Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ይድረስ ለሪፖርተርደላላን ብቻ ሳይሆን ሥርዓቱንም እንጠይቅ

ደላላን ብቻ ሳይሆን ሥርዓቱንም እንጠይቅ

ቀን:

በቅርቡ ኢትዮጵያዊነታችንና ሰብዓዊ ፍጡርነታችን ብሎም የሰው ልጆችን ስብዕና በሚነካና ምናልባትም ለዘመናት ከጭንቅላታችን በማይወጣ መልኩ አይኤስ በተባለ የሽብርተኛ ቡድን የደረሰውን፣ በሐዘንና በቁጭት የምናስታውሰውን አሰቃቂ ግድያ ተመልክተናል፡፡  እንደ ኢትዮጵያ ባሉ  አገሮች ስደት ተመራጭ የሚሆንበት ምክንያት የተሻለ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን በመሻት ስለመሆኑ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ያወጧቸው ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ጥናቶቹ ለሥራና የተሻለ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ፍለጋ የሚሻገሩ ዜጎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ይገልጻሉ፡፡  

ወደ ውጭ ከሚሻገሩት መካከል አብዛኛዎቹ ሕገወጥ ከመሆናቸው ባሻገር የዜጎችን ክብር፣ ደኅንነትና ሰብዓዊ መብት ወደ ጎን በመተው   በደላሎችና ኪራይ ሰብሳቢ በሆኑ፣ የተሰጣቸውን ሕዝባዊና ሕገ መንግሥታዊ መብት ወደ ጎን በመተው በሚሠሩ ግለሰቦች አማካይነት በርካታ ዜጎች ሕይወታቸውን ለአደጋ ያጋለጣሉ፡፡ በየዕለቱም ለጆሮ የሚቀፉ፣ የሚዘገንኑና የብዙ እናቶችን ልብ የሰበረ፣ እረፍት ያሳጣ፣ ሞት፣ ስቃይና በደል ሲደርስ እያየንና እያዳመጥን ቆይተናል፡፡

ኢትዮጵያ በየዓመቱ በርካታ ወጣቶች ጥለዋቸው ከሚሰደዱ አገሮች አንዷ እንደሆነች የታወቀ ነው፡፡ ለወጣቶቹ መሰደድ በርካታ ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡  ኢትዮጵያ ከአፍሪካ አገሮች በኢኮኖሚ ረገድ በፍጥነት እያደጉ ካሉ አገሮች መካከል ስሟ የሚጠራ ቢሆንም፣ ዜጎቿ ግን ከመሰደድ አልቦዘኑም፡፡ በዚህ ምክንያት በሕገወጥ ስደት በርካቶች እየሞቱ ይገኛሉ፡፡ በከተሞች አካባቢ አጥጋቢ የሥራ ዕድል አለመኖሩ፣ በአብዛኛው የሚሠሩ ሥራዎች የዜጎችን ሕይወት ወደ ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር የሚችሉ ባለመሆናቸው፣ በየጊዜው የኑሮ ውድነት እየጨመረ መምጣቱና ሌሎች በርካታ ምክንያቶች ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡

- Advertisement -

በአሁኑ ወቅት ዓለም ወደ አንድ መንደርነት እየተሸጋገረች ነው፡፡  በዚህ ሒደት ውስጥ ዜጎች በተለያዩ አገሮች እየተዘዋወሩ በመሥራት ራሳቸውን፣ ቤተሰቦቻቸውንና አገራቸውን በኢኮኖሚና በቴክኖሎጂ ለውጥ ተጠቃሚ ማድረግ እየተለመደ የመጣ ክስተት ሆኗል፡፡ በርካታ በውጭ የሚኖሩ ዜጎች ለኢኮኖሚ የሚያደርጉት አስተዋጽኦ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ ይህ ሒደት የዜጎችን ክብር፣ ደኅንነትና መብት በጠበቀ መልኩ ሲሆን ደግሞ የበለጠ ጠቀሜታውን እንደሚያጎላው እሙን ነው፡፡

 እንደ ኔፓል፣ ባንግላዴሽ፣ ህንድ፣ ፊሊፒንስ በመሳሰሉ አገሮች ውስጥ ያለው ልምድ እንደሚያሳየው፣ ዜጎቻቸው  በተለያዩ አገሮች በተለይም በዓረብ አገሮች ውስጥ  በሚያደርጓቸው የሥራ ስምሪቶች ላይ የሕግ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ሥርዓቶች ስላሉ በተጠናና ሕጋዊ ማዕቀፍ ባለው መንገድ የሚካሄድ የሥራ ግንኙነት መሆኑን የየአገሮቹ ሪፖርቶች ይጠቁማሉ፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ የኢኮኖሚና የማኅበራዊ እንዲሁም የሳይንስ ዕውቀት ሽግግር ማግኘታቸውንም  ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያም ከዚሁ ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን የውጭ ሥራ ስምሪት ዘርፍን እንደ አንድ ዘርፍ ዕውቅና ሰጥታለች፡፡ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘርፉን የሚቆጣጠር አዋጅ በ1990 ዓ.ም. ታውጆ ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል፡፡ ይህ አዋጅ በሥራ ላይ በቆየበት ጊዜ የታዩትን ክፍተቶች መሙላትና ዘርፉን በተጠናከረ ሁኔታ መምራት አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ አዋጁ አሁን በሥራ ላይ ባለው ሥራና ሠራተኛ ማገናኘት አገልግሎት አዋጅ ቁጥር 632/2001 ተተክቶ በመሠራት ላይ ይገኛል፡፡  

ይሁን እንጂ በአገራችን በውጭ አገር ሥራ ስምሪት ረገድ ኃላፊነት የተሰጠውን የሠራተኛና ማኀበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴርን ስንመለከት የሚታዩት ክፍተቶች የሕግ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት አቅም፣ ዘርፉን ካለማወቅና ትኩረት ካለመስጠት ጋር እጅና ጓንት ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡

ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አማካይነት ባወጣው መግለጫ መሠረት ከጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ  ለስድስት ወራት በውጭ አገር ሥራ ስምሪት ረገድ የሚታዩ የሕግ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ክፍተቶች ተፈትሸው ተገቢውን ማስተካከያ እስከሚደረግባቸው ድረስ  ለሥራ ወደ ውጭ በተለይም ወደ መካከለኛው ምሥራቅ መጓዝ ተከልክሏል፡፡ ነገር ግን በጥቅም የተሳሰሩ የተወሰኑ ሕገወጥ ደላሎች፣ የኤጀንሲ ባለቤቶችና የመሥሪያ ቤቱ ሠራተኞች በመተባበር ዕገዳውና አቅም አልባው የመሥሪያ ቤቱ ተቋማዊ አደረጃጀት  ያመጣላቸውን በረከት ተጠቅመው ዜጎቻችንን ወደ ስደት ያውም በኢትዮጵያ አየር መንገድ በኩል አሳፍረው በሕገወጥ መንገድ እየላኩ በክቡሩ የሰው ሰውነት ላይ ንግድ ማካሄዱን ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲገን አድርገውታል፡፡

