Monday, February 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርት126 ሺሕ ኪሎ ሜትር የሚጓዘው የዓለም ዋንጫ የካቲት 17 አዲስ አበባ ይገባል

126 ሺሕ ኪሎ ሜትር የሚጓዘው የዓለም ዋንጫ የካቲት 17 አዲስ አበባ ይገባል

ቀን:

ብዙዎች የሚመኙት፣ ነገር ግን ጥቂቶች በአራት ዓመት አንድ ጊዜ የሚታደሙበት የዓለም ዋንጫ ዝግጅት በብዙ ውጣ ውረድ የአዘጋጅነቱን ዕድል ባገኘችው ሩሲያ በመጪው ክረምት ይካሄዳል፡፡ በእግር ኳሱ 32 የዓለም ኃያላን የሚፎካከሩበት የዓለም ዋንጫ፣ ከዚያ በፊት ከ50 በላይ አገሮች እንዲጎበኝ በተያዘለት ፕሮግራም መሠረት ቅዳሜ የካቲት 17 ቀን 2010 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል፡፡

የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ከኮካ ኮላ ኩባንያ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የዓለም ዋንጫ ጉብኝት፣ በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአሥር አገሮች የጉብኝት ፕሮግራም ተይዞለታል፡፡ የአዘጋጇ ሩሲያ 35 ከተሞችን ጨምሮ ከ50 በላይ በተመረጡ የዓለም አገሮች ይንቀሳቀሳል ተብሏል፡፡

በሰባቱ ክፍለ ዓለማት ቅርፅ የተሰየመው የዓለም ዋንጫ፣ ከ18 ካራት ወርቅ የተሠራ ሲሆን፣ ክብደቱም 6.142 ኪሎ ግራም ይመዝናል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ1974 ጀምሮ በልዩ ቅርፅ መዘጋጀቱ የሚነገርለት የዓለም ዋንጫ፣ ለአሸናፊው ቡድን ቅጂው ካልሆነ ዋናው እንደማይሰጥ ይታወቃል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በመጪው ክረምት በሩሲያ የሚካሄደው የ2018 የዓለም ዋንጫ ዝግጅት በዓለም ዙሪያ በየቢሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሕዝቦች በጉጉት የሚጠበቅ ሲሆን፣ ዘንድሮ ለአራተኛ ጊዜ በልዩ ሥነ ሥርዓት በተመረጡ የዓለም አገሮች እንዲጎበኝ የሚደረገው ተወዳጅነቱን ለመጨመር ይረዳ ዘንድ የታቀደ መሆኑ ይነገራል፡፡

በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ከ32 የዓለም ኃይል የእግር ኳስ ብሔራዊ ቡድኖች ነጥሮ በሚወጣው አንድ አሸናፊ ቡድን ከፍ እንዲል የሚደረገው የዓለም ዋንጫ፣ ለዚያ የማይታደሉ በሺዎች ለሚቆጠሩ የእግር ኳስ አፍቃሪዎች ሁሉ የስፖርቱ ምልክት ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህንኑ ዋንጫ በመመልከት ሊሰጥ የሚችለውን ጥልቅ ስሜት መካፈል ደግሞ በሕይወት አንድ ጊዜ የሚመጣ አጋጣሚም ተደርጎ እንደሚወሰድ ይታመናል፡፡

በኢትዮጵያና በአፍሪካ ቀንድ የኮካ ኮላ ብራንድ ማናጀር ወ/ት ትዕግሥት ጌቱ የዓለም ዋንጫ ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱ የሚኖረውን ፋይዳ ሲናገሩ፣ ‹‹ዋንጫው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ ዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ነው፡፡ አጋጣሚው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለእግር ኳስ ላለው ጥልቅና የማይሞት ፍቅር የተሰጠውን ዕውቅናና ክብር ያሳያል፡፡ ዋንጫው በአፍሪካ ውስጥ በአሥር አገሮች የሚጎበኝ ሲሆን፣ ከነዚህ አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ፣ ለዚህም የኮካ ኮላ ኩባንያ ለአገሪቱ ሕዝብ ያለውን ክብር ያሳያል፡፡ እግር ኳስ በዓለም ዙሪያ እጅግ ተወዳጅና ተፈቃሪ ስፖርት ነው፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ የዓም ሕዝቦች በአገራቸውና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደረጉ ጨዋታዎች ይከታተላሉ፡፡ የፊፋ የዓለም ዋንጫ ደግሞ በእነዚህ አገሮች ያሉ ከልጅ እስከ አዋቂ የሚገኙ ሕዝቦችን በማስተሳሰር ለሚመርጡት ቡድን ድጋፋቸውን እንዲሰጡ የሚያስችል ነው፡፡ እግር ኳስ በሃይማኖትና በፖለቲካ ሳይገታ ሕዝቦችን አንድ የማድረግ ኃይል አለው፤›› ብለዋል፡፡

የዘንድሮ የዓለም ዋንጫ ጉብኝት የጀመረው በአዘጋጇ ሩሲያ ከመስከረም ወር 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ሲሆን፣ የ2018 የዓለም ዋንጫ ከመጀመሩ አስቀድሞ ከሰባቱ አህጉራት ከተመረጡ 51 አገሮችንና የሩሲያን ጨምሮ በአጠቃላይ 91 ከተሞች ይጎበኛል፡፡ ዘጠኝ ወራት በሚቆየው በዚሁ ጉብኝት ዋንጫው 126 ሺሕ ኪሎ ሜትሮችን ያቆራርጣል፡፡ ይህም በዓለም ዋንጫው የጉዞ ታሪክ ረዥሙ እንደሆነ ይነገራል፡፡

የፊፋውን ፕሬዚዳንት ጂያኒ ኢንፋንቲኖን ጨምሮ ታላላቅ የስፖርት ሰዎች በስፖርት ዓለም፣ ከዓለም ዋንጫ የበለጠ ጎልቶ የሚታይ ምልክት እንደሌለ ይናገራሉ፡፡ እነዚሁ ታላለቅ የስፖርት ሰዎች ሲቀጥሉ፣ ዋንጫው ያለውን አንድነት የመፍጠር ኃይል ሁሉም እንደሚረዳው ጭምር ይስማማሉ፡፡

ለዚህ ዝግጅት ከፊፋ ቀጥሎ ትልቅ ድርሻ ያለው የኮካ ኮላ ኩባንያ፣ ይህ የዓለም ዋንጫ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣው ከሱዳን ካርቱም ስለመሆኑም በመግለጫው ተመልክቷል፡፡ ዋንጫው የካቲት 17 ቀን አዲስ አበባ ሲደርስ፣ በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት አቀባበል ይደረግለታልም ተብሏል፡፡ ከዚያም በብሔራዊ ቤተ መንግሥት  ፕሬዚዳንት  ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) እንዲረከቡት እንደሚደረግም ተነግሯል፡፡

በሁለተኛው ቀን እሑድ የካቲት 18 ቀን በግዮን ሆቴል በሚኖረው ዝግጅትም የዓለም ዋንጫው ለሕዝብ ዕይታ እንደሚቀርብም ታውቋል፡፡

የዓለም ዋንጫው የጉብኝት ሥነ ሥርዓት አስመልክቶ በአዲስ አበባ ሒልተን ረቡዕ ጥር 30 ቀን በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነዲን ባሻ ተገኝተው ነበር፡፡ ይሁንና አቶ ጁነዲን በመድረኩ ከዓለም ዋንጫው ይልቅ ኢትዮጵያ በ2020 ስለምታዘጋጀው የቻን ዋንጫ ዝግጅትን አስመልክቶ የተናገሩት ሚዛን ይደፋ ነበር፡፡ ለዝግጀቱ ሲባል ቀጣዩን ምርጫ ማሸነፍ ዋነኛ ተልዕኳቸው ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...