Sunday, April 14, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

መሠረታዊ ዓላማውን የሳተው የአሥረኛው ዙር የኮንዶሚኒየም ቤቶች የክፍያ ተመን አሉታዊ ተፅዕኖና የመፍትሔ አቅጣጫ

በበለጠ ነ.

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሴንተር ፎር ሒዩማን ሴትልመንት እ.ኤ.አ. ከሰኔ 3 አስከ 14 ቀን 1996 በቱርክ ኢስታንቡል ከተማ በተካሄደ ስብሰባ፣ የኢስታንቡል ዲክላሬሽን በመባል በሚታወቀው መግለጫ ውስጥ ቤት አልባ የሆኑ የየአገሮችን ሕዝቦች ችግር ለማቃለል እንዴት እንደሚቻል፣ ወጪ ቆጣቢ የሆኑ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት የቤት ባለቤት የማድረጊያ የውሳኔ ሐሳቦች ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡ ይህንንም መሠረት በማድረግ በኢትዮጵያ የአዲስ አበባ አስተዳደርና የክልል ከተማ አስተዳደሮች በከተሞቻቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶችን በመገንባት፣ በዕጣና በተለያዩ መንገዶች የማስተላለፍ ሥራ ሲሠሩ መቆየታቸው የሚታወቅ ነው፡፡

እነዚህ ተገንብተው የተላለፉና በመተላለፍ ላይ ያሉ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የተለያዩ ችግሮች ያሉባቸው መሆኑ አሌ የሚባል ባይሆንም ቤት አልባ ዜጎችን ከኪራይ በማላቀቅና ባለቤት በማድረግ ከነችግሮቻቸውና አድሎአዊ አሠራራቸው ጋርም ቢሆን መሠረታዊ ዓላማቸውን እንዳልሳቱ ይታወቃል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም በዚህ መነሻነት በ1997 ዓ.ም 450 ሺህ የሚጠጉ የከተማውን ቤት አልባ ኗሪዎች በመመዝገብና የተገነቡ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን እስከ ዘጠነኛ ዙር ድረስ ማስተላለፉ፣ እያስተላለፈና በማስተላለፍ ሒደት ላይ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በ2005 ዓ.ም እንደገና የቤት ፈላጊውን ነዋሪ አቅምና ፍላጎት መሠረት ያደረገ አዳዲስ ተመዝጋቢዎችንና ዳግም የሚመዘገቡ የ1997 ዓ.ም ተመዝጋቢዎችን በተለያየ ደረጃ በመመዝገብ የቁጠባ መጠን ወስኖ ላለፉት 16 ወራት በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ተመዝጋቢ የመኖሪያ ቤት ፈላጊዎች እየቆጠቡ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡

በቅርቡም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ10/90 እና በ20/80 (ነባር) ለ16 ወራት የቆጠቡ የከተማው ነዋሪዎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ወደ 35,000 ለሚጠጉ ቤት ፈላጊዎች ዕጣ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡ እስከዚህ ጊዜ ያለው ሒደት ከሞላ ጎደል ጥሩ ቢሆንም፣ ከዕጣው ማውጣት በኋላ በቤቶች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ በባለቀለም ብሮሸር ተባዝቶ የተሰራጨውና በሚያዝያ 8 ቀን 2007 ዓ.ም የአዲስ አበባ መስተዳደር ባለሥልጣናት በተገኙበት የአሥረኛ ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች የክፍያ ተመን (በቅድሚያ የሚከፈለውና በየወሩ ለባንክ የሚከፈለው የብድር ተመላሽ ክፍያ) ላይ፣ ከቤቶች ልማት ኃላፊዎች የተሰጠው ምላሽ የሚያሳዝንና የሚያሳፍር ነበር፡፡   

በባንክ የሚቆጠበው የቁጠባ መጠንና የቤቶቹ የክፍያ መጠን በምን መሠረት ላይ ሊወሰን ቻለ?

እያንዳንዱ የመኖሪያ ቤት ፈላጊ አቅሙንና ፍላጎቱን በማገናዘብ በ10/90፣ በ20/80 (አዲስ)፣ በ20/80 (ነባር) እና በ40/60 ሥርዓት ተመዝግቦና የተተመነለትን መጠን ላለፉት አንድ ዓመት ተኩል ለአሥረኛ ዙርና ቀጥሎም ላለው ዙር እየቆጠበ ይገኛል፡፡ በመሀል መቆጠብ ባለመቻልና በሌሎች ምክንያቶች ውላቸውን ያቋረጡ መሆኑ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡

የቤቶች ልማት ኤጀንሲ የተመዝጋቢዎቹን የቁጠባ መጠን ሲተምን መሠረት ያደረገበት መነሻ (Benchmark) ይኖረዋል፡፡ ከተሰጠው ተመን አንፃር ሲታይ የተመዝጋቢውን የመክፈል አቅም (ካለበት ቤት ኪራይ፣ የቀለብ ወጪ፣ የተማሪዎች የትምህርት ክፍያና ሌሎች ያልተገለጹ ወጪዎችን) ግንዛቤ በማድረግ ነው ብል የተሳሳትኩ አይመስልም፡፡ ይህንን የቁጠባ መጠን የወሰነ አካል ቁጠባን ብቻ ግብ ያደረገ ውሳኔ አስተላልፎ ከሆነ በስህተት የተጀመረ ፕሮጀክት ነው ማለት ይቻላል፡፡ የቁጠባው ዓላማ ከዕጣ በኋላም መጨናነቅ ሳይፈጠር አንደኛ የመጀመሪያውን ክፍያ ጫና ሳይኖርበት እንዲከፍል ሁለተኛ ከዕጣ በኋላ ወርኃዊ የባንክ ዕዳ ተመላሽ ክፍያ ሳይሰማው ደኅንነቱ ተጠብቆ እንዲኖር ነው፡፡ ከዚሁ ጎን መታወቅ ያለበት ይህንን ቁጠባ ለመክፈል የሚያንገዳግዳቸው አያሌ ዜጎች እንደነበሩ ያቋረጡትን አኃዝ በየቅርንጫፍ ባንኮቹ መመልከት ይቻላል፡፡ ይህ ብዙ ምርምር የሚጠይቅ ነገር ሳይሆን፣ ያለው የኑሮ ፈተና በሁሉም ጓዳ ያለ እውነታ ነው፡፡

በአሥረኛ ዙር ላይ የቀረበ የቤቶች የክፍያ ተመን ሲወሰን የትናንቱን የቁጠባ መጠን ወደ ጎን ያደረገ፣ የደሃውን (በዛሬይቱ ኢትዮጵያ ሁለት ማኅበራዊ ደረጃዎች ያለውና የሌለው ሲሆኑ፣ መካከለኛ ክፍል የሚባለው ወደ የሌለው ጎራ ከተቀላቀለ ሰነባብቷል) ባለዕጣ የቤት ባለቤትነት መና ያስቀረ፣ የዜጎችን የቤት ባለቤትነት መሠረታዊ መብት (The Right to Housing) የደፈጠጠና የቤቶች ልማት የነበረበትን የኮንስትራክሽን አመራር ግድፈትና ጥፋት በመሸፈን በራሱ ድክመት የባከነውን ገንዘብ  በደሃው ሕዝብ ላይ በመጣል ለማካካስ የታሰበ መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ ለዚህ የተሳሳተ ውሳኔና አፈጻጸም የአዲስ አበባ መስተዳደር በጥቅሉና የአዲስ አበባ ቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮና ሌሎች በተዋረድ ያሉ ጽሕፈት ቤቶች በተናጠል ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑን የሚያመለክት ነው፡፡ 

የቤቶች ልማት የሥራ መሪዎች ኃላፊነት የጎደለው ምላሽ

ሚያዚያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም ታትሞ በወጣው ሪፖርተር ጋዜጣ “በኮንዶሚኒየም ቤቶች ዋጋ ጭማሪ የአስተዳደሩ ከፍተኛ ሹማምንት ጥያቄ ማንሳታቸው ተጠቆመ” በሚል ርዕስ ላይ የቀረበው ዘገባ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ በብዙኃኑ ባለዕጣዎች ላይ የራሱ የሆነ ተፅዕኖ የሚያስከትል መሆኑ ልብ ሊባል ይገባዋል፡፡ የመስተዳደሩ ሹማምንት ለቤቶች ልማት ኃላፊዎች እንዲብራራላቸው ያነሱት ጥያቄ “… አብዛኛውና ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ የግንባታ ግብዓቶች ከአገር ውስጥ መግዛት ተችሏል፡፡ የግንባታ ዋጋ ቀንሶ እያለ በኮንዶሚኒየም ቤቶች ላይ ዋጋ ሊጨመር የቻለበትን ምክንያት ምን እንደሆነ እንዲብራራላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን”፣ እንዲሁም “በጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ መነሻ ግንባታውን ተከታትሎ የሚያስፈጽመው የቤቶች ልማትና ኮንሰትራክሽን ቢሮ ሥር የሚገኙ መሥሪያ ቤቶች የማኔጅመንት ችግር እንጂ የገበያ ጉዳይ አለመሆኑን ምንጮች ገልጸዋል” በሚል ሪፖርተር መዘገቡ ይታወቃል፡፡

ለቀረበው የአስረዱን ጥያቄ ምላሹ ደካማና በአግባቡ ማስረጃ ሊቀርብ እንዳልተቻለ ተገልጿል፡፡ ከዚህ የምንረዳው በቤቶች ልማትና ኮንስትራክሽን ቢሮ ሥር የሚገኙ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡና ከአቅም ችግር እስከ ሙስና ድረስ የተተበተበ አሠራር እንደነበረባቸው የሚያመለክት ነው፡፡

በወቅቱ በተካሄደው ስብሰባ የአዲስ አበባ ከተማ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ ከመስተዳድሩ የሥራ ኃላፊዎች ጋር የነበረውን ስብሰባ ያስረዱበት መንገድ እጅግ የሚያስገርምና ሕዝብን ለማስተዳደር የተሰየሙ መሆናቸውን የዘነጉ ይመስላል፡፡ ከቀረቡት ጥቂቶቹ “የቤቶቹ ዋጋ የሕዝቡን የመክፈል አቅም ያገናዘበ ነው” የሚል ነበር፡፡ ተመዝጋቢው የመክፈል አቅም ካለው ለምን በቁጠባ ትመና ወቅት ከመክፈል አቅሙ ጋር የተገናዘበ መጠን አልተወሰነም? የሕዝቡን የመክፈል አቅም በምን መለኪያ ሊያውቁት ቻሉ? ከቤት ኪራይና ከኑሮ ውድነት ጋር የሚታገለውንና ቁጠባውን እንኳ ለመቀጠል እየተንገዳገደ ያለውን ተመዝጋቢ ለመክፈል አቅም አለው ማለት ሹፈት ይመስላል፡፡ በምዝበራ የበለፀገውን ክፍል ከሆነ ትክክል ናቸው፡፡ ነገር ግን ከራሱ ደመወዝ ውጪ ሌላ ገቢ የሌለው የኅብረተሰብ ክፍልን የሚመለከት ከሆነ ማገናዘብ የጎደለው ድምዳሜ ነው፡፡ 

ዕጣው በመውጣቱ “… አብዛኞቹ የተደሰቱ …” ናቸው፣ የሚለው ዕጣ ሲደርስ መደሰትና ለቤቶቹ የሚከፈለው ዋጋ ተመን ሲገለጽ መደሰት የተለያዩ ናቸው፡፡ ተፈጥሮአዊ በመሆኑ ከተወዳዳሪዎች መሀል የዕጣ አሸናፊ መሆን ያስደሰታል፡፡ ሆኖም ይህ ደስታ ዘላቂ የሚሆነው ከዜጎች የመክፈል አቅም ጋር የተገናዘበ ተመን ሲወጣ ነው፡፡ የወጣው ተመን ደስታን የሚጨምር ሳይሆን ወደ ሐዘንና ተስፋ ወደ መቁረጥ ደረጃ ሊያስገባ ችሏል፡፡ ወደ አዲስ አበባ ቤቶች አስተዳደር ኤጀንሲ በየቀኑ የሚጎርፉት አቤቱታ አቅራቢዎች መበራከትና የአዲስ አበባ አስተዳደር ከፍተኛ ሹማምንት በአሥረኛው ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዙሪያ የጠሩት ስብሰባ፣ የጉዳዩን አሳሳቢነትና ዘላቂ ደስታ የፈጠረ አለመሆኑን አመላካች ናቸው፡፡

ሌላው አስደናቂውና አስገራሚው “ጥቂቶች ድጎማ ተደርጎላቸውም መክፈል ስለማይችሉ እነሱ ምክንያት ተደርገው ብዙ ሊባል ቢቻልም እውነታው ግን የተገላቢጦሽ መሆኑን …” ያሳያል፣ “… በነፃ በመገንባት ማስረከብ ካልሆነ በስተቀር…” የሚሉት ሐሳቦች በከፍተኛ ኃላፊነት ያለ ሰው ሊለው የማይገባ ነው፡፡ ድጎማ ቢደረግላቸውም መክፈል ስለማይችሉ ያሏቸውን የእነዚህን ዜጎች ጉዳይ መንግሥት የመፍታት ኃላፊነት አለበት፡፡ መንግሥት በነፃ ወይም በተመጣጣኝ ክፍያ ገንብቶ ደሃውን የኅብረተሰብ ክፍል የመኖሪያ ቤት ባለቤት ቢያደርግ የሚያስመሰግን እንጂ የሚያስወቅስ አይደለም፡፡ ሥልጣንና አመቺ ሁኔታ የፈቀደላቸው ሀብት በአደባባይ የሚዘርፉ ሰዎች ያሉባት አገር አይደለችም፡፡ ከገቢው ውጪ ምንም ሀብት የሌለው የዚች አገር ዋልታ፣ መከታና ጠበቃ የሆነው ደሃው የኅብረተሰብ ክፍል የቤት ባለቤት ቢሆን ምን ችግር አለው? አገራችን ካለባት ዘርፈ ብዙ ችግሮች አንፃር ተመጣጣኝ የሆነ ነገር ግን በረጅም ጊዜ ተከፍሎ በሚያልቅ ሥርዓት የቤት ባለቤት ማድረግ ሁሉንም ያስማማል ብዬ አምናለሁ፡፡

በንድፈ ሐሳብ ደረጃ በተመጣጣኝ የክፍያ ሥርዓት የቤት ባለቤት ይደረግ ቢባልም፣ በተግባር ግን እየሆነ ያለው በአሥረኛው ዙር ለባለዕድለኞች ዕጣ በወጣላቸው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ገቢያቸው ዝቅ ላለውም ሆነ ‘የተሻለ’ ነው ለሚባሉትም የቤት ባለቤትነታቸውን ተስፋ ለዘለዓለሙ ያጨለመ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ በዕጣው የሚጠበቅበትን ክፍያ ያልከፈለ ዕድሉን አልተጠቀምክበትም (አልተጠቀምሽብትም) ተብለው የሚሰረዙ ስለሆነ፣ የቤት አልባው ኗሪ ቁጥር እያሻቀበ (Mounting Number of Homeless People) እና በተጓዳኝ የተከራይ ቁጥር (Rise of Tenants) በዚያው ልክ እየተለጠጠ ይሄዳል፡፡

በሪፖርተር ጋዜጣ የመጋቢት 27 እና ሚያዝያ 18 ዕትሞች ‘እኔ የምለው’ በሚለው ዓምድ ላይ የወጡ መጣጥፎች የችግሩን ስፋትና በቤት ልማት ሥራ ላይ ያለውን የተዝረከረከ አሠራር በግልጽ ያስቀመጡ ናቸው፡፡ የቤቶች ልማት ሥራ የጥራት፣ የሥነ ምግባር፣ የአስፈጻሚዎችና የፈጻሚዎች አቅም የወረደ መሆኑ በተለያዩ ጊዜያት የቀረቡ ጥናቶች አመላክተዋል፡፡ ሌላው ዝርክርክና ለምዝበራ የተጋለጠ አሠራር መሆኑን ከሚያመላክቱት ጥቂቶቹ፣

 • ደካማ የሥራ አፈጻጸም ያላቸውን የጋራ መኖሪያ ቤቶች ተቋራጮች በጥቅም ትስስር ላይ በተመሠረተ የአሠራር ሥርዓት አዲስ ሥራ በመስጠት፣ ከደረጃ በታች እንዲሠሩ በማስደረግ ለደሃው ኅብረተሰብ የነገ ዕዳ ያስቀምጡለታል፡፡
 • የሥራ ጥራት የሚቆጣጠሩ (ይህ ከመኖሪያ ቤት ግንባታ በተጨማሪ በመንገድ ሥራ፣ በተቋም ግንባታ …) አማካሪ መሐንዲሶች ሥራውን የሚያዩት እነሱ ከሚያገኙት ጥቅምና ድርሻ አንፃር በመሆኑ አሁንም ለደሃው ዕዳ ያከማቹለታል፡፡ 
 • በማኅበራት  የተደራጁትም የግንባታ ግብዓት ሲያቀርቡ የደረሰውና የተላከው ቁጥር የተለያየ እየሆነ በተላከው ቁጥር ይመዘገብላቸዋል፡፡ ይህንን ከድግግሞሽና ከሚሠራው ሥራ መጠን አንፃር ስታዩት የትየለሌ ነው፡፡ አሁንም ለደሃው ዕዳ ይቆልሉለታል፡፡

እነዚህና ሌሎች ያልተጠቀሱ ችግሮች ተንከባልለው በቤቶች ዋጋ ትመና ላይ ያስከተሉት ውጤት በተግባር ሊታይ ችሏል፡፡ ቀጥለን በአጠቃላይ ከደሃው ኅብረተሰብ አቅም በላይ የቀረበው የቤቶች ዋጋ የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች በጥቂቱ እንመልከት፡፡

የሚያስከትለው ተፅዕኖ

የቤት ፈላጊውን አቅምና ችግር ያላገናዘበ የቤት ክፍያ ዋጋ መሠረታዊ ማሻሻያ ካልተደረገበት የሚያስከትላቸው አሉታዊ ተፅዕኖዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

 1. ወደ ቤት ፈላጊነት ጎራ ከሚቀላቀለው ቤት ፈላጊ  በተጨማሪ መፍትሔ በማጣት ዕድሉ የተሰረዘበት ተመዝጋቢ (ለምሳሌ አሥረኛ ዙር) በቤት ማጣት የሚንገላታውን ነዋሪ ቁጥር እንዲያሻቅብ ያደርገዋል፡፡
 2. በዝቅተኛ ገቢ የሚኖሩ ዜጎች በየቀኑ እያደገ ያለውን የቤት ኪራይ ለመጋፈጥ አቅሙ ስለማይኖራቸው በክፍት ቦታዎች ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የላስቲክ ቤቶችን (Squatter Settlements) በመቀለስ ኑሮን የማይገፉበት ምክንያት የለም፡፡ ልከራይ ተብሎ ቢሞከር ዝቅ ያለ ኪራይ ፍለጋ ወደ ከተማ ዳርቻ መባዘንና ተረጋግቶ ለመኖር ወዳለመቻል ሊያመራ ይችላል፡፡   
 3. የዚሁ ቤት አልባ ወላጆች ልጆች የተረጋጋ ትምህርት መማር ያለመቻል ምልክቶቹ እየታዩ ነው፡፡ የወደፊቱ የአገር ተረካቢዎች በትምህርታቸው ተግተው እንዳይማሩ በመደረጉ ለአገር ጠቃሚ ከመሆን ወደ ሸክምነት መቀየር፣ ለአላስፈላጊ ሱሶች መጋለጥ፣ ወደ ወንጀል ሥራ መግባት፣ ለጥቃት መጋለጥና የመሳሰሉ ችግሮችን እንዲጋፈጡ ይሆናሉ፡፡ 
 4. በአሥረኛ ዙር ያልደረሳቸው ዕጣቸውን የሚጠብቁ የ10/90፣ የ20/80 (አዲስ)፣ የ20/80 (ነባር) እና የ40/60 አሁን ጨምሮ በመጣው የጋራ መኖሪያ ቤቶች ዋጋ ምክንያት በምን ተስፋ ነው በትጋት ቆጥበው ሊጠብቁ የሚችሉት? በዚህ ውሳኔ እንዴት ነገን ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ? 

