Saturday, June 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

እኔ የምለዉከታሪክ እንማር

ከታሪክ እንማር

ቀን:

ሰዎች ሰላማችንን ለማደፍረስ የጦርነት ነጋሪት ሊጎስሙ፣ እንቢልታውን ሊነፉና ሊያስተጋቡ ይችላሉ፡፡ ዳሩ ግን ደኅንነታችን አደጋ ላይ የሚወድቀው እነዚህ ሰዎች ስለፎከሩም ሆነ የሚወድቀው የዘመናዊ የጦር መሣሪያ እጅግ በተራቀቀ መንገድ በመሠራቱ ከቶ አይደለም፡፡ የጦር መሣሪያዎች በሳይንሳዊ ዘዴ ከመሠራታቸው ይልቅ ኅብረተሰቡ የሚገኝበት ሁኔታ አንዱ የሌላውን ነፃነት ለመዳፈር፣ ህልውናውን ደምስሶ የራሱን ህልውና ለማረጋገጥ፣ ምኞቱን በሌሎች ችግር ለማስገኘት ጥረት ያደረገ እንደሆነ ነው፡፡ የሰው ልጅ ቢተባበርና ወዳጅነቱን ቢያጠናክር ወደር የሌላቸው ጠቃሚ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን ለማስገኘት ይችላል፡፡ ብዙዎቻችን በሐሳባችን  የኢትዮጵያን አንድነት፣ የኅብረተሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውህደት እንመኛለን፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ የሚፈጠሩ መናኛ ግጭቶችን ለማናርና በዚህ ችግር ተጠቃሚ ለመሆን የሚፈልጉ ኃይሎች ደግሞ አንድነትን ለመሸርሸርና ውህደቱን ለማደፍረስ የማይናቅ ጥረት ያደርጋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ከአንድ ይልቅ ሁለትና ሦስት የተከፈለ ልብ እንዲኖረን ይወተውቱናል፡፡ እንዲህ ያለው አንድነትን የመበተንና ውህደትን የመሸርሸር ችግር ሊወገድ የሚችለው ግን ፍትሐዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነፃ የሆነ አስተሳሰብ ያለአንዳች ገደብ በሕዝብ ዘንድ የናኘና የሰረፀ እንደሆነ ነው፡፡ በእርግጥም ‹‹የእኔን አመለካከት እንጂ የሌላውን አትመን፣ የእኔን ድርጅት አምልክ የሌላው ሁሉ ፋይዳ ቢስ ነው…›› የሚል ግለኛ አስተሳሰብ በሌላ አስተሳሰብ ሲመከት የተሻለ ዘመን ይመጣል፡፡

ባለፍንበት የሶሻሊስት ሥርዓት ግንባታ መሠረታዊ ትምህርት፣ ‹‹ሰዎች ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እኩልነታቸውን ሊያረጋግጡ የሚችሉበት የወዛደር (የላብአደር፣ የሠርቶ አደር) መደብ በአሸናፊነት የወጣ እንደሆነ ነው፤›› የሚል የፕሮፓጋንዳ ሞገድ ሲነፍስብን የነበርን የኅብረተሰብ ክፍሎች እንደመሆናችን መጠን እንደ ሒትለራዊቷ ጀርመን፣ እንደ ሞሶሎናዊቷ ጣሊያንና እንደ ሌሎችም አምባገነን መንግሥታት አገሮች እንሆናለን፡፡ ዛሬ ሌሎች መደቦችም በነፃ የሚንቀሳቀሱበት ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ሥርዓት ይኑር ብንባል ድሮውንም ‹‹ፓርቲያችን ያሸንፋል›› በሚል አጉል አመለካከት ተጀቡነን የኖርን ነንና እነዚህን በቀላሉ መቀበል ያስቸግረን ይሆናል፡፡ ዳሩ ግን ለፈጣን ዕድገት ከነፃ ገበያ ሥርዓት የተሻለ እንዳልተገኘ ሕይወት ራሷ እየመሰከረች ነው፡፡ ነፃ የገበያ ሥርዓት ደግሞ ከነፃ የፖለቲካ ሥርዓት ጋር የተያያዘ በመሆኑ ‹‹ያንተ ድርጅት፣ የኔ ድርጅት ሥልጣን በያዘበት አካባቢ ዝር እንዳይል›› የሚያሰኝ ሳይሆን፣ እንዲያውም ‹‹የተቀናቃኝ ድርጅቶች በአካባቢው መኖር ለእኔ ህልውና ዋስትና ነው፤›› የሚያሰኝ ነው፡፡ በእርግጥም ነጋዴው ከነጋዴው፣ ምሁሩ ከምሁሩ፣ ገበሬው ከገበሬው፣ ፖለቲከኛው ከፖለቲከኛው በነፃ ካልተወዳደረ፣ ካልተቸና ካልተካፈለ በስተቀር አማራጭ በሌለው ጎዳና መጓዝ ለአምባገነን አገዛዝ መዳረግ ይሆናል፡፡ የተለያዩ ሊቃውንት እንደሚነግሩን ነፃ ኅብረተሰብ የሚባለው ሁሉም ሰዎች፣ ጥቁርም ሆኑ ነጭ፣ ደሃም ሆኑ ሀብታም በአገራቸው ተጠቃሚ መሆናቸው የተረጋገጠ እንደሆነ ነው፡፡ ሊቃውንቱ እንደሚመክሩን መንግሥት የሚኖረው ለግለሰቦች እንጂ ግለሰቦች ለመንግሥት ሲሉ አይኖሩም፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ በራሱ ጠቃሚ መሆኑም መታመን ይኖርበታል፡፡ የማንኛውም ሥርዓት ዴሞክራሲያዊነት የሚለካውም ለዚያ ግለሰብ በሚያደርገው ትኩረትና በሚሰጠው ክብር ነው፡፡

ይሁንና በብዙዎቹ በማደግ ላይ በሚገኙ አገሮች መንግሥታት ከጠመንጃ አፈሙዝ እንጂ በሕዝብ ለሕዝብ ተመርጠው፣ የሕዝብ መንግሥት ስላልሆኑ ግለሰቦች የመንግሥትን ፈቃድ ካላገኙ በስተቀር ልዩ ልዩ ተፅዕኖ ሲደረግባቸው ይታያል፡፡ ለምሳሌ በደርግ ሥርዓት ግለሰቦች በፓርቲ፣ በወጣቶች፣ በሴቶች፣ በገበሬዎች፣ በሠራተኞች፣ ወዘተ እንዲሳተፉ እያደረገ የሚገባውን ሁሉ ያገኝ ስለነበር በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለመሳተፍ የማይፈልጉ ሁሉ በግድ እንዲሳተፉ ተደርጓል፡፡ ይህ የተደረገው ያለ ምክንያት አልነበረም፡፡ የመጀመሪያው ምክንያት ከብዛት ጥራት ያላቸው አባላትን ለመምረጥ ነው፡፡ ሁለተኛው በማኅበር የተደራጀን ኃይል በቀላሉ ማንቀሳቀስ ስለሚቻል አስፈላጊ በሆኑ ሠልፎችና ስብሰባዎች በርከት ብለው እንዲታዩ ነው፡፡ ሦስተኛው ምክንያት በርካታ ሆነው ስለሚታዩ በሌሎች ዘንድ ተፅዕኖ እንዲፈጥሩ ነው፡፡ ስለሆነም በምዕራባውያንም ሆነ በምሥራቃውያን አገሮች የወጣት፣ የሴት፣ የልጆች፣ የተማሪዎች፣ የደራስያን፣ የሙዚቀኞች ማኅበራት እንዲቋቋሙ የሚደረገው ተፅዕኖ እንደፈጥሩ ነው፡፡ ስማቸውም ‘ተፅዕኖ ፈጣሪ’ ተብሎ በግልጽ ይታወቃል፡፡ ይህም ሆኖ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ካልተመቻቸው ለሥርዓቱ መቦርቦር ብሎም መውደቅ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡ ይህም የሚያመለክተው ሰዎች ነፃ ሆነው የመረጡትን ለራሳቸው ብሎም ለኅብረተሰቡ ጠቃሚ ሥራ እንዲያከናውኑ ዕድሉ ካልተሰጣቸው በስተቀር፣ የመንግሥት ወዳጅ መስለው ቢቀርቡ እንኳን ያለውዴታቸው እንዲሠሩ ከተደረገ ሰብሳቢዎቻቸውን ለውድቀት የሚዳርጉ መሆናቸውን ነው፡፡               

- Advertisement -

የደርግ መንግሥትን አወዳደቅ በምንተችበት ጊዜ ግን የዚያ ሥርዓት ቅሪት ዛሬ አለ? ወይስ የለም? ብሎ መጠየቁ ተገቢ ይሆናል፡፡ ይሁንና ‹‹አለ›› ቢባል ደግሞ የነፃ አስተሳሰብ፣ የነፃ አመለካከት፣ የነፃ እምነት፣ በአጠቃላይም የዴሞክራሲ ምንነት ስላልገባንና አምባገነን ሥርዓትን የሙጥኝ ብለን በመያዛችን ነው? ወይስ ዴሞክራቶች የሆንን መስሎን አምባገነንነትን እያራመድን ነው? ብለን እንደገና መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ዴሞክራቶች የሆንን መስሎን አምባገነን አመለካከት እያራመድን ከሆንን የሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ነፃነት ማለት ምን ማለት እንደሆነ አንብበንም ሆነ ጠይቀን ለመረዳትና ወኔው ሊኖረን ይገባል፡፡ ዊልያም ኦ ዳግላስ የተባሉት አሜሪካዊ የሕግ ሰው ‹‹የሕዝብ ነፃነት›› በሚል ርዕስ ባሳተሙት መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ ‹‹በአንድ መንግሥት ሥርዓት (በሶቪየት ኅብረትም ሆነ በቻይና እንደሚታየው) ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት በተወሰነ ደረጃ ሊኖር ይችላል፡፡ በፋብሪካዎች፣ በእርሻዎችና በተለያዩ የማኅበራዊ ኑሮ አገልግሎቶች ላይ ምን ዓይነት ፖሊሲ መነደፍ እንደሚኖርበት እጅግ በሰፋ ሁኔታ ሊከራከሩበት ይችሉ ይሆናል፡፡ ይሁንና ‹ሥልጣን የያዘው መንግሥት ነፃ የኢኮኖሚ ሥርዓቱ አያራምድምና አስፈላጊ አይደለም› ብሎ ለመቃወም እስካልተቻለ ድረስ፣ የፈለገው ዓይነት መጨቃጨቅ ቢኖር ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት አለ ብሎ መግለጽ አስቸጋሪ ይሆናል፤›› ይላሉ፡፡

አሜሪካዊው ፕሬዚዳንት የነበሩት ቶማስ ጀፈርሰን ‹‹በበኩሌ የሕዝብ ጥሩ ስሜት ከሁሉም የተሻለ መሣሪያ መሆኑን ራሴን አሳምኛሁ፤›› ብሎ ነበር፡፡ ሕዝብን እርግጥ ለተወሰነ ጊዜ ከትክክለኛው መንገድ አውጥቶ ወደ ተሳሳተ አመለካከት እንዲጓዝ ማነሳሳት ይቻል ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አዶልፍ ሒትለር ሥልጣን ላይ በወጣበት ጊዜ ብዙ ሕዝብ ድጋፉን ሰጥቶታል፡፡ ብዙ ሕዝብ በፍልስፍናው ለመመራት ቁርጠኝነቱን አሳይቷል፡፡ ብዙ ሕዝብም ለዚያ ፍልስፍና መሳካት የሕይወት መስዋዕትነት ከፍሏል፡፡ ፍልስፍናውን ዛሬም ቢሆን ትክክል ነው ብለው የሚያምኑ አሉ፡፡ የጣሊያናዊው ቤኑቶ ሙሶሊኒና የደጋፊዎቹ አካሄድም ከወዳጁ ከአዶልፍ ሒትለር ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ የሁለቱም አምባገነኖች ሕመም ግን ዛሬም ቢሆን በተለይ እኛ ኢትዮጵያውያንን ያመናል፡፡ ይህም ሆኖ አምባገነን መሪዎች ሲወገዱለት ሕዝብ በአጭር ጊዜ ውስጥ ራሱን ያርማል፡፡ ሕዝብ የራሱን መንግሥታት በብቸኝነት የሚቆጣጠር ስህተታቸውንም ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ የሚመራ ነው፡፡ ይህ ሳይሆን ቀርቶ በመሳሳቱ ለመቅጣት መሞከር ግን የሕዝብን ነፃነት ማፈን ይሆናል፡፡ ሕዝብ እንዳይሳሳት ለማድረግ ደግሞ የራስን ጉዳይ አሳምሮ በፕሬስ ውጤቶች እንዲያውቀው ማድረግ ነው፡፡ የመንግሥታችን ዋና መሠረቱ የሕዝብ አስተያየት እንደመሆኑ መጠን ይህንን መብቱን ማረጋገጥ ይኖርብናል፡፡ በዚህም ምክንያት ‘‘ጋዜጣ ከሌለው መንግሥትና መንግሥት ከሌለው ጋዜጣ ምረጥ ብባል ሁለተኛውን አስቀድማለሁ፤’’ ሲሉ ቶማስ ጀፈርሰን የሕዝብን አመለካከትና ስሜት አጢኖ መጓዝ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡

የሕዝብን ስሜት አጢኖ መጓዝ ማለት ደግሞ ባለፈው መንግሥት በደርግ ወይም በምሥራቅ አውሮፓ በነበሩ ኮሙዩኒስት አገሮች ይደረግ እንደነበረው ‹‹መንግሥት እንደዚህ ያሉ ፖለሲ አውጥቷልና እንዴት ተግባራዊ ልናደርገው ይገባናል?›› ብሎ ጨርሶ የማያውቀውና ሐሳብ ለመድረክ በማቅረብ ‹‹ተስማምቻለሁ›› ብሎ ስብሰባ እንዲበተን ማድረግ ማለት አይደለም፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ ፖሊሲው የሕዝቡን ፍላጎት የሚነካ እንዲሆን ከእሱ ከራሱ የመነጨ ሊሆን ይገባዋል፡፡ ጀፈርሰን ሌላው ቀርቶ ይህንን ኅብረታቸውን ለመበተን የሚፈልግ ወይም የሪፐብሊኩን መልክ ለመቀየር የሚሹ በመካከላቸው ቢኖሩ፣ እነዚህ ሰዎች ሐሳባቸውን ለመግለጽ መረበሽ እንደማይኖርባቸው፣ ቁም ነገሩ ስህተትን ግልጥልጥ አድርጎ ለማሳየት የሚቻልበትና እውነት በአሸናፊነት ልትወጣ የምትችልበት ሁኔታ መኖሩ ላይ እንደሆነ ማስረዳታቸው ያለምክንያት አልነበረም፡፡

በሌላ በኩልም የመንግሥት ባለሥልጣናት እንኳን ሕዝብ አንድ ግለሰብ የሚያምናቸውን ሐሳብ እንደምን በሥራ ላይ ሊተረጉሙ እንደሚቻል ማብራሪያ መጠየቅ፣ ማብራሪያውንም ከተጨባጭ ሁኔታ ጋር አጣጥሞ እንዲያቀርብ ማበረታታትና አስፈላጊም ከሆነ እገዛ ማድረግ እንጂ ‹‹አታውቅም›› ወይም ‹‹ያንተ አቋም ከእኔ አቋም ጋር የሚቃረን በመሆኑ የምታመነጨውን ሐሳብ ምን ያህል እውነት ቢሆን አልቀበልህም፤›› ሊሉት ከቶ አይገባም፡፡ በጥብቅ ሊያስብበት የሚገባው ዓቢይ ጉዳይ አንድ ሐሳብ ቀርቦ ከሕዝብ መካከል አንድ ሰው ቢቃወምና የዚያ ሰው ሐሳብ ምን እንደሆነ በውል ሳይገለጥ ቢቀር፣ ነገር ግን የዚያ ግለሰብ ሐሳብ ትክክል ሆኖ ቢገኝ መንግሥትን ብሎም ሕዝብን የሚጎዳ መሆኑ ነው፡፡ ይልቁንም ተጨባጭ ውጤት ሊያስገኝ የሚችል የምሁራን ሐሳብ እንዲታፈን ዙርያ ጥምጥም የሚያስኬድ ኋላቀር አመለካከት ማራመድ በራስ መንግሥት ላይ መቀለድና ለውድቀት መዳረግ ይሆናል፡፡ ስለዚህም የመንግሥት ባለሥልጣናት ሥልጣን ወንበር ላይ ሲቀመጡ ሕዝብን ለማገልገል እንጂ፣ በሕዝብ ለመገልገል ባለመሆኑ የሚመሯቸው ሰዎች ጥሩ ሐሳብ አፈለቁም አላፈለቁም ሉዓላዊነታቸውን ማክበር ይኖርባቸዋል፡፡

በመሠረቱ በአመለካከታቸው የበሰሉ ሰዎች ሐሳባቸውን ሕዝብ እንዲቀበላቸው ልዩ ልዩ ጥረት ቢያደርጉ የሚከለክላቸው የለም፡፡ ከሕዝብ አስተያየት በመነሳት ለመሥራት ቢነሱም፣ ያም የሕዝብ አስተያየት እንደምን በተግባር ላይ ሊውል እንደሚችል ከማሰብ ባሻገር ሊታይ ወይም ይህንን ሠርቻለሁ ለማለት ያህል ብቻ የሚሠራ ከሆነ ግን፣ ሥራው ጥሩ ቢሆንም እንኳን በሕዝብ ዘንድ ተቀባይነትን አያገኝም፡፡ ወይም ለጊዜው ለሕዝብ ጥቅም የማይውል ከሆነ ትርፉ ድካም ይሆናል፡፡ ይህንን አመለካከት በምሳሌ ማቅረብ ይቻል ዘንድ የቀድሞው መንግሥት ባለሥልጣናት በአርሲ ክፍለ ሀገር ገበሬዎችን በአንድ አካባቢ አሰባስበው ሥልጣኔ ለማስፋፋት ይፈልጋሉ፡፡ ይህንንም ሐሳባቸውን በተግባር ለማዋል ከአዲስ አበባ ሳይቀር ባህር ዛፍ እየተቆረጠ መንደሮቹ ወደሚሠሩበት ሥፍራ ይጓዛል፡፡ ወጣቱ፣ ወንዱ፣ ሴቱም ዘመተ፡፡ እያንዳንዳቸው 500 ቤተሰብ የሚይዙ መንደሮችም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሠሩ፡፡ የአካባቢው ገበሬዎችም የለመዱትና የሞቀ ቤታቸውን አፍርሰው ወደዱም ጠሉም በእነዚያ መንደሮች ጎጆ እየተሰጣቸው ገቡ፡፡ ያልለመዱትን መልመድና ብርዱን መቻል ነበረባቸው፡፡ እነዚህንም መንደሮች የቀድሞው ፕሬዚዳንት ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እየተዘዋወሩ ከጎበኟቸው በኋላ፣ ‹‹ማድረጋችን ካልቀረ በቆርቆሮ ቢሠሩ መልካም ነው፡፡ ለሌሎችም አርዓያ ይሆን ነበር፤›› ተባለ፡፡ ስሜታቸውን ተከትለው በጭፍን ይጓዙ የነበሩ ባለሥልጣናትም ‹‹ይበል›› አሉና መንደሮቹ ሁሉ እንደገና ፈርሰው ባለአራት ማዕዘን ቆርቆሮ ቤት ሆኑ፡፡ መኝታና ሳሎን ቤት ተለየላቸው፡፡ ከከብቱ ጋር ማደር ለለመደ ገብሬ ግን አዲሱ ኑሮ ፈጽሞ የሚስማማው አልሆነም፡፡ ዱብ ዕዳ ሆነበት፡፡ ቅሬታውንም በይፋ አሳወቀ፡፡ በመሠረቱ እንዲህ ያለው ችግር የተከሰተው በአገራችን ብቻ አይደለም፡፡ የሊቢያው መሪ ሙአመር ጋዳፊም ሕዝባቸውን የዘላንነት ኑሮውን ትቶ ቀለብ እየተሰፈረለት ሕንፃ ውስጥ በነፃ እንዲኖር ፈልገው ነበር፡፡ ዳሩ ግን ፍላጎት ብቻውን ውጤት ሊያስገኝ ባለመቻሉ የፈለጉት ሳይሆን ቀረ፡፡ ለታይታ የተደረጉ እነዚህ ብቻ አይደሉም፡፡ አንዳንድ ባለሥልጣናት መቶ ሺሕና ከዚያ በላይ ዋጋ ያላቸውን መኪናዎች አስፈላጊ ሲሆን ጭምር መንገድ በሌለባቸው ሥፍራዎች ያስገቧቸዋል፡፡ ድልድይ ባልተሠራበት ወንዝ ለዚያውም በክረምት እንዲያቋርጡ በማድረግ ለጎርፍ የሚዳርጉም አሉ፡፡ እነዚህ ሰዎች ምናልባት የሚፈጽሙት ስህተት ከቀና መንፈስ የመነጨ እንኳን ቢሆን፣ መሠረቱ ለታይታ ሲባል የተከናወነ ስለሚሆን ውጤቱ የሰመረ ሊሆን አይችልም፡፡

