Friday, December 1, 2023

አዳዲስ ውሳኔዎችን ያካተተው የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ አንድምታ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የኦሮሚያ ክልል ከዘጠኝ ክልሎችና ከሁለት የከተማ አስተዳደሮች ሰፊ የቆዳ ስፋትና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር አለው፡፡ የክልሉ የቆዳ ስፋት 284,538 ካሬ ኪሎ ሜትር ይሸፍናል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2017 መረጃ መሠረት የክልሉ የሕዝብ ቁጥር 36 ሚሊዮን ነው፡፡ ክልሉ ከአገሪቱ ክልሎች የበለጠ ሰፊ የቆዳ ስፋት ያለው ከመሆኑ ባሻገር፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር በቀጥታ በድንበር ይዋሰናል፡፡ በደቡብ አቅጣጫ ከኬንያና በምዕራብ በኩል ደግሞ ከሱዳን ጋር ወሰንተኛ ነው፡፡

ባለፉት ሃያ ዓመታት ይህን ሰፊ የቆዳ ስፋትና ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያለው ክልል በበላይነት ሲመራ የነበረው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ብሔራዊ ድርጅት የሆነው የኦሮሞ ሕዝቦች ዴሞክራሲዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ነው፡፡ ኦሕዴድ ክልሉን መምራት ከጀመረ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ቢቆጠርም፣ የክልሉን ወጣቶች ፍላጎትና ጥያቄ መመለስ በሚያስችል ቁመና ላይ እንዳልነበረ በስፋት ሲነገር ነበር፡፡ በክልሉ በነበረው የመልካም አስተዳደር ችግር ሳቢያ በሚነሱ ጥያቄዎች ወጣቶች ሕይወታቸውን ሲያጡና የአካል ጉዳት ሲደርስባቸውም ነበር፡፡

በአገሪቱ ከፍተኛ የሆነ ቀውስ ከተከሰተባቸው ክልሎችና አካባቢዎች መካከል አንዱ የኦሮሚያ ክልል ነው፡፡ በክልሉ ባለፉት ዓመታት ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘና ኦሮሚያ ከአዲስ አበባ ከተማ ማግኘት ስለሚገባት ልዩ ጥቅም፣ እንዲሁም በክልሉ በነበረው የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ሌሎች ችግሮች ምክንያት ወጣቶች በሚያነሷቸው ጥያቄዎች በርካታ ግጭቶች ተከስተዋል፡፡

በ2009 ዓ.ም. የኢሬቻ በዓል ሲከበር በተፈጠረው ግርግር ብቻ በርካታ ዜጎች ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቃወም በሚደረጉ ሰላማዊ ሠልፎች በሚፈጠረው ግርግርና ተኩስ በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡

ከ1997 ዓ.ም. ጀምሮ ክልሉ ከሶማሌ ክልል ጋር ባለው አስተዳደራዊ ወሰን ምክንያት በሚነሱ ግጭቶች በርካቶች ለሞትና ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፡፡ በ2010 ዓ.ም. መግቢያ ብቻ ከሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ጋር በተፈጠረ ግጭት በርካቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በመቶ ሺሕ የሚቆጠሩት ከቀዬአቸው ተፈናቅለዋል፡፡

በአገሪቱ እየተከሰተ ያለውን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመፍታት ሲባልም፣ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለበርካታ ቀናት ባደረገው ስብሰባ በኢትዮጵያ ታሪክ በተለይም ባለፉት 26 ዓመታት ታይተውና ተሰምተው የማይታወቁ ውሳኔዎችን እንዳሳለፈ ይታወሳል፡፡ ለዚህም ኢሕአዴግ ከሩብ ክፍለ ዘመን በላይ ባስቆጠረበት የሥልጣን ዘመኑ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር ሲባል በፍርድ ቤት የተፈረደባቸውና ገና ጉዳያቸው በመታየት ላይ ያሉ ዜጎችን ለመፍታት መወሰኑን ማሳያ ተደርጎ ይጠቀሳል፡፡ በዚህ ውሳኔ መሠረትም በአሥር ሺሕ የሚቆጠሩ እስረኞች እንዲፈቱ መደረጉን የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር)፣ ባለፈው ሳምንት መናገራቸውን መዘገባችን አይዘነጋም፡፡ እስረኞችን የመፍታት ሒደቱ አሁንም የቀጠለ እንደሆነ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ ብሔራዊ ድርጅቶቹ ከየክልሎቻቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ በማዕከላዊ ኮሚቴ ደረጃ ተመሳሳይ ስብሰባ እንዲያካሂዱ፣ እንዲሁም አዳዲስ የውሳኔ ሐሳቦችንና አቅጣጫዎችን እንዲያስቀምጡ ትዕዛዝ ተላልፎ እንደነበር ይታወሳል፡፡ በዚህ መሠረትም ብሔራዊ ድርጅቶቹ ስብሰባቸውን በማካሄድ ላይ ይገኛሉ፡፡

ከኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶች መካከል የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) አንዱ ሲሆን፣ ማዕከላዊ ኮሚቴው ስብሰባውን ካጠናቀቀ ከሁለት ሳምንት በላይ አስቆጥሯል፡፡ 

ሌላው አዳዲስ ውሳኔዎችን ያስተላልፋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረውና ጥር 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ስብሰባውን ያጠናቀቀው የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅት ኦሕዴድ ነው፡፡ ኦሕዴድ ስብሰባውን ሲያጠናቅቅም ጠንከር ያለና ብዙዎችን ያነጋገረ መግለጫ አውጥቷል፡፡

የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ ባካተታቸው የውሳኔ ሐሳቦችና አቅጣጫዎች ላይ የፖለቲካ ተንታኞች የተለያዩ አስተያየቶችን ሲሰጡ ተደምጧል፡፡ በዋናነት በብዙዎች ዘንድ መነጋገሪያ ሆኖ የሰነበተው ጉዳይ፣ ኦሕዴድ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ከሚኖሩ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ተቀራርቦ ለመሥራት ቁርጠኛ ነው የሚለው አንዱ ነው፡፡    

በኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ ከተካተቱ ሐሳቦች መካከል አንዱ፣ ‹‹እንደ ነብር ዥንጉርጉር በሆነው የእርስ በርስ ግንኙነታችን የሐሳብ ልዩነትን ማስተናገድ የሚያስችል አሠራርና ባህል ማዳበር ያስፈልጋል፡፡ ከኃይል የፀዳ፣ በውይይትና በምክክር የሚያምን፣ ይበልጥ ለአገር የሚበጅ ሐሳብ የሚፈልቅበት የውይይት ባህል እንዲዳብር የፖለቲካ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ ነው፡፡ . . . የአገራችን ሕዝብ አማራጭ ሐሳቦች እየቀረቡለት በዴሞክራሲዊ ሒደት የሚጠቅመውን ሐሳብ እንዲመርጥ፣ ለፖለቲካ ፓርቲዎች በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡ ቃል ኪዳኖች ያለመሸራረፍ እንዲተገበሩና ዴሞክራሲ እንዲሰፍን ኦሕዴድ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት እንደሚሠራ በጥልቅ ተወያይቶበት አቅጣጫ አስቀምጧል፤›› የሚለው ይገኝበታል፡፡

ጠበቃና የሕግ አማካሪው አቶ ዘሪሁን ፀጋው ኦሕዴድ  ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በቅርበት ለመሥራት በመወሰኑ ላይ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ኦሕዴድ ጥሪ ያቀረበው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው ለተፈረጁት ግንቦት ሰባትና የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ጭምር ነው ሲሉ ተደምጧል፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ እነሱን ሳይሆን በሰላማዊ ፉክክር ሥልጣን መያዝ ይቻላል ከሚሉት ጋር ነው በማለት ሲከራከሩ ተደምጠዋል፡፡

የሕግ ባለሙያው አቶ ዘሪሁን ኦሕዴድ ጥሪ ሊያቀርብ የሚችለው በክልሉ ስም ተደራጅተው በተቃዋሚ ጎራ የተሠለፉና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው ካልተፈረጁት ጋር ነው ይላሉ፡፡ ኦሕዴድ አንድ ክልል የሚመራ በመሆኑ ሳቢያ፣ በፌዴራሉ መንግሥት አሸባሪ ከተባሉት ጋር አብሮ ለመሥራት ሕጉ የሚፈቅድለት እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡

ነገር ግን ኦሕዴድ አንዱ የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅት እንደ መሆኑ መጠን፣ ሌሎቹን ድርጅቶች በማሳመንና ያለውን መብት በመጠቀም ይህንን ለማድረግ የሚያስችለው መንገድ እንዳለም አቶ ዘሪሁን አክለው ገልጸዋል፡፡

ተንታኞች ኦሕዴድ የክልል ፓርቲ ቢሆንም አገርን ወክሎ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በተለይም አገር ውስጥና ውጭ አገር ካሉት ጋር በቅርበት ለመሥራት መወሰኑ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነው ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ አብሮ ለመሥራት ጥሪ ያቀረበው ለእነማን እንደሆነ በግልጽ ባልተቀመጠበት ሁኔታ ጉዳዩ አከራካሪ ነው ሲሉ የሚሞግቱ አስተያየት ሰጪዎችም አሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ የኦሕዴድ ከፍተኛ አመራሮች አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ሙከራ ባይሳካም፣ ታዋቂው የጂኦፖለቲካ ተንታኝ አቶ ልዑልሰገድ ግርማ በዚህ ሐሳብ አይስማሙም፡፡ አቶ ልዑልሰገድ ኦሕዴድ ከሌሎች ተቃዋሚ ኃይሎች ጋር የአብረን እንሥራ ጥሪ ማቅረቡ ተገቢነት ያለውና ትክክለኛ ውሳኔ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ኦሕዴድ ይህን ውሳኔ ማስተላለፉ የአገሪቱን የፖለቲካ ውጥረት ያረግባል ብለው ከማመን በተጨማሪ፣ ሰላማዊ ትግል የሚያካሂዱትን ኃይሎች እንደሚያነቃቃና በኃይል ሥልጣን እንይዛለን ብለው የሚንቀሳቀሱትን አካላት አስተሳሰብ ሊያስቀይር የሚችል እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ የአብረን እንሥራ ጥሪ ያቀረበላቸው ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ተብለው የተፈረጁትን እንዳልሆነና የሚያሻማ ነገር እንደሌለው አቶ ልዑልሰገድ ጠቁመዋል፡፡

ኦሕዴድ ጥሪ ያቀረበው ነፍጥ ሳያነሱ በሰላማዊ መንገድ እየታገሉ ላሉ በውጭ አገር የሚገኙ ለኦሮሞ ድርጅቶች እንደሆነ አቶ ልዑልሰገድ በመግለጽ፣ ‹‹ምናልባትም ከኤርትራ መንግሥት ጋር እያበሩ ያልሆኑ፣ ነገር ግን አክራሪነት ያላቸውና የመገንጠል አቋም ያላቸውን ጭምር ሊያካትት ይችላል፤›› ብለዋል፡፡  

የኢትዮጵያዊያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) ፕሬዚዳንት ጫኔ ከበደ (ዶ/ር) በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ኦሕዴድ በፀረ ሽብር ሕጉ ወንጀለኛ ተብለው የተፈረጁትን አያካትትም የሚል እምነት እንዳላቸው ጠቁመው፣ በሰላማዊ ትግል ሥልጣን መያዝ ይቻላል ብለው ከሚታገሉት ጋር ለመነጋገር ያቀደ ነው የሚመስለው ብለዋል፡፡

የኦሕዴድ ለኦሮሚያ ክልል ብሎም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብዙ ተስፋ ይዞ የመጣና ብዙ ኢትጵያዊያንን ያስደሰተ ውሳኔ እንዳስተላለፈ ዶ/ር ጫኔ ጠቁመዋል፡፡ ኦሕዴድ አገራዊ ስሜት ያዘለና ሊያግባባ የሚችል፣ ግልጽነትን፣ ተጠያቂነትንና ኃላፊነትን የተላበሰ የውሳኔ ሐሳብ እንዳስተላለፈ አውስተዋል፡፡

የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ በመግለጫው ካካተታቸው ጉዳዮች መካከል ወጣቱንና የክልሉን ሕዝብ በማሳተፍ የአገሪቱን ህልውና መታደግ እንደሚገባ አስምሮበታል፡፡ ይህ የሚጠቁመው አገሪቱ ያለችበት የፖለቲካ ቀውስ አስቸጋሪ እንደሆነና መላ የአገሪቱ ሕዝብና መንግሥት በመግባባት መፍታት ካልቻሉ፣ ልትፈራርስ የምትችልበት አጋጣሚ እንዳለ አመላካች መሆኑን የፖለቲካ ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡

ኦሕዴድ ሀብት ማመንጨት ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖርና በወጣቶች ላይ የታየውን ፍትሕ የመሻት ቁጣ አገርን በማያፈርስ መንገድ፣ በሰላማዊ የትግል ሥልት እንዲተካ አበክሮ እንደሚሠራ አስታውቋል፡፡  

አቶ ልዑልሰገድ የአገርን ህልውና ለመታደግና ግላዊና ቡድናዊ የጥቅም ትስስርን ለመበጣጠስ ኦሕዴድ አቅጣጫ ማስቀመጡ ይበል የሚያሰኝ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ አገሪቱ ባለፉት 25 ዓመታት በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ብዙ መንገራገጮች ገጥመዋት እንደነበር አስታውሰው፣ ይህን ችግር በመረዳትና ለችግሩ መፍትሔ የሚሆን አቅጣጫ ማስቀመጥ ወቅቱ የሚጠይቀው ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

በአስተሳሰብ ድክመት የተነሳም ግለሰቦች በተለይም ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በግልና በቡድን በመደራጀት ጥቅምን የማሳደድና የአገርን ጉዳይ ገሸሽ የማድረግ አባዜ በተደጋጋሚ ሲታይ እንደነበር አቶ ልዑልሰገድ ጠቁመዋል፡፡ በሙስና እየተመዘበረ ያለው ገንዘብ ብዙ እንደሆነና ይህ ደግሞ ከወዲሁ መፍትሔ ካልተበጀለት፣ እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ ይሄዳል የሚል እምነት እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ይህን ሊፈቱና ሊያስተካክሉ የሚችሉ የፖለቲካ ልሂቃን ያስፈልጋሉ ብለዋል፡፡ ኦሕዴድ ‹አገር አደጋ ላይ ነች› ብሎ የክልሉንና የአገሪቱን ሕዝብ ሊያግባባና ሊያስማማ የሚችል፣ የወቅቱን የፖለቲካ ቀውስ ከግንዛቤ ያስገባ ውሳኔ እንዳስተላለፈ ጠቁመው፣ ይኼንን ውሳኔ ሌሎች የኢሕአዴድ ብሔራዊ ድርጅቶች ሊጋሩት እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

ዶ/ር ጫኔ በበኩላቸው፣ ኦሕዴድ በአገሪቱ የተከሰተውን ቀውስ መነሻ በማድረግ ጥናት አድርጎ ውሳኔ ላይ መድረሱን አድንቀዋል፡፡ የቡድናዊና የግላዊ ጥቅመኞችን መረብ መበጣጠስና የአገርን ህልውና መታደግ የሚቻለው፣ በተጨባጭ ለውጥ ሊያመጡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ለረዥም ዓመታት ጥያቄ ሲያቀርብ እንደነበርና ጥያቄውም መፍትሔ ሳያገኝ መቆዩቱን አስታውሰው፣ አሁን ጥያቄውን በሚገባ ለመመለስ ኦሕዴድ ዝግጅት ላይ እንደሆነ የሚጠቁም መሆኑን ገልጸዋል፡፡

‹‹የኦሕዶድ መግለጫ በድፍረት የወጣ፣ ከኦሮሞ ሕዝብም በዘለለ ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ መልዕክት ያስተላለፈ ነው፤›› ሲሉ ዶ/ር ጫኔ ተናግረዋል፡፡ ሌሎች የኢሕአዴግ ብሔራዊ ድርጅቶችም ከኦሕዴድ ልምድ በመውሰድ የአገሪቱን ህልውና መታደግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

ዶ/ር ጫኔ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ለበርካታ ቀናት አድርጎት በነበረው ማጠቃለያ ላይ ብዙ ቃል የገባቸው ጉዳዮች እንደነበሩ አስታውሰው፣ ውሳኔዎቹ እስካሁን እየተፈጸሙ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ መንግሥት ወጣቱን ተጠቃሚ የሚያደርግበት አሠራር ካልተፈጠረ በስተቀር፣ አገሪቱ ለውድመትና ለጥፋት ጫፍ ላይ እንደሆነች ጠቁመው፣ ይህን ጥፋት ለመግታት ደግሞ እንደ ኦሕዴድ ዓይነት ዕርምጃ መውሰድ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

‹‹በመላ የአገራችን ሕዝቦች ይሁንታ አፋን ኦሮሞ የፌዴራል የሥራ ቋንቋ እንዲሆን ድርጅታችን ይሠራል፤›› ይላል የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ መግለጫ፡፡ አቶ ልዑልሰገድ ኦሮሚኛ ቋንቋን የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ማድረግ ተጨማሪ ሀብት እንደ ማግኘት የሚቆጠር እንጂ ሌላ ችግር የለውም ይላሉ፡፡ አፋን ኦሮሞ የሥራ ቋንቋ ሆነ ተብሎ ከዚህ በፊት የነበረውን አማርኛ ቋንቋ ለማጥፋት የሚደረግ ሙከራ ካለ ግን ችግር ሊፈጠር ይችላል ሲሉ አክለዋል፡፡

ዶ/ር ጫኔ በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ፡፡ ኦሮሚያ ክልል በቆዳ ስፋትም ሆነ በሕዝብ ቁጥር ከሌሎች ክልሎች እንደሚበልጥ አስታውሰው፣ ኦሮሚኛ የፌዴራሉ ሁለተኛ የሥራ ቋንቋ ቢሆን ችግር እንደሌለው ገልጸዋል፡፡

የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥና መድረኩ የሚጠይቀውን ትግል በብቃት ለማከናወንና በቀጣይ ጥንካሬውን አጎልብቶ ለመጓዝ ያመቸው ዘንድ 14 በኢሕአዴግ ምክር ቤት የሚሳተፉ አባላቱ በአዲስ እንዲተኩ፣ አራት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ደግሞ እስከሚቀጥለው ጉባዔ እንዲታገዱና አንድ አባል በማስጠንቀቂያ እንዲታለፍ መደረጉን በመግለጫው አስታውቋል፡፡

የውስጠ ድርጅት ዴሞክራሲን ለማስፋትና የአመራሩን የሐሳብና የተግባር አንድነት ለማጠናከር ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ በመግለጫው ተብራርቷል፡፡ ኦሕዴድ የክልሉ ሕዝብ የጭቆና መሠረት የሆኑ አስተሳሰቦችንና አሠራሮችን ሲታገል እንደቆየና ወደፊትም እንዲታገል ጥሪ አቅርቧል፡፡ መደባዊ ጭቆና በአገሪቱ እንዳያቆጠቁጥም የክልሉ ሕዝብ ትግል እንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፏል፡፡

ወጣቱ በሁሉም መስክ በሚያደርገው ትግል ምክንያታዊና ሳይንሳዊ በሆኑ ሐሳቦች እየተመራ፣ ዴሞክራሲያዊነትን በጠበቀና ተደማሪ ለውጦችን በመንከባከብ መልኩ የሁሉም መብት ተከብሮ፣ የአገሪቱና የክልሉ ህልውናና ሰላም እንዲረጋገጥ ወጣቱ ግንባር ቀደም በመሆን ኃላፊነቱን እንዲወጣ የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ለኦሮሞ ምሁራን፣ ለመንግሥት ሠራተኞች፣ ለፀጥታ አካላት፣ ለኦሕዴድ አባላት፣ በውጭ አገር ላሉ የኦሮሞ ተዋላጆች፣ ለኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች፣ ለተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችና ለኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ሕዝቦች መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን፣ በክልሉ ብሎም በአገሪቱ የተጀመሩ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ከዳር እንዲደርሱ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጥሪ አቅርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -