶላር በላይ ወጪ ታደርጋለች፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ካስቴል የምርት መጠኑን ለመጨመር ዝግጅት እያደረገ ነው፡፡ ምርቱን ለመጨመር ደግሞ የወይን እርሻውን ማስፋፋት ግድ ስለሚል በ70 ሔክታር መሬት ላይ ተጨማሪ የወይን ተከላ መጀመሩን ወ/ሪት ዓለም ፀሐይ ተናግረዋል፡፡ አዲሱ የማስፋፊያ እርሻውም አሁን በዓመት እያመረተ ያለውን 1.1 ሚሊዮን ጠርሙሶች ወይን ከ1.8 ሚሊዮን ጠርሙሶች በላይ ያደርስለታል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓመት 1.1 ሚሊዮን ጠርሙስ ወይን እያመረተ ያለው፣ በ162 ሔክታር ላይ በተከለው የወይን ተክል ነው፡፡

አዲሱ ማስፋፊያ የሚካሄደውም ቀደም ብሎ በተረከበው ቦታ ላይ ሲሆን፣ የወይን እርሻውን ለማልማት ከአሥር ሚሊዮን ዩሮ በላይ ወጪ ይጠይቃል፡፡ ኩባንያው ለወይን እርሻውና ለፋብሪካው ተከላ ወስዶ የነበረው መሬት 490 ሔክታር መሆኑ ይታወሳል፡፡ እስካሁን ያልተጠቀመበትን የእርሻ ቦታም በየዓመቱ እያለማ ይሄዳል ተብሏል፡፡

በ70 ሔክታር ይዞታው ላይ የሚተከለው የነጭ ወይን መሆኑ ታውቋል፡፡ የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ የወይን እርሻውን በነጭ ወይን ለመሸፈን የወሰነውም በእስካሁኑ የኩባንያው ገበያ የነጭ ወይን ፍላጐት ከፍተኛ በመሆኑና ይህንን ፍላጐት ለመሙላት እንደሆነ ተገልጿል፡፡

በሁለት አብይ የምርት ስያሜዎች (አኬሽያና ሪፍት ቫሊ) ሥር ወደ ዘጠኝ ምርቶችን እያቀረበ ያለው ካስቴል ወይን፣ ሁለቱንም ዓይነት ወይኖች ወደ ውጭ ቢልክም አፍሪካ ውስጥ የአኬሽያ ምርት ተወዷል ተብሏል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ምርቱ ጠንካራ ስላልሆነና የመጣፈጥ ባህሪ ስላለው ነው፡፡ ይህ የምርት ዓይነት ኢትዮጵያ ውስጥም ከሌለው ምርት በተሻለ የሚመረጥ ነው ተብሏል፡፡ አሜሪካ፣ አውስትራሊያና ቻይና ደግሞ ሪፍት ቫሊ የተባለውን የምርት ዓይነት ይመርጣሉ፡፡

ካስቴል ወይን ወደ ሁለተኛው የምርት ዘመኑ በገባበት በዚህ ወቅት ዓመታዊ የምርት መጠኑን ለመጨመር እየተዘጋጀ ቢሆንም እስካሁን ወደ አትራፊነት አልገባም፡፡ ወ/ሪት ዓለም ፀሐይ እንደገለጹት፣ ካስቴል ወይን ትርፍ እያስመዘገበ ያልሆነው ከዚህ ቀደም ከፍተኛ የሆነ የኢንቨስትመንት ወጪ በመውጣቱና የኢንቨስትመንት ዘርፉም ዛሬ ወይን ተተክሎ ዛሬውኑ ምርት የሚገኝበት ባለመሆኑ ነው፡፡ ካስቴል ወደ ወይን ምርት ከመግባቱ በፊት ለአራት ዓመት ለወይን እርሻው ከፍተኛ ወጪ አውጥቷል፡፡ ይህን ወጪ መልሶ ትርፋማ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው በሦስተኛው የምርት ዘመን ሲሆን፣ አሁን ወደ ሁለተኛው የምርት ዘመኑ ገብቷል፡፡

ካስቴል ወይን የቢጂአይ ኢትዮጵያ እህት ኩባንያ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ 163 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ዝዋይ ከተማ ላለው ኢንቨስትመንቱ ከ25 ሚሊዮን ዩሮ በላይ አውጥቷል፡፡ ከ500 በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት፡፡

    

   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች