Tuesday, December 5, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊከውል ውጪ ግንባታ ያካሄዱ አዲስ የይቅርታ ቅጽ እንዲሞሉ የሚያስገድድ አሠራር ይፋ ሆነ

ከውል ውጪ ግንባታ ያካሄዱ አዲስ የይቅርታ ቅጽ እንዲሞሉ የሚያስገድድ አሠራር ይፋ ሆነ

ቀን:

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ከገቡት ውል ውጪ ግንባታ ያካሄዱ ባለሀብቶች፣ አማካሪ ድርጅቶችና ኮንትራክተሮች ይቅርታ እንዲጠይቁ ያዘጋጀው አዲስ ቅጽ እያነጋገረ ነው፡፡

ባለሀብቶቹ ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ከውል ውጭ ላካሄዱት ግንባታ ዕውቅና ለማግኘት ወደ ባለሥልጣኑ በሄዱበት ወቅት እንዲሞሉ በተሰጣቸው አዲስ የይቅርታ ፎርም ግራ መጋባት እንደፈጠረባቸው፣ ወደፊት ሊያመጣባቸው የሚችለውን ችግር ከወዲሁ በመሥጋት ፎርሙን በመሙላትና ባለመሙላት መካከል እየዋለሉ እንደሚገኙ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከባለሥልጣኑ ዕውቅና ውጪ ገንብተውና አስፋፍተው የተገኙ የግንባታ ባለቤት፣ አማካሪ ድርጅትና ተቋራጩ የሕንፃ አዋጁን ደንብና መመርያ በመጣስ ከሙያ ሥነ ምግባር ውጪ ከፈጸሙት ድርጊት ታቅበው ይቅርታ የሚጠይቁበት ፎርም›› ተብሎ ለተዘጋጀው አዲስ አሠራር፣ ሦስቱም ተዋናዮች የሚፈርሙበት ቅጽ አለው፡፡

ባለሀብቶችን በሚመለከት የተዘጋጀው አዲስ ቅጽ፣ ‹‹ከተሰጠኝ የግንባታ ፈቃድ ውጪ በማሻሻል (ሙሉ በሙሉ በመቀየር) ያለምንም ግንባታ ፈቃድ የሠራሁት ግንባታ አግባብ አለመሆኑን ተረድቼ ለሠራሁት ሥራ ይቅርታ እየጠየቅኩ፣ ዳግም እንደዚህ ዓይነት ስህተት ላልደግም ቃል እገባለሁ፤›› የሚል ከመሆኑ በተጨማሪ፣ ‹‹በወንጀል ብጠየቅ ማንንም ላልወቅስ ተስማምቻለሁ፤›› ይላል፡፡

አማካሪ ድርጅቶችና ኮንትራክተሮች የሚሞሉት ቅጽ ደግሞ፣ ‹‹በተጠቀሰው ግንባታ ላይ በዲዛይን ወይም በኮንስትራክሽን የተሳተፍኩ ሲሆን፣ የሕንፃ አዋጅ (ደንብና መመርያ) በመጣስና የግንባታውን ባለቤት ከሙያ ሥነ ምግባር ውጪ በማማከር (በማሳሳት) በፈጸምኩት ድርጊት ተጸጽቼ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ድርጊት ላይ ተሳትፌ ብገኝ በሕንፃ አዋጁ ተፈጻሚ እንዲሆን፣ በተጨማሪም የማማካር ፈቃዴ (የተቋራጭነት ፈቃዴ) ቢሰረዝና በወንጀልም ጭምር ብጠየቅ ማንንም የማልወቅስ መሆኔን እያሳወቅኩ፣ የገነባሁት ጥራቱን የጠበቀና ደኅንነቱ የተረጋገጠ  መሆኑ ሙሉ ኃላፊነቱ የእኔ መሆኑን፣ ግንባታውን በተመለከተ ኃላፊነቱ ሙሉ በሙሉ የእኔ መሆኑን በፊርማዬ አረጋግጣለሁ፤›› ይላል፡፡

ይህ አዲስ ቅጽ ከመዘጋጀቱ በፊት ማንኛውም ከውል ውጪ ግንባታ ያካሄደ አካል የግንባታ ማሻሻያ በሚጠይቅበት ወቅት በባለሙያዎች በሕንፃው ስትራክቸር ላይ ለውጥ አያመጣም ተብሎ ከታመነ፣ በቅጣት ማሻሻያው ተቀባይነት ያገኝ ነበር፡፡

ነገር ግን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የግንባታ ማሻሻያ ለማድረግ ከ300 በላይ ባለሀብቶች ከተመዘገቡ በኋላ፣ ቅጹን ሞልተው እንዲፈርሙ ቀርቦላቸዋል፡፡ ከተመዘገቡት 300 ባለሀብቶች መካከል እስካሁን ፎርሙን ለመሙላት የደፈረ አለመኖሩን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ግንባታ ፈቃድና ቁጥጥር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መለስ አለቃ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...