Saturday, June 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ሴትነቴ አጉድሎኝ አያውቅም››

ወ/ሮ ትልቅሰው ገዳሙ፣ የግራንድ ሪዞርት ባለቤት

ወ/ሮ ትልቅሰው ገዳሙ በአማራ ክልል ጎጃም ልዩ ስሙ ደጋዳሞት በሚባል የገጠር አካባቢ ነው የተወለዱት፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት አካባቢ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ አዴት በመባል በሚታወቀው ቦታ ተከታትለዋል፡፡ ከዚያም ከባሌ ሮቤ የመምህራን ማሠልጠኛ ገብተው፤ ከዚያ በኋላ ለሰባት ዓመት በአስተማሪነት አገልግለዋል፡፡ በመጨረሻ ደግሞ ወደ ንግዱ ዓለም ገብተዋል፡፡

በባህርዳር ከተማ ጣና ዳር ያሠሩትና በከፍታው በአገሪቱ የመጀመሪያ የሆነው ባለአምስት ኮከብ ሆቴል ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በተገኙበት በቅርቡ ተመርቋል፡፡ ከአስተማሪነት ወደ ኢንቨስተርነት ጉዟቸውንና አዲሱ ‹‹ግራንድ ሪዞርት›› ሆቴልን በተመለከተ የማነ ናግሽ በአካባቢው ተገኝቶ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አስተማሪ እንደነበሩ ሰምቼያለሁ?

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- አዎ፡፡ ከትምህርት በኋላ ለሰባት አመት ያህል አስተማሪ ነበርኩ፡፡ መጀመርያ ሮቤ ግልበታ ግቤ ከ1983 እስከ 1984 አስተምር ነበር፡፡ ከዚያ ወደ አዲስ አበባ መጣሁ፡፡ ወደ አዲስ አበባ የመጣሁት በክልል መደራጀት ሲጀመር በጊዜያዊ ዝውውር ነበርና ወደ ነበራችሁበት ተመለሱ ሲባል በጣም ክፉኛ አለቀስኩ፡፡ በብዙ ትግል የሕክምና ማስረጃ አጽፌ አዲስ አበባ በቋሚነት እንድመዘገብ ተደረገ፡፡

ሪፖርተር፡- ከአስተማሪነት ወደ ንግዱ ዓለም እንዴት ሊገቡ ቻሉ?

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- የአስተማሪነት ሕይወት ከባድ ነበር፡፡ የአካባቢዬ ልጆችና ጓደኞቼ ወደ ንግድ እንድገባ ይነግሩኝ ነበር፡፡ መምህርነት አቁሜ ንግድ ቤት መክፈት ፈለግኩኝ፡፡ በወቅቱ የመንግሥት ሠራተኛ ንግድ ፈቃድ ሊያወጣ ስለማይችል በእህቴ ስም አስወጣሁ፡፡ ጥሩ እሠራ ነበር፡፡ ቀን ቀን ሥራዬን እሠራለሁ፡፡ ጓደኞቼ ይረዱኛል፣ ዕቁብ ይገቡልኛል፡፡ መጀመሪያ ይሰጡኛል፡፡ የመጀመሪያ ትልቅ ብር የቆጠርኩት ዕቁብ ሰብስበው የሰጡኝ 37 ሺሕ ብርን ነበር፡፡ ያንን ዕቁብ ስጨርስ 70 ሺሕ ሁለት መቶ ሺሕ እያለ እየጨመረ መጣ፡፡ ግሮሰሪውን ብዙም አልገፋሁበትም፡፡ ካዛንቺስ ሰማኸኝ በለው ይሠራበት የነበረው ቤት የኔ ነበር፡፡ እኔ ባለቤት መሆኔ አይታወቅም ነበር፡፡ የሰማኸኝ ቤት ነው የሚባለው፡፡ ባለቤቱን ጥሩ ስባል እሱን ነው የምጠራው፡፡ ጥሩ እሠራ የነበረ ቢሆንም ሥራውን ብዙም ስለማላውቀው አልወደድኩትም፡፡ ከዚያ ውጪ መመላለስ ጀመርኩኝ ስጀምርም መቶ ሺሕ ነበር የነበረኝ፡፡ ለምን ሌላ ሥራ አልሠራም ስል ወንድሜ ከሌላ ነጋዴ ጓደኛው ጋር አስተዋወቀኝ፡፡ ከጠፋች ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ ብሎ ዱባይና ቻይና እንዲወስደኝ ነገረልኝ፤ መመላለስ ጀመርኩ፡፡ መጀመርያ ቻይና ነው የሄዱኩት፡፡ በዛ ነው የውጭ ንግድ የጀመርኩት፡፡ በጣም አሰልቺ ነበር፡፡ የተወሰነ ጊዜ ተመላለስኩ፤ ልብስ አመጣ ነበር፡፡ ኮርያ የሚባል ብርድ ልብስም አመጣ ነበር፡፡ ያንንም ሥራ ግን ጠላሁት፡፡

