Tuesday, February 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅበኢትዮጵያ ዳንጐቴ የሲሚንቶ ፋብሪካ በላቦራቶሪ ውስጥ የሚሠራ ሮቦት

በኢትዮጵያ ዳንጐቴ የሲሚንቶ ፋብሪካ በላቦራቶሪ ውስጥ የሚሠራ ሮቦት

ቀን:

ሥጋ ብቻ ለሰው

      …… ከንፈረ ፍሕሶ፣ አባሌሎም ፀጉር፣

      ዐይነ ባትሪዬቱ፣ የጥርስሽ ማማር፣

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ነፀብራቅ ፈገግታ፣ የአልማዝ መደብር፡፡

አካሄደ ቆንጆ ስዕላዊ ቅርጽ፣

እንዲያው አካላትሽ፣ …

      ሳያውቁት፣ ሳያውቁሽ፣

            የሚያስደነግጥ፣

የተቀኘ አዕምሮን ያለፋል ውበትሽ፣

አቤት ግሩም አንቺ፣ ምን ይሆን ፍጥረትሽ!

            ብዬ የነበርኩኝ፣…

የውበትሽ አድናቆት በቁሜ ጠምቆኝ፣

እጆችሽን ይዤ ጎርፍ ቢወስደኝ፣

እንዲህ ነው አዱኛ፣

ይህ ነው መንገደኛ፣

ይቃናል ጉዞው!

            …. ብዬ የፀለይኩኝ፣…

ዛሬ ለመመለስ መጣሬን አይተሽ፣

ምን አጠፋሁ ስትይ እቱ አይጭነቅሽ፣

በማዕበሉ መሀል ለዕጣሽ ስተውሽ፡፡

ያ ሌላኛው ውበት ተደብቆ ኖሮ፣

ባውቀው አሳፈረኝ፡፡

በቃ፣ ደህና ሁኝ፣

ከቶ አታስታውሽኝ፣

ምድረ በዳ አንጎልሽ፣ ግዑዝ ነው ደንቆሮ!

ሥጋ ብቻ ሰውን፣ አይችል ሊያቆይ አሥሮ!

            አይችል ሊያቆይ አሥሮ

  • ደበበ ሰይፉ ‹‹ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ›› (1992)

****************

አባባል

የፈረንሳይ ተወላጅ የሆነ አንድ አዋቂ እንዲህ አለ፡፡ ቃል ለሰው የተሰጠው ሐሳቡን ሊገልጥበት ነው ይባላል፡፡ ይህ ግን ሐሰት ነው፤ ቃልስ ለሰው ልጅ የተሰጠው ሐሳቡን እንዲሸፍንበት ነው፡፡

*****************

አንድ ትልቅ ሊቅ ስለ ስንፍና መጥፎነት ሲናገር እንዲህ አለ፡፡ ማናቸውንም ዓይነት ጥፋት ያጠፋ ሰው ሁሉ ይቅርታ ቢደረግለት የተገባ ነው፡፡ ምሕረት ሊደረግለት የማይገባው አንድ ብቻ አለ እሱም ሰነፍ ሰው ነው፡፡

*****************

ከጥንት ጀምሮ ሲነገር የሚኖር አንድ የላቲን ተረት እንዲህ ይላል፡፡ ጦርነት እንዳይመጣብህ ብትፈልግ ሁልጊዜ ለጦርነት የተሰናዳህ ሆነህ መቀመጥ ይገባሃል፡፡

*****************

በጌታና በድሃ ሰው መካከል የሚገኘው ልዩነት በጣም የተራራቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጌትነትና ድህነት ጎን ለጎን ሲሄዱ ይኖራሉ፡፡

*********************

የሰው ሙያ ሦስት ዓይነት ነው፡፡ አንደኛው ማሰብን ማወቅ፣ ሁለተኛው መናገርን ማወቅ፣ ሦስተኛው መሥራትን ማወቅ፣ አብዛኞቹ ብልህ የሚባሉ ሰዎች ከእነዚህ ከሦስቱ አንደኛውን ብቻ ነው የሚይዙት ወይም መሥራት ያውቁና ትክክል ማሰብ አይችሉም ይሆናል፡፡ ስለዚህ ትክክል ካለማሰባቸው የተነሳ ደክመው የሠሩት ሥራ ሁሉ ይፈርሳል፡፡ ወይም ደግሞ ንግግር አሳማሪዎች ሐሳባቸው ብላሽ ይሆናል፡፡ ትክክል አስቦ ያሰበውን ትክክል አድርጎ በቃል፤ ወይም በጽሑፍ አስረድቶ እንዳሰበውና እንደተናገረውም አድርጎ ትክክለኛ የሚሠራ ሰው እውነት ትልቅ አዋቂ ነው ሊባል ይችላል፡፡

******************

ሥራና ሠሪው

በዓለም ላይ ትልቅ ሥራ ለመሥራት የሚቻለው ሠሪው ሰውና ለመሥራት የተመቸበት ጊዜ እነዚህ ሁለቱ ሲገናኙ ነው፡፡ ትልቁን ሥራ ለመሥራት የሚችለው ሰው ባልተመቸ ጊዜ ሲፈጠር ሊሠራው የሚችለውን ሥራ ሳይሠራው መቅረት ግድ ይሆንበታል፡፡ ልሥራም ቢል ጊዜው አይደለምና አይሆንለትም፡፡ ትልቅ ሥራ ለመሥራት የተመቸ በሆነበት ጊዜ ደግሞ ሊሠራው የሚችል ሰው ባለመፈጠሩ መልካሙ ጊዜ በከንቱ ያልፋል፡፡ እነዚህም ሁለቱ ተፈላላጊ ነገሮች የሚገናኙት በብዙ ዘመን ውስጥ ጥቂት ጊዜ ነው፡፡

– ከበደ ሚካኤል ‹‹ታሪክና ምሳሌ›› (1999)

*******

ቀበሮውና ሚዛኑ

ከብዙ ዓመታት በፊት ሁለት ጦጣዎች አብረው ይኖሩ ነበር፡፡ ታዲያ አንድ ቀን ምግብ ፍለጋ ወጥተው የሚበሉት ነገር አገኙ፡፡

ሆኖም በምግቡ ላይ መጣላት ጀመሩ፡፡

ስለዚህ ‹‹ወደ ቀበሮው ዘንድ ሄደን እርሱ ይገላግለን፡፡›› ብለው ወደ ቀበሮው ሄዱ፡፡ ቀበሮውም ጉዳዩን በጥሞና ካዳመጠ በኋላ ‹‹ምግቡን ሁለት እኩል ቦታ ማካፈል ስላለብኝ ሚዛን መጠቀም አለብኝ፡፡ ነገር ግን አሁን ሚዛን በእጄ የለም፡፡ ዛሬ ጠዋት ሚዛኑን ለአንበሳው ስላዋስኩት ወደ አንበሳው ሄደን ምግቡን እናካፍለው፡፡›› አለ፡፡

እንደደረሱም ቀበሮው አንበሳውን ተጣርቶ ጉዳዩን ነገረው፡፡ እንዲህም አለው ‹‹አንበሳ ሆይ! እነዚህን ጦጣዎች አስታርቃቸው፡፡›› ይህንንም ብሎ ቀበሮው ወደ አንበሳው ዋሻ ሳይገባ ተመልሶ ሄደ፡፡ ጦጣዎቹም የተውትን ምግብ አንስቶ ራሱ በላው፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለም ሁለቱ ጦጣዎች ችግራቸውን ለአንበሳው መንገር ጀመሩ፡፡ ነገር ግን አንበሳው እነርሱን መብላት አንጂ መዳኘት አልፈለገም ነበርና በላቸው፡፡

  • በዩሱፍ አድም ማንደሬ የተተረከ የሶማሌ ተረት

**********

ከመቀፍቀፋቸው በፊት የሚነጋገሩት የናይል አዞዎች

የለንደኑ  ታይምስ እንደዘገበው ‹‹አዞዎች ገና በእንቁላል ውስጥ እንዳሉ እርስ በርሳቸው በመነጋገር›› በተመሳሳይ ጊዜ ይቀፈቀፋሉ። ተመራማሪዎች የናይል አዞዎች ከእንቁላላቸው ከመቀፍቀፋቸው በፊት የሚያሰሙትን ድምፅ ከቀረጹ በኋላ አንድ ላይ ያሉ ሌሎች የአዞ እንቁላሎች ይህን ድምፅ እንዲሰሙት አደረጉ። በዚህ ጊዜ በእንቁላሎቹ ውስጥ ያሉት ያልተቀፈቀፉ አዞዎች ለጥሪው ምላሽ የሰጡ ከመሆኑም ሌላ ይህን ድምፅ ካልሰሙት ሌሎች እንቁላሎች ይበልጥ ይንቀሳቀሱ ነበር። ‹‹ያልተቀፈቀፉ አዞዎች ያሰሙትን ድምፅ የሰሙት ሌሎች አዞዎች በሙሉ በአሥር ደቂቃ ውስጥ እንደተቀፈቀፉ›› ዘገባው ይገልጻል። ምንም ድምፅ ያልሰሙት ወይም ሌላ ዓይነት ድምፅ እንዲሰሙ የተደረጉት እንቁላሎች ግን በተመሳሳይ ጊዜ አልተቀፈቀፉም።

ንቁ! (2009)

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመጣንበትና አብረን የምንዘልቅበት የጋራ እሴታችን ለመሆኑ ነጋሪ ያስፈልጋል ወይ?

በኑረዲን አብራር በአገራችን ለለውጥ የተደረጉ ትግሎች ከመብዛታቸው የተነሳ ሰላም የነበረበት...

አልባሌ ልሂቃንና ፖለቲከኞች

በበቀለ ሹሜ በ2016 ዓ.ም. ኅዳር ማክተሚያ ላይ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ...

አሜሪካ የኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ተገቢነት ቢኖረውም ከጎረቤት አገሮች ጋር በሚደረግ ንግግር መሆን አለበት አለች

መንግሥትን ከፋኖና ከኦነግ ሸኔ ጋር ለማነጋገር ፍላጎቷን ገልጻለች የኢትዮጵያ የባህር...