- ልዩነታቸው በሽምግልና ተፈትቷል ቢባልም አልሰመረም
መስከረም 28 ቀን 2009 ዓ.ም. በተደረገው የሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ ምክንያት አለመግባባት ተፈጥሮ ለሁለት ተከፍለው ከነበሩት አመራሮች፣ የእነ አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር) ቡድን አዲስ ፓርቲ ለማቋቋም ውሳኔ ላይ መድረሱን አስታወቀ፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ውሳኔ ተከትሎ የሰማያዊ ፓርቲ አመራር መሆናቸው በተረጋገጠው ሊቀመንበሩ አቶ የሺዋስ አሰፋ የሚመራው ቡድን፣ በአገር ሽማግሌዎች የተደረገውን የማስማማት ጥረትና የውሳኔው ሐሳብ ተግባራዊ ለማድረግ ፈቃደኛ አለመሆኑ ተጠቁሟል፡፡
የቀድሞ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንር አቶ ይልቃል ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ በአገሪቱ እንደ ልማድ እየታየ የመጣውን የፖለቲካ ፓርቲን መበታተንና መከፋፈል፣ አንድ ቦታ ላይ ለማቆም በማሰብ በፓርቲው አባላት መካከል የተፈጠረውን ልዩነት በአገር ሽማግሌዎች ለመፍታት ሲሠሩ ቆይተው ስምምነት ላይ ደርሰው ነበር፡፡ ነገር ግን በሽማግሌዎቹ ውሳኔ መሠረት ልዩነቶቻቸውን በመተው በአንድ መንፈስ ለመሥራት የእሳቸው ቡድን የተነሳሳ ቢሆንም፣ በእነ አቶ የሺዋስ በኩል በድጋሚ መንገዶቹን ሁሉ ዝግ መደረጋቸውን አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም በወጣቶችና በሴቶች ላይ ትኩረት ያደረገ፣ በዜግነት፣ በአገር ግንባታና መሠረታዊ በሆኑት በነፃነት፣ በእኩልነትና በወገናዊነት ላይ ያተኮረ አገር አቀፍ ፓርቲ ለመመሥረት ከአባላቱ ጋር ተወያይተው ውሳኔ ላይ መድረሳቸውንም አስረድተዋል፡፡ ስለሺ ፈይሳ፣ መዓዛ መሐመድ፣ ወይንሸት ሞላ፣ ምዕራፍ ይመር፣ አዲሱ ጌታነህ፣ ደምሳሽ ኃይሉና ቴዎድሮስ አሰፋ የሚባሉ ሰባት አባላት ያሉት ኮሚቴ መቋቋሙን ጠቁመዋል፡፡
‹‹የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ (ኢአአን)›› የሚል መጠሪያ ያለው ፓርቲ ማቋቋማቸውንና ከየካቲት 5 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማመልከቻ እንደሚያስገቡ አቶ ይልቃል አስረድተዋል፡፡ ፓርቲው ጥላቻንና የእልህ መንፈስን አርጋቢ ሆኖ እንዲሠራ ጥረት እንደሚደረግና በአጭር ጊዜ ውስጥ መሥራች ጉባዔ እንደሚያካሂድ አስታውቀዋል፡፡ በእነሱና በእነ አቶ የሺዋስ መካከል ተፈጥሮ የነበረውን አለመግባባት መርምረው ውሳኔ ያስተላለፉት የአገር ሽማግሌዎችን አመሥግነው፣ ልፋታቸው ተግባራዊ ባለመደረጉ ግን ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡
ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሰማያዊ ፓርቲ የወቅቱ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ እንደገለጹት፣ በሽማግሌዎች አማካይነት ስምምነት ላይ የተደረሰው አንጃቸውን አፍርሰው እንዲመለሱ ነው፡፡ ‹‹በማንኛውም ጊዜ ቢመለሱ እንቀበላቸዋለን፡፡ ሥራ እየሠራን ስለሆነ የፓርቲውን መተዳደሪያ ደንብ አክብረው ወደ ፓርቲው በመመለስ ተስማምተው መቀጠል እስከቻሉ ድረስ፣ በሩ ክፍት መሆኑንና በስምምነታቸው መሠረት እየጠበቅናቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡
ጠበቃው አቶ ተማም አባቡልጉ ሰብሳቢ፣ አቶ ታዲዎስ ታንቱ፣ አቶ ይልማ ደፋሩና አቶ ብርሃኑ ሞገሴ የሚባሉ ግለሰቦች አባል የሆኑበት የእርቅ ሽምግልና ጉባዔ ለወቅቱ የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ የሺዋስ አሰፋ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ መጻፉን፣ በፓርቲው አባላት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በእርቅ እንዲፈታና ሁለቱም ወገኖች በደብዳቤ ጥያቄ ማቅረባቸውን ዘርዝሮ ከስድስት ወራት ውጣ ውረድ በኋላ ኅዳር 30 ቀን 2010 ዓ.ም. ውሳኔ ላይ መድረሱን አስታውሷል፡፡
ሁለቱም ወገኖች በሽምግልናው የተደረሰበትን ውሳኔ ተቀብለው ተግባራዊ እንደሚያደርጉ የገለጹ ቢሆንም፣ በአሁኑ ጊዜ ግልጽ ባልሆነ ምክንያት አቋማቸውን መቀየራቸውንና ለእርቁ መሰናክል መሆናቸውን የሽምግልና ጉባዔው አስታውቋል፡፡ ‹‹ለቃሉና ለህሊናው ያልታመነ ለአገርና ለሕዝብ መታመኑን ለመቀበል እንቸገራለን፤›› ያለው የእርቅ ሽማግልና ጉባዔው፣ ውሳኔውን በአስቸኳይ ተግባራዊ ካላደረጉ አፍራሽ አቋማቸውን በማስመልከት ለኢትዮጵያ ሕዝብ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የሚያሳውቅ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በጉባዔው የማሳሰቢያ መግለጫ ላይ አቶ ብርሃኑ ሞገሴ በሐሳብ ተለይተዋል፡፡ አቶ ብርሃኑ የሚሉት ሁለቱ ወገኖች ጉባዔው ባቀረበላቸው የውሳኔ ሐሳብ መሠረት ለመፈጸም ቃል ገብተው ስለተስማሙ፣ የእርቅ ሽምግልና ጉባዔውም ተግባርና ኃላፊነት እዚያ ላይ በማብቃቱ የእርቅ ሐሳብን እንደ ፍርድ ቤት ውሳኔ አስገድዶ ማስፈጸም አይቻልም ብለዋል፡፡ በመሆኑም ‹‹ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ›› አካሄድ ውስጥ መግባት እንደሌለባቸው ገልጸው የልዩነት ሐሳባቸውን አስፍረዋል፡፡
የጉባዔውን ሰብሳቢ አቶ ተማም አባቡልጉን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሁለቱ ወገኖች በደብዳቤ እንዲያስማሟቸው ጠይቀው ነበር፡፡ ሽማግሌዎች ያሉንን ለመቀበልና ተግባራዊ ለማድረግም በመስማማት የሽምግልና ጉባዔ መቋቋሙን፣ ለስድስት ወራትም ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፈው እንዲስማሙ ማድረጋቸውን አስረድተዋል፡፡ በተስማሙት መሠረት የሽማግሌዎቹን ውሳኔ ተግባራዊ የማያደርጉ ከሆነ፣ የነበረውን ሁሉ ዘርዝረው ለሕዝብ ይፋ እንደሚያደርጉ አቶ ተማም አስታውቀዋል፡፡