Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ በሰባት ወራት ውስጥ ከ188 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ገቢ አስመዘገበ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ወደ ሥራ ከገባ ዘጠነኛ ዓመቱን ያስቆጠረው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ እ.ኤ.አ. በ2017 (የበጀት ዓመቱ በአውሮፓውያን አቆጣጠር መሠረት) ሰባት ወራት ውስጥ በወጪ ንግድ የባንክ አገልግሎት አማካይነት ከ188 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን ገለጸ፡፡ በ2010 ሰባት ወራት ውስጥ ያገኘው ትርፍም እ.ኤ.አ. በ2016 ሙሉ ዓመት ካገኘው በከፍተኛ ደረጃ ብልጫ እንዳለው ባንኩ  አስታውቋል፡፡

ባንኩ በየዓመቱ የሚያከብረው የወጪ ንግድ ቀን ሰኞ ጥር 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲካሄድ እንደተገለጸው፣ በሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ ማግኘት የቻለው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ብልጫውን ይዟል፡፡

የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ አቤ ሳኖ እንዳመለከቱት፣ ዓምና በተመሳሳይ ወቅት ከወጪ ንግድ አገልግሎት አግኝቶ የነበረው 124 ሚሊዮን ዶላር ነበር፡፡ ዲሴምበር 2017 መጨረሻ ላይ ከዘርፉ የተገኘው ገቢ ግን 188 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ የባንኩ ፕሬዚዳንት አስታውሰው፣ በዚህም ባንኩ ከየትኛውም ጊዜ በላይ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበበት ወቅት መሆኑን ያመላክታል ብለዋል፡፡

በባንኩ የወጪ ንግድ ቀን አከባበር ፕሮግራም ወቅት የቀረበው መግለጫ እንደሚያመላክተው፣ ባንኩ ከወጪ ንግድ የሚያገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ እ.ኤ.አ. በ2016 ከመቀነሱ በቀር በተቀረው ጊዜ በየዓመቱ እያደገ መሄዱን ያሳየ ነው፡፡

ባንኩ እ.ኤ.አ. በ2012 ከወጪ ንግድ ዘርፍ 44.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ከዚያም 61.4 ሚሊዮን ዶላር አስመዝግቧል፡፡ በ2015 140 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት ዕድገቱን እያሻሻለ መምጣቱን ያሳያል፡፡ ይሁንና በ2016 ከወጪ ንግድ ያገኘው የውጭ ምንዛሪ ገቢ ወደ 124 ሚሊዮን ዶላር ዝቅ ብሎ እንደነበር ፕሬዚዳንቱ ጠቅሰዋል፡፡ ይሁን እንጂ በ2017 ከዘረፉ ያገኘው ገቢ በ64 ሚሊዮን ዶላር ጨምሮ ወደ 188 ሚሊዮን ዶላር መድረስ እንደቻለ ባንኩ አስታውቋል፡፡

ባንኩ ከተለያዩ መመዘኛዎች አኳያ፣ በኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ድርሻ መያዙን የሚያሳዩ መረጃዎችን የጠቀሱት አቶ አቤ፣ ቀዳሚ አድርገው ያቀረቡትም የባንኩን የተቀማጭ ገንዘብ ዕድገት ነው፡፡ ባንኩ በዕለቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢው እንዲያድግ ላደረጉ ላኪዎች፣ ከፍተኛ አስቀማጮችና ለዚህ ውጤት አብቅተውኛል ላላቸው ደንበኞች ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ በተለይም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ አስገኝተውልኛል ላላቸው አምስት ኩባንያዎች ዕውቅና ሰጥቷል፡፡

ዓምና በተመሳሳይ ወቅት የወጪ ንግድ ቀን ሲያከብር፣ በዲሴምበር 2016 መጨረሻ ወቅት የባንኩ ተቀማጭ ገንዘብ መጠን በ48 በመቶ አድጎ የ16.8 ቢሊዮን ብር እንደደረሰ ያስታወሱት አቶ አቤ፣ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 5.5 ቢሊዮን ብር ተቀማጭ ገንዘብ ማሰባሰባቸውን ተናግረዋል፡፡ ይሄ ከፍተኛ ውጤት እንደሆነ የገለጹት አቶ አቤ፣ ባንኩ በተለያዩ የባንክ አገልግሎቶች ያገኘው ውጤትም የባንኩን ዓመታዊ የትርፍ ዕድገት ከፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡ ይህንን በተመለከተ አቶ አቤ እንደገለጹት፣ ባንኩ ዓምና ያገኘው ትርፍ 378 ሚሊዮን ብር ቢሆንም፣ በ2010 ዓ.ም. ሰባት ወራት ውስጥ ብቻ የተገኘው ትርፍ ብልጫ የያዘ ሆኖ ተገኝቷል፡፡

‹‹2010 በጀት ዓመት ሰባት ወራት ብቻ የባንኩ ትርፍ 422 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ይኼ ከእናንተ ጋር በመሥራታችን ጭምር የተገኘ ውጤት ነው፤›› በማለት የባንኩን ደንበኞች አመስግነዋል፡፡

ከታክስና ከሌሎች ተቀናሽ ወጪዎች በፊት፣ በሰባት ወራት ውስጥ የተገኘው የትርፍ መጠን፣ በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ የተሻለ እንቅስቃሴ ማሳየቱን የሚጠቁም ነው ያሉት አቶ አቤ፣ ይህ ውጤትም በትርፍና በተቀማጭ ገንዘብ መጠን አኳያ ከግል ባንኮች በአራተኛ ደረጃ እንዲቀመጥ እንዳበቃው ገልጸዋል፡፡

ከብድር አቅርቦት አኳያም እስከ ዲሴምበር 2017 ድረስ ባንኩ የሰጠው የብድር መጠን ወደ አሥራ አንድ ቢሊዮን ብር አሻቅቧል፡፡ በመደበኛና በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት በጥምር የተሰጠው ይኼ ብድር በባንኩ የዘጠኝ ዓመታት ቆይታውን ለደንበኞች የተሰጠ ከፍተኛ የብድር መጠን መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በተለይ በዚህ ወቅት ለተለያዩ የቢስነስ ዘርፎች የሚቀርበው የብድር መጠን ጣሪያ በተጀመረበት ወቅት የዚህን ያህል ብድር መስጠት መቻሉ ባንኩ ያለውን አቅም እንደሚያሳይም የባንኩ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎትን በቀዳሚነት መስጠት የጀመረው ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ በዚህ የአገልግሎት ዘርፍ እንደ ቀዳሚነቱ ብልጫ የወሰደባቸውን ተግባራት እንደፈጸመ ተመልክቷል፡፡ ከወለድ አልባ አገልግሎት ከአምስት ዓመት በፊት ሥራ ሲጀምር በወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት የሰበበው ተቀማጭ ገንዘብ 359 ሚሊዮን ብር ብቻ ነበር፡፡ ባለፈው ወር መጨረሻ ላይ ግን ይኼ ተቀማጭ ገንዘብ 2.6 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ የባንክ ኢንዱስትሪውን ሲቀላቀል የሚታወቅበት ተግባሩ ከሌሎች ባንኮች በተለይ በአንድ ጊዜ 26 ቅርንጫፎችን በመክፈት ሥራ መጀመሩ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፣ ከዚህም በኋላ ቅርንጫፍ በማብዛት በተከታታይ የከፈታቸው ቅርንጫፎች አሁን ላይ 230 ደርሷል፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት ሁለት ዓመታት ባንኩ የቅርንጫፍ ማስፋፋት ሥራው እንደቀዘቀዘ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ 91.2 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ ሲቋቋም፣ እስካለፈው ወር መጨረሻ ድረስ የተከፈለ ካፒታሉን 1.3 ቢሊዮን ብር ማድረሱን ገልጿል፡፡ ወደ ሥራ ሲገባ የነበሩበትን ከአምስት ሺሕ በላይ ባለአክሲዮኖች ደግሞ በአሁኑ ወቅት ከ12 ሺሕ በላይ እንዳደረሰም ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች