የአፍሪካ ሙዚቃና ባህል ልውውጥ ፌስቲቫል (አፍሪካ ሚውዚክ ኤንድ ካልቸራል ኤክስቼንጅ ፌስቲቫል)፣ የአፍሪካ ቀንን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ የሙዚቃ ፌስቲቫል ሲሆን፣ ከወራት በፊት በግዮን ሆቴል ሲካሄድ ከተለያዩ የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ድምፃውያንን አሳትፏል፡፡ መርሐ ግብሩ በተካሄደበት ወቅት ከዘፋኞቹ ጎን ለጎን የታዳሚዎችን ቀልብ የሳቡት ባይላሞር በሚባል የዳንስ ትምህርት ቤት ውስጥ ከሚያስተምሩ መምህራን ጋር ይደንሱ የነበሩ ታዳጊዎች ናቸው፡፡
ታዳጊዎቹ ክብ ሠርተው ከመምህራኑ የሚያዩትን ዳንስ አስመስለው ለመንቀሳቀስ ይሞክራሉ፡፡ የአፍሪካና የላቲን ሙዚቃዎች እየተለዋወጡ ሲከፈቱላቸው ምቱን ይከተላሉ፡፡ ታዳጊዎቹ የዳንስ ችሎታ ባይኖራቸውም እንቅስቀሴዎቹን ለመረዳት ይጣጣሩ ነበር፡፡
የዳንስ ትምህርቱ መደበኛ ያልሆነና በአጋጣሚ የተገኘ ቢሆንም፣ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የዳንስ ትምህርት ቤቶች ቁጥር መበራከቱ ይስተዋላል፡፡ እንደ ሳልሳ ያለ ዳንስን በመምረጥ፣ በአንድ ዳንስ ላይ ብቻ ያተኮረ ትምህርት የሚሰጡ ትምህርት ቤቶች ይገኛሉ፡፡ የተለያዩ የዳንስ ስልቶችን በማጣመር የሚያሠለጥኑ ተቋሞችም አሉ፡፡
በዋነኛነት የላቲን ዳንሶችን ያማከለ ሥልጠና ከሚሰጡ መካከል ቢላቲኖ፣ ባይላሞር፣ ኢትዮሳልሳና ጁቬንቱስ ክለብ ይጠቀሳሉ፡፡ ዳንሱን ከአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጋር አጣምረው የሚሰጡ ጂሞችም እየተበራከቱ ነው፡፡ ከወራት በፊት በጁቬንቱስ ክለብ በተገኘንበት ወቅት ቤሊ ዳንስን ከኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ ጋር አዋህደው የሚያስተምሩትን ካናዳውያን ዳንሰኞች ናይላና ክሪስቴል አግኝተን ነበር፡፡
ዳንሰኞቹ በካናዳና ፈረንሣይ ቤሊ ዳንስ ያስተማሩ ሲሆን፣ ትሩፕ ኬሊያፕ ሊቤትራይብ የተሰኘ የዳንስ ቡድን አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሌ ዳንስን ከጉራግኛ፣ ትግርኛ፣ አፋርኛና ኦሮምኛ ጋር በማጣመር ያስተምራሉ፡፡ ዳንሰኞቹ እንደሚሉት፣ ቤሊ ዳንስን ጨምሮ የተለያዩ አገሮችን ዳንስ የማወቅ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ቁጥር መጨመሩ የዳንስ ትምህርት ቤቶች ለመበራከታቸው ምክንያት ሆኗል፡፡
ከተማሪዎቹ መካከል ዳንሰኝነት መሆንን ግባቸው አድርገው የሚማሩ እንዳሉ ሁሉ፣ የግል ስሜታቸውን ለማርካት የሚሠለጥኑም ይገኙበታል፡፡ ሳልሳን እንደ ስፖርት ወስደው ተክለ ሰውነታቸውን ለማሳመርና ጤናቸውን ለመጠበቅ የሚማሩም ይጠቀሳሉ፡፡ ሠርግን ለመሰሉ መርሐ ግብሮች የዳንስ ትምህርት የሚቀስመውም ጥቂት አይደሉም፡፡
የ26 ዓመቱ ዮናስ ሲሳይ፣ በኢትዮ ሳልሳ ትምህርት ቤት የዳንስ ሥልጠና (በባይላሞስ ክለብ) የወሰደው ከአምስት ዓመት በፊት ነበር፡፡ ‹‹ሳልሳ በጣም ስለሚያዝናናኝ የስድስት ወር ሥልጠና ወሰድኩ፤›› ይላል፡፡ ከመሠረታዊ ትምህርቱ ጀምሮ የሦስት ወር ሥልጠና ከወሰደ በኋላ ተጨማሪ ሦስት ወር አክሎበታል፡፡
ከተማሪዎች መካከል እንደ አካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚያዩትና ዳንሰኛ ለመሆን የሚፈልጉ እንደነበሩም ያስታውሳል፡፡ ተመርቀው ከወጡ በኋላ ጀማሪዎችን ለማስተማርና አዳዲስ የዳንስ ስልቶችን እርስ በርስ ለመማማርም አዘውትረው ወደ ባይላሞስ ክለብ ያቀናሉ፡፡
ዮናስ ዳንሱን ከተማረ በኋላ ባይላሞስ እየሄደ ከመደነስ በተጨማሪ ለፍቅረኞች ቀን በሚዘጋጁ ምሽቶች ላይም ሳልሳ ይደንሳል፡፡ በዘንድሮው የፍቅረኞች ቀንም በኔክሰስ ሆቴል ከጓደኞቹ ጋር ሳልሳ ያቀርባል፡፡ ዳንሱ በጥንዶች የሚደነስ እንደመሆኑ ለፍቅረኞች ቀን ከሚመረጡ ስልቶች ቀዳሚው ነው፡፡ አብረውት የተማሩ ጓደኞቹ ከፍቅረኞች ቀን ውጪ በኩባና ሌሎችም ኤምባሲዎች መርሐ ግብሮች ሲኖሩ ዳንስ እንደሚያሳዩ ይናገራል፡፡
እሱ እንደሚለው፣ ለዳንሱ ፍቅር ስላለው እንቅስቃሴዎቹን ለመልመድ ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ ‹‹በአንድ ወር ብዙ ነገሮች ተምሬ ዳንስን ለማሳመር የሚረዱ (ከለሪንግ) እንቅስቃሴዎች ወደ መለማመድ ነበር የገባሁት፤›› ይላል፡፡ ትምህርቱን ሲጀምር መማሪያ ሲዲ የተሰጠው ሲሆን፣ በየጊዜው ችሎታውን ለማሳደግ ኦንላየን የዳንስ እንቅስቃሴዎች ይከተታላል፡፡ ታናሽ እህቱንም ማሠልጠን ጀምሯል፡፡
የ21 ዓመቷ ኢየሩሳሌም ጥላሁንም ሳልሳ ለመማር የወሰነችው ለዳንሱ ጥልቅ ፍቅር ስላላት ነው፡፡ ከስምንት ወር በፊት በኢትዮ ሳልሳ ትምህርት ቤት የተማረች ሲሆን፣ መደበኛ ሙያዋ በግንባታ ዘርፍ ቢሆንም ወደ ዳንሱ ታዘነብላለች፡፡ ‹‹ዳንስ እወዳለሁ፡፡ ከዳንስ ደግሞ ሳልሳን እመርጣለሁ፤›› ትላለች፡፡ ሂፕ ሃፕና የአፍሪካ ዳንስ ከመደነስ በተጨማሪም ሳልሳ ትደንሳለች፡፡
ዳንሱ በጥንዶች የሚደነስ ሲሆን፣ በጥንዶች መካከል የሚደረገውን እንቅስቃሴ ከመማሯ በፊት በግል የሚደረገውን የሰውነት ንቅናቄ ተምራለች፡፡ ‹‹የቻልኩት በአጭር ጊዜ ነው፡፡ በየሳምንቱ እሑድ በባይላሞስ የሳልሳ ምሽት እየሄድኩ እደንሳለሁ፤›› ትላለች፡፡ በየሳምንቱ ሐሙስ ዓለም ሕንፃ ወደሚገኘው የዳንስ ማሠልጠኛም ትሄዳለች፡፡
የሳልሳ ምሽቶች ሲዘጋጁ የሳልሳ ተማሪዎችና ዳንሱን የሚችሉ ይታደማሉ፡፡ ‹‹ዳንሱን ለማይችሉ ሰዎች ብዙም ትርጉም አይሰጥም፡፡ ለሚደንሱ ሰዎች ግን አስደሳች ምሽት ነው፤›› ስትል ትገልጻለች፡፡ ከሳልሳ ዳንስ ምሽቶች ውጪ ብዙም የሳልሳ ዝግጅቶች ስለሌሉ በምሽቶቹ ከመደነስ ሌላ አማራጭ የላትም፡፡
‹‹ሳልሳ ዳንስ እንደ ሱስ ሆኖብኛል›› የምትለው ኢየሩሳሌም፣ የዳንስ ትምህርት ቤቶች ቁጥር እየጨመረ መምጣቱን ትገልጻለች፡፡ ትምህርት ቤቶች ከመብዛታቸው ጋር በተያያዘም ስልቱ እየተለመደ መጥቷል፡፡ ዳንሱ ‹‹ነፃ እንቅስቃሴ›› መሆኑ እንዳሚያዝናናት ትናገራለች፡፡ ወደ ቀድሞ ትምህርት ቤቷ አዘውትራ በመሄድ አዳዲስ እንቅስቃሴዎች ትማራለች፡፡ ለጀማሪዎችም እውቀቷን ታካፍላለች፡፡ ‹‹በዳንሱ የሚመራኝ ወንድ ስለሚያስፈልግ መደነስ ከሚችሉ ወንዶች ጋር አዳዲስ እንቅስቃሴዎች እለማመዳለሁ፤›› ትላለች፡፡
ሳልሳን ጨምሮ ማሬንጌ፣ ቻቻንና ሌሎችም የላቲን ዳንሶችን ከሚያስተምሩ ትምህርት ቤቶች መካከል ባይላሞር ይጠቀሳል፡፡ ከሰባት ዓመት በፊት የተመሠረተው ትምህርት ቤቱ፣ የመሠረታዊ (ቤዚክ) እና ከፍተኛ (አድቫንስድ) ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ተማሪዎች በየሦስት ወር ከአንድ ደረጃ ወደ ሌላው ይሸጋገራሉ፡፡ ባይላሞርን ከመሠረቱት አራት መምህራን አንዷ ሜላት መብራቱ እንደምትለው፣ በየጊዜው አዳዲስ እንቅስቃሴዎች መማር ስለሚቻል ትምህርቱ የሚያልቅ አይደለም፡፡
ከ20 ዓመት በፊት ከኩባ የመጡ መምህራን ዳንሱን ካስተማሯቸው በኋላ ነበር ትምህርት ቤቱን የከፈቱት፡፡ በወቅቱ ስለ ዳንሱ በቂ ግንዛቤ ስላልነበረ ተማሪዎቻቸው በጣት የሚቆጠሩ ነበሩ፡፡ ዳንሱን ለማስለመድ በአዲስ ዓመት፣ በፍቅረኞች ቀንና ሌሎችም ዝግጅቶች እያስናዱ ማሳየት ጀመሩ፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስለ ዳንሱ የሚያውቁና የሚወዱት ሰዎች ተበራክተው፣ እስከ ዛሬ ከ2,500 በላይ ተማሪዎች አሠልጥነዋል፡፡ ከተማሪዎቹ መካከል ትምህርት ቤት የከፈቱም ይጠቀሳሉ፡፡
በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ትምህርት ቤቶች ዳንስ ከማሠልጠን ጎን ለጎን የሳልሳ ምሽቶች ያዘጋጃሉ፡፡ የየትምህርት ቤቱ ሠልጣኞችና ሌሎችም የዳንሱ ፍቅር ያላቸውም ይታደማሉ፡፡ ‹‹ሰው ስለዳንሱ ሲገነዘብ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች ቁጥር ጨምሯል፡፡ አሁን ላይ ብዙ ሰው ሳልሳ መቻል ይፈልጋል፡፡ ዳንሱን ስለሚወዱት የሚመጡና ክብደት ለመቀነስ ከመጡ በኋላ የሚወዱትም አሉ፤›› ትላለች፡፡ እንደ ጊዜ ማሳለፊያ ወይም እንደ መዝናኛ የሚወስዱትም ይገኙበታል፡፡
ወደ ትምህርት ቤቱ ከሚመጡት መካከል ጥንዶችና ጓደኞሞች ይገኙበታል፡፡ ቦሌ መድኃኔዓለም አካባቢ የሚገኘው ኤኮ ላውንጅ ውስጥ ትምህርቱ ይሰጣል፡፡ በየሳምንቱ ዓርብ የሳልሳ ምሽቶች ይካሄዳሉ፡፡ ‹‹የሳልሳ ትምህርት ቤቶች በተለያየ ቀን የሳልሳ ምሽት ያዘጋጃሉ፤›› ትላለች መምህርቷ፡፡
እሷ እንደምትለው፣ ስለ ሳልሳ ዳንስ ያለው ግንዛቤ እየተሻሻለ ቢመጣም አሁንም ዳንሱን ‹‹ከኢትዮጵያ ባህል የሚጻረር›› የሚሉ አልታጡም፡፡ ትምህርት ቤቱ ከዳንስ ጋር በተያያዘ በበጎ አድራጎት ሥራዎች ላይ በመሳተፍና በተለያዩ ዝግጅቶች ሳልሳ ዳንስ በማሳየት ከሰው ለመቀራረብ ይጣጣራሉ፡፡ ‹‹ዳንሰ ሴቶችን በራስ መተማመንና ወንዶችን ኃላፊነት የሚያስተምር ነው፤›› የምትለው መምህርቷ፣ ይኼንን ባህል ለማሳደግ ታዳጊዎችን የማሠልጠን ዕቅድ እንዳላቸው ትናገራለች፡፡
መነሻቸውን አህጉረ አፍሪካ ያደረጉ የላቲን ዳንሶች ዛሬ ላይ የላቲን አገሮች መገለጫ ቢሆኑም መሠረታቸው አፍሪካ ነው፡፡ ይኼንን በመመርኮዝም ሳልሳን ከኢትዮጵያ ባህላዊ ውዝዋዜ ጋር አዋህዶ የማቅረብ ዕቅድ እንዳላቸው ትገልጻለች፡፡ ኮንቴምፕረሪና ሂፕ ሃፕ ዳንሶች ከኢትዮጵያ ውዝዋዜ ጋር ሲቀላቀሉ የተገኘው ቀና ምላሽ ለሳልሳ እንደሚሰጥም ያምናሉ፡፡
‹‹ሳልሳ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው ዳንስ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ውዝዋዜ ጋር ማቀላቀሉ አገሪቱ የበለጠ እንድትታወቅ ይረዳል፤›› ትላለች፡፡ መምህራኑ በተለያዩ አገሮች በሚዘጋጁ የሳልሳና ባቻቻ ፌስቲቫሎች የሚሳተፉ ሲሆን፣ ተሳትፏቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ስላለው ሳልሳ ግንዛቤ እንደሚፈጥር ታምናለች፡፡ ከዚህ ቀደም በኒውዮርክ፣ በዱባይና በሌሎች አገሮች ፌስቲቫሎችም ተሳትፈዋል፡፡
ጆንሰን ሰይፉ ወልደሥላሴ ኢትዮ ሳልሳ ትምህርት ቤትን የመሠረተው ከአምስት ዓመት በፊት ሲሆን፣ ከትምህርት ቤቱ ውጪ መገናኛ በሚገኘው ዓለም ጂምናዚየምና በጁቬንቱስ ክለብም ያስተምራል፡፡ ሳልሳ ዳንስን የሚመለከተው ከጤና፣ ከማኅበራዊ ግንኙነት፣ ከባህልና ከጥንዶች ትስስር አንፃር ነው፡፡ ከሳልሳ ዳንስ በተጨማሪ ላምባዳ፣ ባሳላማና ሌሎችም ዳንሶችም ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ባለፉት ዓመታት ከ2,000 በላይ ሰዎች ያሠለጠነ ሲሆን፣ ጤንነታቸውን ለመጠበቅ የሚሹና ለዳንሱ ፍቅር ስላላቸው የሚማሩም ገጥመውታል፡፡ ተማሪዎቹን በየስድስት ወሩ በልዩ መርሐ ግብር ያስመርቃል፡፡
ከትምህርት ቤቱ የሚወጡ ተማሪዎች፣ በሳልሳ ምሽት ከመገናኘታቸው ባሻገር ጀማሪዎችን በማሠልጠንም ይሳተፋሉ፡፡ ‹‹እንደ ቤተሰብ ነን›› ሲልም ትስስራቸውን ይገልጸዋል፡፡ በበጎ አድራጎት ተግባሮች በጋራ ይሳተፋሉ፡፡ በየሦስት ወሩም ከአዲስ አበባ ወጥተው ይዝናናሉ፡፡ ‹‹ትምህርት ቤቱ የሚያሠለጥናቸው በተለያየ ሙያ የተሰማሩ ሰዎች በየሙያቸው አንዳቸው ሌላቸውን ያግዛሉ፤›› ይላል፡፡
ሳልሳ የሚወዱ በሕክምና፣ በቢዝነስና በሌላም ሙያ የተሠማሩ ተማሪዎች ከተመረቁ በኋላ የሚገናኙበት መንገድ ይፈጥራል፡፡ ትምህርቱን ከመጀመራቸው በፊት እርስ በርስ ለመረዳዳት ቃል የሚገቡበት ሰነድ አዘጋጅቶ ያስፈራርማል፡፡ በባይላሞስ ክለብ የሚሰጠውን ትምህርት ከወሰዱ መካከል ከ19 እስከ 55 የሚሆናቸውን ተማሪዎቹን ይጠቅሳል፡፡
በሳልሳ ምሽቶች ተገኝተው ጥንዶች ሲደንሱ የሚያዩ ሰዎች ትምህርቱን ለመውሰድ መነሻ ይሆናቸዋል፡፡ ጆንሰን እንደሚለው፣ በየጊዜው የሚመረቁ ተማሪዎች ጓደኞቻቸውን እንዲማሩ ይገፋፏቸዋል፡፡ ትምህርት ቤቱ ከኩባ፣ አርጀንቲናና ቬንዝዌላና ሌሎችም የላቲን አገሮች ኤምባሲዎች ጋር በቅርበትም ይሠራል፡፡
በኢትዮ ሳልሳ በ14 ዙር ተማሪዎች ተመርቀው ወጥተዋል፡፡ በየወሩ 250 ብር የሚከፈል ሲሆን፣ የስድስት ወር ሥልጠና መውሰድ ይቻላል፡፡ በሐዋሳ፣ ሻሸመኔና ሌሎች ከተሞች የፍቅረኞች ቀን ሲከበር ዳንስ አቅርበዋል፡፡ በተማሪዎች መካከል ውድድር እየተካሄደም አሸናፊዎች ይሸለማሉ፡፡ በቀጣይ ሜቄዶንያን ለመርዳት የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም እንደሚኖራቸውም መምህሩ ይናገራል፡፡
የሳልሳ ትምህርት ቤቶች ቁጥር መጨመሩ ዳንሱን ለመማር ያለው ፍላጎት ማደጉን ያሳያል ይላል፡፡ ከሳልሳ ትምህርት ቤት የወጡ ተማሪዎች የራሳቸውን ትምህርት ቤት መክፈታቸውና ዳንሱ በስፋት መተዋወቁ ለውጥ ማምጣቱንም ያክላል፡፡ በዳንሱ አማካይነት ማኅበራዊ ትስስር እንደሚጠነክር ስለሚያምንም፣ ተማሪዎቹ እንዲቀራረቡ ይገፋፋል፡፡ ተማሪዎቹ ዳንስ ማሠልጠንና በጎ አድራጎትን ጨምሮ በተለያዩ ክንውኖች መተባበራቸው የትስስሩ ውጤት መሆኑንም ያምናል፡፡ ከዚህ ቀደም በመደበኛ ትምህርት ካስተማረው በተጨማሪ፣ ለአሜሪካ ኤምባሲና ለአፍሪካ ኅብረት አባላትም ሥልጠና ሰጥቷል፡፡ ዳንሱ እያገኘ ያለው ተቀባይነት እውቅና ማሳያም ይሆናል፡፡
በአቢሲኒያ የሥነ ጥበብና ሞዴሊንግ ትምህርት ቤት ከሚሰጡ የዘመናዊ ዳንስ ዓይነቶች አንዱ ሳልሳ ነው፡፡ መሥራቿ ገነት ከበደ እንደምትለው፣ በመደበኛ ለአሥር ወራት ከሚሰጠው ትምህርት በተጨማሪ ክረምትም ኢመደበኛ ሥልጠና መውሰድ ይቻላል፡፡ ‹‹ከባህላዊ ውዝዋዜ ትምህርት ጋር ሲነጻጸር ዘመናዊ ዳንስ መማር የሚፈልጉት ታዳጊዎችና ወጣቶች ናቸው፤›› ስትል ትገልጻለች፡፡
ብዙዎች ባህላዊ ውዝዋዜ መማርን ቢመርጡም ዘመናዊ ዳንስ የሚማሩም አሉ፡፡ በቅርቡ በወጣው መርሐ ግብር መሠረት መምህራንና ተማሪዎችም የብቃት ማረጋገጫ ፈተና እንዲወስዱ እንደሚደረግ ገነት ትናገራለች፡፡ በአገር አቀፍ ደረጃ የዳንስ ሥርዓተ ትምህርት መቀረጹና ምዘና መካሄዱ ሙያውን እንደሚያስከብረው ታምናለች፡፡
‹‹ተመሳሳይ ሥርዓተ ትምህርት መከተሉ፣ ትምህርቱ ወጥ እንዲሆን ያደርጋል፤›› ትላለች፡፡ ሙያው ክብር እንዲኖረው እንደሚያግዝም ታክላለች፡፡ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በቴክኒክና ሙያ ጥምረት የወጣውን የደረጃ መመዘኛ የሚያልፉ ተማሪዎች ሰርተፍኬት ይሰጣቸዋል፡፡ ይህም ለብቃታቸው ማስረጃ ሆኖ ማገልገሉ ለሙያዊ ሕይወታቸውን ጠቀሜታ እንዳለው ትገልጻለች፡፡ ‹‹ሙያው በልምድ ብቻ ሳይሆን በዕውቀት መደገፍ አለበት፤›› የምትለው ገነት፣ የዳንስ ትምህርት ፈር እንዲይዝ ወጥ ሥርዓተ ትምህርት መተግበሩና መመዘኛ መስፈርት መዘጋጀቱ እንደሚረዳ ታምናለች፡፡