Tuesday, February 27, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

‹‹ዓሳውን ለማጥመድ ዋናተኛ መሆን አያስፈልግም››

(የአክሰስ ሪል ስቴት ቤት ገዥዎች ድምፅ

ቤታችንን ለማግኘት ሕጋዊ መስመር ተከትለን ጥያቄ ማቅረብ ብቻ በቂያችን ነው፡፡ ከ350 በላይ የምንሆን የአክሰስ ሪል ስቴት ቤት ገዥዎች፣ ‹‹የመጀመርያ ምርጫችን ከአክሰስ ሪል ስቴት ጋር በገባነው ውል መሠረት ያለ ምንም ተጨማሪ ወጪ ኩባንያው ቤታችንን ሠርቶ እንዲያስረክበን፤›› ይህም ተፈጻሚ እንዲሆን መንግሥት ገለልተኛና ፕሮፌሽናል የጊዜያዊ ሞግዚት ባለአደራ ቦርድ በማቋቋም ያሉትን አማራጮች አሟጦ እንዲጠቀም በአክብሮት ጥቅምት 2010 ዓ.ም. ፒቲሽን በመፈራረም ጥቅምት 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በተጻፈ ሸኚ ደብዳቤ ችግሩን ለመፍታት ቀና ደፋ ለሚለው የመንግሥት አካል መድረኮችን በማዘጋጀት በቀጥታ ከቤት ገዥዎች ጋር ቢገናኝ በማለት ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት በግልባጭ ለንግድ ሚኒስቴር ማመልከታችን ይታወሳል፡፡

ሆኖም ጉዳዩን ለሚከታተለው የመንግሥት አካል ለውሳኔ ይረዳ ዘንድ፣ መንግሥታችን ገለልተኛና ፕሮፌሽናል የጊዜያዊ የሞግዚት አስተዳደር የባለአደራ ቦርድ በማቋቋም ኩባንያውን በበላይነት እንዲቆጣጠር የጠየቅንበትን ምክንያቶች፣

 1. በስሙ ቤት የገዛው ንፁህ ላቡን የሚፈልግ ቤት ገዥ አቤቱታውን ወይም ድምፁን የሚያሰማበት ገለልተኛና ተጠያቂ አካል ባለማግኘቱ፣
 2. አሁን ያለው የቤት ገዥ ኮሚቴ ሕጋዊ በሆነ መንገድ ያልተደራጀና ተመጣጣኝ ውክልና የሌለው በቤት ገዥዎች የግለሰብ ወኪል የሚመራ ጠቅላላ ቤት ገዥዎችን የማይወክል በመሆኑ፣
 3. ይህ የቤት ገዥ ኮሚቴ ከቤት ገዥው ጠቅላላ ጉባዔ ዕውቅና ውጪ በቤት ገዥው ስም መጀመርያ መሬቱ ይሰጠን በማለትና ተጨማሪ ወጪ አውጥተን እንገነባለን በማለት ትክክለኛ የቤት ገዥውን ጥያቄ ላለፈው ሦስት ዓመት ባለማንፀባረቁ፣
 4. በአክሰስ ኩባንያ ውስጥ የቦርድ አባላት ማኔጅመንትና የቤት ገዥ ኮሚቴ በመደባለቁ ጠያቂና ተጠያቂ የማይለይበት ደረጃ በመድረሱና አዲስ ጠንካራ ገለልተኛ ቦርድ እንዲሰየም ባለመፈለጉ፣
 5. የአክሰስ ኩባንያና መሪው በስህተት ጎዳና ሲጓዝ በነበረበት ወቅት የነበሩ የቦርድ አባላትና ማኔጅመንት አሁንም በነበሩበት አኳኋን በወንበራቸው ላይ መሆናቸው፣    
 6. የኦዲት ኮርፖሬሽን በአክሰስ ላይ ያደረገው ኦዲት ሪፖርት ኩባንያው ያለው ሀብት ከዕዳው በእጅጉ እንደሚበልጥ የሚገልጽ ቢሆንም፣ በቤት ገዥዎች ኮሚቴ ለራሳቸው በሚያመች ሁኔታ ኦዲት ሪፖርቱን እየቆራረጡ በመግለጽ ኩባንያውን የከሠረ በማስመሰል እየተጠቀሙበት በመሆኑ፣
 7. ንፀኋኑ ቤት ገዥ የሚፈልገው በውሉ መሠረት ያለምንም ተጨማሪ ወጪ ቤቱን መረከብ ቢሆንም፣ ይህ ተግባራዊ መሆን የማይችል ከሆነ መገለጽ ያለበት በገለልተኛ የመንግሥት አካል በመሆኑ፣
 8. የቦርዱ አባላቶች ቤት ገዥዎች በመሆናቸው ገለልተኛ ተጠያቂ አካል ባለመኖሩ፣
 9. ዓሳውን ለማጥመድ ዋናተኛና መሆን እንደማያስፈልግ ሁሉ የቤት ገዥ ዓብይ ኮሚቴ አቤቱታ አሰሚ ብቻ መሆን ሲገባው፣ ለኩባንያው ገንዘብ አበዳሪና አስተዳዳሪ፣ የቦርዱ ጥምር ኮሚቴ አባል፣ በተጨማሪም የቴክኒክ የችግር ፈቺ ኮሚቴ አባል በመሆን ረድፉን /ሐዲዱን/ በማሳቱ ታማኝነትን በማጣቱ፣
 10. ቤት ገዥው የገዛው ቤት እንጂ መሬት ባለመሆኑ፣
 11. የአክሲዮን ባለድርሻዎች ጠንካራና ገለልተኛ ቦርድ የማቋቋም የአቅም ውስንነት ስላለባቸው፣
 12. የቤት ገዥው ቅድመ ዓላማና ባህርይ ቁልፍ መረከብ እንጂ በማኅበር ተደራጅቶ መሬት በመረከብ ከቤት ገዥነት ወደ ሪል ስቴት ባለቤትነት ነጋዴነት/መሸጋገር ባለመሆኑ፣
 13. የቤት ገዥዎች ዓብይ ኮሚቴ ገና ለገና መሬት እንወስዳለን በሚል የኩባንያው ንብረት እንደ ቅድመ ክፍያ ሕገወጥ ውል በማዋዋል ውል መስጠቱን የሚጠቁም ማስረጃ /የውል ስምምነት ረቂቅ /2 ገጽ ተያይዟል/ በመገኘት ይህም ለአማራጭ ችግር አፈታት እንቅፋት በመሆኑ፣
 14. ሁሉም ባለድርሻ ነኝ የሚል ወገን ኩባንያው አዋጭነት በጥልቀት በመረዳት ከውጭ ኩባንያ ጋር በመጣመር ማሠራት እንደሚቻል በጥልቀት ስለተገነዘቡ እኔ ላስፈጽም፣ እኔ ላስፈጽም! የሚለውን ሩጫ ለመግታትና ኩባንያውን ሕጋዊ መስመር ለማስያዝ፣
 15. በማንኛውም ወገን የሚቀርበውን የመፍትሔ ሐሳብ ለግል ጥቅም እንዳይጠለፍ በገለልተኛ ወገን እንዲፈተሽና ወደ ተግባር እንዲለወጥ፣
 16. እኛ ተጎጂ ቤት ገዥዎች ሙሉ እምነታችን በመንግሥት ዕገዛ ላይ ብቻ በመሆኑ ችግራችን በግለሰብ፣ በኮሚቴና በማኅበራት ይፈታል የሚል እምነት ስለሌለን፣ ኩባንያው ከውጭ አልሚ ባለሀብት ጋር በመጣመር ቤቱን ሠርቶ እስኪያስረክበን ድረስ መንግሥት ተቆጣጣሪ የሆነ የጊዜያዊ የሞግዚት ባለአደራ ቦርድ በማቋቋም ኩባንያውን  እንዲረከበው፡፡

ከዚህ በላይ በተቀመጡት 16 ነጥቦች ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ግልጽ እንዲሆን በማብራራት መንግሥት ገለልተኛ የሆነ ፕሮፌሽናል የዳይሬክተሮች ቦርድ ለአክሰስ ሪል ስቴት እንዲያቋቁም እንፈልጋለን፡፡

የቤት ገዢዎችም ቤት የገዛነው በግል በነፃ ህሊናችን እንጂ በኮሚቴ ባለመሆኑ በኮሚቴ ፍላጎት አግባብነት በሌለው የመሬት ጥያቄ ከመወናበድ ይልቅ በነፃ ህሊናችን የፒቲሽኑን ሐሳብ ሁላችንም ተረድተን ለመንግሥት ትክክለኛ አግባብነት ያለው ጥያቄ ብናቀርብ መንግሥት በቀናት ውስጥ መልስ እንደሚሰጠን እምነታችን የፀና ነው፡፡

(በስማቸው ቤት የገዙ የአክሰስ ሪል ስቴት ኩባንያ ደንበኞች)

* * *

ከክልል ወደ አገራዊ አመለካከት እንሸጋገር

የጥር 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ሪፖርተር ጋዜጣን ሳነብ ገጽ 16 ላይ ይድረስ ለሪፖርተር በሚለው ዓምድ ሥር ‹‹ጀግንነት በአካባቢ ተወላጅነት አይቃኝም፤›› በሚል ርዕስ የሰፈረ ሂሳዊ ግምገማ አነበብኩ፡፡ ጸሐፊው ውብሽት ተክሌ ከገርጂ ናቸው፡፡ የጽሑፋቸው ፍሬ ነገር፣ እኔ እንደተረዳሁት፣ ‹‹. . . ዝክረ ጃጋማ ኮሚቴ፣ በቀድሞ ፕሬዚዳንት መቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ የበላይ ጠባቂነት መቋቋሙ፣ ጀግንነትን በአካባቢ ተወላጅነት የመቃኘት ውስንነትና ጠባብነትን ስለሚያንጸባርቅ ከዚህ የአመለካከት ቅንፍ ውስጥ ሰብሮ መውጣት ይገባል የሚል ነው፡፡

ውብሸት ዘገርጂ ሂስ ሰንዝረው ዘወር አላሉም፡፡ የጀግንነት ቅኝት፣ ከአካባቢ ተወላጅነት በላይ፣ በላቀ ብሔራዊ መስፈርት የሚገመገምበት ሥርዓት ሊጤን ይገባል ብለዋል፡፡ ይኸን ውብ ድንቅ አባባል እኔም እጋራዋለሁ፡፡ የእኔ መነሳሳት የውብሸትን ሂሳዊ ዳሰሳ ከመጋራት ባሻገር፣ እሳቸው አጠንክረውና በማስረጃ አጥረው በከተቡት ላይ የጎደለ መስሎ የታየኝን ለማከል ነው፡፡ ውብሸት እንደ ተነተኑትም፣ በርካታ ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ሉዓላዊ፣ ነፃነትና አንድነት፣ በሰላሙም በጦርነትም ጊዜ በዋጋ የማይለካ አገልግሎት አበርክተዋል፡፡ የሕይወት መስዕዋትነት የከፈሉም ነበሩ፡፡ ባይገርመን ዛሬም አሉ፡፡ ይህ የአገር ባለውለታነት፣ ኢትዮጵያን በተጠናወታት አመፃዊ የመንግሥት ሥልጣን ሽግግር ዋጋ እያጣ፣ ከዚያም ባለፈ የኢትዮጵያ እውነተኛ ታሪክ እየተነቀፈና እየተወገዘ፣ እየተበረዘና አዳዲስ ታሪክ በድቡሽት ላይ ለመሥራት ሲሞከር እየታዘብን ነው፡፡ የጀግንነትና በአካባቢ ተወላጅነት ቅኝት መንስዔም አንዱ ፍላጎት ከዚህ በላይ የተጠቀሰው የታሪክ ቀውስ ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ የውብሸትን ቁም ነገር ለመጋራት ወደ ተነሳሁበት ተጨማሪ ነጥቦች ልመለስ፡፡

የሐውልት መታሰቢያ የሚቆምላቸው፣ የአደባባይና የአውራ ጎዳና ከዚያም ባለፈ የመንደሮች (የሠፈሮች) መጠሪያ በየስማቸው የሚሰየምላቸው መለዮ ለባሽና ሲቪል የአገር ባለውለታዎች አሉን፡፡ የጥንታዊትንና የአዲሲቱን ኢትዮጵያ የሉዓላዊ ነፃነትና አንድነት ተጋድሎ ጀግኖች አርበኞችና እንደዚሁም፣ የሰላም ጊዜ የአገር ግንባታ ብፁአን አባቶች የሚዘከሩባቸው መታሰቢያዎች ስየማ፣ በደረጃ ቅደም ተከተል፣ በፈርጅ ተለክቶና ተለይቶ፣ አስፈላጊ ሆኖ ከታየም፣ የብሔር ስብጥር ታሳቢ ተደርጎ፣ በብሔራዊ ደረጃ መተግበር ይገባዋል፡፡