ለዚህ ማሳያ የሚሆነው ትልቅ አገራዊ ጥቅም የሚያስገኘው ይህ የሥራ ዘርፍ  በሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ በዳይሬክቶሬት ብቻ እንዲመራ መደረጉና ይህም በፌዴራል መሥሪያ ቤት በአደረጃጀት እንኳ እስከታችኛው መዋቅር ድረስ ያልወረደ መሆኑ አንዱ ነው፡፡ በተጨማሪም በዳይሬክቶሬቱ ውስጥ የሚገኙ ሠራተኞች ስለዘርፉ ያላቸው ግንዛቤ አጠያያቂ መሆኑም ቀላል ማሳያ ይመስለኛል፡፡ የመሥሪያ ቤቱን የማስፈጸም አቅም ለመፈተሽ ይረዳ ዘንድ ሌላ ነገር ልጨምር፡፡ በውጭ አገር ሥራ ስምሪት ረገድ የሚታዩ የሕግ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ክፍተቶች ተፈትሸው ተገቢውን ማስተካከያ እስከሚደረግባቸው ድረስ  ከጥቅምት 15 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ ለስድስት ወራት ዕገዳ የተደረገ መሆኑን ሚኒስቴሩ ቢገልጽም፣ ዕገዳው ከአንድ ዓመት ከስድስት ወራት በላይ መቀጠሉን ስንመለከት፣ ምን ያህል የማስፈጸም ብቃቱ ደካማ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ ተራዝሞም ከሆነ ይኸው ሊገለጽ ይገባ ነበር፡፡

ስደትን  እንደ ኢትዮጵያ ካለች አገር በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስቀረት ይቻላል ብሎ ማመን እንደማይቻል የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ ይህንን ከተቀበልን የዜጎችን ክብር፣ ደኅንነትና መብት አስጠብቆ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ አገር ተጠቃሚ ለማድረግ ከሌሎች አገሮች ልምዶች በመነሳት ያሉትን የሕግ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ሥርዓቶች ማስተካከል ተገቢ መስሎ ይታየኛል፡፡

ይህም ሲባል የአደረጃጀት ሥርዓቶችን በመቀየርና ዘመናዊነት በተላበሰ መንገድ አሠራሮችን ማሳደግ ከተቻለ፣ በደላሎችና በኪራይ ሰብሳቢዎች ተተብትቦ የተያዘውን  ሕገወጥ የስደት ጉዞን በመቀነስ የዜጎች ክብር፣ ደኅንነትና መብት ተጠብቆ በኃላፊነትና በተጠያቂነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን አድርጎ ማስኬድ ያስችላል፡፡ ለዚህም ይረዳ ዘንድ በጉዳዩ ላይ በቂና ጥልቅ ጥናቶችን ማካሄድ፣ ስለውጭ ሥራ ስምሪት በቂ ግንዛቤና ዕውቀት እንዲኖር ማስቻል፣ አሠራሩን እስከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል በማውረድ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያለበትን ሥርዓት በቀላሉ መዘርጋትን ጨምሮ፣ በተቋም ደረጃ በብቁ ሙያተኞችና በአሠራር በደንቦች ታግዞ ማደረጃትና ማዋቀር አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡

የተሻለ ነገር መፈለግ የማይቆም የሰው ልጆች ፍላት እስከሆነ ድረስ እስከመቼ እንዘን? አስከመቼ የእናቶችን እንባ እንመልከት? አስከመቼስ የስደተኛን ስቃይ እያየንና እየሰማን እንደ ግለሰብም እንደ አገርም እየተቆጨን ጊዜ እንቁጠር? አሁንም መፍትሔው እንደ አገር የሕግ፣ የአሠራርና የአደረጃጀት ሥርዓቶችን ማስተካከልን የመሳሰሉ መንግሥት እንዲወጣቸው የሚጠበቁ ግዴታዎች፣  እንደ ማኅበረሰብም እያንዳንዱ ዜጋ ሕጋዊ መስመሮችን ተከትሎ መጓዝን የመመርመር፣ የማጣራትና መብትን የመጠቀም ግዴታዎችን መወጣትም ግድ ይላል፡፡  

(ቻላቸው ደሳለኝ፣ ከአዲስ አበባ)

*********

በፕላስቲክ ኢንዱስትሪው እሳት አደጋ ወቅት በሰዓቱ መገኘታችን ይታወቅልን

ሚያዝያ 17 ቀን 2007 ዓ.ም. ከቀኑ 8 ሰዓት ተኩል በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 06 ክልል ውስጥ ኒያላ ሞተርስ ፊት ለፊት የሚገኘው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ፕላስቲክ ኢንዱስትሪ ባልታወቀ ምክንያት የእሳት አደጋ ተከስቶ ነበር፡፡ ከኢንዱስትሪው የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ እንድንቆጣጠር ለእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ቦሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ከቀኑ 8 ሰዓት ከ32 ደቂቃ ላይ ጥሪ ደርሶናል፡፡

የአደጋው ሁኔታ የኢንዱስትሪ ቃጠሎ በመሆኑ ከነሙሉ የሰው ኃይሉ ወደ አደጋው ሥፍራ በማምራት በሁለት ደቂቃ ውስጥ አደጋ በተከሰተበት ቦታ ደርሰው የሕይወትና የንብረት ማዳን ሥራውን በዕውቀት ላይ ተመሥርተው በመሠራት አደጋው ሳይስፋፋ የመቆጣጠር ሥራ ማከናወናቸው እየታወቀ፣ የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱም ሆነ አደጋው የደረሰበት ተቋም ኃላፊዎች በአደጋው ሥፍራ ተገኝተው የአደጋ መከላከሉን ሥራ እየተከታተሉ በነበረበት ወቅት እነሱን ስለአደጋው ሁኔታ፣ የአደጋ ጊዜ ተሽከርካሪና ባለሙያ በምን ያህል ሰዓት ጥሪ ደርሷቸው በምን ያህል ሰዓት ውስጥ እንደደረሱ ሳይጠየቁ፣ በፕላስቲክ ኢንዱስትሪው አደጋው እንደተከሰተ ለባለሥልጣኑ ተደውሎለት ከአንድ ሰዓት በላይ መዘግይተው መድረሳቸውን የፋብሪካው ሠራተኞችና በአካባቢው የነበሩ የዓይን እማኞች ለሪፖርተር ጋዜጣ ገልጸዋል ተብሎ ረቡዕ ሚያዝያ 21 ቀን 2007 ዓ.ም. በወጣው ሪፖርተር ዜና አምድ፣ ገጽ 40 ላይ ለአንባቢያን ዘገባ አሰራጭታችኋል፡፡

በመሆኑም ባለሥልጣኑ በሰው ኃይልና በዘመናዊ የአደጋ ተሽከርካሪ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶችን አደራጅቶ ለኅብረተሰቡ የሚሰጠው አፋጣኝ ምላሽ፣ ልኬት በሚካሔድበት ደረጃ መሠረት አገለግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡ ይህ በሆነበት ወቅት ከአደጋ ቦታው ጥሪ ደርሶት በሥፍራው የደረሰውና የአደጋውን ሒደት ሲቆጣጠር የነበረው የቦሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፣ በቅርብ ርቀት እየተገኘ ከአንድ ሰዓት ቆይታ በኋላ ነው የደረሱት ተብሎ የተዘገበው የተቋሙን ስም ለማጥፋት የተደረገ ይመስላል፡፡ ስለዚህ ሀቁ ከላይ የተጠቀሰው በመሆኑ፣ ትክክለኛ ዘገባ ለመዘገብ በአደጋው ቦታ የነበሩ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን ኃላፊዎችና አደጋ የደረሰበት ተቋም የተለያዩ ኃላፊዎችን ጠይቆ መዘገብ ሲቻል፣ ይህ አለመደረጉ የጋዜጣውን ተዓማኒነት የሚያጎድልና ዘገባውም ሚዛናዊነት የጎደለው በመሆኑ ማስተባበያ እንዲሰጥበት እንጠይቃለን፡፡

 (የእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች መከላከልና መቆጣጠር ባለሥልጣን፣ ቦሌ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት)

ከአዘጋጁ፡- በአደጋው ወቅት ስለአደጋው የሚመለከታቸውን ኃላፊዎች የሪፖርተር ዘጋቢ ጠይቆ ምርመራ እየተደረገ መሆኑን እንደገለጹለት መዘገቡ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በባለሥልጣኑ ችግር ሳይሆን በትራፊክ መጨናነቅ መዘግየቱን የራሱ አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ሠራተኞች እንደገለጹ መዘገቡም መዘንጋት የለበትም፡፡    

********

 

ለ40/60 ቅድሚያ የሚሰጠው በመጀመርያው ቀን ለቆጠቡ ብቻ መሆኑ አሳዛኝ ነው

ለቁጠባ ቤቶች ተመዝጋቢዎች በማለት የመጀመርያ ቀን ምዝገባ ከመካሔዱ በፊት ለሚመዘገበው የቤት ፈላጊ ኅብረተሰብ በባንክ በኩል የተሰራጨው በራሪ ወረቀት ላይ 100 ከመቶ (ሙሉ ክፍያ) የፈጸሙ ቅድሚያ ያገኛሉ የሚል መረጃ ተሰራጭቶ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲን ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊን አነጋግሬ እንደተረዳሁት ቅድሚያ ዕጣ ውስጥ የሚገቡት ቤት ፈላጊዎች በመጀመርያው ቀን ብቻ የተመዘገቡት 2,000 ቤት ፈላጊዎች ብቻ ናቸው፡፡ ከመጀመርያው የምዝገባ ቀን በኋላ ማለትም ምዝገባው በተጀመረ በሁለተኛው ወርም ሆነ  በሦስተኛው ሙሉ ክፍያም ቢፈጽሙም የመጀመርያ ዕጣው ውስጥ የማይገቡ መሆኑን ከገለጻቸው ተረድቻለሁ፡፡

አንድ የ40/60 ቤት ፈላጊ 40 ከመቶ ቅድሚያ ለከፈለ፣ ቀሪውን ክፍያ ያገናዘበ ወለድ መክፈል እንዲችል ከባንክ ጋር ከተሳሰረ በኋላ ዕጣ ውስጥ የማይገባበት ምክንያት አልገባኝም፡፡ ይህ የቤት ፕሮግራም የተዘጋጀው መካከለኛ ገቢ ላላቸው ቤት ፈላጊዎችን በቁጠባ የቤት ተጠቃሚ ለማድረግ እንጂ በመጀመርያው ቀን በአንድ ጊዜ ሙሉ ክፍያ የመፈጸመ ብቻ የመጀመርያ ዕጣ ተጠቃሚ መሆኑ አግባብ አይደለም፡፡

ሌላው አንድ ቤት ፈላጊ 40 ከመቶ ክፍያ ከመፈጸመ ዕጣ ውስጥ የማይገባው ለምንድን ነው? በማለት ላቀረብኩት ጥያቄ፣ ከቁጠባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ አንድ ኃላፊ አገላለልጽ እንደተረዳሁት፤ በ40/60 ፕሮግራም መመርያ መሠረት መታቀፍ የማይችል በ10/90 እና 20/80 ፕሮግራም መታቀፍ ይኖርበታል፤ ጥያቄዬ ይኼ ግን  አይደለም፡፡ የ40/60 ዕጣ አወጣጥ ጉዳይ እንጂ በማለት፣ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ቤት ፈላጊዎች የተለየ ጥያቄ አይደለም ብያለሁ፡፡ በእውነቱ ከሆነ ስንቱ መካከለኛ ገቢ ያለው ነዋሪ ቤት ፈላጊ ነው በአንድ ቀን ሙሉ ክፍያ መፈጸም የሚችለው? ባለሀብት ከሆነ መሬት በሊዝ ገዝቶ፣ መኖሪያ ሕንፃ ገንብቶ መጠቀም ይችላል፡፡ የባንክ የብድር መርህ እንኳ 30/70 ነው፡፡ የ40/60 ፕሮግራም የቁጠባ ቤቶች ግንባታ የተፈገለበት ምክንያት መጀመርያውኑ የቤቶቹ ግንባታ ከተማ ውስጥ ይሆናል ስለተባለ፣ የትራንስፖርት ወጪው ዝቅተኛና ገንዘብ የሚቆጥብ በመሆኑ እንጂ ሌላ ተዓምር ኖሮት አይደለም፡፡

እንዲህ የሚሆነው መንግሥትን ያላግባብ ለማስወቀስ ነው በማለት ስከራከራቸውም በድረገጽ ተከታተል ብለው አድራሻ ሰጥተውኝ ተለያይተናል፡፡ የቤቶች ሥርጭት ግልጽና ፍትሐዊ ቢደረግ፣ ይህ ሁሉ የቅድሚያ ዕጣ ሩጫ አንዳንድ የቤት ልማት ፕሮጀክቱ ኃላፊዎችና ከእነሱ ጋር ቅርበት ያላቸው ግለሰቦች በመጀመርያው ምዝገባ ቀን ብቻ ሙሉ ክፍያ የፈጸመ የመጀመርያ ዕጣ ውስጥ ገብቶና ሠንጋተራና በሌሎችም ቅርበት ባላቸው አካባቢዎች ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ ያሉትን የቁጠባ ቤቶች ቅድሚያ የማግኘት ዕድል ማመቻቸት እንዳለ ታዝብናል፡፡ ምስጢሩን ያወቁና የተደራጁ ሰዎች መሐል ከተማ ሠንጋተራ አካባቢና ሌሎች ቦታዎች ላይ የተገነቡትን ቤቶች በቅድሚያ ለማግኘት እንዲችሉ የታቀደ እስኪመስል ድረስ  ቤቶቹን በአፋጣኝ አጠናቀው ለመውሰድ ወይም ለመነገድ እየተቻኮሉ ነው የሚል ጥርጣሬ አድሮብኛል፡፡

የሚከተለውን ከቤቶች ዋጋ ክለሳ ጋር ማስተካከያ ቢደረግ

በተግባር እንደሚታየው የ40/60 የቁጠባ መኖሪያ ቤቶች የሚገነቡት ከተማ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ካልተሳሳትኩ እንደ ቦሌ አራብሳ ባለው አካባቢ ከአያት ሰባት ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቆ ከተማው ዳርቻ ላይ የሚገኘውን ያካትታል፡፡ ከሪፖርተር እንደተረዳሁት የቤቶቹ ዋጋ ላይ ክለሳ እንደሚደረግ ነው፡፡ የእነዚህ የቁጠባ ቤቶች ዋጋ ለመጨመር በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቁጠባ ቤቶች ልማት ኤጀንሲ ጥናት እያካሄደ ከሆነ፣ እንደግብዓት ሊጠቀምበት ስለሚችል የሚከተለው ከቤቶች መሸጫ ዋጋ ጋር ተካቶ ቢታይ መልካም ነው፡፡

ለምሳሌ ለ50 ዓመታት ለትራንስፖርት የሚከፍለውን እንዲሁም የቤት ዋጋ ክፍያ አካተን ብንወስድ፣ በንግድ የሚተዳደር ግለሰብ ወይም የመንግሥት ሠራተኛ የ40/60 ቤት በዕጣ ቦሌ አራብሳ ላይ ቢደርሰው፣ ለሥራ ከተማ ደርሶ ለመመለስ ለትራንስፖርት በቀን 40 ብር ገደማ ወጪ ቢያደርግ ማለትም በዓመት ይህንን ባወጣ፤ ለ365 ቀናት ለ50 ዓመት 730,000 ብር ይሆናል፡፡ የባለሦስት ክፍል መኖሪያ ቤት ዋጋ ከወለድ በፊት 384,000 ብር የሚከፈልበት በመሆኑ ከትራንስፖርት ወጪው ጋር ሲደመር በግርድፉ 1,114,000 ብር ይሆናል፡፡ ሠንጋተራ አካባቢ የሚደርሰው የትራንስፖርት ወጪው ዝቅተኛ ስለሚሆን የቤት ክፍያውን ከመክፈል ባሻገር ተጨማሪ ጫና አይፈጠርበትም ማለት ነው፡፡ ልዩነቱ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ የዋጋ ክለሳው ይህንን ሊያጤን ይገባዋል፡፡

ለ40/60 ተመዝግበው የነበሩ የቁጠባ ቤት ፈላጊዎች ‹‹ከ7,000 በላይ የሚሆኑት አንፈልግም በማለት ምዝገባቸውን አሰርዘው ገንዘባቸውን አስመልሰው የወጡ ሲሆን ከ8,000 በላይ የሚሆኑ ተመዝጋቢዎች ደግሞ ሙሉ ክፍያ ፈጽመው በመጠባበቅ ላይ ናቸው፤›› ተብሎ በጋዜጣው ተዘግቧል፡፡ ስለዚህ የሽያጭ ዋጋ ክለሳው ሥሌት ይህንንም ያካተተ መሆን ይገባዋል፡፡

40 ከመቶ የቆጠበ ከባንክ ጋር በማስተሳሰር ወደፊት የሚኖረውን የገንዘብ መጠን ያገናዘበ ሒሳብ ከነወለዱ የሚከፍል በመሆኑ፣ ዕጣ ውስጥ ቢታቀፍ ነውር የለበትም፡፡ ሌላው ዕጣ ሊወጣ የሚገባው ቢያንስ ከ5,000 እስከ 10,000 ለተጠናቀቁ ቤቶች እንጂ ምርጥ ቦታ ላይ የተገነቡና ብዛት የሌላቸው  ወይም 2,000 ላለሞሉ የቁጠባ ቤቶች ብቻ፣ ያውም ሙሉ በሙሉ ላልተጠናቀቁ መሆን የለበትም፡፡ ቤቶች ለጥቂቶች በጥድፊያ ሰጥቶ ለማስነገድ ነው የሚል ጥርጣሬ ስላለኝ ነው፡፡ ዘግይተውም ቢሆን ዕጣ ከመውጣቱ በፊት ቅድሚያ መቶ ከመቶ ክፍያ የፈጸሙ 8,000 ዜጎች በሙሉ በመጀመርያው ዕጣ ውስጥ ቢካተቱ ችግሩ ምኑ ላይ ነው? ለምን በመጀመርያው ቀን ሙሉውን ለከፈሉ 2,000 ቤት ፈላጊዎች ብቻ ይሆናል? ይህንን ቁጠባ የቤቶች ልማት ኤጀንሲ ኃላፊዎች በግልጽ ቢያብራሩት መልካም ይሆናል፡፡ የቁጠባ ቤቶች ስሙ እንደሚገልጸው እያስገነባ ያለው ለቆጠቡ የመኖሪያ ቤት ፈላጊ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የቤት ባለቤት ለማድረግ ነው፡፡

ስለሆነም መጀመርያ ላይ የሚወጣው ዕጣ 40 ከመቶ የቆጠበም ቢሆን ዕጣ ውስጥ ቢካተት ፍትሐዊ ይሆናል፡፡ ገንዘብ እየቆጠቡ በመጠባበቅ ላይ ያሉ 166,000 የተመዘገቡ ቤት ፈላጊዎችንም ከማሳዘን ይቆጠባል፡፡ ገንዘባቸውን እያወጡ ራሳቸውን የሚያገሉ ሰዎች ቁጥርም ይቀነስ ይሆናል፡፡ መንግሥት ጉዳዩን ተገንዝቦ ክለሳ አድርጎ ቢያስተካከል የሚል አስተያየት አቀርባለሁ፡፡

 (ያለው ድልነሳው፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...