ሌላው ትኩረት ሊሰጥበት የሚገባው ጉዳይ ሰዎች በጎሳቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ ቋንቋቸው፣ በፖለቲካዊ አመለካከታቸው ሳይለዩ የመኖር መብት ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ አብረው እንዲኖሩ የሚያደርጋቸው በጋራ የሚከፋፈሉት ማኅበራዊ ልምድ ነው፡፡ ለምሳሌ ድሮ ከንባታና ሀዲያ በሚባለው አካባቢ የሚኖሩ ሕዝቦች ዘር ቆጥረው የእገሌ ጎሳ ነኝ የሚሉ ቢሆኑም፣ ከንባታው በሀድያ፣ ሀድያው በከንባታ የመኖር መብት አለው፡፡ የሽግግሩ መንግሥት አካባቢዎችን በብሔር ብሔረሰብ ሳይሆን በቋንቋ እንዲከለል ያደረገበት ዓይነተኛ ምክንያትም መሠረታዊ ትንታኔ ካለው አመለካከት፣ ይልቁንም በኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት የነበረውን የጭቆና አገዛዝ እንዲወገድ እንጂ፣ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሚፈልግበት ክልል፣ ወረዳና ቀበሌ እንዳይኖር አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን በየትኛውም ሥፍራ እንዳይኖሩ የሚከለክል ሕግም አልወጣም፡፡ አነስተኛም ሆነ ታላቅ ባለሥልጣንም ጠይቆ መረዳት እንጂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለማስፈን የሚደረገውን ጥረት በሚያደናቅፍ መንገድ መተርጎም እጅግ በጣም አደገኛ ነው፡፡ እንደ ቋንቋው ሁሉ ፖለቲካዊ አመለካከት፣ ርዕዮተ ዓለማዊ ግንዛቤ፣ እምነት፣ ወዘተ የግለሰቦችን መሠረታዊ መብት በማይነካ መንገድ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መንቀሳቀሱን ማከታተል ተገቢ ነው፡፡ ስለዚህም ባለሥልጣናት፣ በተለይም ዴሞክራሲያዊ አመለካከት ያላቸው የፖለቲካ ባለሥልጣናት የጎሳ፣ የብሔርና የብሔረሰብ ጥያቄ ይልቁንም አንዱ ሌላውን በኃይል አንበርክኮ የበላይ ለመሆን ፍላጎት ሲወርድ ሲወርድ የመጣ ሰብዓዊ ባህርይ መሆኑን አውቀው ለሰዎች ሁለንተናዊ ነፃነት፣ እኩልነትና በወንድማማችነት አብሮ መኖር ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይህ መሆን ሲገባው በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የራሳቸው ጎሳ ወይም ብሔረሰብ ወይም ብሔር ጎልቶ እንዲታይ መሞከር ሁከት የተሞላበት ማድረጉ የታወቀ ነው፡፡ የብዙዎቹ የዓለማችን የፖለቲካ ባለሥልጣናት ውድቀትም ከጠባብ አመለካከታቸው ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

እዚህ ላይ ክፉዎቹ ባለሥልጣናት በተለይም አምባገነን የድሮ ባለሥልጣናት የሚቀናቀኗቸውን፣ የሚነኩባቸውን፣ ግድፈታቸውን የሚነቅፉባቸውን፣ የማያምኑበትን ሥራ እንዲሠሩ ሲጠይቋቸው አይሆንም የሚሏቸውን ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖችን በልዩ ልዩ መንገዶች ያጠቁ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ‹‹ይህን ጥጋበኛ እሰርልኝ፣ ግረፍልኝ፣ ቅጣልኝ፤›› ማለትም የተለመደ ነበር፡፡ ሕግና ደንብ ቢኖርም የሚያገለግለው ለባለሥልጣናቱ ስለነበር ሕዝብ በዚህ ረገድ ሲበደል ቆይቷል፡፡ ዛሬ ዜጎችን ቀደም ሲል በነበረው መንገድ ማጥቃት ባይቻል በሕግ እያስታከኩ፣ ወይም ወንጀል እንዲሠሩ እየገፋፉ ወይም የሕጉን ትርጉም እያጣመሙ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ተግባር ማከናወን የማይቻልበት ሁኔታ የለም፡፡ ሁላችንም የአሮጌው ሥርዓት ውጤቶች እንደ መሆናችን መጠን ችግሩን ደረጃ በደረጃ ለማስወገድ ጥረት ካልተደረገ በስተቀር፣ አጭርና ቀጥተኛ መንገድ አይገኝለትም፡፡ መንግሥት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እገነባለሁ ሲልም የቀድሞ ፀረ ዴሞክራሲ አመለካከቶችን እያስወገድኩ፣ በዚህ ሒደት የሚከሰቱትን ስህተቶች እያረምኩ እጓዛለሁ ከማለት ውጪ ሊሆን አይችልም፡፡ ዋናው ቁም ነገር፣ የዴሞክራሲውን ሥርዓት ለመገንባት ታጥቀው የተነሱ ኃይሎች በሥልጣን ላይ ሆኑም አልሆኑም፣ ሕዝብ በተወካዮቹ አማካይነት የሥልጣኑ ተካፋይ ተቆጣጣሪ፣ ቢያሻው ነቃፊ፣ በሚፈልገው ሰው የመመራት የማይፈልገውን ደግሞ ከሥልጣን በማስወገድ ወሳኝ ሚና ያለው መሆኑን ማመኑ ላይ ነው፡፡ የፈላጭ ቆራጭ ዘውዳዊ፣ ወታደራዊና ብቸኛ ፓርቲ አገዛዝ ወድቆ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲመሠረት፣ ሰዎች ያለአንዳች ገደብ ሐሳባቸውን በነፃ እንዲያስተላልፉ፣ ተቃውሞአቸውንም ሆነ ድጋፋቸውን በሰላማዊ ሠልፍ እንዲገልጹ የአያሌ ታጋዮች ሕይወት ማለፉ፣ ኢትዮጵያውያን በሰው አገር ተሰደው እየተንከራተቱ ፀረ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገረሰስ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረጋቸው፣ የብዙዎች ማኅበራዊ ሕይወት መናጋቱ፣ በመጨረሻም ሕዝባዊ ሥርዓትን የሚመሠርት የሽግግር መንግሥት መቋቋሙ ለዚህ እንጂ በአምባገነን ሥርዓት ምትክ ሌላ አምባገነን ሥርዓት ለመተካት እንዳልሆነ መታወቅ አለበት፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣን ለሕዝብ ታማኝ ሲሆን፣ ሕዝብም ለባለሥልጣናቱ በገዛ ፍላጎቱ የሚተባበር፣ የመንግሥት ዕቅድንና መርሐ ግብርን በቅንነት የሚፈጽም፣ ለሕግና ለደንብ የሚገዛ ይሆናል፡፡

ከዚህ አንፃር ዙሪያ ዙሪያውን ከመሄድ ወጥተን የኢሕአዴግን አስተዳደር በቀጥታ እንገምግመው፡፡ በተለይም ባለፉት አሥርና አሥራ አምስት ዓመታት በማኅበራዊውና በኢኮኖሚው አውታር የተከናወኑት ዓበይት ተግባራት አመርቂና አኩሪ ናቸው ብሎ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ያምናል፡፡ በኢኮኖሚውና በማኅበራዊ አውታሩም ከፍተኛ ለውጥ አለ፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ብዙ ርቆ መሄድ አያስፈልግም፡፡ አዲስ አበባን ብቻ በማየት ለውጡን ማድነቅ ይቻላል፡፡ ቢሆኑም ገና ሥራ መጀመሩ ስለሆነ፣ «ይህንን ሠርተናልና እንኩራራለን የሚያስብል» አይደለም፡፡ መንግሥት ሥልጣን የሚይዘው ለመሥራት ነው፡፡ በዴሞክራሲያዊ አገሮች መንግሥት ካልሠራ ሕዝብ  ዴሞክራሲያ በሆነ መንገድ ሊሠራ የሚችል ሌላ ሊተካ ይችላል፡፡ ወይም በራሱ ፈቃድ ‹‹ለመሥራት ሞክሬ ነበር፣ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች አልቻልኩም፤›› በማለት ሥልጣኑን ይለቃል፡፡ በዴሞክራሲያዊ አገሮች ሥልጣን የነብር ጅራት ተደርጎ አይወሰድም፡፡ በዴሞክራሲ ምክንያት የሚነሱ ጥያቄዎችን ሁሉ በአንድ ጊዜ መፍታት ባይቻልም፣ ችግሮቹ እንዳሉ አምኖ ደረጃ በደረጃ እንደሚፈቱ ሕዝብን ማስረዳትና ማሳመንም አንድ ሥራ ነው፡፡ ‹‹እኔ የምነግርህን ስማ›› ማለት ብቻ ሳይሆን ማዳመጥ መቅደም ይኖርበታል፡፡ የዴሞክራሲያዊ መብት ጥሰቶች እንደሆኑ ተደርገው በየትኛውም ተቋም በሚገኙ አጭበርባሪዎች የሚቀርቡ ሐሳቦች ቢኖሩ፣ ምን ያህል ስህተት እንደሆኑ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት አድርጎ ማሳወቅ ነው፡፡ ዕርምጃ መውሰድ ነው፡፡ የኢሕአዴግን ካባ ደርበው የሕዝብን ችግር የሚያባብሱ ባለሥልጣናት ይኖሩ እንደሆነም በጥሩ መነጽር ማስተዋል ነው፡፡

ለምሳሌ ኢሕአዴግ ሀቁን ለሕዝብ ቀድሞ ለማቅረብ ባለመቻሉ ወይም እውነታውን በአስመሳዮች በመነጠቁ ምክንያት፣ በስንት ሰማዕታት ያካበተውን ፍቅር ምን ያህል እንደቀነሰ ወደ ሕዝብ ወረድ ብሎ ማየት ይኖርበታል፡፡ አባላት ባይሆኑም ኢሕአዴግ ሲነካ እንደ ንብ ሲናደፍ የነበረው የኅብረተሰብ ክፍል ዛሬ በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ መመርመር ይገባዋል፡፡ ከኢሕአዴግ ጋር ዝምድና የቋጠሩ ግለሰቦችና ቡድኖች ቋጠሮአቸውን ማጥበቃቸውን ወይም ማላላታቸውን ፈትሾ መረዳት መሠረታዊ ተግባሩ መሆን አለበት፡፡ አጋሮቹ ባላፈሰሱት ላብና ወዝ ጮማ የሚቆርጡና ውስኪ የሚያንቆረቁሩ፣ በተሾሙ በአጭር ጊዜ ውስጥ በዝርፊያ የራሳቸውን አዲስ መደብ የፈጠሩ፣ በዳኝነት ወንበር ላይ ተቀምጠው ፍርድ የሚገመድሉ፣ የመንግሥት የልማት ድርጅቶችን እንዲያለሙ ኃላፊነት ቢሰጣቸው የራሳቸውንና የወዳጅ ዘመዶቻቸውን ኪስ የሚያደልቡ ከሆኑ ድርጅቱ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አባባል ‹‹ፈንጂ ወረዳ›› ውስጥ ነው፡፡ ለመሆኑ ሕዝብ መንግሥት ያከናወናቸው መልካም ተግባራትን እንዳያደንቅ፣ ሕዝብ በሙሉ ልብ የልማት አጋር እንዳይሆንና መጪውን ብሩህ ዘመን እንዳያይ የሚያደርጉት እነዚህ ሰዎች ቢሆኑስ? ስለሆነም ሕዝብ የተገኘው ልማት የራሱ እንዲመስለው፣ የሰፈነው ሰላም አስተማማኝ መሆኑን እንዲቀበል፣ የተዘረጋው የዴሞክራሲ መድረክ ለአንድ ቡድን ወይም ለሌላ ሳይሆን፣ ለመላው ሕዝብ መሆኑን እንዲያምን ጓዳ ጎድጓዳውን መፈተሽ ይኖርበታል፡፡ ለመሆኑ በመጪው የምርጫ ዘመን ኢሕአዴግ ሥልጣኑን ይዞ ቢቀጥል (መቀጠል እንኳን ይቀጥላል) የቀን ጅቦቹን ምን ያደርጋቸዋል? የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ይህንን መሠረታዊ ጥያቄ የሚያቀርበው በዚህ ረገድ የሚወስደው ዕርምጃ ምን እንደሆነ በግልጽ ባለማሳወቁ ነው፡፡ ወይም ዳር ዳሩን ወይም በደምሳሳው ‹‹የአስተዳደር በደል መኖሩን ተገንዝበናል›› ከማለት በስተቀር ‹‹እነዚህ፣ እነዚህ፣ እነዚህ ችግሮች አሉብን፤ እነዚህንም ችግሮች በዚህ መንገድ እናስወግዳቸዋለን…›› በማለት ጠንከር ተደርጎ ሲነገር ባለመስማቱ ነው፡፡ በጉልበት ሳይሆን በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመጓዝ ታጥቆ መነሳቱን ሕዝብ ማመን የሚችለው ይህን በግልጽ ሲያሳውቅ ነው፡፡ 

የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ከ20 ዓመታት በፊት በጽሑፎቹ እንደጠቀሰው ሁሉ ዴሞክራሲያዊ አካሄድ ካለ፣ ተቀናቃኝ የፖለቲካ ድርጅቶች የኢሕአዴግን ድክመት አንድ በአንድ እየተነተኑ ባቀረቡ መጠን፣ ኢሕአዴግም የተቀናቃኞቹን ሕፀፅ ሳይሸፍን ወደ አደባባይ ስለሚያወጣ በዚህ አጋጣሚ ሕዝብ ድምፁን ለማን መስጠት እንደሚችል ይረዳል፡፡ ምንም እንኳን የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀናቃኞቻቸውን ጥሰው ለማለፍ በሚያደርጉት እሽቅድምድም ከፍተኛ ውካታ እንደሚኖር የተረጋገጠ ቢሆንም፣ የመንግሥትም ሆነ የግል ፕሬሶች ሕዝብ ትክክለኛውን አቅጣጫ ተከትሎ እንዲጓዝ ሐሳቦችን በሥልት ማስተናገድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የግል ፕሬሶች የተቀናቃኝ ልሳን አለመሆናቸው የሚረጋገጠው በዚህ ጊዜ እንደሆነ ሁሉ የመንግሥት ፕሬሶች የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ፕሬዚዳንት በነበሩበት ጊዜ እንደገለጹት፣ ፕሬሶች ሥልጣን ከያዘው ጋር ሁሉ በመሠለፍ የማያጨበጭቡ መሆናቸውን የሚያስመሰክሩት በዚህ ጊዜ (በምርጫ ጊዜ) ይሆናል፡፡ ሁሉም የፕሬስ ውጤቶች ነፃ ሐሳብን አስተናግደዋል፡፡ የተካሄደው ምርጫም ዴሞክራሲያዊ ነበር የሚባለውም በዚህ ጊዜ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ጠንካራ ሕጋዊ ተቃዋሚ ካልገጠመው በስተቀር አምባገነንነትን ማምጣቱ የማይቀር ይሆናል፡፡ ኦስዋልድ ስፔንግለር (1880 – 1936) የተባለ ጀርመናዊ ፈላስፋ፣ ‹‹ለመፈንዳት የቀረበ አብዮት የሚያመለክተው በገዥዎችና በተቃዋሚዎች ዘንድ ፖለቲካዊ የልብ ትርታው ካለመደማመጥ የሚነጭ መሆኑን፣ በሥልጣን ላይ ያለው ኃይል በዚህ ጊዜ ብልጥ ቢሆን አስፈላጊውን ዕርምጃ በመውሰድ አስተማማኝ ሁኔታ መፍጠር ይኖርበታል፡፡ እንደዚህ ያለው አዎንታዊ ዕርምጃ ባለመወሰዱ እ.ኤ.አ. በ1789 በፈረንሳይ፣ እ.ኤ.አ. በ1918 በጀርመን ጦርነት ተከስቷል፡፡ አሳዛኝ ውጤት የነበረው ሁኔታ የተከሰተው የፖለቲካ መሪዎች ስህተታቸውን በወቅቱ ለማየት ባለመቻላቸውና እንዲያዩ ጥረት ቢደረግም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ነው፡፡ በዚህም ሒደት ራሳቸውም መስዋዕት ከመሆን አልዳኑም፤›› ሲል አስገንዝቧል፡፡

ለብዙዎቻችን የአሁኑ የሕይወት ዘመን ብቻ ወሳኝ እየመሰለን በዚህ አቅጣጫ ብቻ ለመጓዝ እንፈልጋለን፡፡ ከታሪክ ተጠያቂነትም ለማምለጥ እንመኛለን፡፡ ነገር ግን ዶ/ር ጎድፍሬይቲ አንደርሰን ‹‹ዘ ፓስት ኢዝ ኦልዌይስ ፕረዘንት›› በተሰኘ መጽሐፋቸው እንደገለጹት፣ ማድረግ ያለብንና የሌለብን ከትናንት ታሪካችን ጋር የተያያዘ ስለሆነ ከታሪክ መማር ይኖርብናል፡፡ ታዲያ ታሪክ ምን ያስተምረናል? ከክርስቶስ ልደት በፊት 43 ዓመት ያህል ቀደም ብሎ የሞተው ሮማዊው ልሳነ መልካም ፖለቲከኛ፣ ፈላስፋና ጸሐፊ ሲሴሮ ከታሪክ መማር እጅግ አስፈላጊ መሆኑን አስመልክቶ በተወሰነ ጥልቅ አመለካከቱ፣ ‹‹ታሪክ ስላለፈው ጊዜ ትክክለኛ መረጃ የሚሰጥ፣ ሀቅ የሚፈነጥቅ፣ በቃል ያለን መሠረታዊ የሚያደርግ የዕለት ተዕለት ሕይወት መመርያ የሚሆን፣ የሩቅ ዘመንን ትኩስ ዜና የሚያቀርብልን ነው፤›› ሲል ይነግረናል፡፡ ከሮማዊው ሲሴሮ በፊት የነበሩ ሮማውያንም ሆኑ ግሪካውያንም ወደፊት የምናከናውነው ተግባር ካለፈው ታሪክ ተምረን መሆን እንደሚኖርበት አጥብቀው ያሳስቡናል፡፡

እንዴት በዴሞክራሲያዊ አመራር አገር መመራት እንዳለበት በስምንተኛው ክፍለ ዘመን ቅድመ ክርስቶስ የነበረው የስፓርታ ሕገ መንግሥት መሥራች ሊከርገስ፣ ከ639 እስከ 559 ዓ.ዓ. የነበረው አቴናዊው ሰሎን፣ ከ495 እስከ 429 ዓ.ዓ የነበረው አቴናዊው ፔርክልስ፣ ከ427 እስከ 347 ዓ.ዓ የነበረው ግሪካዊ ፕላቶ፣ ከ203 እስከ 130 ዓ.ዓ የነበረው ግሪካው የታሪክ ሰው ፓሊቢዬስ፣ ብዙ እጅግ በጣም ብዙ ያስተምሩናል፡፡ በአውሮፓውያን ማዕከላዊ የሥልጣኔ ዘመን የነበሩት እንደ ጆን ኦቭ ሳሊዝበሪ (1115 እስከ 1180) ያሉ እንግሊዛውያን፣ እንደ ሴንት ቶማስ አክዊናስ (1225 እስከ 1274) ያሉ ጣሊያናውያን፣ ‹‹ዱሞናርኪያ›› እንደጻፈው ዳንቴ አሊጊየሪ (1265 እስክ 1321) ያሉ ዕውቅ ደራስያን ብቻ ሳይሆኑ፣ ዕውቅ ፈላስፋና ታሪክን አገናዝበው የሚጽፉ ዜጎች መንግሥትና ሕዝብ በግራም ሆነ በቀኝ አዝማሚያ ተስፋፍተው ስህተት እንዳይፈጽሙ አስጠንቅቀዋል፡፡ የብዕራቸው ጫፍ የሚያመነጨው ሐሳብ ሌት ተቀን ያለዕረፍት የሚያስቡ አዕምሮአቸው ለሰዎች ጥቅም መሥራት እንዳለበት ያሳስቡናል፡፡ ስለሰማያዊው ሳይሆን ስለሰው ዓለም መንግሥት በተመለከተም በአመለካከታቸው ምጡቅ የነበሩ እንደነ ያኮፕ ክርስቶፍ ቡርካሃር (1818 እስከ 1897) ያሉ የስዊስ የታሪክ ሰዎች እንደ ጣሊያናዊው ኒኮሎ ማኪያቬሊ (1469 እስከ 1527) ያሉ እንደ ቶማስ ሆብስ (1588 እስከ 1679) ያሉ እንግሊዛውያን የዓለማችን የፖለቲካ መሪዎች፣ ‹‹መሪዎች›› ተብለው ሥልጣን የጨበጡ ምን ማድረግ እንዳለባቸው፣ ስለሰማያዊው አምላክ የሚያስተምሩም ወሰናቸው እስከ ምን ደረጃ እንደሆነ ማንንም ሳይፈሩ በሰላ ብዕራቸው አመልክተውን አልፈዋል፡፡

በኢንግላንድ የፓርላማና የፓርላማ ሰዎችን በሥልጣን ገደብ በሚመለከት ሰፊ ትንታኔ የሰጡት የሃይማኖት፣ የማኅበራዊ ኑሮ እኩልነት እንዲኖር ይታገሉ የነበሩት ሌቨረርስ (1647 እስከ 1649) እንኳን ብዙ የሚያካፍሉን ዕውቀት አላቸው፡፡ እንደ ጆን ሎክ (1632 እስከ 1704) ያሉ እንግሊዛውያን፣ እንደ ፈረንሳዊው ፈላስፋ ዣን ዣክ ሮሶ (1712 እስከ 78) ያሉ፣ እንደ ስኮትላንዳዊው ፈላስፋ ዴቪድ ሁም፣ እንደ እንግሊዛዊው ባለሥልጣንና የፖለቲካ ጸሐፊ ኢድመንድ ቡቲክ (1729 እስከ 97) ያሉ ሰዎች ሕዝብን አስማምቶ ማደር ማለት ምን ማለት እንደሆነ፣ የሲቪል መንግሥት ምን ማድረግና አለማድረግ እንዳለበት፣ በተለይም ደግሞ ከሌሎች ውድቀት ምን መማር እንደሚኖርብን ከተለያዩ አገሮች ታሪክ እየጠቀሱ በጣፋጭ ብዕራቸው ያስነብቡናል፡፡ በሐሳባቸው የጠለቀ ባህር ገብተን እንድንዋኝ ሲያደርጉን እንኳን አዕምሮአችንና አካላችንን የሚያፍታታ እንጂ የሚያደክምና እንዲሰለች አያደርጉም፡፡ እንዲያውም ከአንዱ ሐሳብ ወደሌላው፣ ከአሮጌው ወደ አዲሱ አመለካከት እየጠለቅን በሄድን ቁጥር የዕውቀታቸው ብርሃን የበለጠ እየፈነጠቀልን ስንወረውረው የነበረው አስተሳሰብ መሠረት እንዲኖረው፣ ከተወላገደ እንድናስተካክለው፣ ከተሳሳተ እንድናርመው ያደርገናል፡፡ ወኔ ብቻ የትም ስለማያደርስ ከታሪክ መማር የግድ ያስፈልጋል፡፡

እውነቱን ለመናገር በመላው ኢትዮጵያ የሚንቀሳቀስ ሰው በሄደበት ሁሉ የሚሰማው በመንግሥት ባለሥልጣናት ዘንድ የአፈጻጸም ችግር መኖሩን ነው፡፡ መንግሥትም ይህን አይክድም፡፡ ዳሩ ግን ‹‹የፖሊሲ ችግር ባለመኖሩ ችግሩ በሒደት የሚፈታ ነው፤›› በማለት ያስረዳል፡፡ እርግጥ ነው ለዘመናት የነበረ ችግር በአሥርና በሃያ ዓመታት አይፈታም፡፡ ለአንድ አገር ዕድገትም ጥሩ ፖሊሲ መኖር ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡ ጥሩ ፖሊሲ ከሌለ ልማት እውን ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ያን ፖሊሲ የሚያስፈጽም ሳይሆን፣ ሽባ የሚያደርግ ባለሥልጣን በየቦታው ካስቀመጡ፣ ወይም የሕዝብን ብሶት እያደመጡ አፋጣኝ ዕርምጃ ካልወሰዱ ወይም ትክክለኛ የአሠራር ሥርዓት ካልተዘረጋ የፖሊሲው መኖር ለአገሪቱና ለሕዝቡ ምኑ ነው? ፖሊሲውን ቀርጾ ፋይል ውስጥ ለማስቀመጥ ከሆነ በእርግጥም ፋይዳ የሌለው ፖሊሲ ይሆናል፡፡ በሩቁ ለማሳየት ከሆነ ደግሞ የአሜሪካ ፖሊሲም፣ የእንግሊዝ ፖሊሲም፣ የፈረንሳይ ፖሊሲም፣ የጀርመን ፖሊሲም በሩቁ ይታዩናል፡፡ ነገር ግን የእነሱ ፖሊሲዎች በሩቁ የምናያቸውና እያየን የምንጎመጃቸው ሲሆኑ፣ ፋይል ላይ የተቀመጡት የእኛ ፖሊሲዎች ካሉ ግን ተግባራዊ መሆንና የሥርዓቱን ፍትሐዊነት ማረጋገጥ አለባቸው፡፡ የአንድ ቀበሌ፣ የአንድ ወረዳ፣ ወይም ክልል ባለሥልጣን የተቀረፀውን ፖሊሲ በማወቅም ሆነ ባለማወቅ እየጣሰ በራሱ መንገድ እንደፈለገው እየሠራ ከሆነ ‹‹ተው! በሥልጣን ላይ የተቀመጥከው ለዚህ አይደለም፤›› ሊባል ይገባል፡፡ ቆመጥ ወይም ሌላ ይዞ የሚጓዝ ፖሊስ ያላግባብ ንፁኃን ዜጎችን የሚመታበት ወይም የሚያስፈራራበት፣ ወይም የሚኳሽበት ከሆነ ‹‹ተው! የሠለጠንከው ለዚህ አይደለም፤›› ሊባል ይገባል፡፡ ዳኛ በጉቦ፣ በምልጃና በፖለቲካ ወገንተኝነት ፍርድን የሚገመድል ከሆነ ‹‹ተው! ወንበሩ ላይ የተቀመጥከው ፍርድን ለመገምደል አይደለም፤›› መባል አለበት፡፡ ባለሥልጣናት አብዛኛውን ጊዜ በስብሰባ በማሳለፋቸው ባለጉዳዮች ይጉላሉ እንደሆነ ‹‹ተው! በስብሰባ ሰበብ ሕዝብን አታጉላሉ፤›› መባል አለባቸው፡፡ የመንግሥትና የግል ሚዲያዎች የሌለውን እንዳለ አስመስለው እያቀረቡ ሕዝብን ለማጭበርበር ይፈልጉ እንደሆነ፣ ‹‹ተው! በሙያው ሥነ ምግባር መሠረት ሥሩ፤›› ሊባሉ ይገባል፡፡ ሌሎችም እንደዚሁ፡፡

ስለዚህም የአሁኖቹም ሆኑ የወደፊት ባለሥልጣናት እ.ኤ.አ ከ1874 እስከ 1950 የነበረው ደብራዩኤል ማኬንዜንማ፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ማለት በአነስተኛው ትንታኔ የተሰባሰበ የሕዝብ አስተያየት ነው፡፡ አነስተኛውን ወይም ምንም አስተያየት የማይቀበል ግን በፍጥነትም ይሁን በቅርቡ ወደ ፈላጭ ቆራጭነት የሚቀየር ይሆናል፤›› እንዳሉት፣ ወይም ከ1882 እስከ 1945 የነበሩት አሜሪካዊው ፕሬዚዳንት ፍራንክሊን ዴላኖ ሩዝቬልት፣ ‹‹ታሪክ እንደሚያረጋግጠው አምባገነንነት ሊመሠረት የሚችለው ከጠንካራና ታማኝነቱ ውጤታማ ከሆነ መንግሥት ሳይሆን፣ ደካማና ተስፋ ቢስ ከሆነ መንግሥት ነው፡፡ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ ከሥጋትና ከረሃብ የሚያድናቸውን መንግሥት ካቋቋሙ ውጤታማ ይሆናሉ፡፡ ካላቋቋሙ ግን አይሆኑም፡፡ አንድና ትክክለኛ የሆነ የማያቋርጥ የነፃ መንገድ ሊኖር የሚችለው፣ የሕዝብን ፍላጎት ጠንካራ የሆነ መንግሥትና መንግሥትን ለመቆጣጠር መብቱን ያረጋገጠ ጠንካራና ማንኛውም መረጃ ያለው ሕዝብ ነው፤›› በማለት የገለጹት ትምህርት ነውና እንከተለው፡፡ ከ1842 እስከ 1910 የነበረው ዊልያም ጀምስ፣ ‹‹አገር ከአገሮች ሁሉ የበለጠ ቅድስት ልትባል የምትችለው እያንዳንዱን ቀን በጥቅም ላይ የሚያውል፣ ያለማንም ተፅዕኖ ተግባሩን የሚያከናውን፣ ገንቢ አስተያየትና ተቃውሞ የሚያቀርብ፣ ለሚደግፈው ድምፁን የሚሰጥ፣ ብልፅግናን በፍጥነት ለማምጣት የሚጥር ሕዝብ ሲሆን ነው፤›› ሲል ያሰፈረው ወርቅ አስተሳሰብም የዕለት ተዕለት መመርያችን አድርገን ልንወስደው ይገባል፡፡

ስለዚህም የመጪው ዘመን ባለሥልጣናት በጠንካራ የሕዝብ እምነት ሕዝብን በማስተባበር እንዲሠሩ፣ ረሃብንና እርዛትን ለማስወገድ የሚቻልበትን ዘዴ ረጋ ብለው እንዲቀይሱ፣ ሕዝብ አስተሳሰቡን በነፃ እንዲገልጽ እንዲያደርጉ፣ ዴሞክራሲ ከቃል ይልቅ በተግባር እንዲተረጎም እንዲያደርጉ የሚያስችላቸውን መንግሥት እንዲመሠርቱ የግለሰብ ጥሪ ይቀርብላቸዋል፡፡ ይህን ዘመን ታላቅ ትዕግሥትና ጥበብን በሚጠይቅ ችሎታ ለማለፍ ሲቻልም፣ የዚህ ዘመን ባለሥልጣናት በእርግጥም ታላላቅ ሰዎች ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ውድ አንባቢያን፣ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ኢሕአዴግን ወይም ሌሎችን የፖለቲካ ድርጅቶች ለመንቀፍ ወይም ለመደገፍ አይደለም፡፡ ጸሐፊውም ኑሮው በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኝ፣ ዝናብ በሚያንጠባጥብ ጣራ ሥር ተቀምጦ የሚጽፍ ነገር ግን ደስተኛ ነው፡፡ ጸሐፊው በአሁኑ ጊዜ ካሉት የፖለቲካ ድርጅቶች የአንዱ አባል እንዳልሆነም ያረጋግጣል፡፡ ጽሑፉ የመነጨውም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ሆኖ ከማየት ጉጉት ነው፡፡ ካጠፋ ‹‹ዓፉ ወይም ይቅር›› በሉት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...