Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ግንቦት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. በሬክተር ስኬል መለኪያ 7.3 በርዕደ መሬት በተመታችው ኔፓል በርካቶች ሕይወታቸው እንዳለፈ ይነገራል

ትኩስ ፅሁፎች

እንጉርጉሮ 

የቤትሽን ከለላ  ፥ ስትንቂ፣ ስትንቂ፣

ንፋስ ወሰደልሽ ፥ ቁርጥሽን እወቂ፤

አጥማቂሽ ነበረ፤ አራቂሽ ነበረ፤

ምን አስከፍትሽው ፥ ዛሬ ፊቱ ዞረ?

*******

ነሐሴ ታምር ሆኖ ፥ ሱባዔ – ፍልስታ፣

እንኳን የሰው ልጅ ፥ አፈሩም ጾም ፈታ፡፡

*******

ጨለማው ሲገፈፍ፣ ሌሊቱ ሲነጋ፣                            

እርሙን አወጣጥተን፣ በላን የሰው ሥጋ፡፡

*********

ከነፍስ ተቃቅረን ፥ ተስማማን ከሥጋ፤

ዓለምንም ቀጨን፣ ተናንቀን ከሞት ጋ፡፡

******

ሁሉን ገፈታትረሽ ፥ ‘ቆሜያለሁ’ ብለሽ፣

ዝናቡ ዘነበ፣ አፈሩ አዳጠሽ፡፡

******

ሳይወሰን በፊት ፥ የእርድ ከብቱ ምርጫ፣

እኛ ተገፋፋን ፥ ለጾም – ፍቺ ቅርጫ፡፡

******

ንፋስ ከበረታ፣ አንደ’ዜ ካ’የለ፣

የሣር ትንሽ የለ፣ የዛፍ ትልቅ የለ፥

ሁሉንም ይዞ ብር … እያንጠለጠለ፡፡

*****

ስንቱን ምስኪን ኗሪ ሲሰፍሩ፣ ሲሰፍሩ፥

ዛሬ በተራቸው ፥ ከመስፈሪያ ኖሩ፤

ከሕዝብ ጋር ተጋፉ፣ ከተማውን ዞሩ፤

“ፈሪ ናቸው” ያሉት ፥ እንግዲህ ይፈሩ፡፡

****

የሰው ሁሉ እንባ ፥ ብሶ፣ ተባብሶ፣

በክረምቱ ወርዶ ፥ በነሐሴ ፈስሶ፣

ገላን አፈራርሶ፣ ሥጋን አበስብሶ፣

አስጨንቆት ሄዶ ፥ ሕዝቡን አስለቅሶ፡፡

– ዮሐንስ ሞላ “የብርሃን ልክፍት” (2005)

                        *******

ቆንቋናው ስኮትላንዳዊ

በአውሮፓውያኑ የቀን አቆጣጠር የፌብሩዋሪ ወር 29 ቀናት የሚኖሩት በአራት ዓመታት አንዴ ነው፡፡ በሌሎቹ ሦስት ዓመታት ግን 28 ቀናት ብቻ ነው ያሉት፡፡ እናላችሁ ታዲያ አንዱ ስኮትላንዳዊ በስንት ፍለጋ ፌብሩዋሪ 29 ቀን የተወለደች ልጃገረድ ፈልጐ አገባ፡፡ ይህን ያደረገውም ያለምክንያት አልነበረም፡፡ ለባለቤቱ በየዓመቱ የልደት ስጦታ ከመግዛት ይልቅ በአራት ዓመት አንዴ በሚከበረው ልደቷ ወቅት ብቻ ገፀ በረከት ለመስጠት ነበር፡፡

ስኮትላንዳውያኑ አምፖሎቻቸው ሲቃጠሉባቸው ምን ያደርጋሉ?

      ባስቸኳይ ተሰባስበው የራስ አገዝ ቡድን ያቋቁማሉ – ጨለማን ተቋቁሞ የመኖር ዘዴ የተሰኘ ማኅበር፡፡ ሌሎች እንደሚሉት ደግሞ ኮሚቴ ያቋቁሙና አንዱ አምፖሉን ለመለወጥ እንደሚያስፈልግ የሚገልፅ ደብዳቤ ይፅፋል፡፡ ሁለተኛው በጀት ይመድባል፡፡ ሦስተኛው አምፖሉን ያወርዳል፡፡ አራተኛው አምፖል እንዲገዛ ትእዛዝ ያስተላልፋል፡፡ በመጨረሻም አምስተኛው አምፖሉ ሊተካ እንደሚገባ ለፀሃፊው ትእዛዝ ያስተላልፋል፡፡

******

ቱሪስት፡- “የተቃጠለ አምፖል ለመተካት ስንት ስኮትላንዳውያን ያስፈልጋሉ?

ስኮትላንዳዊ፡-  “ኧረ ገና መቼ ጨለመና!”

ቱሪስት፡- የተቃጠለ አምፖል ለመቀየር ስንት ስኮትላንዳውያን ያስፈልጋሉ?

ስኮትላንዳዊ፡- ስኮትላንዳውያኑን አምፖል አይቀይሩም፤ ጨለማ ውስጥ መቀመጥ ስለሚረክስ ያን ይመርጣሉ፡፡

-አረፋዓይኔ ሐጐስ “የስኮትላንዳውያን ቀልዶች” (2005)

******

ውሸትን የሚቃወም የሀዲያ ብሂል

  “ከመዋሸት፣ መስገብገብ ይሻላል”

 “ውሸት ቦታ አይዝም፣ ሆፍቾ ብረት አይቆርጥም”

 “የውሸታም፣ ቋንቋው ሰባት ነው”

 “ውሸታም ራሱ አውርቶ፣ ራሱ ያፍራል”

 “የማይገድለውን ሰው ፈርቶ፣ ሊገድል በሚችል አምላክ ማለ”

*****

-አለባቸው ኬዕሚሶ እና ሳሙኤል ሀንዳሞ “የሀዲያ ህዝብ ታሪክና ባህል” (2002)

  •  

‹‹በአርበኝነቴ ክብርና ማዕረግ ሥም ላልነቃነቅ ቃል ገብቻለሁ አልኩ››

‹‹ምንድነው ማሙሽ አይበሉኝ ትልቅ ሰው አይደሉም እንዴ እንዴት አይገባዎትም… ተሰብስበን ዘብና አለቃ እየተጫወትን ነበር… በቃ…››

‹‹ከእነማን ጋር ነበር እየተጫወታችሁ የነበረው›› ለጥቂት ጊዜ ዝም አለ፡፡ በጨረፍታ ተመለከተና ‹‹አላውቃቸውም›› አለ፡፡

‹‹አዳምጠኝ ማሙሽዬ… አሁን እየተጫወትኩ ነበር አልክ፡፡ መልሰህ ከነማን ጋር ስትጫወት እንደነበር አታውቅም፡፡ የሆንከውን በትክክል ለምን አትኖርም?››

የዘበኛው ደወል ያንቃጭላል፡፡ የጨለማው ጥልቀት እየጨመረ ነው፡፡ ጥላውና አፍንጫው ብቻ ይታየኛል፡፡ ቀኝ እጁን ለሰላምታ ግንባሩ ላይ እንደቀሰረ ነው፡፡

‹‹እንግዲህ ካልገባዎት ልንገርዎት…ከዚህ ሱቅ ከረሜላ ገዛሁና እዚያ ከሚታየው አግዳሚ ወንበር ላይ ቁጭ አልኩ፡፡ ትልልቅ ልጆች ተሰብስበው መጡና ከበቡኝ ‹በላ ጦርነት…ጦርነት…መጫወት አትፈልግም?› አሉኝ፡፡ ተስማማን እና ድርሻ ተሰጥቶን ጫወታውን ጀመርን፡፡ ከሁላችንም ትልቁ ልጅ ጄኔራል ሆኖ ተመረጠና እሱም ሹመት ሲሰጥ ወደኔ ቀርቦ፣ ‹አንተ ሃምሳ ዓለቃ ነህ› አለኝ፡፡ ከዚያ ከአግዳሚው ወንበር እየመራኝ እዚህ አመጣኝና ትዕዛዝ ሰጠኝ ‹ይህ ጠቅላይ ማዘዣችን ነው፡፡ እኔ ቦታ ቀይር እስከምልህ ድረስ እዚህ ቦታ በጥበቃ ላይ ትቆያለህ፡፡ አንተ እያለህ ጠላት አይደፍረንም በማለት ተማምነንብሃል› አለኝ፡፡ እኔም በአሣርፍ ሳዳምጥ ከቆየሁ በኋላ ትዕዛዙን መቀበሌን በተጠንቀቅ እንደሚያዩኝ በሰላምታ ገለጥኩ፡፡ ጄኔራላችን መስማማቴን በአድናቆት ፈገግታ ተቀበለኝና ግዳጅህን በትክክል መወጣትህን በአርበኝነት ክብርና ሥምህ ቃል ኪዳን ግባና አረጋግጥልኝ አለኝ፡፡ ‹በአርበኝነቴ ክብርና ማዕረግ ሥም ካለአዛዤ ትዕዛዝ ከዚህ ቦታ ላልነቃነቅ ቃል ገብቻለሁ አልኩ፤› አለና ንግግሩን ተግ አደረገ፡፡