የመፍትሔው መንገድ

 1. በዚህ ችግር ዕጣ ደርሶህ ካልከፈልክ የራስህ ጉዳይ ነው ተብሎ በጥሎ ማለፍ መልክ የሚታይ አይደለም፡፡ ዜጎች መኖሪያ ቤት የማግኘት መብት አላቸው፡፡ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ (Social Housing) ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ስለሆነ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርም ሆነ መንግሥት ሊያጤኑትና ተግተው መፍትሔ ሊፈልጉለት ይገባል፡፡
 2. የጋራ መኖሪያ ቤቶቹ የወጣባቸው ትክክለኛ ወጪ (ጥሬ ዕቃዎቹ ከአገር ውስጥ መቅረባቸው ታሳቢ ተደርጎ) እና በወጪ ቆጣቢ አሠራር ዘዴ (Modular System) እስከተሠሩ ድረስ፣ እንደገና ገለልተኛ በሆነ የባለሙያ ስብስብ ተጠንቶ በሚገኘው ውጤት መሠረት የዋጋ ክለሳ ማድረግ፡፡
 3. በሕንፃው ውስጥ የመኖሪያ ቤቶቹ ያሉበት ወለል ልዩነት ግምት ውስጥ በማግባት ለዋጋ ትመና እንደ አንድ መሥፈርት መታየት አለበት፡፡ ለምሳሌ ባለአራት ፎቅ የጋራ መኖሪያ ሕንፃ የመሬት ወለል (Ground Floor) ዋጋና የመጨረሻ ወለል ዋጋ (ለምሳሌ ኮርኒስ ሥራን የተመለከተና ሌሎች) ልዩነቱ ሊታይ ይገባዋል፣
 4. ለዛሬ የተጋነነ ወጪ ምክንያት የተባሉ በሕገወጥ መንገድ ሀብት ለማጋበስ የሚፈልጉ የቤቶች ልማት ተዋናዮችን (ደካማ ሥራ ተቋራጮች፣ አማካሪ መሐንዲሶች፣ በማኅበራት የተደራጁ ግብዓት አቅራቢዎችና ሌሎች) ማጥራት ያስፈልጋል፡፡ በግልጽ እንደሚታወቀው ትናንት ለተፈጸመ ሙስና ዛሬ ዋጋ የሚከፍሉት ድሆች ናቸው፡፡ የተጋነነ ዋጋ እንዳይኖር ቁርጠኛ ውሳኔ ያስፈልጋል፡፡    
 5. የጋራ መኖሪያ ቤቶች መነሻ ክፍያውና ወርኃዊ የባንክ ክፍያ መክፈል እንደተጀመረ ወዲያው ቤቱን ለአገልግሎት መጠቀም አይቻልም፡፡ ብዙ የሚቀሩ የፊኒሺንግ ሥራዎችና ባለዕጣው የሚኖርበት የቤት ኪራይ ወጪዎች የሚፈታተኑ ናቸው፡፡ ስለዚህ የሚከፈለውን የቤት ዋጋ በረጅም ጊዜ ተከፍሎ በሚያልቅ መልኩ ቢሆን የተሻለ ያደርገዋል፡፡

በአጠቃላይ በአሥረኛው ዙር የጋራ መኖሪያ ቤቶች ቤት ማስተላለፍ ሥራ ላይ ከመጠመድ፣ መጀመሪያ የተደረገውን የዋጋ ጭማሪ እንደገና ማየት የሚያስፈልግበት ጊዜ ላይ መሆኑ ሊታወቅና ሊመከርብት ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles