Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝያረጀን በሬ ወይፈኖቹ ልፈውት ሄዱ……!!!

ያረጀን በሬ ወይፈኖቹ ልፈውት ሄዱ……!!!

ቀን:

ከጠዋት ጀምሮ ስሜቱ አንድ ነገር ይናገራል፡፡ ካረፍንበት ራዲሰን ብሉ ሆቴል ወደ ቁርስ መመገቢያው ሲወርድ ራሱ ረፈድ አድርጎ ነበር፡፡ እኛ ወዳለንበት ወንበር ሲደርስ አንድ ነገር ተነፈሰ፡፡ “ምነው ፍርኃት ያዘኝ እንዴ ልጆች?” ብሎም አለፈ፡፡ ፊቱ፣ የሩጫው ዝግጅትና ለማሸነፍ አለመሮጡ ቤተኛ ከሆነበት ዓለም ሊገለል ስለመሆኑ በግልጽ ይናገራሉ፡፡

እሱ ለማንም ለመናገር አልደፈረም፡፡ የማንቸስተር ሩጫ አዘጋጆች እንኳ ይህንን አያውቁም፡፡ የቀጥታ ሥርጭቱን የሚሠራው ቢቢሲም ይህን ውሳኔ በጭራሽ አልሰማም፡፡ ድንገት ግን ከውድድሩ አንድ ቀን በፊት እራት እየበላን ስጠይቀው፣ “ምን ታደርገዋለህ? ተፈጥሮ ራስዋ ይህንን ትነግራሀለች፤” አለ፡፡ ከውድድሩ አንድ ቀን በፊት ስለዝግጅቱ ሲያወራ ይህን ማለቱ በውሳኔው ስለመፅናቱ እርግጠኛ አድርጎኝ ነበር፡፡ “ለመጨረሻ ጊዜ ለውድድር ሱሪ አውልቄ ቁምጣ የማጠልቀው ነገ ብቻ ነው፤” ሲለኝ ደግሜ ጠየቅኩት፡፡ “ኒውዮርክ ላይም እኮ እንደዚያ ብለህ ነበር፡፡ አሁንም…..”፣ “አይ ያኔ እኮ ሕመምም፡፡ ነበር አሁን ግን በቃኝ ሰውነትህ እንደ ድሮው ሳይታዘዝ ሲቀር በቃኝ ማለት አለብህ፡፡ እኔም በቅቶኛል፤” አለ፡፡

ይህን ነገር ኃይሌ ለማንም አለመናገሩ አስገራሚ ነበር፡፡ እኔም ብሆን ከውድድሩ በኋላ ኃይሌ ምን እንደሚል እየጓጓሁ ነበር ወደ ከተማዋ [ማንቸስተር] ማዕከል ያመራሁት፡፡ ወደ ሩጫው ከመግባቱ በፊት ወደ ተንቀሳቃሹ መፀዳጃ ቤት ገባ፡፡ ተወዳዳሪዎቹን ሳይቀላቀል በፊት ደግሞ ይህን አለ፡፡ “እነ ሩኒ በኳሱ እኛም ደግሞ የተቻለንን በሩጫ በማንቸስተር ታውቀናል፡፡ አሁን ደግሞ እንሞክራለን፡፡ ለማሸነፍ ሳይሆን ዱብ ዱብ ለማለት…” የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ ድሮም ካለ አንደኝነት ሌላ የሚዋጥለት ሰው አይደለም፡፡ አንደኝነቱን ለማስጠበቅ ከሚቻለው እስከ ማይቻለው ድረስ ሁሉንም መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ ሐጂ አዲሎ የእሱ አብሮ አደግ ነው፡፡ አንድ ቀን ከአሰላ ለማጣሪያ ወደ አዲስ አበባ ስታዲየም አብረው መጡ፡፡ የጠዋቱ ማጣሪያ ሳይሳካ አለቀ፡፡ የኃይሌ እግር የአውራ ጣቱ ቆዳ ተቀደደ፡፡ ውጤትም ሳይኖረው እግሩም ተቀዶ፣ የከሰዓቱም ሌላ ዕድል እንዳያመልጠው ኃይሌ አንድ ነገር መዘየድ ነበረበት፡፡

መርፌ ይዞ መጣ፡፡ ሐጂና ሌሎች ጓደኞቹ ደንግጠው ቢያዩትም ለእሱ ዋናው ነገር የእግሩ እንደ ጫማ መሰፋት ሳይሆን የከሰዓቱ አሸናፊነት ብቻ ነበር፡፡ እናም አደረገው፡፡ በጭካኔ የራሱን እግር በመርፌና በክር ጠቀመው፡፡ ከስፌቱ በኋላ ከሰዓት ተወዳደረና ማጣሪያውን አለፈ፡፡ “በተቃራኒውና በኃይሌ መካከል ያለውን የዓላማ ጉዳይ ልዩነት ያወቁት ያኔ ነበር፡፡ በውስጤ ኃይሌ የምንጊዜም ምርጥ አትሌት እንደሚሆን ውስጤ ነገረ፤” በማለት ሐጂ ይናገራል፡፡ ኃይሌ በትናንቱ [ግንቦት 2 ቀን 2007 ዓ.ም.] የአሥር ኪሎ ሜትር ውድድር 16ኛ ነው የወጣው፡፡፡ እናም እንደገባ ከበርናንድ ላጋት ሞቅ ያለ አቀባበል ነው የጠበቀው፡፡ ላጋት በ40 ዓመቱ ሦስተኛ ነው የወጣው፡፡ ኃይሌን እንዲህ አለው፡፡ “አንተ ነህ የኔ አትሌቲክስ ምሳሌ፡፡ ድሮ ብቻ እንዳይመስልህ አሁንም ቢሆን፡፡ ማቆም ሳስብ እንደ ኃይሌ ጠንክሬ መሮጥ አለብኝ ነው የምለው፡፡ በቃ እንገናኛለን …” ተለያዩ፡፡

በደቂቃዎች ልዩነት የኃይሌ የሩጫ ውድድር መጨረሻ ቃለ መጠይቅ ቀጠለ—

“ሩጫዉ እንዴት ነበር?”

“ሩጫው ነው ሹፈቱ? ሹፈቱ ማለትህ ነው? ሹፈት ነው እንጂ ሩጫ አደለም፡፡ የምልክ ያረጀን በሬ ወይፈኖቹ ልፈውት ሄዱ፡፡ ያው ወይፈኖቹን አየሃቸዉ አይደል….?”

“የስንብት ሩጫ ነውና ምን ተሰማህ?”

“ይነካል በጣም… አንደኛ ፊት ለምደህ ከኋላ መሆን የምልህ ይደብራል፡፡ ያለኝን ሂጃለሁ፣ ያለኝን ሠርቻለሁ ስለዚህ ማቆሙ ጥሩ ነው፡፡ አሁን ቻው ቻው አልኩኝ…”

“እንዲው ይቆጨኛል አላደረኩትም የምትለው ነገር አለ?”

“በጣም የሚቆጨኝ በኦሊምፒክ ማራቶን አለመሮጤ ብቻ ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ ሁሉንም ነገር አሳክቻለሁ፡፡ ከዚህ በኋላ ቢዝነሱም አለ፡፡ ሩጫውም አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜም ምሳሌ እሆናለሁ፡፡ ያው አረማመዴም አያስጠላም አይደል…?” ሳቅ…

ኃይሌ ፈገግታ ለመመገብ በተዘጋጁ ጥርሶቹና እንባ ባቀረሩ ዓይኖቹ ወደ ሁለተኛው ሩጫ ከሕዝብ ጋር ለመሮጥ ወደ ዝግጅቱ መሄድ ጀመረ፡፡ በዚህ መሀል የእሱ የቅርብ ወዳጅ የሆነውን የቢቢሲው ሮብ ዋከርን ከማስተዋወቅ ሥራው መሀል ጠራሁት፡፡ እባክህን ስለኃይሌ ሩጫ ማቆም ትንሽ ነገር በለኝ፡፡ በፍፁም ማመን አልፈለገም፡፡ ደጋግሞም ኃይሌ አቆመ እርግጠኛ ነህ? ለቢቢሲ እኮ አልተናገረም አለኝ፡፡ ይኸውልህ እሱ ሁለተኛውን ሩጫ ከሕዝብ ጋር ከመሮጡ በፊት ጠይቀውና ለእኛ ደግሞ ሐሳብህን ትሰጠናለህ አልኩት፡፡

ኃይሌን አስቆመውና ጠየቀው፡፡ እውነታውን ሲነግረውም የሕዝቡ ሩጫ እንዲዘገይ አድርጎ ያልተጠበቀውን መርዶ ራሱን በእጁ እያከከ ተናገረ፡፡ ማንቸስተር በሐዘንና በአድናቆት ጭብጨባ ለደቂቃ ያህል ተረበሸች፡፡ “እወዳችኋለሁ አመሰግናለሁ፡፡ ኃይሌ ከጤና ሩዋጮቹ ጋር ሁለተኛ ሩጫውን ጀመረ፤” በርናንድ ላጋት በሰማው ነገር እጅጉን ካዘኑት መሀል አንዱ ነው፡፡ የእኔ የመሮጥ ምሳሌ ያለውን ሰው ከደቂቃዎች በኋላ ከእንግዲህ በማቆሙ ብቻ ምሳሌ እንደሚሆን አረጋገጠ፡፡

“በእርግጥም ከዚህ በኋላ ኃይሌ ከጤናዎቹ ጋር ይሮጣል፡፡ ነገር ግን ቢያንስ ለ100 ዓመታት ያህል የማይዘነጋ ገድል ሠርቷል፡፡ እናም ወይ ጠቅላይ ሚኒስተር አልያም ፕሬዚዳንት ሆኖ እንደማየው ተስፋዬ ነው፤” ሮብ ዋከር የኃይሌ ወኪል ጆስ ሄርመንስ ሳይቀር ለውሳኔው እንግዳ ነበሩ፡፡ ከውድድሩ አንድ ቀን በፊትም የማቆሙ ዝና በኢቢሲ ይፋ ሲሆንም የቀድሞው ዓይነት ማቆም ነው የሚል ስሜት በብዙዎች ዘንድ አድሮ ነበር፡፡ ኃይሌ ለምን ማቆሙን አስቀድሞ ማወቅ ለሚገባቸው አልተናገረም ለሚለው ጥያቄ ግን ጊዜ ምላሽ የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በግለሰብ ደረጃ ከማንም በላይ ኢትዮጵያን ያስተዋወቀ ሰው ነበር፡፡ አሁን ከሙያው ጋር ተለያይቷል፡፡ (ሰይድ ኪያር በፌስቡክ ገጹ ላይ ያሰፈረው)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...