Saturday, June 10, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ለብሔራዊ መግባባትና አንድነት የሚረዱ ዕርምጃዎች ይፋጠኑ!

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የተጀመረው እስረኞችን የመፍታትና ክስ የማቋረጥ ዕርምጃ ሰሞኑን ቀጥሎ፣ 746 እስረኞችና ተጠርጣሪዎች እንዲለቀቁ እንደተወሰነ ሰሞኑን ተሰምቷል፡፡ ከዚህ ቀደም ሲል በፌዴራል 115፣ በደቡብ ክልል 413፣ በኦሮሚያ ክልል 2,345፣ እንዲሁም በአማራ ክልል 2,905 ታሳሪዎች መፈታታቸው አይዘነጋም፡፡  በተገባው ቃል መሠረት የእስረኞች መፈታት እንደ አንድ ትልቅ ዕርምጃ ሊቆጠር ይገባል፡፡ በተለያዩ ምክንያቶች ተፈርዶባቸው የታሰሩና ክስ የተመሠረተባቸው ዜጎች ከእስር መለቀቃቸው ለአገር ዕፎይታ ነው፡፡ ጅምሩ ተጠናክሮ በመቀጠል ሌሎች ታሳሪዎችና ተከሳሾችም ይለቀቁ ዘንድ መንግሥት በብርቱ ሊያስብበት ይገባል፡፡ እልህና ግትርነት የተሞላበት የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ገጽታው ተለውጦ፣ ወደ ብሔራዊ መግባባትና አንድነት ማምራት ተገቢ ነው፡፡ ይህ ዕውን እንዲሆን ደግሞ ገዥው ፓርቲ፣ አጋሮቹ፣ በተቃውሞ ጎራ የተሠለፉና የአገር ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች በሙሉ በሰከነ መንፈስ ለመነጋገር የሚችሉበት ሁሉን አቀፍ መድረክ እንዲፈጠር መበርታትና መድፈር ያስፈልጋል፡፡ እስካሁን ከነበረው አዙሪት ውስጥ ጨክኖ መውጣት የግድ ይላል፡፡

በዚህ በሠለጠነ ዘመን ለሕግ ብቻ በመገዛት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዴት መገንባት እንዳለበት ተቀምጦ መነጋገር ተገቢ ነው፡፡ እስካሁን ይታዩ የነበሩ መላ ቅጣቸው የጠፋና በመጪው ትውልድና በታሪክ ፊት የሚያስጠይቁ አሳዛኝና አሳፋሪ ድርጊቶች መወገድ አለባቸው፡፡ በታላቁ የኢትዮጵያዊነት የጋራ አጀንዳ ሥር በእኩልነትና በመከባበር ተቀራርቦ መነጋገርና አገሪቱ የገጠማትን ፈተና በብልኃት ማለፍ የዚህ ትውልድ ታላቅ ኃላፊነት ነው፡፡ ጠባብ ብሔርተኝነትና ቡድናዊ መሳሳብ ለዚህች ታሪካዊ አገርም ሆነ ለዚህ ጨዋና አስተዋይ ሕዝብ አይመጥንም፡፡ ግልጽነትና ተጠያቂነት እየጠፋ ብዙ በደሎች ደርሰዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶች እየተገፈፉ ዜጎች አሳራቸውን አይተዋል፡፡ ለአገር ግንባታ የሚጠቅሙ በርካታ ልምድና ክህሎት ያሉዋቸው ወገኖች እየተገፉ አገር ለኪሳራ ተዳርጋለች፡፡ የአገሪቱ ንፁኃን ዜጎች ሕይወት በከንቱ እንደ ቅጠል እንዲረግፉ ያደረጉ አሳዛኝ ስህተቶች ተፈጽመዋል፡፡ የሕግ የበላይነት እየተጣሰ ሕገወጦች ያሻቸውን አድርገዋል፡፡ የአገር ሀብት እንደ ነቀዝ የሚያወድሙ ሌቦች እንደ አሸን ፈልተዋል፡፡ ዜጎችን በገዛ አገራቸው ባዕድና የበይ ተመልካች ያደረጉ መድሎዎች በስፋት ተፈጽመዋል፡፡ በእነዚህና በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች ሳቢያ የአገር ህልውና አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ ከእንዲህ ዓይነቱ አስፈሪና አስደንጋጭ ችግር ውስጥ በአስቸኳይ ለመውጣት የጋራ መግባባት መፈጠር አለበት፡፡ ለዚህም ሲባል ሁሉም ወገን ወገቡን ጠበቅ አድርጎ መነሳት ይኖርበታል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በአገሪቱ የታዩ ነውጦችና ሁከቶች መነሻ ምክንያት፣ የተጠራቀሙ ብሶቶች መሆናቸውን መቼም ቢሆን መካድ አይቻልም፡፡ ምንም እንኳ በጣም ከዘገየ በኋላ ኢሕአዴግ ጣቱን ወደ ውጭ መቀሰር ትቶ ራሱን ተጠያቂ ቢያደርግም፣ የገባውን ቃል በማክበር አሁንም የተፋጠኑ ዕርምጃዎችን መውሰድ አለበት፡፡ ከሕዝብ የቀረቡለት መሠረታዊ ጥያቄዎች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስሱ ስለሆኑ፣ ምላሽ አሰጣጡ ደግሞ ችግሮችን ከሥር መሠረታቸው በማብጠርጠር መሆን አለበት፡፡ በዚህ መሠረት መፍትሔዎችን ለማምጣት የሚቻለው ሕዝብ ጠያቂ አሕአዴግ መላሽ በመሆን ብቻ አይደለም፡፡ አሁን ላጋጠሙ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የሌሎች ወገኖች ተሳትፎ ያስፈልጋል፡፡ ‹አንድ አይነድ አንድ አይፈርድ› እንዲሉ ከዚህ በፊት የተሠሩ ስህተቶች ታርመው ትክክለኛውን ጎዳና መያዝ የሚቻለው፣ የአገር ጉዳይ የሚያገባቸው ወገኖች በሙሉ የሚፈለግባቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ ሲደረግ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ራሱን እንደ አንድ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ በማየት፣ በሕጉ መሠረት ሌሎች ተሳትፎአቸው ሳይገደብ እንዲንቀሳቀሱ የተቆላለፈውን በር መክፈት አለበት፡፡ አገር ሰላም ሆና ሕዝብ በነፃነት መንቀሳቀስ የሚችለው ሌላው ቢቀር በአገሪቱ ሕገ መንግሥት ውስጥ የሠፈሩ መሠረታዊ መብቶች ሲከበሩ ነው፡፡ ይህ ሕገ መንግሥት አንድ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ እንዲገነባ ቃል የተገባበት ሰነድ ሲሆን፣ በዚህ መሠረት መነሳሳት ቢቻል እንኳ በርካታ ችግሮች ይወገዳሉ፡፡

ዘወትር እንደምንለው ከአገር ህልውና በላይ ምንም ነገር የለም፡፡ አገር ዙሪያዋን ባሰፈሰፉ ጠላቶች ተከባ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚደረገው ኢዴሞክራሲያዊ ሽኩቻና እርባና ቢስ መተናነቅ ሊገታ ይገባል፡፡ አሸናፊም ተሸናፊም የማይኖርበት ዕልቂትና ውድመት ከሶማሊያ፣ ከየመን፣ ከሶሪያ፣ ከሊቢያና ከመሳሰሉ አገሮች በቂ ልምድ ተወስዶበታል፡፡ ሞኝ ይመስል ከሌሎች ስህተት አለመማርና እዚያው አረንቋ ውስጥ መዘፈቅ በታሪክ ፊት ይቅር የማይባል ስህተት ነው፡፡ ይህች ታሪካዊ አገርና ይህ ጨዋና አርቆ አሳቢ ሕዝብ ይከበሩ፡፡ ኢትዮጵያ የነፃነት ተምሳሌትና የሥልጣኔ አብሪ ኮከብ የነበረች ታላቅ አገር ናት፡፡ ወደ ታላቅነቷ መመለስና በነፃነት የሚኖርባት አገር እንድትሆን ማድረግ ሲገባ፣ በእልህና በግትርነት መተናነቅ ከጥፋት በስቀር የሚፈይደው የለም፡፡ እስረኞችን በመፍታት የተጀመረው ዕርምጃ ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የበለጠ ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር፣ ከወዲሁ በቅንነትና በአገር ፍቅር ስሜት መነሳሳት ይገባል፡፡ የዘመናት ቂምና ቁርሾ ይዞ ‹ይለይልን› የሚሉት አጉል ድንፋታ በዚህ ዘመን ያስንቃል እንጂ አያስሞግስም፡፡ አጉል ጀብደኝነት የዴሞክራትነት መገለጫም አይደለም፡፡ ከሰብዓዊነት እየተለያዩ ጭካኔና በቀልን ማለም ጤነኝነት አይደለም፡፡ ሥልጣን በጉልበት መያዝም ሆነ ሥልጣን ላይ በጉልበት ለመንሰራፋት መሞከር ፀረ ዴሞክራሲ ድርጊት ነው፡፡ ይህ ዘመን ለሐሳብ የበላይነትና ልዕልና ቅድሚያ የሚሰጥበት እንጂ፣ አምባገነንነትን በማራባት ሥልጣን ላይ የሚንፈራጠጡበት አይደለም፡፡ ይህ ዓይነቱ ድርጊት ከሕዝብ ጋር የበለጠ ያናክሳል እንጂ አያወዳጅም፡፡

በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች በሙሉ ሊገነዘቡ የሚገባው፣ ፖለቲካ የትርፍ ጊዜ ሥራ ወይም የተወሰነ ቡድንን ጥቅም ለማሳካት የሚደራጁበት ንግድ አይደለም፡፡ በሌላ በኩል በብዙዎቹ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ በገሃድ እንደሚታየው፣ የአኩራፊዎች መሰባሰቢያ ዋሻም መሆን የለበትም፡፡ የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የተዘጋጀ ፓርቲ ራሱን የቻለ ዘመናዊ አደረጃጀት፣ ዘመኑን የሚመጥን  የፖለቲካ ፕሮግራምና ዓላማ ኖሮት አባላቱንና ደጋፊዎቹን በፅናት ማታገል የሚችል መሆን ይኖርበታል፡፡ ሕዝብን ሲቀርብም አጀንዳውን በሚገባ ቀርፆ ማሳመን መቻል አለበት፡፡ የሚቀናቀነውን ፓርቲ ድክመት ብቻ እየተከታተለ ባለበት የሚረግጥ የፖለቲካ ፓርቲ አሁንም አለሁ ከሚል ቢመክን ይሻላል፡፡ አሁን የሚያስፈልገው ሰላማዊው የፖለቲካ ምኅዳር በሚገባ ተከፋፍቶ በሕግ የበላይነት ሥር ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ ትግል ማድረግ መቻል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በዕውቀት የበሰሉ፣ በልምድ የዳበሩ፣ ከሕገወጥነት የራቁ፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት መጣል የሚችሉ፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ የሚያምኑ፣ ልዩነትን የሚያከብሩ፣ ሕዝብን የሚያከብሩና የልብ ትርታውን የሚያዳምጡ፣ ለዴሞክራሲያዊ መርሆዎች የሚገዙ፣ ወዘተ. ዜጎች ናቸው የሚያስፈልጉት፡፡ ከዚህ ውጪ አሁን በስፋት እንደሚታየው መርህ የለሾች፣ አሉባልተኞች፣ የሰዎችን ነፃነት የሚጋፉ፣ ጠባቦች፣ ትምክህተኞችና ለዘመኑ አስተሳሰብ የማይመጥኑ ከንቱዎች ለአገር ምንም ፋይዳ የላቸውም፡፡ የዘመኑን ትውልድም አይመጥኑም፡፡ እነዚህን ከፖለቲካው ጎራ ገለል በማድረግ ለዘመኑ የሚበጁትን ይዞ መቀጠል ብሔራዊ መግባባትንና አንድነትን ያፋጥናል፡፡ ይህ ልብ ሊባል ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በሰላም መኖር አለበት፡፡ መብቱ መከበር አለበት፡፡ በእኩልነትና በነፃነት የሚኖርባት አገር እንድትኖረው ስለሚፈልግ በዚህ መጠን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ የሕዝቧ ገነት እንጂ ሲኦል መሆኗ ማብቃት አለበት፡፡ እስር ቤቶች የወንጀለኞች ማረሚያ እንጂ የተፎካካሪ ማሰሪያ መሆን የለባቸውም፡፡ ሕዝቡ ለዘመናት ተከባብሮና ተፋቅሮ፣ እንዲሁም ተጋብቶና ተዋልዶ የሚኖርባት ኅብረ ብሔራዊት አገር የጠባብ ብሔርተኞች መፈንጫ ልትሆን አይገባም፡፡ ኅብረ ብሔራዊት አገር በሕዝቦቿ እኩልነትና መፈቃቀድ ላይ መመሥረት የምትችለው ለሐሳብ ብዝኃነትም ዕውቅና ሲሰጥ ነው፡፡ በሐሳብ መለያየት ሞት ስላልሆነ፣ የሐሳብ ልዩነት ለዘለዓለም ይኑር መባል አለበት፡፡ በዚህ መንፈስ መነጋገርና መግባባት ሲቻል ሌላው ዕዳው ገብስ ነው፡፡ ለዓመታት ከገነተረውና በቂም በቀል ከተመረዘው አሳፋሪና ኋላቀር አመለካከት በመላቀቅ መነጋገርና መደራደር ይለመድ፡፡ ተወደደም ተጠላ ለዚህች አገር ከሰላማዊና ከዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ትግል ውጪ ሌላው ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ቢሞከርም ተስፋ የለውም፡፡ ይልቁንስ ለብሔራዊ መግባባትና አንድነት የሚረዱ ዕርምጃዎች እንዲፋጠኑ ሁሉም ወገን የበኩሉን ይወጣ!   

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ18 ቀናት ግዢ መፈጸሚያ ብቻ እንደሚሆን አይኤምኤፍ ተነበየ

ኢትዮጵያ በ2023 የሚኖራት የውጭ ምንዛሪ ክምችት ለ0.6 ወር ወይም...

ብሔራዊ ባንክ ለጥቃቅንና አነስተኛ ብድሮች ዋስትና መስጠት ሊጀምር ነው

ኢንተርፕራይዞችን ብቻ የሚያገለግል የፋይናንስ ማዕከል ሥራ ጀመረ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ...

አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ የሁለትዮሽ የምንዛሪ ገበያ እንዳይኖር ሊመክሩ ነው

ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍና ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ ያለውን...

ባንኮች ከሚያበድሩት 20 በመቶውን የግምጃ ቤት ሰነድ እንዲገዙበት የሚያስገድድ መመርያ ፀደቀ

ሁሉም የንግድ ባንኮች ከሚለቁት ብድር ውስጥ 20 በመቶውን በየወሩ...
- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

አያሌ የውኃ “ጠርሙሶች”ን በጫንቃ

መሰንበቻውን በአይቮሪ ኮስት መዲና አቢጃን የምትኖር አንዲት ሴት፣ በሚደንቅ...

ወልቃይትን ማዕከል ያደረገው የምዕራባዊያን ጫና

በትግራይ ክልል የተከሰተው የዕርዳታ እህል ዘረፋ የዓለም አቀፍ ተቋማት...

ከቀጣዩ ዓመት በጀት ውስጥ 281 ቢሊዮን ብሩ የበጀት ጉደለት ነው ተባለ

ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት...

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

አገር አጥፊ ድርጊቶች በአገር ገንቢ ተግባራት ይተኩ!

ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በመንስዔዎች ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ መግባባት ሊኖር የሚችለው ደግሞ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር የሚያስችል ዓውድ ሲፈጠር ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ዕውን...

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን...

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና...