በአያሌው አስረስ
ታላቁ የህዳሴ ግድብ በአንድ ወይም በሌላ የሕዝብ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡
ሲጀምር የተቃወሙ ወገኖች አሁን ወደ ደጋፊነት መጥተዋል፡፡ ዓለም እየተነጋገረበት ያለው ይህ ግድብ ሥራው ካለቀ በኋላም በሚያስከትለው የኃይል አሠላለፍ ለውጥ ምክንያት መነጋገሪያነቱ ይቀጥላል፡፡
ህዳሴ የሚለው ቃል ወደ ግድቡ የተሻገረው ዘገይቶ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አፈሩን ያቅልላቸውና ‹‹ህዳሴ›› የሚለውን ቃል የተጠቀሙት ለአዲሱ ጎጃምንና ሸዋን ለሚያገናኘው ለዓባይ ድልድይ ነው፡፡ ለአጭር ጊዜ ይሁን እንጂ ግድቡ ‹‹የኢትዮጵያ ሚሊኒየም ግድብ›› ተብሎ ሲጠራ ቆይቷል፡፡ የስም ለውጥ ለእሱ አዲስ አይደለም፡፡ በዕቅድ ላይ በነበረበት ጊዜ የሚሠራው ሥራና የሚሠራበት ቦታ ቢታወቅም፣ ‹‹ፕሮጀክት ኤክስ›› እየተባለ ሲጠራ መቆየቱ ተነግሯል፡፡ እንዲህ መባሉ በሥራው ከሚሳተፉ ሰዎች ውጪ ሌሎች ትኩረት እንዳይሰጡ መረጃ አነፍናፊዎች ዕድል አንዳያገኙ መንገድ ሳይዘጋ አንዳልቀረ እገምታለሁ፡፡
መንግሥት ስለታላቁ የህዳሴ ግድብ ያለውን ዓላማና ግብ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለዓለም ይፋ ያደረገው መጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. እንደነበር ይታወሳል፡፡ ‹‹እኛ ሳናውቅና እስካልተስማማን ድረስ በዓባይ ወንዝ ላይ ምንም ማድረግ አትችሉም፤›› ሲሉ የነበሩት ግብፆችም የሰሙት በዚሁ ቀን ነው፡፡ የመጀመሪያው መደፈር! መንግሥት እንዲህ ዓይነት ትልቅ ፕሮጀክት ሲጀምር ሕዝብን ማማከር ነበረበት ያሉም ነበሩ፡፡ ሐሳቡ ተገቢነቱ ባያጠራጥረም ዓባይ ደግሞ እንዲህ የሚዝናኑበት አጀንዳ አለመሆኑ መረሳት የለበትም፡፡ የተመረጠው ዕርምጃ የነብሩን ጭራ ግጥም አድርጎ መያዝ፣ ከያዙም አለመልቀቅ ትክክል ነው፡፡
ያን ሰሞን ግብፆች በዓረብ አብዮት እየተናጡ ስለነበር፣ የኢትዮጵያ መንግሥት አጋጣሚውን እንደተጠቀመበት አድርገው የተቹ ነብሩ፡፡ መንግሥት የዓረብ አብዮትን በማምጣት የተጫወተው ሚና ስላልነበረውና ተዘጋጅቶ የጠበቀው ስላልሆነ ለሐሳቡ ዋጋ መስጠት ይቸግረኛል፡፡ ድፍረቱን ነው መውደድ!
ጉዳዬ ብሎ መንግሥት የመሠረት ድንጋይ ያስቀመጠላቸው ፕሮግራሞች ሃያና አሥራ አምስት ዓመት ቆይተውም አንድም ነገር ያልተደረገላቸው አሉ፡፡ ቸርችል ጎዳና ቴዎድሮስ አደባባይ ላይ ይቆማል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የአፄ ቴዎድሮስ ሐውልት አንዱ ሲሆን፣ ሌላው የዓድዋ ጦርነት አንድ መቶኛ ዓመት በ1988 ዓ.ም. ሲከበር በቦሌ ክፍለ ከተማ ከሃያት ሆስፒታል በስተምሥራቅ ይሠራል ተብሎ የተከለለው የዓድዋ መታሰቢያ መናፈሻ (ፓርክ) ነው፡፡ በሐውልቱ ንድፍ የሙያው ሰዎች ሲከራከሩና ሲያማርጡ ከርመው ወረቀት ታቅፈው እንደቀሩ ሁሉ፣ በመናፈሻው ሥራ ድርሻ ይኖራችኋል የተባሉት በአዲስ አበባ የአፍሪካ አገሮች ዲፕሎማቶች አፈር በልቶት የቀረ ሰሌዳ ከመትከል ያለፈ ዕድል አልጠበቃቸውም፡፡
ተመሰገን ነው የህዳሴው ግድብ እንዲህ ያለ ዕጣ አልገጠመውም፡፡ እንዲያውም የግድቡ ሥራ መጀመሩ በይፋ በተገለጠበት ለሁኔታው በሚመጥን ቃል ‹‹በተበሰረበት›› ቀን በቦታ የነበርን ሰዎች ያየነው፣ ወደ ሥራው የገቡ አሥር አሥራ አምስት የኮንስትራክሽን መኪናዎች ድንጋይ ሲፈልጡና አፈር ሲዝቁ ነው፡፡ አካባቢው ተጠርጎ ግድቡ ሲጠናቀቅ ሁለቱ ተራሮች በግድቡ የኮንክሪት ግንብ የሚገናኙበት ቦታ ተመልክቶም ነው፡፡
የግድቡ መሠረት ያርፈበታል ተብሎ የተነግረኝ የዓባይ ውኃ መፍሰሻ ወይም መልካ (Water Bed) በእኔ ግምት አራት መቶ ሜትር ይሰፋል፡፡ ወንዙ ዓባይ የሚገደበው ውኃ ባይሆን ኖሮ የህዳሴው ግድብ መሠረት መነሳት የነበረበት ለዘመናት የተከማቸውን ደለል ጠርጎ ነበር፡፡ የሆነው ዓባይ ባለበት መፍሰሱን ቀጥሎ በመካከልም ለውኃው መቀልበሻ ቦታ ትቶ ከወንዙ ቀኝ የግድቡን ሥራ መጀመር ነው፡፡ አምና የቅልበሳ ሥራ ተሠርቶ ዓባይ በሰው ሠራሸ ቦይ እንዲፈስ ከተደረገ በኋላ በግራ አራት በሮች ያሉት የውኃ መፍሰሻ (Calvert Box) ተሠርቶ፣ በአሁኑ ጊዜ በመጠናቀቅ ላይ ይገኛል፡፡ ሥራው እንዳለቀ ዓባይ ወደ ነበረበት ይመለስና በተዘጋጁለት በሮች ሲወጣ ይቆያል፡፡ ዓባይ በጊዚያዊነት ሲፈስበት በነበረበት ቦታ ላይ ሦስተኛው የግድቡ ክፍል ሥራ ሲቀጥል ግድቡ በሙሉ አካሉ በሙሉ ገጹ ገሃድ ይሆናል ማለት ነው፡፡ የአሥራ ስድስቱ የኃይል ማመንጫ ቤቶች (Power Houses) ሥራም ጎነ ለጎን እየሄደ ነው፡፡
የግብፁ ፒራሚድ 146.5 ሜትር ቁመት ሲኖረው መሠረቱ 230.4 ሜትር በ230.4 ሜትር፣ ማለትም 53 ሺሕ ካሬ ካሬ ሜትር ይሰፋል፡፡ የህዳሴው ግድብ ቁመት 176 ሜትር ነው፡፡ ከግብፁ ፒራሜድ በ30 ሜትር ይበልጣል፡፡ የግድቡ የውስጥ ለውስጥ ስፋት በአማካይ 135 ሜትር መሆኑ ተነግሮኛል፡፡ ይህን ከእኔ ግምት ጋር ሳገናኘው የግድቡ መሠረት ማለትም የተዘቀዘቀው ፒራሜድ አናት ስፋት 54 ሺሕ ካሬ ካሬ ሜትር ይሆናል፡፡ ይህን ሁሉ መሬት በዳምጠው እየዳጡ፣ ሰሚንቶ እያጠጡና እየጠቀጠቁ (ኮንክሪት እያደረጉ) ወደ ላይ መውጣት ቀላል ሥራ አለመሆኑን ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ ግድቡ መሬት እየለቀቀ ወደ ላይ በሄደ ቁጥር የውስጥ ለውስጥ ስፋቱን እያጠበበ ወደ ጎን በግራና በቀኝ ከንፉን እያሰፋ ከአካባቢው መሬት ጋር እየተሳሰረና እየተዋሀደ በመሄድ፣ 176 ሜትር ላይ ከወንዙ ግራና ቀኝ የሚገኙትን ሁለቱን ተራሮች በማስተሳሰር ይደመደማል፡፡
ይህን በሐሳባችን ስናሰላው ግድቡ 56 ፎቅ ቤት ያህል ገዝፎ ወይም ብዙዎቻችን የምናውቀውን አዲስ አበባ የሚገኘውን የአዋሽ ባንክን ሕንፃ ሦስት እጥፍ ረዝሞ ይታየናል፡፡ እዚህ ቦታ ላይ ግድቡ ማለትም የተዘቀዘቀው ፒራሜድ (እግሩ) 1.8 ኪሎ ሜትር የአግድመት ርዝመት የ11 ሜትር የውስጥ ለውስጥ ስፋት ይኖረዋል፡፡ በአጭሩ መኪና እንደልብ ማሽከርከር የሚያስችል ሰፊ ኮንክሪት አውራ ጎዳናም ሆኖ ያርፋል፡፡
ሌላው የግድቡ ከፍተኛ አካል በመገንባት ላይ ያለው የውኃ አቃፊ ግድቡ (Saddle Dam) ነው፡፡ እሱ ራሱ ሲጠናቀቅ ከመሬት በላይ 52 ሜትር ከፍታ 5.2 ኪሎ ሜትር (ከመገናኛ ራስ መኮንን ድልድይ) ርዝመት ይኖረዋል፡፡ ይህን አባጣ ጎባጣ የሌለውን ይህን ተራራ ለመገንባት 17 ሚሊዮን ሜትር ኪዩብ ምርጥ ማቴሪያል ጥቅም ላይ ይውላል፡፡
አዲስ አበባ 527 ካሬ ካሬ ኪሎ ሜትር ትሰፋለች፡፡ የህዳሴው ግድብ ሙሉ በሙሉ በውኃ ሲሞላ 1.874 ካሬ ካሬ ኪሎ ሜትር፣ የአዲስ አበባን ሦስት እጥፍ መሬት በውኃ ይሸፍናል፡፡ ይህ ሰው ሠራሽ ሐይቅ የቱሪስት መስህብ ሆኖ እንደሚያገለግል ቢታመንም፣ በዚህ ረገድ የተጀመረ ነገር አይታይም፡፡ አሶሳ ሌላ ተቀናቃኝ ከተማ እንዳይወለድ ሰግታ ይሆን? እሱ ደግሞ መወለዱ አይቀርም፡፡
የህዳሴው ግድብ አራተኛ ዓመት በዓል ላይ የቤሻንጉል ክልል ፕሬዚዳንትን ክቡር አቶ አህመድ ናስርን በዚያ ጥድፊያ ውስጥ አንድ ደቂቃ ለማይሞላ ጊዜ አግኝቻቸው ነበር፡፡ አካባቢውን ለማስጠናት ሐሳብ እንዳለ ነግረውኛል፡፡ በክልሉ የቴሌቭዥን ፕሮግራም የሰጡትን መግለጫም ተከታትያለሁ፡፡ የሰማሁት ጉዳዩ በቂ ትኩረት ተሰጥቶታል ማለት ግን የሚያስችል አይደለም፡፡ ግድቡ ውኃ መያዝ የሚጀምርባቸው አንዳንድ ተርባይኖች ኃይል የሚያመነጩበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ግድቡ በሚቀጥሉት አምስት ስድስት ዓመታት ሙሉ በሙሉ በውኃ ይሞላል ብለን ብናስብ ምንም ዝግጅት ሳይደረግ ቀኑ ደርሶ ‹‹የግድቡ ጎብኝዎች ደረጃውን የጠበቀ ማረፈያ ባለማግኘታቸው እየተቸገሩ ነው›› የሚል ዘገባ ልንሰማ ነው ማለት ነው፡፡ የእኛ ነገር ጦር መጣ ሲሉት ዛቢያ ቆረጣ እንዳይሆን እፈራለሁ፡፡
ለመንገድ ያለ ቅርበትን ለወደፊት ልማት ያለ ምቹነትን ከግምት አስገብተው የካርታ ሥራ ሙያተኞች ሊለሙ የሚችሉ ከተሞችንና አዳዲስ አካባቢዎችን ከወዲሁ ማመልከት ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ የክልሉ መንግሥት በሚሊዮን ብር ሳይሆን በቢሊዮን በጀት መድቦ ወደ ሥራ መግባት አለበት፡፡ የግል ባለሀብቱን ከወለድ ነፃ የሆነ ብድር ተጠቃሚ በማድረግ በማልማቱ ሥራ አንዲያግዝ ማነሳሳት መልካም ነው፡፡ የሙሽራ አጃቢ ተለምኖ እንጂ ለምኖ አይመጣም፡፡
በግድቡ ግንባታ ላይ የፌዴራል መንግሥቱና የክልል መንግሥታት እንደተረባረቡት ሁሉ ከተሞችን በማርገዝና በመውለድ መረባረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ግድቡን ለቱሪዝምና ከውኃ ጋር ለተየያዙ ልማቶች ማዋል የክልሉ የብቻ ሸከም የሚሆንበት ምክንያት መኖር የለበትም፡፡ የክልሉ መንግሥት ዋና ዋና ሥራዎችን ለይቶ ይህ የአንተ ድርሻ ነው ብሎ ለክልል መንግሥታት ቢያከፋፍል ጥሩ ነው፡፡ በታዳጊ ክልልነቱ ቤንሻጉል ጉሙዝ ክልልን የማገዝ ኃለፊነት ያለበት ኦሮሚያ በዚህ በኩልም ማሰብ ይኖርበታል፡፡ በየአጋጣሚው ‹‹አሻራችንን እናስቀምጣለን›› የሚሉ ሁሉ እዚህ ላይ እንዳይረባረቡ የሚከለክል ነገር አለ?
በነገራችን ላይ የህዳሴው ግድብ ተፈጥሯዊ ምክንያት የዘቀዘቀው የፒራሚዱን ቅርፅ ብቻ አይደለም፡፡ የግብፅን የማናለብኝ ትምክህት ጭምር እንጂ፡፡ በዚህ በኩል ሲታይ ደግሞ የህዳሴው ግድብ ለመላ ኢትዮጵያውያን የነፃነታቸው ምልክት ሆኖ ይቆማል፡፡ ነውም!
የመሠረት ድንጋይ ብለው ቢያከብሩህ
ዝም ብለው አይምሰልህ፡፡
አንተ ባታይ የሚያይልህ
አንተ ባትሰማ የሚሰማልህ
አንተ ባትናገር የሚናገርልህ
እልፍ ምስክር አቁመዋል
በዛሬና በነገ መሀል፡፡
አበሻ ከዳር እስከ ዳር
ዓባይን እንገድባለን ብሎ ሲፎክር፤
ጠብ ሳይል አንድም ቃል
ምስክር ሁሉ ሰምቷል፡፡
የሐበሻ ቃል መሬት ቢወድቅ
አንተ ብቻ አይደለህም
አገር አብሮህ ነው የሚሳቀቅ
ዓለም አቁሞህ ነው የሚስቅ
ጉባ – መጋቢት 24/2003
(በዕለቱ በቦታው ለተሰማኝ ስሜት የተጻፈ)
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