Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ጎርባጣው ባቡር

በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው የአዲስ ጂቡቲ የምድር ባቡር መሳፈር ጀምረናል፡፡ ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ድረስ በሚዘልቀው የባቡር መስመር ወደ 19 ከተሞች መጓዝ ቢቻልም፣ በአሁኑ ወቅት መንገደኞች የሚያስተናገዱት በአራት ከተሞች ብቻ ነው፡፡

አዲሱ የኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር በቅርቡ ጉዞ የጀመረው 28 ተሳፋሪዎችን ይዞ ነበር፡፡ ከዚያን ወዲህ ያለው የተሳፋሪ ቁጥር ከዚህ በላይ እንደጨመረ ይታመናል፡፡ ብዙ የሚጠበቅበት የመንገደኞች የባቡር ትራንስፖርት አጀማመሩ ስንጠብቀው የነበረውን ያህል አልሆነም፡፡ የባቡሩ ጉዞም ቢሆን ከትክክለኛው የፍጥነት ወሰን በግማሽ ቀንሶ የሚጓዝ ነው፡፡ በአራት ሰዓት ‹‹ድሬ›› የመድረስ ጉልበት ያለው ፈጣኑ ባቡራችን፣ አሁን ላይ ድሬ ለመድረስ ሰባት ሰዓታት ይወሰድበታል፡፡ ለዚህ ከሚሰጠው ምክንያት ውስጥ አንዱ ባቡሩ በሚያልፍባቸው አንዳንድ አካባቢዎች በተደጋጋሚ እንስሳትና ሰዎች ስለሚገቡ ከአደጋ ለመቆጠብ ሲባል ከፍጥነት ልኩ በታች እንዲጓዝ በመደረጉ ነው፡፡

ከዚህ አንፃር ከፍጥነቱ ቆጠብ ብሎ ወደ ሥራ መግባቱ አግባብ ነው ቢባል እንኳ፣ እስከመቼ እንዲህ ፍጥነቱ ተንቀርፍፎ ይጓዛል? የሚለው ጥያቄ ምላሽ ይሻል፡፡ ከዚህ ጥያቄ ባሻገር ግን በዚህ ፍጥነቱም ቢሆን የባቡር ተጠቃሚዎችን ቁጥር የበለጠ ለማብዛት የሚያስችል አቅም ይዞ፣ በቂ ዝግጅት አድርጎ ሥራ ጀምሯል ለማለት የማያበቁ ክፍተቶች አሉበት፡፡ በአንድ ዓመት ከመንገደኞች ብቻ ሁለት ሚሊዮን ዶላር እንደሚገኝ ታስቦ ሥራ የጀመረው ይህ ባቡር፣ አሁን ባለው ፍጥነት ከቀጠለና ለደንበኞቹ ምቹ የአገልግሎት አሰጣጥ ካልተገበረ በቀር ያሰበውን ገቢ ያገኛል ብሎ ማሰብ ይከብዳል፡፡

ስለዚህ የታሰበውን ያህል መንገደኛ ሊያገኝ የሚያስችል አሠራር ካለመዘርጋት ጋር የተያያዘ ችግር ከወዲሁ እየታየበት ነው፡፡ ለመንገደኞች ምቹ የአገልግሎት አሰጣጥ መዘርጋት የግድ ቢሆንም፣ አሁን ከምንመለከተው የአገልግሎት አሰጣጥ አንፃር መንገደኞችን እንደሚፈለገው ለማስተናገድ የሚያስችል አቅም ሳይፈጥር ወደ ሥራ ተቻኩሎ ገብቷል ከሚያስብሉት ምክያቶች ውስጥ፣ አንድ መንገደኛ የጉዞ ቲኬት ለመግዛት የት አካባቢ መሔድ እንደሚገባው በሚገባ አለመገለጹ ይጠቀሳል፡፡ ከአዲስ አበባ ወደ ድሬዳዋ ወይም አገልግሎቱ ወዳለባቸው ከተሞች በባቡር ለመሄድ የሚፈልግ ተጓዥ፣ የጉዞ መነሻ ጣቢያውን በአግባቡ እንዲያውቅ በቂ ሥራ  አልተሠራም፡፡ አዲስ አበባ ላይ ሆነን እየታዘብን ያለነው ይህ መሠረታዊ ችግር ሲሆን፣ ወደ ጂቡቲ የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ ደንበኞች የሚስተናገዱበት አግባብም እዚህ ካለው የተለየ ይሆናል ብለን አንገምትም፡፡

የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጡን የበለጠ ትችት ውስጥ የሚከተው ሌላም ችግር አለ፡፡ የባቡር የመነሻ ጣቢያውን በፍለጋ አግኝተው አገልግሎቱን ያገኙትም ቢሆኑ፣ የጉዞ ቲኬት እንዲቆርጡ የሚገደዱት ለቡ ባቡር ጣቢያ ድረስ በመሄድ ነው፡፡ ትኬት ለመቁረጥ እዚያ ከከተማው የትየለሌ ድረስ መጓዝ አድካሚና አሰልቺ ስለመሆኑም በምሬት እየተናገሩ ነው፡፡ ቲኬቱን ከቆረጡ በኋላ ደግሞ በጉዞው ዕለት ወደ መነሻ ጣቢያው ለመድረስ የሚፈጀው ጊዜና የሚጠይቃቸው ወጪ፣ የባቡር አገልግሎቱን አማራጭነት ከወዲሁ ጥያቄ ውስጥ የሚከተው አሠራር እየሆነ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ጂቡቲ የምድር ባቡር የመንገደኞች የትራንስፖርት አገልግሎቱን ሲጀምር፣ ቲኬት ለመቁረጥም ሆነ ወደ መነሻ ጣቢያው ለመድረስ ያለው የትራንስፖርት ችግር ግምት ውስጥ የገባ አይመስልም፡፡ ይህንን በቀላል ምሳሌ መግለጽ ይቻላል፡፡ ወደ አዳማ ለመሄድ የባቡር ቲኬት ለመቁረጥና ከቆረጡም በኋላ፣ በጉዞው ቀን ለመሳፈር ለቡ ባቡር ጣቢያ ለመድረስ ለትራንስፖርት የሚያወጣው ወጪ ከአዲስ አበባ አዳማ ለመጓዝ ከተወሰነው የባቡር ትራንስፖርት ታሪፍ በላይ መሆኑን መተንተን አያሻም፡፡ ግልጽ ነው፡፡

ይህንን አባባል በቀላሉ ለመግለጽ፣ መስቀል አደባባይ አካባቢ የሚገኝ ተጓዥ ለቡ ባቡር ጣቢያ ሄዶ ቲኬት ለመቁረጥና ለመመለስ በመደበኛ ታክሲ ከ40 ብር በላይ ያወጣል፡፡ በተለይ ከጀሞ ሦስት ወደ ለቡ ባቡር ጣቢያ ድረስ ለመሔድ መደበኛ ታክሲ ባለመኖሩ፣ በአካባቢው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ባጃጆች በትንሹ ከጀሞ ሦስት ወደ ባቡር ጣቢያ ደርሶ ለመመለስ ከ40 እስከ 50 ብር ይጠይቃሉ፡፡

ይህ ወጪ በሁለት ምልልስ ቢሰላ ከ150 ብር በላይ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ከአዲስ አበባ አዳማ በባቡር ለመጓዝ 90 ብር እየተከፈለ ቲኬት ለመቁረጥና በጉዞ ቀንም ለመሳፈር የሚጠይቀው የትራንስፖርት ወጪ ከፍተኛ መሆን፣ ተጓዦች ሌሎች አማራጮችን እንዲፈልጉ እንጂ ባቡሩን እንዲማትሩ አያደርጋቸውም፡፡

ሰሞኑን አንድ የማውቀው ሰው ድሬዳዋ ለመጓዝ በማሰብ ትኬት ለመቁረጥ ይፈልግና ወደ ባቡር ጣቢያው ለመድረስ ለታክሲ 120 ብር የኮንትራት ከፍሏል፡፡ በማግሥቱ በጉዞው መነሻ ዕለትም በተመሳሳይ ዋጋ ኮንትራት ይዞ ባቡር ጣቢያው ጋ መድረስ ግድ ስለሆነበት፣ ቲኬት ለመቁረጥና ባቡር ጣቢያው ለመድረስ በሁለት ምልልስ ለኮንትራት ታክሲ ብቻ 240 ብር አውጥቷል፡፡ ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ ለመጓዝ የሚከፍለው ዝቅተኛ ዋጋው 340 ብር ነው፡፡ ስለዚህ በባቡር ለመጓዝ ከሚጠይቀው ወጪ በላይ ቲኬት ለመቁረጥና ወደ ጣቢያ ለመድረስ የሚወስደው ወጪ ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ለምን እንዳልታሰበ ግራ ያጋባል፡፡ ቲኬት ለመቁረጥ የሚጠፋው ጊዜም ቢሆን፣ በገንዘብ ቢተመን አክሳሪ ነው፡፡ ድርጅቱ በቂ ዝግጅት ሳያደርግ ወደ ሥራ ገብቷል የሚለውን አስተያየት ለመቀበል የምንገደደውም ለዚህ ነው፡፡

ባቡርን የሚያህል ያውም ዘመናዊ ትራንስፖርት አቅርቦ፣ አገር አቋራጭ የሚሰጡትን የቲኬት አገልግሎት እንኳ መስጠት አለመቻል ምን ያህል እንዳልታሰበበት የሚጠቁም ነው፡፡ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አማካይ ቦታ ቲኬት መሸጫ ቢሮ ከማደራጀት በላይ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር ዘመናዊነቱን ማሳየት መጀመር ይገባው ነበር፡፡ ይህን አለመተግበሩም ያሳዝናል፡፡ ይህ እንኳ ቢቀር በውክልና አገልግሎቱን አለመስጠቱ፣ ተጓዦች ተጉላልተው ቲኬት እንዲቆርጡ አስገድዷል፡፡

ችግሩ እየታየ እንኳ አማራጮች መፍትሔዎችን ለመጠቀም አልተቻለም፡፡ ሌላው ቢቀር የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና መሥሪያ ቤት በሚገኝበት የቀድሞው አራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ ውስጥ ከሚገኙ ቤቶች አንዱን ክፍል ለቲኬት መሸጫ ማድረግ የደንበኞቹን ድካምና ወጪ ሊቀንስ እንደሚችል ለምን እንዳልታሰበበት ይደንቃል፡፡ ለፖስታ አገልግሎት ድርጅት ቲኬት ሽጥልኝ ቢባልስ፣ ጂቡቲ ትቃወማለች ማለት ይሆን? አሁን ላይ በባቡር መጓዝ ጣዕም የለውም፡፡

ተጓዦችን ከአንድ ቦታ አሰባስቦ ወደ ለቡ ጣቢያ የሚወስድ የትራንስፖርት አገልግሎት በጊዜያዊነት ቢቀርብም፣ የደንበኞችን ፍላጎት እንደሚጨምር ለምን አልታሰበም፡፡ መስመሩ መደበኛ የትራንስፖርት አገልግሎት እየተሰጠበት ባለመሆኑ፣ ተጓዦች ባቡር ጣቢያው ወደሚገኝበት ቦታ ለመድረስ ያለባቸውን ችግር ታሳቢ ያደረገ መላ መፈለግ ይቻል ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር የኢትዮ ጂቡቲ የባቡር ትራንስፖርት አገልግሎት የግዝፈቱን ያህል ተገልጋዮቹን በሚገባ ለማስተናገድ የሚያስችል አቋም ላይ አይደለም ብለን የምንጠቅሰው ሌላው ጉዳይ፣ ለቡ ባቡር ጣቢያ የት እንደሆነ እንኳ በአግባቡ አለመገለጹ ነው፡፡ ቀድሞ ነገር ሁሉም ሰው ለቡ በትክክል የት አካባቢ ይገኛል? ብሎ ቢጠይቅ አይፈረድበትም፡፡ ሲቀጥልም ትክክኛው አቅጣጫው በየት በኩል ነው? ምን አማራጭ መንገዶች አሉት የሚለውን ለማወቅ ጠቋሚ ምልክት የለውም፡፡

የታክሲ አሽከርካሪ የባቡር ቲኬት ለመቁረጥ የፈለገ ተሳፋሪ ይዞ ባቡር ጣቢያውን ለማግኘት ታክሲውን አቁሞ መረጃ ሲጠይቅ ተመልክቻለሁ፡፡ ቀድሞ በተሰጠው መረጃ መሠረት ‹‹ጀሞ 3 አደባባይ ስትደርስ በግራ በኩል ካሉ መንገዶች አንዱን ተጠቀም…›› ጀሞ አደባባይ ከደረሰ በኋላ ግን ባቡር ጣቢያው ወዴት ነው? ብሎ በጥየቃ  ለመሄድ ተገድዷል፡፡

የኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር አገልግሎት እንደው በጥድፊያ ነው የተገባበት የሚያሰኘው ሌላም ነገር ይጠቀስ ከተባለ፣ አንድ ተጓዥ ምን ያህል ዕቃ መያዝ ይችላል? ስንት ነው የሚከፈለው? ወዘተ. የሚለውንም መረጃ ለማወቅ አለመቻሉ ነው፡፡

ፈጣኑ ባቡር የተንቀረፈፈ አገልግሎቱና የፈሰሰበትን ገንዘብ ያልመጠነ አገልግሎት ማቅረቡ ለምን? ብለን በቁጭት የምንጠይቀው በቀላሉ ሊሠሩ የሚችሉ ነገሮች ባለመሠራታቸው ነው፡፡ ብዙ የተደከመበት፣ ብዙ ገንዘብ የፈሰሰበት ይህ የባቡር አገልግሎት እንዲህ ባለው ክፍተት ስሙ መነሳቱ እጀ ሰባራ ያደርጋል፡፡ ደግሞስ ይህንን የባቡር ትራንስፖርት ለማስተዳደር በዓመት 59 ሚሊዮን ዶላር የምንከፍለው የቀለጠፈና ዘመናዊ አገልግሎት ለማግኘትስ አይደል እንዴ? ስለዚህ የኢትዮ ጂቡቲ የምድር ባቡር የመንገደኞች የአገልግሎት አሰጣጡን ያቀላጥፍ፣ ብዙዎችም እንዲጎበኙት መትጋት አለበት፡፡ የሚመርጡት እንጂ የሚረግሙት መሆን  የለበትም፡፡ እንደ አንዳንዶቻችን ይህንን የዘመነ ባቡር ተመልክተን የሰጠነውን አድናቆት ሌሎች እንዲቋደሱ ለማድረግ አገልግሎቱ ይዘምን፡፡ በምቾት ያለ ሥጋት እንድንጓዝበት ተመቻችቶ የተሠራው ባቡር ላይ ያለ ችግር እንሳፈር፡፡

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት