Monday, July 22, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየውጭ ምንዛሪ እጥረት ምርታማነትን እየጎዳ ነው

የውጭ ምንዛሪ እጥረት ምርታማነትን እየጎዳ ነው

ቀን:

  • ከአካባቢ ማኅበረሰብ ጋር በተፈጠሩ ግጭቶች ፋብሪካዎች ምርት አቁመዋል

የውጭ ምንዛሪ እጥረት የአምራች ኢንዱስትሪውን እግር ከወርች ይዞ አላላውስ እንዳለ የተለያዩ ፋብሪካዎች ገለጹ፡፡

የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥና ከአካባቢው ማኅበረሰብ ጋር የተፈጠሩ ችግሮች ለከፍተኛ ችግር እንደዳረጓቸው አምራቾች ለፌዴራል መንግሥት አስታውቀዋል፡፡

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ጋር የካቲት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ከባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው የምክክር መድረክ፣ የተለያዩ ፋብሪካዎች ባለቤቶችና ተወካዮች በውጭ ምንዛሪ እጥረት ምክንያት ምርታማነታቸው እንዳሽቆለቆለና ህልውናቸው አደጋ ውስጥ እንደገባ ገልጸዋል፡፡

የእምነበረድና ቴራዞ አምራቾች ማሽነሪዎች በብዛት እንደሚጠቀሙ ገልጸው፣ ለማሽኖች መለዋወጫ መግዣ የሚሆን የውጭ ምንዛሪ በማጣት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡

የሆራይዘን አዲስ ጎማ ፋብሪካ ተወካይ ኩባንያው ጎማዎችን በአገር ውስጥ አምርቶ ለገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ በማዳን ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ቢሆንም፣ ኩባንያቸው ለሚያስመጣቸው ግብዓቶች  የሚውል የውጭ ምንዛሪ በማጣቱ በተወሰኑ የጎማ ምርቶች ላይ ብቻ እንዲያተኩር ተገዷል ብለዋል፡፡

የቀለም ፋብሪካ ባለቤቶች በበኩላቸው የውጭ ምንዛሪ በማጣታቸው ግብዓቶችን ለማስገባት እንዳልቻሉ ገልጸው፣ ይህም ምርታማነታቸውን በከፍተኛ መጠን እንደቀነሰውና ብዙዎች ምርት በማቆም ላይ እንደሆኑ አስረድተዋል፡፡

ከብራይት ቀለም ፋብሪካ የመጡት አቶ አብርሃም ብርሃኔ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አገራዊ ችግር መሆኑን እንደሚረዱ ገልጸው፣ ባለው ውስን የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀም ላይ ችግር እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ‹‹አነስተኛ የሥራ ካፒታል ያላቸው ፋብሪካዎች በዓመት አንድ ጊዜ የውጭ ምንዛሪ ይፈቀድላቸዋል፡፡ በዓመት አምስት ሚሊዮን ዶላር ውሰድ ቢባል አንድ አነስተኛ ፋብሪካ ሊከብደው ይችላል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ግን 50,000 ዶላር እየወሰደ ሊሠራ ይችላል፡፡ ሌላው ችግር 50,000 ዶላር የሚፈልገውና አምስት ሚሊዮን ዶላር የሚፈልገው እኩል አንድ ዓመት እንዲጠብቁ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡

የውጭ ምንዛሪ ጥያቄ ሲያቀርቡ የሚያስመጧቸውን ዕቃዎች ፕሮፎርማ ለብሔራዊ ባንክ እንደሚያቀርቡ የገለጹት አቶ አብርሃም፣ ከወራት በኋላ የዕቃዎቹ ዋጋ የሚጨምር በመሆኑ አስመጪው ከሌላ አቅራቢ ለመግዛት ጥያቄ ሲያቀርብ በባንኩ ተቀባይነት እንደማያገኝ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ፕሮፎርማውን ካቀረባችሁበት ግዙ፣ አሠራራችን አይፈቅድም የሚል ምላሽ ነው የሚሰጠን፡፡ የቀነሰ ዋጋ ከሌላ አምራች ብናቀርብም መጀመርያ ካቀረባችሁበት ግዙ እንባላለን፡፡ ይህ የውጭ ምንዞሪ ማዳን ነው ወይስ ማባካን?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

ከጎዳ ጠርሙስና ብርጭቆ አክሲዮን ማኅበር የመጡት አቶ ኪሮስ አብርሃ በበኩላቸው፣ ኩባንያቸው ወደ ምርት ለመግባት ዝግጅቱን ካጠናቀቀ ከአንድ ዓመት በላይ ቢሆንም በውጭ ምንዛሪ ዕጦት ምክንያት ወደ ምርት መግባት እንዳልቻለ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ዝም ብለን ተቀምጠን የሕዝብ ገንዘብ እየበላን ነውና መፍትሔ ብንሰማ ደስ ይለናል፤›› ብለዋል፡፡

የአዋሽ መልካሳ አሉሙኒየም ሰልፌትና ሰልፈሪክ አሲድ አክሲዮን ማኅበር ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ተሰማ፣ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኙና ከውጭ የሚገቡ ዕቃዎችን የሚተኩ ፋብሪካዎች ቅደሚያ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል፡፡  

‹‹አንዳንድ ፋብሪካዎች የቅደሚያ ቅድሚያ ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ለምሳሌ የእኛ ፋብሪካ የውኃ ማጣሪያ ኬሚካል ነው የሚመረተው፡፡ ሰፊው ሕዝብ የሚጠጣው ውኃ የሚታከመው እኛ በምናመርተው ኬሚካል በመሆኑ እንደ መድኃኒት ቅድሚያ ሊሰጠን ይገባል፤›› ብለዋል፡፡

ባለሀብቶቹ የውጭ ምንዛሪ እያገኙ ያሉት አምራቾች ሳይሆኑ አስመጪዎች ናቸው የሚል አቤቱታ አሰምተዋል፡፡ አንዳንድ አምራቾች በበኩላቸው የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ ምርታማነታቸውን እየጎዳ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ጠርሙስና ብርጭቆ አክሲዮን ማኅበር ተወካይ አቶ በላይ ሥዩም ፋብሪካው ጠርሙሶች በብዛት በማምረት በተለይ ለቢራ ፋብሪካዎች በማቅረብ ላይ እንደሆነ ገልጸው፣ ‹‹የገበያ ችግር የለብንም፣ ትርፋማ ነን፡፡ ነገር ግን በየጊዜው ያለማስጠንቀቂያ በሚገጥመን ድንገተኛ የኤሌክትሪክ ኃይል መቋረጥ በምርታችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሌላው በአምራች ኢንዱስትሪው የተነሳው ዋነኛ ችግር ከአካባቢ ማኅበረሰብ ጋር የሚፈጠሩ ግጭቶች ናቸው፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የሚገኙ ፋብሪካዎች ከወጣቶች ጋር በሚፈጠሩ ግጭቶች ምርት እስከማቆም እንደደረሱ ተናግረዋል፡፡

አቶ በላይ የአዲስ አበባ ጠርሙስና ብርጭቆ ፋብሪካ ባቢሌ አካባቢ የፋብሪካ ግብዓት የሚያመርትበት ቦታ እንዳለው ገልጸው፣ በማዕድን ማውጫው ላይ የሚሠሩት ከአካባቢው የተቀጠሩ ሠራተኞች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአካባቢው ወጣቶች የድርጅቱ ተሽከርካሪዎች ጭነው ሲወጡ፣ ምንነቱ የማይታወቅ ክፍያ በመጠየቅ መስታወት ሁሉ የሰበሩበት አጋጣሚ እንዳለ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያዊያንና በቻይናዊያን ባለሀብቶች ባለቤትነት የተያዘው ኩባንያ ሁለት ተጨማሪ ፋብሪካዎችን በ200 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ለመገንባት ዝግጅት ላይ ባለበት ወቅት፣ እንዲህ ያለ ሕገወጥ ድርጊት መፈጸሙ ኢንቨስትመንቱን እንዳያስተጓጉል ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል፡፡

ሌሎች ባለሀብቶችም ተመሳሳይ ብሶት አሰምተዋል፡፡ የፈሙ ኢንዲስትሪያል ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ወንደሰን የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ የጀመራቸውን ጥረቶች እንደሚደግፉ ተናግረዋል፡፡ አሠራሩ ግን እስከ ወረዳ ዘልቆ ወጥነት የለውም ብለዋል፡፡ ኩባንያቸው የመጀመርያው የጅብሰም ቦርድ አምራች መሆኑን የገለጹት አቶ ዳንኤል፣ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አውጥቶ ያለማውን የጥሬ ዕቃ ማምረቻ ካባ እንዳይጠቀም በመከልከሉ፣ ፋብሪካቸው ምርት ካቋረጠ 13 ወራት እንደተቆጠሩ ገልጸዋል፡፡

      ‹‹ፋብሪካችን ምርት በማቋረጡ ከውጭ ጂብሰም ቦርድ በውጭ ምንዛሪ ተገዝቶ እየገባ ነው፡፡ ጂብሰም ቦርድ ማለት 85 በመቶ ድንጋይ ተፈጭቶ የሚገኝ ምርት ነው፡፡ ስለዚህ ድንጋይ ሰብስበን በዶላር እያስገባን ነው፤›› ያሉት አቶ ዳንኤል፣ ድርጅታቸው ምርት ቢያቆምም ለሠራተኞች ደመወዝ በመክፈል ላይ እንደሆነ በምሬት ገልጸዋል፡፡

      የአዋሽ መልካሳ አሉሚኒየም ሰልፌት ፋብሪካ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተሾመ ተሰማ በበኩላቸው፣ ፋብሪካቸው በዋነኛነት የሚጠቀመው ካኦሊን የተባለ ማዕድን የሚያቀርብላቸው የኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክሲዮን ማኅበር የማዕድን ማውጫው ከሚገኝበት አካባቢ ማኅበረሰብና ከወረዳ አስተዳደር ጋር በተፈጠረ አለመግባባት በመዘጋቱ፣ የካኦሊን አቅርቦት እንደተቋረጠበት ተናግረዋል፡፡ ‹‹አሁን እያመረትን ያለነው በመጋዘናችን ካለ ካኦሊን ክምችት ነው፡፡ ክምችቱ ግን ከሁለት ሳምንት በኋላ የሚያልቅ በመሆኑ ምርት ለማቋረጥ እንገደዳለን፤›› ብለዋል፡፡

      የኢስት ሲሜንት ኩባንያ ተወካይ ፋብሪካው ጥሬ ዕቃ የሚያመርትበት ካባ በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው፣ የአካባቢው ኅብረተሰብ  የጭነት ተሽከርካሪዎች በሚፈጥሩት አቧራ በመማረሩ ‹‹አስፋልት ካልተሠራ ተሽከርካሪዎቹ ማለፍ አይችሉም፤›› በማለት እንቅስቃሴ መገታቱን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ኢስት ሲሜንት ከጳጉሜን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ ምርት እንዳቋረጠ ተናግረዋል፡፡

      ከአምራቾች ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሀላላ የውጭ ምንዛሪ እጥረት አገራዊ ችግር መሆኑን ጠቅሰው፣ መፍትሔውም ያለው በአምራች ኢንዱትሪው ዘንድ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹እኛ መፍትሔ ሰጪ አካል ነን፡፡ የኢንዱስትሪዎች ምርታማነት በማሳደግና ወደ ውጭ የምትልኩትን ምርቶች በመጨመር የውጭ ምንዛሪ ገቢ ማሳደግ አለባችሁ፤›› ብለዋል፡፡ አምራች ኢንዱስትሪዎች የውጭ ምንዛሪ በሚያገኙበት ሁኔታ ላይ ከብሔራዊ ባንክ ኃላፊዎች ጋር በመነጋገር ጥረት እንደሚደረግ የገለጹት አቶ ሳሙኤል፣ አንዳንድ ጊዜ ችግሩ ከአቅም በላይ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

      የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥን በተመለከተ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ኃላፊዎች ጋር በየጊዜው ውይይት እንደሚደረግ የገለጹት አቶ ሳሙኤል፣ በዚህ ረገድ መሻሻሎች እንዳሉ ጠቁመው የበለጠ ለመሥራት ጥረት እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

      የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር) ከአምራቾች ለቀረቡ ቅሬታዎች ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ የውጭ ምንዛሪ እጥረቱ የተከሰተው ኢኮኖሚው

የሚያመነጨው የውጭ ምንዛሪና የሚያስወጣው ተመጣጣኝ ባለመሆኑ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የወጪና የገቢ ንግድ ሚዛን ተዛብቷል፡፡ የአምራች ኢንዱስትሪው አፈጻጸም ጥሩ አይደለም፡፡ ከሁለት ዓመት በላይ ይሆናል፡፡ ይህ አገራዊ ችግር መሆኑን ተረድቶ በውጭ ምንዛሪ ግኝት ላይ በጋራ መረባረብ ያስፈልጋል፡፡ መንግሥት አምራች ኢንዱስትሪው ያጋጠመውን ማነቆ የማስወገድ ኃላፊነት አለበት፤›› ብለዋል፡፡

ሚኒስትር ዴኤታው ወጣቱ ያነሳው የተጠቃሚነት ጥያቄ ፍትሐዊ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ወጣቱ ያነሳው ጥያቄ ከልማቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ይኑር የሚል ነው፡፡ ጥቂት ከባለሥልጣናት ጋር ግንኙነት ያላቸው በኔትወርክ ተሳስረው ሀብት ይፈጥራሉ፡፡ ሰፊው ሕዝብ የበይ ተመልካች ሆኗል፡፡ ይህ ሊቀጥል እንደማይችል የኢትዮጵያ ሕዝብ ነግሮናል፤›› ብለው፣ የወጣቱን ጥያቄ በኃይል መጨፍለቅ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡

መንግሥት በቂ የሥራ ዕድል ባለመፍጠሩ ኃላፊነት እንዳለበት የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፣ ለወጣቱ ምላሽ ሊሰጥ የሚችለው አምራች ኢንዱስትሪውን ይዞ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ካባዎችን ከደላሎች ነጥቆ ለሥራ አጥ ወጣቶች መስጠቱ ትክክለኛ ዕርምጃ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡  

ይሁን እንጂ ከዚህ ጋር ተያይዞ ሕገወጥነት መስፋፋቱን አምነዋል፡፡ ኦሕአዴድ በቅርቡ ባካሄደው ጉባዔ የሥራ አጥ ወጣቶችን ጥያቄ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እንደተወያየበት ገልጸው፣ ለወጣቱ የሥራ ዕድል የመፍጠር ጥረቶች እንደተጠበቁ ሆነው፣ ከመስመር የወጡ ድርጊቶችን ሥርዓት ለማስያዝ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡ በቅርቡ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ከፍተኛ አመራሮችና የወረዳ አመራሮች የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ እንደሚዘጋጅ ተናግረዋል፡፡ ‹‹የሕግ የበላይነት እንዲከበር ክልሉ ይሠራል፡፡ ፌዴራል መንግሥት ይደግፋል እንጂ በዚህ ላይ በዋነኝነት የሚሠራው ክልሉ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ኢስት ሲሜንት የገጠመውን ችግር አስመልክቶ በሰጡት ምላሽ ራሳቸው አካባቢውን መጎብኘታቸውንና ከማኅበረሰቡ ጋር መወያየታቸውን ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከመንገዱ በሚነሳው አቧራ ነዋሪዎች ለተለያዩ በሽታዎች መጋለጣቸውን፣ ከመተንፈሻ አካላት ጋር በተያያዙ የጤና ችግሮች ሳቢያ ሕይወታቸውን ያጡ እንዳሉ፣ ሰብላቸውም እንደጠፋ ነግረውናል፡፡ እናንተ ቅድሚያ የምትሰጡት ለሰው ሕይወት ነው ለፋብሪካ የሚል ጥያቄ ነው ያነሱልን፤›› ብለው፣ አስፋልት መንገድ እንደሚሠራ የተገለጸላቸው ቢሆንም ባለመሠራቱ ዕርምጃ መውሰዳቸውን አስረድተዋል፡፡

‹‹ዘጠኝ ዓመት ያህል እየሞቱ ቢጠባበቁም ቃል የተገባላቸው የአስፋልት መንገድ ሊሠራ አልቻለም፡፡ ውሸት ሲሰለቻቸው የመኪኖቹን እንቅስቃሴ አግደዋል፤›› ያሉት ሚኒትር ዴኤታው፣ መንገዱን የመሥራት ኃላፊነት የኩባንያው ሳይሆን የመንግሥት መሆኑን ጠቁመው ጉዳዩ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በመቅረቡ መፍትሔ ያገኛል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡

የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓት አምራች ኢንዱስትሪ ለኢኮኖሚው 20 ቢሊዮን ብር ያህል አስተዋጽኦ የሚያደርግ ሲሆን፣ ባለፉት ስድስት ወራት 26.8 ሚሊዮን ዶላር ከኤክስፖርት ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 13.9 ሚሊዮን ዶላር ማስገባቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...