-አብርሃም ረታ ዓለሙ ‹‹አባቶችና ልጆች›› (2007)

****

ብልጭታና መብረቅ

የነጎድጓዳማ ዝናብ መንፈስ በጉ ስለጠፋበት ፍለጋ በወጣ ጊዜ እጅግ በጣም እየዘነበ በጉን በፍለጋ ላይ ሳለ የነጎድጓዱ መንፈስ ከአንዲት እንሽላሊት ዘንድ ይደርስና የጠፋበትን በግ አይታ እንደሆነ ጠየቃት፡፡

እርሷም “አይ! አላየሁትም፡፡ በዝናቡ ምክንያት በጣም በርዶኝ ስለነበረ ፀሃይ እየሞኩ ነበር፡፡” ብላ መለሰችለት፡፡

እርሱም “ታዲያ ምን ትመክሪኛለሽ? የጠፋብኝንስ በግ እንዴት ላገኘው እችላለሁ? ማንስ ይሆን የሰረቀው?” ብሎ ጠየቃት፡፡ እንሽላሊቷም “ግንደ ቆርቁር ጋ ሄደህ እርሷ የምታውቀውን ትነግርሃለች፡፡” አለችው፡፡

ነጎድጓዱም ወደ ግንደ ቆርቁር ሄዶ “በጌ ጠፍቶብኛልና አይተሽዋል?” ብሎ ጠየቃት፡፡

ግንደ ቆርቁሯም “እኔ የተለመደ ሥራዬን እየሠራሁ፣ እየቆረቆርኩ ነበርና በግህን አላየሁትም፡፡” አለችው፡፡

እርሱም “እናስ ታዲያ የጠፋብኝን በግ እንዴት ላገኘው እችላለሁ?” አላት።

እርሷም “እስኪ ወደ እስስት ዘንድ ሂድ ። ሌሎች እንስሳትን ባየ ጊዜ የሚደበቀው አንዳች ክፉ ነገር ቢሠራ ነው። በፀፀት ምክንያት፡፡” አለችው፡፡

ነጎድጓዱም “በርግጥ የተደበቀበት ምክንያት ገብቶኛል፤በጌን ሠርቆት ወይም መርዞት መሆን አለበት፡፡” ብሎ አሰበ፡፡

ይህንንም ካለ በኋላ ወደ እስስት ዘንድ በማምራት እስስቱ ዘንድ እንደደረሰ “በል ና ውጣ ፣አንተ እስስት!” ብሎ ቢጣራም እስስቱ ከአንድ ዛፍ ስር ተደበቀ፡፡

ነጎድጓዱም እስስቱን ፍለጋ ከዛፉ ጀርባ ቢዞርም እስስቱ ግን ጫካው ውስጥ ገብቶ ተደበቀ፡፡

ሆኖም በመጨረሻ ነጎድጓዱም እስስቱን አግኝቶ “በጌን የሰረቅኸው አንተ ነሃ! በልተኸው ወይም መርዘኸው ይሆናል፡፡” ብሎ ነጎድጓዱ እስስቱን ሰነጣጠቀው፡፡

እስከዛሬም ድረስ ነጎድጓዳማ መብረቅ በመጣ ጊዜ በሽማሌዎች ዘንድ “ወደ ውጪ ወጥታችሁ ዛፍ ስር አትቁሙ፤ ምክንያቱም መብረቁ በጉን የሰረቀበትን እስስት እየፈለገ ነው፡፡” የሚል ብሂል አለ፡፡

የዚህም ተረት መልዕክት ክፉ ነገሮችን ሰርተው እንደሚደበቁ ሰዎች አትሁኑ የሚል ነው፡፡

በአዬሻ ቱሽክሎ የተተረከ የማሌ ተረት (ደቡብ ኦሞ)

  • ከኢትዮጵያ ተረቶች ገጽ

 

 

 

 

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች