በውብሸት ሙላት
አራተኛው ዙር የሕዝብ ቆጠራ በቅርቡ የሚካሔድ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ቀድሞ ከተከናወኑትም የተሻለ ጥራት እንዲኖረው በቆጠራው የሚሰማሩትም ይሁኑ ተቆጣጣሪዎቹ ለእዚሁ አገልግሎት ሲባል ጥቅም ላይ የሚውሉ ኮምፒውተሮችን እንደሚጠቀሙ ይፋ ሆኗል፡፡ የሚሰበሰበው መረጃ የተሻለ ጥራት እንዲኖረው ለማድረግ ያግዛል፡፡ ኮምፒተሮቹ ላይ የሚጫኑት ፕሮግራሞች ላይ ስህተት ከሌለ ወይም ካልተፈጠረ በስተቀር በወረቀት ላይ ከሚሠራው እንደሚሻል ዕሙን ነው፡፡
ከተለያዩ አገሮች የሕዝብ ቆጠራ ታሪክ መረዳት እንደሚቻለው ቆጠራን ተከትሎ የሚመጡ አለመግባባትና ሙግቶች አሉ፡፡ የቆጠራው ውጤት መንግሥታዊ ውሳኔዎች ላይ የሚያስከትለው ተፅዕኖ እንደሚኖርም የታወቀ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ ከበጀት፣ ከማኅበራዊ አገልግሎት ማቅረብ፣ በየደረጃው በሚኖሩ ምክር ቤቶችና አጠቃላይ መንግሥታዊ መዋቅር ውስጥ ከመወከልና ከመሳተፍ ጋር ተያይዞ አለመግባባት ተከሥቷል፡፡ የተወሰኑ አገሮችም ካለመግባባት አልፎም ግጭትም ተፈጥሯል፡፡ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱም ቀውስ ውስጥ የገባባቸው አገሮችም ነበሩ፡፡
የሕዝብ ቆጠራ ውጤትን መነሻ በማድረግ አለመግባባት፣ ግጭት እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ ቀውስም ሊከተል እንደሚችል ስለሚታወቅ ጥንቃቄውን በሕገ መንግሥት ላይ ይገለጻል፡፡ ቆጠራ እንዲኖርም እንዴት መከናወን እንዳለበትም በሕገ መንግሥት ማስቀመጥ የተለመደ ነው፡፡ ቢያንስ ጥቅል በሆነ መልኩ፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያው የአሜሪካ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ እ.አ.አ. በ1787 የፀደቀው ሕገ መንግሥት አንቀጽ 1 ክፍል 2 ቁጥር 3 ይኼንኑ ጉዳይ የሚገዛ ነው፡፡
በየአሥር ዓመቱ ማከናወንም በአገሮች ዘንድ የተለመደ ነው፡፡ በኢትዮጵያም ጭምር፡፡ በእርግጥ በ1987 ዓ.ም. ከተከናወነ ቀጣዩ በ1997 ዓ.ም. መደረግ ነበረበት፡፡ ይሁን እንጂ የተከናወነው በ1999 ዓ.ም. ነው፡፡ ይፋ ባይሆንም ሕገ መንግሥቱ ላይ በየአሥር ዓመት መከናወን እንዳለበት የሚገልጸው ንዑስ አንቀጽ ተሻሽሏል ማለት ነው፡፡ በእርግጥ ከዚህ አንፃር ዘንድሮ የሚከናወነውም ቢሆን አንድ ዓመት ዘግይቷል፡፡ በየትኛው የሕገ መንግሥት አንቀጽ መሠረት አንድ ዓመት ማዘግየት እንደተቻለ አይታወቅም፡፡ ምናልባት የ1997ቱን ለማስተላለፍ ሲባል የቀረበው ማሻሻያ (ለሕዝብ ይፋ ያልሆነ) ላይ በእዚህ መንገድ ማስተላለፍ እንደሚቻል ማሻሻያው ላይ ተካትቶ ካልሆነ በስተቀር፣ ሕገ መንግሥቱ በየአሥር ዓመቱ ቆጠራ መደረግ እንዳለበት ብቻ ነው የሚገልጸው፡፡ ሊተላለፍ የሚችልበትን ሁኔታ አይገልጽም፡፡
የዚህ ጽሑፍ ትኩረት ግን የሕዝብ ቆጠራ በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ ሊኖረው የሚችለውን አንድምታና እነዚህ አንድምታዎች አሉታዊ ውጤት እንዳያስከትሉ አስቀድሞ ጥንቃቄ የማድረግን አስፈላጊነት ለማሳየት ነው፡፡
የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 103 ሙሉ በሙሉ የሕዝብ ቆጠራን ብቻ ይመለከታል፡፡ ስድስት ንዑሳን አንቀጾችም አሉት፡፡ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ትኩረት ያመለክታል፡፡ ይዘቱን በሁለት መክፈል ይቻላል፡፡ የመጀመርያው የቆጠራውን አካል አወቃቀር፣ ተጠሪነት፣ ኃላፊነት የሚመለከት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የቆጠራን አስፈላጊነትና ግብ ይመለከታል፡፡
የሕዝብ ቆጠራን የማከናወን ኃላፊነት ብቻ ያለው ኮሚሽን መቋቋም እንዳለበት አንቀጽ 103(1) ላይ ተገልጿል፡፡ የኮሚሽኑ አባላትም በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማሉ፡፡ የኮሚሽኑ ተጠሪነትም ለምክር ቤቱ ነው፡፡ ኮሚሽኑም ዋና ጸሐፊና አስፈላጊ ሠራተኞችም ይኖሩታል፡፡ የኮሚሽኑ ተግባራትም በዋናነት አገሪቱን ሕዝብ መቁጠርና ማጥናት ነው፡፡ ቆጠራውን ደግሞ በየአሥር ዓመቱ የማከናወን ግዴታ አለበት፡፡
የጥናቱ ወይም የቆጠራው ውጤት ደግሞ ለተለያዩ ጥቅሞች ሊውል ቢችልም የምርጫ ወረዳዎችን ለማካለል ይውላል፡፡ የምርጫ ወረዳዎችን የሚያካልሉት የፌደሬሽን ምክር ቤትና የምርጫ ቦርድ ናቸው፡፡
ከሕገ መንግሥቱ በተጨማሪ ስለ ሕዝብ ቆጠራ ብቻ ራሱን ችሎ የወጣ አዋጅም አለ፡፡ በእርግጥ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣንን በሚመለከት የወጣው አዋጅም በተወሰነ መልኩ ከሕዝብ ቆጠራ ጋር ግንኙነት አለው፡፡ የባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽኑ ዋና ጸሐፊ በመሆን ያገለግላል፡፡ በአጠቃላይ የቆጠራ ውጤቱንም በመተንነተንና በማሰራጭት ረገድም ከፍተኛ ሚና አለው፡፡ በየአሥር ዓመቱ ከሚከናወነው ውጭ ያሉትን ሕዝብን የሚመለከት ጥናቶችን ባለሥልጣኑ ያከናውናል፡፡
ከኮሚሽኑ ማቋቋሚያ አዋጅ መረዳት እንደሚቻለው የቆጠራው ግብ የሕዝቡን ኑሮ ለማሻሻልና ሕገ መንግሥቱ ላይ በተቀመጠው መሠረት ፖለቲካዊ ሥርዓትን ለማከናወን ሲባል ይከናወናል፡፡ በአገር አቀፍም ይሁን በሌሎች ከእዚያ በታች ባሉ እርከኖች ላይ ለሚደረጉ ምርጫዎችን ለማከናወን አስፈላጊ መሆኑንም አጽንኦት ይሰጠዋል፡፡ ለተለያዩ ዕቅድ ዝግጅት፣ ክትትል፣ ትንተና፣ ጥናትና ምርምር የማድረግ ዓላማዎችንም ያካትታል፡፡
የኮሚሽኑን አባላት አመራረጥ በተመለከተ አዋጁ ሰብሳቢው በፌደራል ደረጃ ያለ ሚኒስቴር ወይም ከዚያ በላይ ሥልጣን ሊኖረው እንደሚገባ እንዲሁም ጸሐፊው ደግሞ የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ባለሥልጣን ኃላፊ እንደሚሆን ተገልጿል፡፡ እንዲሁም የኮሚሽኑ አባላት የሚውጣጡባቸውን መሥሪያ ቤቶችና የአስተዳደር እርከኖችም ተወስኗል፡፡ በመሆኑም ሕገ መንግሥቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰጠውን ሥልጣን በመገደብ ከየት ከየት በመምረጥ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዕጩነት መቅረብ እንዳለባቸው አዋጁ ገደብ አብጅቷል፡፡
ከዚህ አንፃር ሰብሳቢው ሚኒስትር ወይም ከዚያ በላይ ሥልጣን ያለው፣ ጸሐፊውን የማዕከላዊ ስታትስቲክስ መሥሪያ ቤት ኃላፊ፣ ከዘጠኙ ክልሎች እንዲሁም ከአዲስ አበባና ከድሬዳዋ ከተማ መስተዳድሮች፣ ከተቋማት ደግሞ ከፌዴሬሽን ምክር ቤትና ከምርጫ ቦርድ አባላት የሚውጣጡ ናቸው፡፡ በእርግጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ አዋጅ የተገደበውን ሥልጣን ሕገ መንግሥታዊነት ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኮሚሽኑን አባላት ተቀብሎ ማጽደቅ ወይም አለማጽደቅ እንጂ ሕግ አውጭው የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥልጣን መቀነሱ ተገቢነቱ ወይም ሕገ መንግሥታዊነት ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል፡፡
በሕዝብ ቆጠራ ወቅት ከሚወሰኑ ጉዳዮች ውስጥ አንደኛው ብሔር ነው፡፡ በአጠቃላይ የአገሪቱን ሕዝብ በሙሉ ከመቁጠር ባሻገር በወረዳ፣ በዞን፣ በክልል፣ በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በጾታ ወዘተ ቆጠራ ይከናወናል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በተለይ ብሔርንና ሃይማኖትን መሠረት በማድረግ የሚቀርቡት ውጤቶች ለግጭትና ለቀውስ መነሻ ሲሆኑ ይስተዋላል፡፡ የአገሮችም ተሞክሮም የሚያሳየው ይኼንኑ ነው፡፡
በተለይም ሁለትና ከእዚያ በላይ ብሔሮች በሚገኙባቸውና የተለያዩ የፖለቲካ ሥርዓቶችና ውሳኔዎች በሚሰጥባቸው አገሮች የብሔሮች ቁጥር ሲያወዛግብና ለቀውስም ምክንያት ሲሆን ይስተዋላል፡፡ ሃይማኖትም ተመሳሳይ ውጤት ያስከተለባቸውም አገሮችም አሉ፡፡
የሕዝብ ቆጠራ በርካታ ፋይዳዎች አሉት፡፡ የፖለቲካ መሠረትን ጠንቅቆ አውቆ በዚያው መሠረት ለመሥራት ይጠቅማል፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ ብሔሮች በሚገኙባቸው አገሮች ደግሞ የብሔር ፉክክርንም ሊያስከትል ይችላል፡፡ በቆጠራ ውጤት መሠረት የምርጫ ወረዳዎች ይከለላሉ፡፡ ፓርቲዎች ደጋፊዎቻቸውን ከግምት በማስገባት የምርጫ ወረዳን ሊያካልሉም ይችላሉ፡፡
ኢኮኖሚ ነክ የሆኑ ውሳኔዎችንም ለመስጠትም ግብዓት ይሆናል፡፡ ገቢ ክፍፍልና ድጎማ ለማድረግ ሲባልም የቆጠራውን ውጤት በመጠቀም የበጀት ድጎማ ይዘጋጃል፡፡ ሕዝባዊ አገልግሎት ለመስጠት፣ ሥራ ያለውን ከሌለው ለመለየት ይረዳል፡፡ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ለማዳረስ ወይም ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለማሰራጨት ጥቅም ላይ ይውላል፡፡ አንዳንድ አገሮች ደግሞ የመጠለያ (የቤት)፣ የትምህርት፣ የጤናና የወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ፖሊሲዎችን ለማውጣትና ለመተግበር ይጠቀሙበታል፡፡
ከላይ የተገለጹትን ለመዘወር ሲባል ቁጥሩን መለዋወጥም የአገሮች ታሪክ ምስክር ነው፡፡ ቆጠራን ተከትሎ የሚመጣ ሙግትና ክርክርም ማስተዋልም የተለመደ ነው፡፡ እንደውም “ቆጠራ የክርክር ገፈራ ወይም ድርቆሽ ነው” ይባላልም፡፡ ቆጠራ ከተካሄደ አለመግባባት ስለሚበዛ ክርክርና ሙግትም ይበዛል፡፡ በዚህ ምክንያት ነው የሙግት ገፈራ የሚባለው፡፡
ሆን ተብሎም ይሁን በቆጠራ ወቅት በሚፈጠር ስህተት በጥቅል ሕዝቡን አንዳንዴም የተወሰነን ቡድን ብቻ ነጥሎ ዝቅ አድርጎ መቁጠርም አለ፡፡ አንዱን ከፍ አንዱን ዝቅ በሚልበት ጊዜ ውዝግብ መኖሩ አይቀሬ ነው፡፡ የአሜሪካን በምሳሌነት እንመለከት፡፡ በ1940 በተደረገው ቆጠራ ከአጠቃላይ ሕዝቡ 5.4 በመቶ ዝቅ ሲል የነጮቹ ግን 5 በመቶ የጥቁሮች ግን 8.4 በመቶ ነበር፡፡ በ1980 ደግሞ ከአጠቃላይ ሕዝቡ 1.2 በመቶ ዝቅ ሲል የጥቁሮች ግን 4.9 በመቶ ነበር፡፡
በርካታ አገሮች ቆጠራ ተከትሎ በመጣ አለመግባባት ለብዙ ቀውሶች ተዳርገዋል፡፡ አልባኒዎችና ሙስሊሞች ዝቅ ተደርገዋል በሚል በ1994 መቄዶኒያ ላይ ቀውስ ተፈጥሮ ነበር፡፡ መቄዶንያ ከአንደኛው የዓለም ጦርነት በፊትም በተደጋጋሚ ታምሳለች፡፡ ናይጀሪያ ደግሞ በጣም የባሰ ነው፡፡ የሰሜኑ ግዛት (ሐውሳ-ፉላኒ) በደቡቡ (ይሩባና ኢግቦ) ከተበለጠ በትክክል እንደተቆጠረ አይወሰድም፤ ሆን ተብሎ የተፈበረከ እንደሆነ ነው የሚታሰበው፡፡ የሰሜኑም ቢሆን ከወትሮው ከፍ ካለ በደቡቡ ዘንድ ተቀባይነት የለውም፡፡ በ1962 በተደረገው ቆጠራ ደግሞ ከፍተኛ ትርምስ ተነስቶ ነበር፤ ኃላፊዎቹም ተባረዋል፡፡
እንግዲህ ከቆጠራ ጋር በተያያዘ የግጭቶች መነሻቸው ዘርን፣ ብሔርን፣ ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ብሔር እንዴት እንደሚቆጠር እንመልከት፡፡ ጀምስ ስኮት የሚባል ምሁር እንደሚለው ቆጠራ መሬት ላይ ያለውን ሁኔታ እንዳለ ከመግለጽና ከማንፀባረቅ ባለፈ አዳዲስ እውነታዎችም ይፈጠርበታል፣ ይገነባበታል፣ ይፈበረክበታል፡፡ አዳዲስ ማንነት ይፈጠርበታል፡፡ አዳዲስ ንጽጽርም ያስከትላል፡፡ አዳዲስ መበላለጥም እንዲሁ፡፡
መንግሥታትም በአገር ደረጃ እንዲኖር የሚፈልጉትን የብሔር ሁኔታና ምጥጥን ለማስተካከል ይጠቀሙበታል፡፡ ጀምስ ስኮት በመቀጠልም “መንግሥት የሚፈልገውን መስፈርት የሚያሟላ ሕዝብንም መፍጠሪያ መሣሪያ ነው፤” ይለዋል፡፡ በመሆኑም አንድን ብሔር ከሌላ ለመለየት የሚያገለግሉ መለኪያዎችንም በጥንቃቄ ያወጣሉ፡፡
የግለሰብን ብሔር ለማወቅ፣ ምሥራቅ አውሮፓ የግለሰቡን የብሔር ማንነትን በመጠየቅ ቆጠራ ሲያደርጉ፤ ሩሲያ ግን በወላጆች የዘር ግንድ እንጂ ማንም ሰው ራሱን በሚገልጸው ወይም በሚፈልገው መንገድ እንዲገልጽ አይፈቅዱም ነበር፡፡ የሚናገረው ቋንቋም ቢሆን ብሔርን ለመለየት መለኪያ አይሆንም፡፡
ከሩሲያ በተለየ መንገድ፣ ፊንላንድና ኩቤክ (ካናዳ) የአፍ መፍቻ ቋንቋን መሠረት በማድረግ የግለሰብን የብሔር ማንነት ይለያሉ፡፡ ዓለም አቀፉ የስታትስቲክስ ምክር ቤት (ኮንግረስ) ግን ቆጠራ በሚደረግበት ጊዜ ብሔርን በቀጥታ ከመጠየቅ ቋንቋን በመጠየቅ እንዲለዩ ነው የሚመክረው፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በፊት የተደረጉ ቆጠራዎች ብዙዎቹ በዚህ መንገድ የተከናወኑ ናቸው፡፡ በምክንያትነት የሚጠቀሰውም የሰዎች የብሔር ንቃት ዝቅተኛ ደረጃ ላይ መገኘቱ ነው፡፡
በፓኪስታንም ቢሆን የብሔር ቁጥር የሞት ሽረት ነው፡፡ ምክንያቱ ደግሞ ክልሎቹንም ለመቆጣጠር ፌዴራል መንግሥቱ ላይ ለመወከልም ወሳኝ በመሆኑ ነው፡፡ ሊባኖስም ቢሆን እንደዚያው ነው፡፡
አንዳንድ ጊዜ ተቆጣሪዎቹ የቆጠራውን ዓላማና በቆጠራው ውጤት ላይ ተመርኩዞ የሚገኝ ነገርን በማሰብ ግለሰቦች የብሔር ማንነታቸውንም የሚወስኑበት አጋጣሚዎች አሉ፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ መለኪያዎቹ በራሳቸው የብሔርን ቁጥር ከፍም ዝቅም የሚደርጉበት አጋጣሚዎች አሉ፡፡ ከአፍ መፍቻ ቋንቋ ይልቅ፣ ለሥራ የሚገለገሉበትን ቋንቋ በሚወሰድበት ጊዜ ቁጥሩ ላይ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ በቀጥታ ብሔርን መጠየቅም እንዲሁ በቋንቋ ከመቁጠር ይለያል፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ የወላጆችን ብሔርም የሚጠቀሙ አሉ፡፡ በእነዚህ መለኪያዎች መሠረት የሚገኘው ቁጥር የተለያየ የሚሆንበት ዕድል ከፍተኛ ነው፡፡
በርካታ አገሮች ብሔርን መለየት የሚፈልጉት አዎንታዊ የድጋፍ ዕርምጃ ለማድረግ ቢሆን አንዳንድ አገሮች ደግሞ የግለሰቦችን የብሔር ማንነት መሠረት ያደረገ ቆጠራ ፍጹም የማይቀበሉ አሉ፡፡ በተለይ ፈረንሣይ ብሔርና ሃይማኖት ከግምት ያስገባ ቆጠራ ማድረግ ፍጹም ክልክል ነው፡፡ የፈረንሣይ ሉዓላዊነት በማናቸውም መንገድ፣ በምንም ሁኔታ የማይከፋፈል እንደሆነ ሕገ መንግሥቱ ስለሚደነግግ ብሔርም ሃይማኖትም አይቆጠርም፡፡ በ1991 ዓ.ም. የሕገ መንግሥት ፍርድ ቤታቸውም ይኼንኑ ሐሳብ በማጠናከር ወስኗል፡፡
ወደ ኢትዮጵያ እንመለስ፡፡ ብሔርን፣ ብሔረሰብን ወይም ሕዝብን እንደ ቡድን ለመለየት የሚያገለግሉት መስፈርቶች የሚከተሉት መሆናቸውን ከሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 39 መረዳት ይቻላል፡፡ እነዚህም ተመሳሳይ ባህል ወይም ልምዶች፣ አንድ የእርስ በርስ መግባቢያ ቋንቋ፣ የጋራ ወይም የተዛመደ ሕልውና፣ የሥነ ልቦና አንድነትና በአንድ በተያያዘ አካባቢ መኖር ናቸው፡፡
እነዚህ እንደ ቡድን ዕውቅና ለማግኘት ወይም ብሔር ለመሆን ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ በግለሰብ ደረጃ ደግሞ ማንም ሰው ብሔሩ ምን እንደሆነ ለመወሰን ግን በሕገ መንግሥቱ የተቀመጠ መለኪያ የለም፡፡
የአንድ ሰው የብሔር ማንነቱን ለመለየት ወይም ብሔሩ ምን እንደሆነ ለማወቅ በሕዝብ ቆጠራ ወቅት አገልግሎት ላይ የዋለው መለኪያ የሚቆጠረውን ሰው ራሱን ብሔሩ ምን እንደሆነ እንዲናገር በመጠየቅ ነው፡፡ የብሔሮቹ ስም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ይሰጣል፡፡ በዝርዝሩ ውስጥ ከተመለከቱት ጋር እንዲዛመድ በማድረግ ይቆጠራል፡፡ ወይም ከዝርዝሩ ውጭ ከሆነም የብሔሩ ስም ይገለጻል፡፡ ካልሆነም “ሌሎች” በሚል ጥቅል ምድብ ውስጥ ይካተታል፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውስጥ ውክልና ያላቸውን በዝርዝሩ ውስጥ እንደሚካተቱ ይጠበቃል፡፡ ምክር ቤቱ ከስድሳ ሰባት ጀምሮ አሁን ሰባ ሰባት ብሔሮች ላይ ደርሷል፡፡ በ1987ቱ የቤት ቆጠራ ወቅት በኢትዮጵያ 84 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ነበሩ፡፡ በ1999ኙ ደግሞ 85 ሲሆኑ፣ በ1987ቱ ከነበሩት አምስቱ ይቀሩና ሌሎች ስድስት ተጨምረዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነቱ አቆጣጠር ግጭት የማስነሳት ዕድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡ ለእዚህ ደግሞ የቅማንት ጉዳይ ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡ ዝርዝሩን እንመለስበታለን፡፡
በኢትዮጵያ የግለሰቡን የብሔር ማንነት የሚወሰንው የሚቆጠረው ሰው ወይም መረጃውን የሚሰጠው ነው ማለት ነው፡፡ በመሆኑም የግለሰቡን ብሔር ለመለየት የአፍ መፍቻ ቋንቋ ጥቅም ላይ አይውልም፡፡ የአፍ መፍቻ ቋንቋ የብቻው ይቆጠራል፡፡ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ማለት ደግሞ አንድ ሕፃን ከእናቱ ጋር የሚግባባበት ወይም አፉን የፈታበት ሳይሆን ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር የሚግባቡበት፣ በቤት ውስጥ ለመግባባት የሚጠቀሙበት ቋንቋ እንደሆነ ተተርጉሟል፡፡
ሌላው ሃይማኖትን የሚመለከት ነው፡፡ የ1987ቱና የ1999ኙ ቆጠራ ላይ ሃይማኖትን በሚመለከት ስድስት ምድቦች አሉ፡፡ ኦርቶዶክስ (ተዋህዶ፣ ቅባትና ጸጋ)፣ ካቶሊክ፣ ፕሮቴስታንት፣ እስልምና ትውፊታዊና ሌሎች የሚል፡፡ ጆሆቫ፣ ባሃሁላ በሌሎች ሥር ይካተታሉ፡፡
የብሔርና የሃይማኖት ማንነት ከላይ በተገለጹት መንገድ እንዲለይ ይደረጋል ማለት ነው፡፡ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ዕውቅና ያልተሰጣቸው ነገር በቆጠራው ውጤት የተገለጸ ወይም ቀድሞ በነበረው ላይ ተገልጾ በሚቀጥለው ላይ አለመኖር ግጭት ሊያስነሳ እንደሚችል ዕሙን ነው፡፡
በ1987ቱ ቆጠራ ወቅት የቅማንት ሕዝብ ብዛት 172,327 የነበረ ሲሆን፣ በ1999ኙ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሪፖርቱ ላይ ግን ስሙ አልተነሳም፡፡ በዚህ ባለፈም የሁለቱን ቆጠራ ውጤት ስናጤን በአሥራ ሁለት ዓመታት ልዩነት አምስት ጠፍተው ስድስት መጨመራቸውን ሲሆን፣ በተለይ የቅማንት ደግሞ ይኼን ያህል ቁጥር ኖሮት አለመካተቱ የበለጠ ይገርማል፡፡
በ1999ኙ ሕዝብና ቤት ቆጠራ ሪፖርት መሠረት ቢያንስ ከአማራ ክልል ሁለት፣ ከኦሮሚያም ሁለት ብሔረሰቦች ሲቀነሱ፣ ደቡብ ክልል ላይ ደግሞ ተጨምረዋል፡፡ እንደዚህ ዓይነት ድርጊቶች የተፈጸሙት በድንገት ወይንም በቸልተኝነት ወይንም ሆን ተብሎ ይሁንም አይሁንም ያልታሰበ ችግር ሊያከትሉ እንደሚችሉ መታወቅ አለበት፡፡ የብሔረሰቦችንም ግንኙነት በእጅጉ ያሻክራል፡፡
የ1999ኙ የስታትስቲክስ ሪፖርት የአማራ ክልል ሕዝብን በተመለከተ ያስነሳውን ጭቅጭቅ እናስታውሳለን፡፡ በ1987ቱ ቆጠራ ከአገሪቱ አጠቃላይ ሕዝብ 25.9% የያዘ ሲሆን፣ በ1999ኙ ግን ቀንሶ 23.3% ሆነ፡፡ በተጨማሪም ዓመታዊ ዕድገት ምጣኔው 1.7 መሆኑ ውጤቱ ያሳያል፡፡ የአገሪቱ አማካይ ምጣኔውም 2.1፣ የአፋር 2.2 እና ከፍተኛው የጋምቤላ 4.1 ነበር፡፡ ኋላ ላይ ዓመታዊ የዕድገት ምጣኔው ተስተካክሎ ከፍ ማለቱን ያስታውሷል፡፡
የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ዓመታዊ የፌዴራል የበጀት ድጎማ ላይም ከፍተኛ አንድምታ ይኖረዋል፡፡ ከእዚህ አንፃር የ2007 ዓ.ም. በጀት ሲጸድቅ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለበጀት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የተሻሻለውን አማካይ ምጣኔ ታሳቢ ተደርጎ የድጎማ በጀት ድልድል መዘጋጀት እንደነበረበትና በስህተቱ ምክንያት የክልሉ ሕዝብ በነፍስ ወከፍ ሊያገኝ ይችል የነበረው ድጎማ ስለቀረበት ይህም መስተካከል እንደነበር ጥያቄ ቀርቦ እንደነበር በመገናኛ ብዙኃን ተገልጿል፡፡
የበጀት ድጎማ ሲደረግ አንዱ መስፈርት የሕዝብ ቁጥር ነው፡፡ ለምሳሌ በ1987 የበጀት ዓመት ለድጎማ መለኪያ የነበሩት በመቶኛ ሲገለጹ ለክልሎቹ ሕዝብ ብዛት 30፣ ከማዕከል ለሚኖር ርቀት 25፣ ገቢ ለማመንጨት አቅም 20፣ ከዓመት በፊት ለልማት ለተመደበው የበጀት ዓመት 15 እና ለክልሉ የቆዳ ስፋት አሥር ነጥቦች ተሰጥተውት ነበር፡፡ በ1988 የበጀት ዓመት ደግሞ ከላይ የነበሩት መነሻዎች ቀርተው ሦስት ነገሮችን በመውሰድ እኩል 33.3 ከመቶ ነጥብ ተሰጣቸው፡፡ እነዚህም የሕዝብ ብዛት፣ ክልሉ ያለበት የዕድገት ደረጃና በ1987 የበጀት ዓመት የሰበሰቡት የገቢ መጠን ናቸው፡፡
በሚቀጥለው ዓመት ደግሞ መስፈርቶቹ አሁንም ሦስት ሲሆኑ፣ ለሕዝብ ብዛት 60 ከመቶ፣ በልማት ላሉበት ደረጃ 25 ከመቶ እንዲሁም ላላቸው ገቢ የማመንጨት አቅም 15 ከመቶ ነጥብ ተሰጠ፡፡ ከእነዚህ የምንረዳው የሕዝብ ብዛት ለበጀት ድጎማ ጉልህ ድርሻ ያለው መሆኑን ነው፡፡
ለማጠቃለል የሕዝብ ቆጠራ ውጤት ለብዙ ውሳኔዎች በግብዓትነት እንደሚውል የታወቀ ነው፡፡ ቆጠራው በአግባቡና በጥንቃቄ እንዲሁም በገለልተኝነት መመራት ያለበት መሆኑን ነው፡፡ በእርግጥ ሕገ መንግሥቱ ስለኮሚሽኑ ገለልተኝነት ዝምታን መርጧል፡፡ በተግባርም የኮሚሽኑ አባላት ጥንቅርም ገለልተኝነቱን አይመሰክርም፡፡ የሆነው ሆኑ በርካታ ብሔሮችና ሃይማኖቶች በሚገኝባት አገራችን የሕዝብ ቆጠራ ከፍተኛ ጥንቃቄን የሚጠይቅ ተግባር ነው፡፡ አሳሳቢነቱን ደግሞ የቅማንት ማኅበረሰብም ሆነ የአማራ ጥሩ ማሳያ ናቸው፡፡ በተለይ ደግሞ የቆጠራው ውጤት ተአማኒነት ያለው መሆኑ ወሳኝ ነው፡፡ እንደ ሌሎች አገሮች ከሕዝብ ቆጠራ ጋር የሚያያዙ አለመግባባቶች እንዴት መፈታት እንዳለባቸው ግልጽ አሠራር ካለመኖሩ አኳያ ከፍተኛ ጥንቃቄን ይጠይቃል፡፡
አዘጋጁ፡- ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