Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየቅዱስ ላሊበላ ውቅር መቅደሶችን የመታደግ ጅምር

የቅዱስ ላሊበላ ውቅር መቅደሶችን የመታደግ ጅምር

ቀን:

‹‹…የምገልጽበት ቋንቋ የለኝም፡፡ የዚህን ክቡር ሰው፣ ከሁሉም መሬታውያን በጥበብም ሆነ በሥነ ጽድቅ የከበረ ላሊበላ ከአንድ ደንጊያ፣ ከአንድ አለት ፈልፍሎ ዐሥር አብያተ ክርስቲያናትን ያነፀው ዐቢይ ሥራ የምገልጽበት ልሳን የለኝም::›› ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት በዛጒዬ ሥርወ መንግሥት ዘመን በላስታ ላሊበላ የተሠሩትን ዕፁብ ድንቅ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን ያከናወናቸው የቅዱስ ላሊበላን ገድል በኋላ ዘመን ላይ የጻፈው ደራሲ ውሳጣዊ ስሜቱን የገለጸበት ነበር፡፡

የነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ሥራ አስደናቂነት ለመግለጽ ቃል እንዳነሰው እነዚህ ላሊበላ ባንድ ቋጥኝ ያሠራቸው፣ ሰሎሞን በጢሮስ ንጉሥ በኪራም እየተረዳ በኢየሩሳሌም ካሠራው ቤተ መቅደስ እንደሚበጥልም አመስጥሯል፡፡ የላሊበላም ጥበብ ከሰሎሞን መብለጡን ጭምርም በመግለጽ ሰው ሁሉ እየመጣ ባይኑ እያየ ሊያደንቃቸው የሚገባ መሆኑንም ‹‹በላሊበላ እጅ የተሠሩትን ዕፁብ ድንቅ ግብረ ሕንፃዎችን ለማየት የሚፈቅድ ይምጣና በዓይኖቹ ይይ (ይምጻእ ወይርአይ በአዕይንቲሁ) ነበር፤›› ያለው፡፡

አቶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ኑቢያ አክሱም ዛጒዬ›› በሚባለው መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ የቅዱስ ላሊበላን ገድል የጻፈው ጸሐፊ ምንም ያህል የተሳሳተው ነገር የለም፡፡ የነዚህን የአብያተ ክርስቲያናት ሥራ የተመለከቱ የውጭ አገር ሰዎች እሥፍራው ድረስ እየመጡ ባይናቸው እያዩ ተደንቀዋል፡፡ ከተመለከቱትም ውስጥ ይኼን የመሰለ በቋጥኝ ውስጥ እየተፈለፈለ የተሠራ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት በዓለም አለመኖሩን የገለጹም ብዙ ናቸው፡፡

‹‹አዲሲቱ ኢየሩሳሌም›› የሚል ተቀጽላ ያገኙት የመካከለኛው ዘመን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በዐረፍተ ዘመኑ ካገር ቤት እስከ ባሕር ማዶ የብዙዎች ጎብኚዎችን፣ ተሳላሚ ምዕመናን ቀልብ መያዝ ችለዋል፡፡ በዚህም ሳይገደብ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት- ዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሆኖ መመዝገብ መሥፈር ችለዋል፡፡

የላሊበላ ገጽታ

በኢትዮጵያ በርካታ አስደናቂ አብያተ ክርስቲያናት ይገኛሉ፡፡ ከነዚህም መካከል ገናና የሆኑት ካንድ አለት ተፈልፍለው የታነፁት ናቸው፡፡ የአገሪቱ የክርስትና መነሻ መዲና ከሆነችው አክሱም ደቡባዊ አቅጣጫ በተለያዩ መንገዶች ከ240 ኪሎ ሜትር እስከ 394 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው ቅዱስ ላሊበላ ከተማ የሚገኙት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የኢትዮጵያን ጥንታዊ የኪነ ሕንፃ ትውፊትን በግሩም ሁኔታ የሚያንፀባርቁ ናቸው፡፡ 11 ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በጉያዋ የያዘችው ላሊበላ በኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ምዕመናን በየወቅቱ የሚዘልቁባት የሚሳለሙበት ሥፍራ ናት፡፡

በታሪክ እንደሚወሳው የከተማዋ የመጀመሪያ መጠሪያ ሮሃ ሲሆን በ12ኛው ምዕት ዓመት የነገሠው ንጉሥ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናቱን ያነፀው እርሱ በመሆኑ ከተማዋ ስሙን አግኝታለች፡፡

11ዱ አብያተ ክርስቲያናት በሦስት የተለያዩ ሥፍራዎች ሲገኙ፣ ስድስቱ በሰሜን አቅጣጫ፣ አራቱ በሊባ (ደቡባዊ ምሥራቅ) አቅጣጫ ሆነው የሚገናኙበት መስመር አላቸው፡፡ 11ኛው ቤተ ክርስቲያን- ቤተ ጊዮርጊስ ብቻውን ተነጥሎ ነው ያለው፡፡

በሰሜናዊ ክበብ የሚገኙ (1) ቤተ መድኃኔ ዓለም (2) ቤተ ማርያም  (3) ቤተ መስቀል (4) ቤተ ደናግል (5) ቤተ ሚካኤል (6) ቤተ ጎልጎታ ሲሆኑ፤ በሊባ በኩል (7) ቤተ አማኑኤል (8) ቤተ አባ ሊባኖስ (9) ቤተ መርቆርዮስ (10) ቤተ ገብርኤልና ቤተ ሩፋኤል ይገኛሉ፡፡ በምዕራባዊ አቅጣጫ ለብቻው ያለው ከላይ ወደታች ተፈልፍሎ የታነፀው 11ኛው ቤተ ጊዮርጊስ ይገኛል፡፡

ውቅሮቹ እምን ላይ ይገኛሉ?

የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት በዕድሜ ብዛት በደረሰባቸው ተፈጥሯዊ ጫና ምክንያት በተለይ ከአሠርታት ዓመታት ወዲህ ከተወሰደው ዕርምጃ አንዱ በከባድ የብረት ምሰሶ ከለላ እንዲሆንላቸው የተሠራላቸው ጥላ ነው፡፡ ለአምስት ዓመት ታስቦ የተጋረዱት ጥላዎች ከጥቅማቸው ጉዳታቸው ስላመዘነና በጥናትም በመረጋገጡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲነሱ መወሰኑን መግለጹ ይታወቃል፡፡

ይሁን እንጂ ጥላው እንዲነሳ መወሰኑን ለአስፈላጊ ጥገናም 20 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግም ሚኒስቴሩ ይፋ ቢያደርግ የብረት ጥላዎቹን የማንሳት ሥራ መቼ እንደሚጀመር አልተገለጸም፡፡

በወቅቱ እንደተገለጸው፣ በላሊበላ በአሳሳቢ ሁኔታ ውስጥ ካሉት ቅርሶች መካከል እነ ቤተ መድኃኔ ዓለም፣ ቤተ መርቆሪዎስ በዕድሜ ብዛት በደረሰባቸው ተፈጥሯዊ ጫና ምክንያት እየተፈረካከሱ ፈተና ውስጥ መግባታቸውን ቅርሱን ለመጠገን የተወሰዱ ዕርምጃዎች አንፃራዊ ለውጥ ከማምጣት ይልቅ ወደተባባሰ ችግር እያመሩ መሆኑንም ተመልክቷል፡፡

የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን (ቅጥጥባ)፣ ከስምንት መቶ ዓመታት በላይ ካስቆጠሩት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካከል፣ ቀደም ባሉት ዓመታት በቤተ ገብርኤል- ሩፋኤል ካከናወነው የጥገና ፕሮጀክት በመነሳት በሌሎች ቤተ መቅደሶች ላይም ዕድሳት ማድረግ የሚያስችለውን እንቅስቃሴ ባለፈው ጥር ወር መገባደጃ ላይ ጀምሯል፡፡ ቅጥጥባ ከወርልድ ሞኒዩመንት ፈንድ (የዓለም ቅርስ ድጋፍ) ጋር በመሆን በቤተ ጎልጎታና ቤተ ሚካኤል ላይ የጥገናና እንክብካቤ ሥራ ለመሥራት የሚያስችለውን የጥገና ፕሮጀክት ጥር 26 ቀን 2010 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡

ቅጥጥባ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ ፕሮጀክቱ የሚከናወነው በአሜሪካ ኤምባሲ አማካይነት ከአሜሪካ አምባሳደሮች ድጋፍ (ፈንድ) ለባህላዊ ቅርሶች ከተሰኘው ተቋም በተገኘው ግማሽ ሚሊዮን ዶላር (13.7 ሚሊዮን ብር ግድም) እና ወርልድ ሞኒዩመንት ፈንድ በሚጨምረው 119,500  ዶላር ነው፡፡ ስምምነቱን በላሊበላ ከተማ የተፈራረሙት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣንና ወርልድ ሞኒዩመንት ፈንድ ናቸው፡፡

ባለሥልጣኑ በድረ ገጹ እንዳብራራው፣ የቤተ ጎልጎታ ቤተ ሚካኤል ጥገና ፕሮጀክት ያነገባቸው ሦስት ዋና ግቦች  በቤተ ክርስቲያናቱ ላይ የጥገና ተግባር በማከናወን ቅርሱን ከጉዳት መታደግ፤ በቤተ ገብርኤልሩፋኤል ላይ የተገኘውን ተሞክሮ ማጎልበትና  የአገር ውስጥ የእጅ ሙያ ባለቤቶችን አቅም ማሳደግ ናቸው፡፡

ፕሮጀክቱ የሚደገፈው በአሜሪካ ኤምባሲ፣ በወርልድ ሞኒዩመንት ፈንድ፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ በላሊበላ ከተማ አስተዳደር፣ በአማራ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መሆኑ ታውቋል፡፡

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክል ራይነር፣ ከላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መካከል ለቤተ ጎልጎታና ቤተ ሚካኤል ቤተ መቅደሶች ዕድሳት ማድረግ የሚያስችል የፕሮጀክት ስምምነት ጥር 26 ቀን በተፈረመበት አጋጣሚ ‹‹ላሊበላ ትናንትን ከዛሬ ጋር ያገናኘ መንፈሳዊ ድልድይ ነው!›› በማለት ከመግለጽ አልተቆጠቡም፡፡

ቅርሶችን ለመታደግ የታሰበው የሕግ ማዕቀፍ

     መሰንበቻውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ለአደጋ የተጋለጡ ቅርሶችን በዘላቂነት ለመታደግ የሚያስችል የሕግ ማዕቀፍ እየተዘጋጀ ነው።

አገራዊ ቅርሶችን በዘላቂነት ለመጠገን የሚያስችል ‹‹የቅርስ ፈንድ›› የተሰኘ የሕግ ማዕቀፍ የማዘጋጀት ኃላፊነት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ወስዶ እየሠራ ነው። ማዕቀፉ በዋናነት ለቅርስ ጥገና የሚሆን ፋይናንስ ማሰባሰበን ያለመ እንደሆነም ተመልክቷል።

የቅርስ ጥገና በርካታ መዋለ ንዋይ በመጠየቁመንግሥት በተጨማሪ ሌሎችም እንዲሳተፉበት እንደሚደረግ፣  በቀጣይም አደጋ ላይ ያሉ የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናትን በሙሉ ለመጠገን የሚያስችል የፋይናንስ አቅም ለመፍጠር የሚሠራ አገራዊ ኮሚቴ እንደሚቋቋምም የባህል ቱሪዝም ሚኒስቴር በቅርቡ ማሳወቁ ይታወሳል።  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...