Wednesday, July 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ለካንሰር ሕክምና የልህቀት ማዕከልነት ታጨ

ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ለካንሰር ሕክምና የልህቀት ማዕከልነት ታጨ

ቀን:

በታደሰ ገብረማርያም

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል የካንሰር ሕክምና የልህቀት ማዕከል እንዲሆን ታጨ፡፡ ለተግባራዊነቱም ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍና አገር አቀፍ የሕክምና ተቋማት የተውጣጡ ከፍተኛ ባለሙያዎች የተሳተፉበት ግብረ ኃይል መቋቋሙን የፒፕል ቱ ፒፕል አመራሮች አስታወቁ፡፡

ሆስፒታሉ ወደ አጠቃላይ የካንሰር ሕክምና ማዕከል ከተለወጠ ለካንሰር ታካሚዎች ምርመራና እስከ መጨረሻው ድረስ የሚዘልቅ ሕክምና ለመስጠት የሚያስችል አቅም እንደሚኖረው አመራሮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል ከሌሎች መንግሥታዊ ሕክምና ተቋማት መካከል የካንሰር ማዕከል ሆኖ የታጨው አንጋፋውና የመጀመርያው የሕክምና ማዕከል በመሆኑ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ብዙዎቹን ሐኪሞችና ስፔሻሊስቶች አሠልጥኖ ለሥራ ማብቃቱ፣ የተለያዩ ፌሎሺፖች የሚካሄድበት መሆኑ፣ የፖቶሎጂና የላብራቶሪ ሩሲሊቲዎች ከሌሎች የሕክምና ተቋማት በበለጠ ተመቻችቶ መገኘቱ ለዕጩነቱ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው፡፡

በአገሪቱ ከሚገኙ ጥቂት ፕሮፌሰሮች መካከል አብዛኞቹ በጥቁር አንበሳ ሪፈራል ሆስፒታል መገኘታቸው፣ የመንግሥትን ፕሮግራም ማከናወኛና የተቋቋመውም በሕዝብ የገንዘብ አስተዋጽኦ መሆኑ ለመታጨቱ ሌላ ምክንያት ናቸው፡፡ ማዕከሉን ዕውን ለማድረግ በተቋቋመው ግብረ ኃይል የፒፕል ቱ ፒፕል፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ በቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬ የሚመራው ብሔራዊ የካንሰር ኮሚቴ፣ የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ተወካዮች አባል መሆናቸውን አመራሮቹ ተናግረዋል፡፡

የፒፕል ቱ ፒፕል ተወካይ በግብረ ኃይሉ ውስጥ ያለው የሥራ ድርሻ ባለሙያዎችን ለማቅረብ የሚያስችል ሥልት ይቀይሳል፡፡ አሜሪካ የሚገኙ የሕክምና ተቋማት በማዕከሉ አወቃቀር ሕክምና አሰጣጥና በሌሎችም ተጓዳኝ በሆኑ ሥራዎች ላይ መሳተፍ የሚቻልበትን አቅጣጫ ያስቀምጣል፣ ኮሌጁ ደግሞ ካንሰርን ለማከም የሚረዱ አገልግሎቶችን በተቀናጀ መልኩ የሚቀርብበትን አካሄድ ያመቻቻል፡፡

የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ በካንሰር ዙሪያ የሚሠሩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ምን ዓይነት እንቅስቃሴ እንዳላቸውና ምን ማበርከት እንደሚችሉ፣ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የማዕከሉ ዕውነት መሆን  ካለው ስትራቴጂ ጋር የሚሄድበትን መንገድ ያስተካክላል፣ ብሔራዊ ኮሚቴው ያለውን መረጃና ድጋፍ ይዞ ይቀርባል፡፡

የፒፕል ቱ ፒፕል ሶሳይቲ መሥራችና ፕሬዚዳንት እናውጋው መሐሪ (ዶ/ር)፣ ድርጅታቸው ትሪያንጉላር ፓርትነርሺፕ (የሦስትዮሽ አጋርነት) የሚባል ዶክትሪን (አስተምህሮ) እንዳለው፣ አስተምህሮውም ኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች፣ ሌሎች የምዕራባውያን ተቋማትና አገር ውስጥ ያሉ ተቋማት አብረው ቢሠሩ በአገሪቱ የጤና ሥርዓት ላይ ትልቅ ለውጥ ማምጣት ይቻላል የሚል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ዕድገትና ልማት በትክክል ሊመጣ የሚችለው ብቃት ያለው የሰው ወይም ብቁ የሆነ የሰው ኃይል ማፍራት ሲቻል፣ ጥሩ ትምህርትና የጤና ሥርዓት ሲኖር ነው፡፡ በተረፈ ግን በዓለም ላይ ብቁ የሆነ የሰው ኃይል፣ ጥሩ የትምህርትና የጤና ሥርዓቶች የሌለው አገር ሲያድግ አይታይም፤›› ብለዋል፡፡

የፒፕል ቱ ፒፕል የትምህርት ዘርፍ ምክትል ፕሬዚዳንት ከበደ ቤኛ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ ከ2004 ዓ.ም. እስከ 2007 ዓ.ም. የካንሰር ሕክምና በሚሰጡ ሆስፒታሎች ውስጥ ከተሰበሰበው መረጃ ለማወቅ እንደተቻለው፣ በአገሪቱ ካሉት ካንሰሮች የሴቶች የጡት ካንሰር በአንደኛ ደረጃ፣ የማኅፀን በር ጫፍ ካንሰር በሁለተኛ ደረጃ፣ የፕሮስቴት ካንሰር በሦስተኛ ደረጃ ተቀምጠዋል፡፡ የተጠቀሱትን ካንሰሮች ግን ቶሎ ከተደረሰባቸው መዳን በእርግጠኝነት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ቁጥር እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ ከዚህ ሳቢያም ደግሞ ካንሰር እየተንሰራፋና አድማሱን እያሰፋ በመሄድ ላይ ነው፡፡ በጡት ካንሰር ሳቢያም የሚከሰተው የእናቶች ሞት ቁጥር እየበዛ መምጣቱም መታወቅ ይኖሩበታል ያሉት ደግሞ የፒፕል ቱ ፒፕል በጎ ፈቃደኛና የካንሰር ሐኪም ጋሌና ሳሊም (ዶ/ር) ናቸው፡፡

ካንሰርን ለመከላከል ያለው ኃይል የተወሰነ ሲሆን፣ በዚያው ልክ ደግሞ የሜዲካል፣ ራዲዬሽንና የሰርጂካል ኦንኮሎጂስቶች እጥረት እንዳለ፣ በዚህም የተነሳ የጡት ካንሰር ችግር ያለባቸው ሴቶች ተገቢውን ሕክምና ለማግኘት ቢያንስ አንድ ዓመት መጠበቅ ግድ እንደሆነባቸው ነው በጎ ፈቃደኛዋ የተናገሩት፡፡

የጡት ካንሰር በጊዜው ከተደረሰበት ሊዳን እንደሚችል፣ ነገር ግን ከዘገየ ወደ ደረጃ ሦስትና አራት እንደሚጠጋ የገለጹት ዶ/ር ጋሌና፣ አሜሪካ ውስጥ የካንሰሩ መጠን በተጠቀሰው ደረጃ ላይ የሚገኙ ሴቶች አሥር ከመቶ ሲሆኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን 50 ከመቶ በላይ እንደሆኑ አመልክተዋል፡፡

ፒፕል ቱ ፒፕል ዋና መሥሪያ ቤቱ አሜሪካ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ፣ በካናዳ፣ በስዊድን፣ በስዊዘርላንድና በጀርመን ቅርንጫፎች እንዳሉት ለማወቅ ተችሏል፡፡    

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከተቋሙ የሠራተኞች ማኅበር አመራር ጋር እየተወያዩ ነው]

ጤና ይስጥልኝ ክቡር ሚኒስትር? ሰላም! በአስቸኳይ እንደፈለጉኝ መልዕክት ደርሶኝ ነው የመጣሁት። አዎ።...

የሱዳን ጦርነትና የኢትዮጵያ ሥጋት

የሱዳን ጦርነት ከጀመረ አንድ ዓመት ከአራት ወራት አስቆጠረ፡፡ ጦርነቱ...

ግለሰብ ነጋዴዎችን በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ለማድረግ ያለመው ረቂቅ አዋጅ ተከለሰ

በምትኩ የንግድ ተቋማት በአስገዳጅነት የንግድ ምክር ቤት አባል ይሆናሉ...

አሳርና ተስፋ!

ከቱሉ ዲምቱ ወደ ቦሌ ጉዞ ልንጀምር ነው፡፡ ገና ከመንጋቱ...