በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ከሚያዝያ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ለመጨረሻ ጊዜ ለአንድ ዓመት የግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜ ከተራዘመላቸው ፕሮጀክቶች መካከል፣ አሁንም ሊጠናቀቁ ያልቻሉ በርካታ ፕሮጀክቶች በመኖራቸው ዕርምጃ መውሰድ የሚያስችል የውሳኔ ሐሳብ አቀረበ፡፡
የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ጥር 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ፣ በከተማው ውስጥ በሊዝ ቦታ ወስደው ከሚያዝያ 2008 ዓ.ም. በኋላ የሊዝ ውል ማሻሻያ የተደረገላቸውና ለመጨረሻ ጊዜ አንድ ዓመት የግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜ የተራዘመላቸው አሁንም ግንባታ ያላጠናቀቁ አልሚዎች በሁሉም ክፍላተ ከተሞች ተንሰራፍተው ይገኛሉ፡፡
‹‹አብዛኛዎቹ አልሚዎች ለመኖሪያ አገልግሎት የተሰማሩ ሆነው የግንባታ ደረጃቸው ደግሞ የማጠናቀቂያ ሥራ የሚቀራቸው፣ ከግማሽ በላይ ግንባታ ያካሄዱ ከመሆናቸው አንፃር ሲታይ ዕርምጃ ለመውሰድ አስቸጋሪ ነው፤›› ሲል የመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት ገልጾ፣ ‹‹የተጀመረውን ልማት ከማስቀጠል አንፃር ያለውን ጉልህ ድርሻ፣ እንዲሁም የመልካም አስተዳዳር ጥያቄ የሚያስነሳ መሆኑም ከግንዛቤ ገብቶ፣ የግንባታ ማጠናቀቂያ ጊዜው ካበቃበት ጊዜ ጀምሮ የሚታሰብ ቅጣት እንዲጣል፤›› ሲል ጽሕፈት ቤቱ የውሳኔ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
የሊዝ አዋጅ ቁጥር 721/2004 ከፀደቀ በኋላ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሊዝ አዋጁን ለማስፈጸም የሚያስችሉ የሊዝ ደንብ ቁጥር 49/2004 እና የሊዝ መመርያ ቁጥር 11/2004 ፀድቀው ሥራ ላይ ውለዋል፡፡ እነዚህ ሕግጋት ተግባራዊ መደረግ ከጀመሩ በኋላ ለመሬት ባንክና ማስተላለፍ ጽሕፈት ቤት በተሰጠው ሥልጣንና ተግባር መሠረት፣ በአዲስ አበባ ከተማ በሊዝ ቦታ ወስደው የግንባታ መጀመርያ ወይም የማጠናቀቂያ ጊዜ ያለፈባቸውን አልሚዎች መከታተልና መቆጣጠር መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ነገር ግን ጽሕፈት ቤቱ እንደገለጸው፣ በመመርያ ቁጥር 11/2004 አንቀጽ 39(2) መሠረት መመርያው ከመፅደቁ በፊት በሊዝ ቦታ ወስደው ግንባታ ጀምረው ያላጠናቀቁ አልሚዎች፣ ከሁለት እስከ አራት ዓመት እንደ ግንባታ ደረጃቸው ማራዘሚያ እየተሰጠቸው ግንባታ እንዲያጠናቅቁ ጥሪ ተደርጓል፡፡
በጥሪው መሠረት ቀርበው በተሰጣቸው ጊዜ ውስጥ ያላጠናቀቁት በድጋሚ ቅጣት ሲጣልባቸው ቆይተዋል፡፡ ነገር ግን ቢሮው ከሚያዝያ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የሰጠው የአንድ ዓመት ጊዜ ማራዘሚያ የመጨረሻው እንዲሆን አስታውቆም ነበር፡፡
እስከ የካቲት 2010 ዓ.ም. ድረስም ቢሆን በርካታ ግንባታዎች በሒደት ላይ ስለሚገኙ፣ ጽሕፈት ቤቱ አዲስ የቅጣት ፓኬጅ በማዘጋጀት የውሳኔ ሐሳብ ለመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ማቅረቡ ታውቋል፡፡