ሪፖርተር፡- አዋጪ አልነበረም? ከዚያስ ፊትዎን ወዴት አዞሩ?

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- ሥራውን ጠላሁት አንድ ቀን ቤጂንግ አንድ ከተማ ላይ በረንዳ ላይ ሆኜ ስቅስቅ ብዬ አለቀስኩ፡፡ ጧት ተነስተን ሌሊት ነው የምንገባው፡፡ ስንዞር እንውላለን የምንገባው እግራችን አብጦ ነው፡፡ ‹‹እባክህ ጌታዬ የተረጋጋ እንጀራ ስጠኝ›› ብዬ ለመንኩት፣ ከዚያ አንድ መኖሪያ ቤት ገዛሁ፡፡ እሱን ኮላትራል አድርጌ ከባንክ ተበደርኩ፡፡ ከዚያ ትራንስፖርት ቢዝነስ ውስጥ ግቢ ሲሉኝ መጀመርያ አውቶቡስ ገዛሁ፡፡ ከዚያ ሦስት ሆኑ፡፡ ጧት ጋቢ ለብሼ አውቶቡስ ተራ እሄድ ነበር፡፡ ሥራዬን በርቀት መተው አልወድም፡፡ እያንዳንዷን ነገር እከታተላለሁ፡፡ አሁንም አይተኸኝ ከሆነ ለሰከንድም አልቀመጥም፡፡ እዞራለሁ ‹‹ምን አለ፣ ምን ጎደለ›› ብዬ አያለሁ፡፡ ከዚያ ወንድሞቼን አምጥቼ እነሱን ትኬት ቆራጭ አደረግኩ፡፡ አብሬ እንደ ጎረምሳ አውቶቡስ ተራ ሄጄ እቆማለሁ፡፡ ይህ ሥራም አስቸጋሪ ነበር፡፡ ከዚያ ለተወሰነ ጊዜ ከሠራሁ በኋላ አንድ የጭነት መኪና ደገምኩ፡፡ ከቢዝነስ ሰዎች ጋር ተመካክሬ ቦቴ ይሻላል ተብሎ ሦስት ቦቴ ገዛሁ፡፡ ከዚያም ሦስት ቦቴዎች ጨመርኩ፡፡ ከዚያ የራሱ ሥራ አስኪያጅ መቅጠር ጀመርኩ፡፡ እናም ቻኩ የሚባል ፒኤልሲ አቋቋምኩ፡፡ በሰፊው ወደ ትራንስፖርት ገባሁ፡፡ ሥራውንም ወደድኩት፡፡ በእርግጥ ፈተና አለው፡፡ ሾፌሮች አደገኞች ናቸው፡፡ እኔ አንድ ዘዴ ስዘይድ እነሱ ሌላ ዘዴ ሲያመጡ፣ እንዲሁ ስንዋደቅ፣ ለሥራ ጎበዝ እንደሆንኩ የሚያውቅ አንድ ጓደኛዬ ቻይኖች የያዙት ሥራ አለ አለኝ፡፡ ከዚህም ከዚያም ብዬ ከባንክ ተበድሬ አምስት ሚሊዮን ብር ቀብዱን ከፈልኩና 40 ገልባጭ ገዛሁ፡፡ በአንድ ጊዜ አርባዎቹ ገቡልኝ፡፡ ኮንስትራክሽን ጥሩ ሠራሁ፡፡ እንደገና 20 የጭነት መኪና ገዛሁ፡፡ ዶዘሮችም ገዛሁ፡፡ በኋላ ቦቴዎችን ስገዛ ከዚያ ተዛማጅ ሥራ ማደያ መግዛት አለብኝ ብዬ በደብረማርቆስ የማደያ መሬት ሰጡኝ፡፡

ማደያ የተመረቀ ዕለት ብዙ ሰው ነበር፡፡ ከዚያ አንድ ቤት እሠራለሁ ብዬ ለሕዝቡም ለራሴም ቃል ገባሁ፡፡ በአንድ ዓመት ከስምንት ወር ውስጥ ‹‹ጂፕላስ ስሪ›› ሃምሳ የመኝታ ክፍል ያለው ሠራሁ፡፡ አሁን አራት ዓመት ሆኖታል፡፡ በዛን ጊዜ ሳስመርቀው ይህ ሆቴል ያረፈበትን መሬት ተቀብዬ መሠረት ተጀምሮ ነበር፡፡ የጣና ዙሪያን ለማልማት ከተመረጡ ባለሀብቶች አንዷ ነበርኩ፡፡ ወረቀት ላይ ሲታይ ፕላኑ ብዙ አልገባኝም ነበር፡፡ ይህንን የሚያክል መሆኑን አልገባኝም፡፡ መጀመርያ ለሙሉ ሕንፃ ይሆናል ብዬ የገዛሁት ብረት መሠረቱን እንኳ አላስጨረሰም፡፡ ውኃ እየወጣ እየተሞላ ሳይ ‹‹መቼ ነው ከዚህ ጉድጓድ ወጥቶ የማየው?›› እላለሁ፡፡ እግዚአብሔር ይመስገን እዚህ ደረስኩ፡፡

ሪፖርተር፡- ግንባታው ምን ያህል ጊዜ ወሰደ? ምን ያህልስ ወጪ ሆነ?

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- አምስት ዓመት ፈጅቷል፡፡ እስካሁን ያወጣነው ወደ 680 ሚሊዮን ብር ይደርሳል፡፡ 200 የሚሆኑ የቀን ሠራተኞች ነበሩ፡፡ 

ሪፖርተር፡- የሆቴሉ ጀነራል ማናጀር ማነው? አሁንስ ምን ያህል ቋሚ ሠራተኛ አለ?

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- ጀነራል ማናጀሩ እንግሊዛዊ ነው፡፡ የ25 ዓመት ልምድ አለው፡፡ አሁን 347 ቋሚ ሠራተኞች አሉ፡፡ ጥሩ እንሠራለን ብዬ አስባለሁ፤ ከእግዚአብሔር ጋር፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ባለሀብት የማይደፍረው ዓይነት ይመስላል፡፡ ይህን ያህል ትልቅ ሆቴል ክልል ላይ ለመሥራት እንዴት ደፈሩ?

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- እንግዲህ ክልሉ አምኖበት ነው መሬት የሰጠን፡፡ እኔም አንድ ነገር ቶሎ አልወስንም፤ ከወሰንኩ ግን ተግባራዊ ማድረግ አለብኝ፡፡ ከሠራሁ እንደሚያተርፍ አውቃለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙ ሰው ቋሚ የመንግሥት ሥራ ትቶ ሌላ ሥራ ውስጥ መግባት ይፈራል፡፡ የእርሶ ተሞክሮ ግን ሌላ ይመስላል፡፡

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- በገጠር ተወልጄ ያደግኩ ነኝ፡፡ ውጭ አገር ቤተሰብ የለኝም፡፡ አሁን እኔ እዚህ ከደረስኩ በኋላ ነው ወደ ከተማ እየገቡ ያሉት እንጂ ከዚያ በፊት ገጠር ውስጥ የሚኖር ቤተሰብ ብቻ ነው የነበረኝ፡፡ ስለዚህ የዛ ዓይነት ትልቅ ህልም አልነበረኝም፡፡ መማር ነበር የመጀመርያ ህልሜ፡፡ ወደ ቢዝነሱ ከመጣሁ በኋላ ግን ቀን በቀን ለውጦች ነበሩ፡፡ እሱ ደግሞ ይገፋሃል፡፡ እንዳታቋርጠው ያደርግኸል፡፡ እሱ ኃይል ነው እዚህ ያደረሰኝ፡፡

ሪፖርተር፡- ማኅበረሰባችን ሴቶች ላይ ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ይህ ተፅዕኖ ሥራዎት ላይ ያሳደረው ነገር ነበር?

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- ሴት ናት ብሎ የሚደፍረኝም የለም፡፡ እኔም ራሴን አስከብሬ ነው የምኖረው፡፡ ‹‹ሴት ስለሆንኩ በዚህ ያጠቃኛል፤ ይበድለኛል›› በሚል አንድም ቀን አስቤው አላውቀም፡፡ ማንም ወንድ የሚያደርገውን ነገር አደርጋለሁ፡፡ ስለዚህ ሴትነቴ አጉድሎኝ አያውቅም፡፡

ሪፖርተር፡- ብዙዎች ወደ ውጭ አገር ሔደው እንዲያልፍላቸው የሚመኙ ናቸው፡፡ እርስዎ በወጣትነትዎ እንደዛ አላሰቡም?

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- አልወደውም፡፡ ውጪ ሄደው በሚቀሩ በጣም ነው የምናደደው፡፡ እያንዳንዱ ሰው ለአገሩ አስተዋጽኦ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ባለሙያ ከዚያ ቁጭ ብሎ የሰው አገልጋይ ከሚሆን መጥቶ በአገሩ አንድ ሰው ሁለት ሰው ቢቀይር አገር የመለወጥ ዕድል ይኖራል፡፡ አንድ ሰው ኢንጂነሪንግ አጥንቶ ታክሲ ከነዳ፣ ሕክምና አጥንቶ ድንጋይ ካቀበለ ለአገር ኪሣራ ነው፡፡ ትርጉም የለውም፡፡ እኔ ውጪ አገር ቪዛዬን እንኳን ጨርሼ አላውቅም፡፡ ሥራዬን ከጨረስኩ አገሬ ነው የምመጣው፡፡ ሥራዬም ኑሮዬም ሞቴም አገሬ ላይ እንዲሆን ነው የምፈልገው፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ሁሉ ጥንካሬዎ ከየት የመጣ ነው?

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- ትልቅ ሐሳብ ነበረኝ፡፡ አሁንም ገና እቀጥላለሁ ብዬ ነው የማምነው፡፡ ይበቃኛል ብዬ አላውቅም፡፡ እርካታ የለኝም፡፡ በመሥራት ማደግ መከበር እንዳለ አውቃለሁ፡፡ የሚያልፍልህ በምንም አይደለም በሥራ ነው፡፡ እኔ ለምሳሌ ሠራተኞቼ ሲሸከሙ አብሬያቸው እሸከማለሁ፤ ዕቃ ሲያወርዱ አብሬ አወርዳለሁ፡፡ እነሱን ያቃታቸውን ሁሉ አንጠልጥዬ ነው የማወጣው፡፡ ከልጅነቴ ጀምሮ ሠርቼ ነው ያደግኩት፡፡ እህቴ ናት ያሳደገችን፣ የአስተማሪ ሚስት ነበረች፡፡ ውኃ መቅዳት ካለብኝ፣ ውኃ እቀዳለሁ፤ እንጀራ መጋገርም ካለብኝ እጋግራለሁ፡፡ እግር ማጠብ ካለብኝ እግር አጥባለሁ፡፡ እኔ ጋር ያሉ ልጆችም የእኔን ባህል ይዘው ነው ያደጉት፡፡

ሪፖርተር፡- ለወደፊቱ ምን ላይ ለመሠማራት ሐሳብ አለዎት?

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- ቱሪዝምን ማስፋፋት እፈልጋለሁ፡፡ የተሟላ ግራንድ ትራቭል እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ፡፡ ለምሳሌ የራሴ አውሮፕላን እንዲኖኝ እፈልጋለሁ፡፡ ደግሞ ማድረግም እችላለሁ፡፡ ጀልባዎች አሉኝ፣ ፈጣን ናቸው፣ ዋጋቸው ውድ ነው፡፡ ሪፖርተር፡- የስኬትዎት ምስጢር ምንድን ነው?

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- ሰው ብዙ ነገር ሊያወራ ይችላል፡፡ የስኬቴ ምስጢር ግን አንዳች ነገር አይደለም፡፡ መሥራት ብቻ ነው፡፡ ምንም ምስጢር የለኝም፡፡ ሥራን መውደዴ፣ ሥራን ማክበር ሥራን ማወቅ ሥራን መከታተል፣ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ግራንድ ሪዞርት ምን ዓይነት ሆቴል ነው?

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- በውስጡ እጅግ ዘመናዊ ኪችን አለን፡፡ አራት ሺሕ ሰው በአንዴ መመገብ የሚችል ሦስት ኪችን አለው፡፡ ኮልድሩሙ በአንድ ጊዜ ከ20 በሬ በላይ ማስተናገድ የሚችል ነው፡፡ ሳውና፣ ስቲም፣ ጃኩዚ፣ ማሳጅ፣ ባር፣ ሬስቶራንት አለው፡፡ የወንዶችና የሴቶች የውበት ሳሎን፣ ናይት ክለብ፣ ሴንትራል አየር ኮንዲሽነር አለው፡፡ ጀልባዎቹ 25 ሰው ማስተናገድ የሚችል ባር ያለው ሁለት መኝታ ያለው፣ መጥበሻ ያለው፣ ሻወር ቤት ያለው ፈጣን ጀልባ ነው፡፡ በጣም ዘመናዊ ፔንት ሐውስ አለው፡፡ በሦስት ሰከንድ ውስጥ የሚበራ የራሱ አውቶማቲክ ጄኔሬተር አለን፡፡ የሚመጠጥ ሽንት ቤት አይደለም ያለን፡፡ በራሱ የሚመጥ ፕላንት ነው ያለው፡፡ በአንድ ጊዜ እስከ 1200 ሰዎች ማስተናገድ የሚችል አዳራሽ አለ፡፡ አራት ትናንሽ የኮንፈረንስ አዳራሾች አሉት፡፡ 500 የሚሆኑ መኝታ ክፍሎች አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በምርቃቱ ላይ ተገኝተው ነበር፡፡ ምን አሉዎት?

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- ‹‹በርቺ፣ በዚህ ቀጥይ፣ በየትኛውም የአገራችን ክፍል ሪዞርት ብትሠሪ ይኸኛው ስም የራስሽ ሆኖ ይቀጥላል›› ብለውኛል፡፡ 

ሪፖርተር፡- ይኼ ሆቴል በባህርዳር ምናልባት ትልቁ ነው የሚሆነው አይደል?

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- በአገሪቱም የመጀመርያ ነው፡፡ የዚህ ያክል ከፍታ ያለው ሆቴል በአገሪቱ የመጀመርያ ነው፡፡ ትናንት [በምርቃቱ ጊዜ] አልተናገርኩም ዛሬ ግን ልናገር፡፡ አንድ ሁለት ቢሮዎች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ በሆቴል ደረጃ ግን በከፍታው የመጀመርያ ነው፡፡ ባለአምስት ኮከብ ሆቴሎች አሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ G+17 ሆቴል ግን የለም፡፡

ሪፖርተር፡- ለሌሎች ምን ይመክራሉ?

ወ/ሮ ትልቅሰው፡- ለሁሉም ጠንክሮ መሥራት ይገባል፡፡ ሴቶች የወንዶች ጥገኞች ካልሆን ከወንዶች በተሻለ ስኬታማ እንሆናለን፡፡ ስለዚህ ሁሉም ጠንክሮ ይሥራ ነው የምለው፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

የአየር መንገድ ተጓዦች በሻንጣ የሚያስገቡትን የልብስና የጫማ ብዛት የሚገድብ ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ከቀረጥ ነፃ ይገቡ የነበሩ ዕቃዎች 87 በመቶ እንዲቀንሱ ተደርጓል መንገደኞች...

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የምንዛሪ ገበያ እንዳይኖር ሊመክሩ ነው

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ያለውን...

ግራ አጋቢው የኤሌክትሪክ መኪና ጉዳይ

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ በወርኃ ጥቅምት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ 39...