ከታሪክ ሽሚያ የተነሳ በርካቶች የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ገድል ሳይወደስ (ሳይጽፍ)፣ መታሰቢያ ሐውልት ሳይቆምላቸው፣ አውራ መንገድ፣ አደባባይ፣ ትምህርት ቤትና ሆስፒታል በየስማቸው ሳይሰየምላቸው ቀርቷል፡፡ አፈና ነበር፡፡ (የታሪክ ሽሚያውን ደባ ቅድመ አብዮት (1966 ዓ.ም.) በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስም ተሰይመው የነበሩትን መታሰቢያዎች ብዛት ማጤን ይቻላል)፡፡

ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በፊት (1922 ዓ.ም.)፣ ከዘመነ መሳፍንት ወዲህ የነበረውን እንኳ ብንመለከት አፄ ቴዎድሮስና የጦር አበጋዛቸው ፊታውራሪ ገብርዬ፣ አፄ ተክለ ጊዮርጊስ፣ አፄ ዮሐንስ አራተኛና የጦር አበጋዛቸው ራስ አሉላ አባ ነጋ፣ አፄ ምኒልክና እቴጌ ጣይቱ ብጡል፣ ራስ ጎበና ዳጬ፣ ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት፣ ንጉሥ ሚካኤል የዓድዋ ድል ጀግኖች የሚገባቸውን ያህል ዕውቅና ተነፍገው ታሪካቸው ታፍኖ መቆየቱን ታዝበናል፡፡

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የግማሽ ምዕተ ዓመት የነበረውን ሥርዓት በቅንነትና በታማኝነት ያገለገሉ የሲቪልና የጦር መሪዎች፣ ልዑል ራስ ካሳ ኃይሉ፣ ልዑል ራስ ሥዩም መንገሻ፣ የጦር ሚኒስትር ራስ ሙሉጌታ ይገዙ፣ ራስ ደስታ ዳምጠውና ልዑል ራስ እምሩ ኃይለ ሥላሴ በጠቅላላው የ1928 ዓ.ም. የፋሽስት ኢጣሊያን የግፍ ወረራን ለመመከት የኢትዮጵያ ሠራዊት በየጦር ግንባሮቹ ያዘመቱ ጀግኖች አባቶች ገድል የሚገባውን ያህል መቼ ተዘከረ? እስከ መቼስ ቸል ይባላል? ውለታ መላሽ መንግሥት. . . ፡፡

ንጉሠ ነገሥቱም ከተሰደዱ በኋላ በነበረው የአምስት ዓመት የነፃነት ታጋድሎ እንደ ተዓምር የተቆጠረ ገድል ያስመዘገቡ የአርበኞች ቁንጮ ራስ አበበ አረጋይ፣ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ ደጃዝማች ኃይለ ማርያም ማሞ፣ ደጃዝማች ፍቅረ ማርያም አባተ ጫን፣ ደጃዝማች ታከለ ወልደ ኃዋርያት፣ ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ፣ ደጃዝማች ዑመር ስመቱር፣ ወ/ሮ ልኬለሽ በያን፣ ወ/ሮ ከበደች ሥዩም፣ ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ፣ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ፣ ራስ መስፍን ስለሽ፣ ደጃዝማች በቀለ ወያ፣ አብዲሳ አጋ፣ ዘርዓይ ደረሰ (ጥቂቶቹን ለመጥቀስ ያህል) እንደተረሱ ቀርተዋል፡፡

ውብሸት ከጠቀሷቸው ወደር የሌለው የጀግንነት ክብር Beyond the call of Duty የላቀ የክብር ሜዳዬ ጀብዱ ከተሸለሙት ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ጋር እኩል የተሸለሙት ጄኔራል ተስፋዬ ኃብተ ማርያም በአድናቆት እናስባቸዋለን፡፡ እኝህ ጀግና አባት ዛሬም በሕይወት አሉ፡፡ የጦር ሜዳ ውሎ የሚለው ግለ ታሪካቸውን በ5,000 ኮፒ ስምንት ጊዜ ተደጋግሞ ታትሞ ለንባብ በቅቷል፡፡

በጥር 20 ሪፖርተር ደብዳቤዎች ዓምድ ሥር ከተጠቀሱት ኢትዮጵያውያን የዲፕሎማሲ አባቶች መካከል አንዱና ግንባር ቀደሙ ብላቴን ጌታ ኅሩህ ወልደ ሥላሴ እንደነበሩ ይታወቃል፡፡ እኒያ ታላቅ ዲፕሎማት ለቁጥር የሚያዳግቱ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ባለቤትም ነበሩ፡፡

ከመንፈሳዊ አባቶች መካከል የኢትዮጵያ የመጀመርያው ፓትሪያርክ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ወርቃማ ታሪክ ምልክት ተደርገው ሊዘከሩ ይገባቸዋል፡፡

ውድ አንባቢያን ነገር ላለማብዛት እንጂ፣ በጥንታዊትና በአዲሲቷ ኢትዮጵያ በውጭ ግንኙነት (ዲፕሎማሲ)፣ በመልካም አስተዳደር፣ በኢኮኖሚያና ማኅበራዊ ዕድገትና ልማት፣ በሙዚቃና ቴአትር፣ በሥነ ጽሑፍና በስፖርት፣ ወዘተ ዘመን ተሻጋሪ የሥራ ውጤት አስመዝግበው ያለፉና ዛሬም በሕይወት የሚገኙ የአገር ታላቅ ባለውለታዎች ነቅሶ መዘከር ይቻል ነበር፡፡

የእኔም ሆነ የውብሸት ዘገርጂ ሙግት ለጄኔራል ጃገማ ኬሎ ሐውልት መቋቋም የለበትም አይደለም፡፡ ጃጋማ አንድ ጎሳ ወይም ቡድን ጀግና አልነበሩም፡፡ የታላቋ ኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ ጀግና ነበሩ፡፡ ሌላው የአርበኝነት ተጋድሏቸው እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ዛሬም በዘመነ ኢሕአዴግ ሥልጣን የሕዝብ ነው፣ የሥልጣን ምንጭና ባለቤት ሕዝብ ነው፡፡ የመንግሥት ሥልጣን ዝውውር ከጠመንጃ አፈሙዝ የመዞር አዙሪት ተቋርጦ፣ በሕዝብ ድምፅ መስጫ ሳጥን ይተካ የሚለውን ክብር ንዑስ ዓላማ ሲያውጅ የነበረውን ኢትዮጵያዊነት ማኅበር፣ ከክቡር ሐዲስ ዓለማየሁ፣ ደጃዝማች ዶ/ር ዘውዴ ገብረ ሥላሴ፣ ቢትወደድ ዘውዴ ገብረ ሕይወትና ሌሎችም አገር ወዳድ ዜጎች ጋር መሥርተው፣ በሰላማዊ መድረክ ሲታገሉ የነበሩ ታላቅ፣ አዎ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነበሩ፡፡ በነገራችን ላይ እኔም የዚህ ማኅበር አባል ነበርኩና በቅርብ አውቃቸውም ነበር፡፡

በእነዚህ የታላላቅ ጀግኖች አርበኞችና ሌሎችም የአገር ባለውለታዎች በክልል ወይም በብሔራዊ ደረጃ መዘከር ስብሰለሰል፣ ጎንደሮች (የጎንደር ዩኒቨርሲቲ) የአፄ ቴዎድሮስን ሐውልት ማቆማቸውን፣ እንደዚሁም ሸዋዎች (አማራዎች) የአፄ ዘርዓያቆብን ሐውልት ለማቆም የመሠረት ድንጋይ መጣላቸውን ወሬ ሰማሁ፡፡ የወሬ አባቴን፣ ቴዎድሮስም ሆኑ ዘርዓያቆብን የአማራ ዝርዮች ቢሆኑም፣ የኢትዮጵያ ስመ ጥር መሪዎች ነበሩ፡፡ እንደነሱ ያሉ ታላላቅ የአገር ባለውለታዎች መዘከር የሚገባቸው በማዕከላዊ መንግሥት ደረጃ እንጂ፣ በክልል ደረጃ መሆን እንዳልነበረበት ለማስረዳት ሞክሬ ነበር፡፡ እሱ ግን እንዲህ አለ፣ ‹‹ለአፄ ዘርዓያቆብ 550 ዓመት፣ ለአፄ ቴዎድሮስ 150 ዓመት በተገቢ ደረጃ (መንግሥት) ሐውልት እስኪቆምላቸው ተጠበቀ፡፡ ጥበቃው ዋጋ እንደሌለው አገሬው ተረድቶ፣ የራሱን ዕርምጃ ወሰደ›› በማለት ኩም አደረገኝና የዝክረ ጃጋማ ክልላዊ እንቅስቃሴ ተገቢ መሆን ወይም አለመሆንን ለመንቀፍ ወይም ለመደገፍ የብዕሬ ትባት ተሰለበ፡፡

(አባ ገንባው፣ ከቦሌ)

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles