Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ተሟገትመፍራትስ የራስን ብቸኛ አሸናፊነት ነው

መፍራትስ የራስን ብቸኛ አሸናፊነት ነው

ቀን:

በቶላ ሊካሳ

የኢትዮጵያ የምርጫ ሥርዓት ተዋናዮች፣ ተሳታፊዎችና “አላፊ አግዳሚዎች” ጭምር የምርጫ 2007ን ቅድመ ምርጫ ግምገማ ለማድረግ የአንድ ቀን መጅሊስ ካደረጉበት ወቅት ቀደም ብሎ ጀምሮ የተነሳ አንድ ጉዳይ የዛሬውን እሑድ የሚመለከት ነበር፡፡ ግንቦት ዘጠኝ ራሱ የኢትዮጵያ የ2007 ምርጫ ቅድመ ምርጫ ጭብጥ ሆነ ማለት ነው፡፡

የዛሬ ሳምንቱ የእሑድ ግንቦት 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ሪፖርተር ጋዜጣ ራሱ ጉዳዩን “ምርጫ ቦርድ ግንቦት 9 ቀን ሠልፍም ሆነ ስብሰባ ማድረግ እንደማይቻል አስታወቀ” በማለት ዘግቦት ነበር፡፡ በዜናው ውስጥ የተወሳውን በአንድ ፓርቲና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መካከል የተነሳውን የዚህን የመከረኛ የሰለማዊ ሠልፍና የአደባባይ ተቃውሞ የሚመለከት አተካሮ ጉዳይ ለጊዜው ወደ ጎን ትተን፣ ወደ ዛሬው ዋና ጉዳያችን የምናመራው ግን የሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ የፖለቲካ ስብሰባ ነገር አሁንም የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ፖለቲካ (የምርጫም ጭምር) የጎን ውጋት ሆኖ መቀጠሉን ሳንዘነጋ ነው፡፡ አለመዘንጋታችንን እያስመዘገብን ነው፡፡

- Advertisement -

የግንቦት ወር በአገራችን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳ ውስጥ ልዩ ቦታ ያለው ወር ነው፡፡ ይህ የሆነው በአጋጣሚ ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥታዊ ቅንጅት በተበጀለት አሠራር ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመንና የሥራ ጊዜ ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሠረት የምክር ቤቱ የሥራ ጊዜ ከመስከረም ወር የመጨረሻ ሳምንት ሰኞ እስከ ሰኔ ሰላሳ ድረስ ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጠው ለአምስት ዓመታት ሲሆን፣ ይህ የአምስት ዓመት የሥራ ዘመኑ ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሄዶ መጠናቀቅ አለበት፡፡

ይህ በሕገ መንግሥቱ በራሱ ውስጥ የተጻፈና የተሰጠ የጊዜ ሰሌዳ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሰኔ ሰላሳ ላይ የሚያበቃ የአንድ ምክር ቤት የሥራ ዘመን ቢያንስ ከሰኔ አንድ ቀን በፊት አዲስ ምክር ቤት መምረጥ ስላለበት ግንቦት ከወራት ሁሉ ልዩ ቢሆን፣ እንደ ግንቦት ሰባት ያለ ልዩ ስም እና ልዩ ትዝታ ያለው ቀን ቢያስመዘግብ የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም፡፡

በነገራችን ላይ ከወራት ሁሉ ግንቦትን ካነሳንበት አግባብ ይልቅ ከግንቦት ውስጥ ግንቦት ሰባትን እንዲህ አድርገን በማውሳታችን ሀራጥቃ (heretic) አድርገው የሚቆጥሩ፣ ግንቦት ሰባትን እንዳወደስን ወይም እንዳገነንን አድርገው የሚፈሩ መኖራቸው የአገራችን ፖለቲካ የሕመም ምልክት ነው፡፡ ግንቦት ሰባት ከተባለው ድርጅት እንጀምር፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር  ቤት በመንግሥት አቅራቢነት በሽብርተኝነት ከፈረጃቸው ድርጅቶች መካከል አንዱ ግንቦት ሰባት መሆኑ የ“አደባባይ ምስጢር” ብቻ አይደለም፡፡ የአደባባይ ውሳኔ፣ አገር ለሕዝቡ፣ አገር ለመላው ዓለም ያስታወቀው መልዕክት ነው፡፡ ይህ ራሱ ስለድርጅቱ ያስወራል፡፡

ድርጅቱ በፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ እንደተደነገገው በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ የሽብርተኝነት ወንጀል ፈጽሟል፣ የሽብርተኝነት ወንጀል ለመፈጸም ተዘጋጅቷል፣ ሽብርተኝነትን አበረታትቷል፣ ወይም ደግፏል፣ ወይም በሌላ መንገድ ከሽብርተኝነት ጋር ተያያዥነት ያለው ሆኖ ተገኝቷል ተብሎ በሽብርተኝነት ድርጅትነት መሰየሙ ብቻ በገዛ ራሱ ምክንያት ግን “ግንቦት ሰባት”ን ማለትም ስያሜውን ሐረጉን ውጉዝ ከመአርዮስ የሚያደርግ አይደለም፡፡

ማንም ሰው በስሙ ነገደ፣ ስሙን አልይ አልሰማ አለ በተለይ ግንቦት 7 ቀን 1997 ዓ.ም. የሕዝብ ቀን ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ሕዝብ የዴሞክራሲ ትግል ታሪክ ውስጥ ትልቅ ቦታ ያለውና ሊዘከር የሚገባ ነው፡፡ ዛሬ ድረስ በየፊናችን በጄ ያላልነው ብዙ ቁም ነገርም አስጨብጦናል፡፡

የግንቦት ሰባት የዕለቱ ጉዳይ ሲወራና ሲነገር ከምርጫ 97 አጠቃላይ ማዕቀፍ ውስጥ የሚነጠል አይደለም፡፡ የምርጫ 97 መሰናዶ፣ ብዙ ጭቃ ያወጣው ክርክሩና ቅስቀሳው፣ የመጨረሻው የዋንጫ ግጥሚያው ሁሉ የግንቦት ሰባት መነሻዎች ነበሩ፡፡ እስኪ ጥቂት የዕለቱን ውሎ እንመልከት

“እንከን የለሽና ሰላማዊ ምርጫ” የአገር ብሔራዊ መዝሙር ቢሆንም፣ ይህ የአስመሳይነትና ልብስና ጓንት እንዳይደርብ ሁሉም ቆቅ ሆኖ ጠበቀ፡፡ በምርጫ ቦርድ የመጨረሻ ሰዓት ገለጻ ሳይወሰኑ፣ ባመራረጥ ላለመሳሳት መራጮችና ሕዝብ የበኩላቸውን ዝግጅት አደረጉ፡፡ ዓይናቸውን አነቁ፤ ከሌሊቱ አሥር እና አሥራ አንድ ሰዓት ጀምሮ ሕዝብ ሠልፍ ያዘ፡፡ በጎታታ መስተንግዶና በጊዜያዊ መስተጓጎል ሳይመረርና ለሁከት ማመካኛ ሳይሆን እንዲያውም መላ እያማከረ፣ ከደንብ ውጪ የሆኑና አጠራጣሪ ድርጊቶችን (አድሏዊ ገለጻን፣ ጣልቃ ገብነትን፣ ምልክት የተደረገባቸው የተባሉ የምርጫ ወረቀቶችን፣ የሚለቅ የጣት ቀለምን፣ ወዘተ) እዚያው በዚያው እየጠቆመ፣ በስልክና በመልዕክተኛ እያጋለጠ ቁርሴና ምሳዬ ሳይል ታገለ፡፡ ሰላማዊና ጨዋ ትግል፡፡ አልጋ የያዙ ሕመምተኞች ተደግፈው፣ ትኩስ ሐዘንተኞች እንባቸውን ውጠው፣ ያልጠኑ አራሶች ወገባቸውን አስረው ድምፅ ሰጡ፡፡

የምርጫው ማክተሚያ (12 ሰዓት) እየቀረበ ሲመጣ ሕዝብ ድምፁን ሳይሰጥ ላለመሄድ በተለያየ መንገድ አሁንም ሕጋዊና ሰላማዊ ተፅዕኖ አደረገ፡፡ አሥራ ሁለት ሰዓት ላይ በምርጫ ጣቢያ የተገኘ መራጭ ሁሉ ሳይመርጥ አይሄድም በሚለው የምርጫ ደንብ የመጠቀም ዕድሉንና መብቱን ላለማጣት ብርድን፣ ድካምንና እንቅልፍን አሸንፎ እስከ እኩለ ሌሊት እስከ ዘጠኝና አሥራ አንድ ሰዓት ድረስ ድምፅ ሰጠ፡፡ ምርጫ ካበቃም በኋላ በድምፅ ቆጠራ ላይም ማጭበርበር እንዳይፈጸም አሁንም በሕጉ ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ አስደናቂና ታይቶ የማይታወቅ ፍጥጫና ትንቅንቅ ሲካሄድ ታየ፡፡ በዚህ አማካይነት የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ያህል እንደተንገሸገሸ፣ ፍትሕና ዴሞክራሲን ምን ያህል እንደተጠማ ለኢትዮጵያ ፖለቲከኞችና ለዓለም አሳወቀ፡፡

ድምፅ የመስጠት ሂደቱ ከቦታ ቦታ እንደነበረው ልዩነትና ርዝማኔ እሑድ ማታን አካትቶ ሰኞ አጥቢያ ድረስ ሄዷል፡፡ በዚህ መካከል እሑድ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት ላይ መንግሥት በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አንደበት የአዲስ አበባና የአካባቢው የፀጥታ ኃይሎች ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ በሆነ አንድ ወጥ ዕዝ ሥር መግባታቸውንና የአንድ ወር የሠልፍና ከቤት ውጪ ስብሰባ መከልከሉ “ታወጀ” ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ

“መላ የአገራች ሕዝቦች መብታቸውን አስከብረውና በድምፃቸው ተጠቅመው መንግሥታቸውን ለሦስተኛ ጊዜ በሚያቋቁመበት በአሁኑ ጊዜ፣ ከጥንቃቄ ጉድለት በሰውም ሆነ በንብረት ላይ ጉዳት እንዲደርስ መፍቀድ እንደሌለብን በማመን በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች በሙሉ በአንድ ዕዝ ሥር ገብተው ተጠሪነታቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዲሆን” መደረጉን፣

“አዲስ አበባ በሰባት የፀጥታ ቀጣናዎችና በበርካታ ንዑስ ቀጣናዎች ተከፋፍላ የመላውን የኅብረተሰብ፣ ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል አስተማማኝ ፀጥታ እንዲኖራት ለማድረግ አስፈላጊው ዝግጅት ሁሉ መጠናቀቁን፣

“የከተማው የሲቪል አስተዳደር ፀጥታን በተመለከተ ከተቋቋመው ዕዝ ጋር ተባብሮ እንዲሠራ›› መደረጉን፣

“ይህ በዚህ እንዳለ ሕዝቡ በመብቱ ተጠቅሞ የሰጠው ድምፅ ተቆጥሮ በምርጫ ቦርዱ በይፋ የሚገለጽበት ሁኔታ ሰላማዊና አንዳችም ግርግር የሌለበት እንዲሆን ለማድረግ ሲባል፣ በአዲስ አበባ ከተማ እንደ ሁኔታው እየታየ ማስተካከያ ሊደረግበት የሚችል … ለአንድ ወር ሠልፍና ከቤት ውጪ የሚደረግ ሕዝባዊ ስብሰባ” [ከግንቦት 8 ቀን 1997 ዓ.ም.] መከልከሉን፣

“የሕዝቡን ውሳኔ በትዕግሥትና በፀጋ ለመቀበል ባለመፈለግ ይህን መመርያ ተላልፎ በሚገኝ ክፍል ላይ የፀጥታ አስከባሪ ኃይሎች ጥብቅ ዕርምጃ እንዲወስዱ መመርያ” መተላለፉን ገልጸው፣

“በመጨረሻም መላው የአገራችን ሕዝቦች በታሪካቸው ታይቶ በማይታወቅ ደረጃ ዴሞክራሲያዊ ምርጫ ለማካሄድና የውጤቱም ተጠቃሚዎች ለመሆን በመቻላቸው፣ እንኳን ደስ ያላችሁ እያልኩ ከምርጫው ማግሥት ጀምሮ መደበኛ ሥራችሁን በተረጋጋ መንፈስ እንድታከናውኑ አሳስባለሁ፤” አሉ፡፡

ከምርጫው ዕለት በኋላ ብዙ ነገር ድብልቅልቁ ወጥቷል፡፡ የተሰናባቹ ፓርላማ የሥራ ዘመን ከማብቃቱ ከአንድ ወር በፊት አዲስ ምርጫ ተካሂዶ መጠናቀቁ ቀርቶ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን በተቋቋመበት ሕግ ዕውቅና ያገኘው ችግር ራሱ “የሰኔ 1 ቀን 1997 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከጥቅምት 22 እስከ ኅዳር 1 ቀን እንደዚሁም ከኅዳር 5 እስከ ኅዳር 7 ቀን 1998 ዓ.ም. በአዲስ አበባና በአንዳንድ የአገራችን አካባቢዎች ተከስቶ የነበረውን ሁከት” አስከተለ፡፡ ተቃዋሚዎችን ብቻ (ከአንድ ወንበር በስተቀር) የመረጠው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ፋይዳ ቢስ ሆኖ ቀረ፡፡ ጭራሹኑ ወደ አዳማ ዞሮ የነበረው የኦሮሚያ ክልል መቀመጫ መልሶ ወደ አዲስ አበባ መጣ፡፡ ብቸኛው የአገሪቱ የፌዴራል ግዛት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት አባላት ምርጫ ከአገር አጠቃላይ ምርጫ ወጥቶ ከአካባቢ ምርጫዎች ጋር ሠልፍ ገባና በዚያው ቀረ፡፡ ወዘተ.

ከምርጫ 97 በኋላ እና በእሱ ምክንያት የመጣው ችግር ሰፊና ውስብስብ ቢሆንም፣ ግንቦት ሰባት በዴሞክራሲያዊ ትግል ታሪካችን ውስጥ ያለው ቦታ ከፍተኛ ነው፡፡ ያስጨበጠንም ቁም ነገር ገና አሟጠን ያልጨረስነው ምናልባትም ማጣጣም፣ ያልጀመርነው ፋይዳ ያለው ነው፡፡

ከሌሎች መካከል

  • የምርጫ አስፈጻሚዎች በፓርቲ ተልዕኮ ሥር መሆናቸውንና የነበረው መዋቅር ነፃ ምርጫም ሆነ ዕርማት የማካሄድ ብቃት እንደሚጎድለው አጋለጠ፡፡ የተሻለ ነፃነት ያለው የአባላቱም ስብስብና የሥራ ቆይታ ጊዜ የፓርቲዎችንና የሕዝብን ልብ የረታ አዲስ የምርጫ አስፈጻሚ አካል የማደራጀትን አስፈላጊነት ቁልጭ አድርጎ አመለከተ፡፡
  • የፍትሕ፣ የነፃነትና የዴሞክራሲ ጥማት ሲባልና ፖሊስ፣ ፖሊስና ወታደር፣ ብሔርና ሃይማኖት የማይል የመላ ሕዝብ ጥማት መሆኑን ቁልጭ አድርጎ መሰከረ፡፡
  • በግዳጅ፣ በቅጥፈትና በፖለቲካ ጉቦ እያወናበዱ በሰላም ማጣትና በጦርነት እያስፈራሩ መግዛት የማይቻል መሆኑን ያንን ሁሉ የቅድመ ምርጫ፣ የስብሰባና የሠልፍ ቴአትር ባዶ አስቀርቶ እውነቱን ፍርጥ አድርጎ ያሳየ ምርጫ ነበር፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ አገሪቷንና ሕዝቦቿን በተባበረ ፖለቲካ ጠቅልሎ የሚመራ ኃይል በሌለበት ብልጣ ብልጥነትና የአጋጣሚ አድፋጭነት ሁሉ በሚላወስበት ሁኔታ ውስጥ፣ ኢሕአዴግንና ተቃዋሚዎችን አንድ ምክር ቤት ውስጥ ከትቶ ጉድ ሊያሳይ ለፈተና ያቀረበ ምርጫ ነበር፡፡

ያ ምርጫ ራሱ የግንቦት ሰባት ምርጫም ሆነ ሌላ ማንኛውም ምርጫ የኢትዮጵያ የህልውና ቁርጥ የሚታወቅበት ምርጫ ነው የሚል ግምት ተስፋና ግምገማ ጭራሽ አሳሳች መሆኑን ጭምር ምስክር ሆኖ አረጋገጠ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ደጋግመው ይሉት እንደነበረው የጥፋት አማራጭ መሸነፍ አለበት፡፡ ይህ ግን ሁሉንም ወገን የሚመለከት ነው፡፡ የጥፋት አማራጭ የሚሸነፈውም በድምፅ ብልጫ ሳይሆን፣ በየትኛውም ወገን ውስጥ ባሉ ዴሞክራቶች ትግል ነው፡፡

ምርጫ 97 በዴሞክራሲ ትግሉ ውስጥ ልዩ ቦታ ያለው ምዕራፍ መሆኑ እውነት ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ምርጫ 97 እንዳረጋገጠው የኢትዮጵያ ሕዝቦች መጪ ዕጣ የተንጠለጠለው በአንዱ ወይም በሌላው ምርጫ ወይም በአንድ ቡድን መውረድና መውጣት ላይ ሳይሆን፣ ያሉት የፖለቲካ ቡድኖች ሁሉ የሕዝቦችን እውነታና ፍላጎት ለማጤንና ተደጋግፎ ኃላፊነትን ለመሸከም በመቻል ላይ ነው፡፡ ዛሬ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደርና ዕድገት፣ ሰላምና አገር አለኝ ብሎ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ መሆኑ የማይድበሰበስ ሀቅ ነው፡፡ ይህ የዛሬው የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ለምሳሌ በ1990 ዓ.ም. በኢትዮ ኤርትራ ግጭት ጊዜ ከነበረው እጅግ የከበደ ነው፡፡ የሚጠይቀውም የመላ ሕዝቦችንና ምሁራንን ንቅናቄ ከምንጊዜው የላቀ እንጂ ያነሰ አይደለም፡፡ ከልካይና ተከልካይ ሊኖር የማይችልበት፣ ትችት ደርድሮ ኃላፊነቴን ተወጣሁ ወይም ሥልጣን አላገኘሁ፣ ፓርላማ አልገባሁ ብሎ ዘወር የማይባልበት ከገዢዎች ጋር አመለካከታችንና አቋማችን አይታረቅም በሚል ሰበብ ተመልካች የማይኮንበት አገራዊ ተልዕኮ ነው፡፡ ትልቁ ፈተና ይህ ነው፡፡

የድምፅ ብልጫ ‹‹አግኝቻለሁ›› እና ሥልጣንን ለብቻዬ እጠቀልላለሁ ማለት በዚህ ተልዕኮ ላይ ጉዳት ያስከትላል፡፡ እኔ ብቻ ልክ ሁሉንም ዘርፍ በእኔ ሰዎች ልቆጣጠር ባይነትና በግዴታና በማንቀጥቀጥ ልማትን ለማምጣት መሞከር ፋይዳ ቢስ መሆኑም ሲበዛ ታይቷል፡፡ በዚህ ረገድ እኔ ብቻ ባይነት የኢሕአዴግ የችግሮች ሁሉ ችግር ነው፡፡ ኢሕአዴግ እኔ ብቻ ካልገዛሁ፣ ሁሉንም እንቅስቃሴ ተቀጥላዬ ካላደረግሁ የሚል ድርቅነው በቀላሉ የሚበገር አይደለም፡፡ አገር ከወታደራዊው አገዛዝ የተላቀቀበት ለውጥ የኔ ብቻ የመስዋዕትነት ውጤት ነው፡፡ የሕዝቦችን ጥቅም የምወክልና የማራምድም እኔው ብቻ ነኝ፡፡ የእኔን መስመር የተቃረነ ጠላት (ኢሠፓ፣ ትምክህተኛ፣ ጠባብ፣ አሸባሪ) ነው ማለት የኢሕአዴግ እኔ ብቻ ባይነት ችግር ነው፡፡

ሥልጣንና ትክክለኛነት የእኔ ብቻ ከሚል እምነትና አመለካከት ኢሕአዴግ እስካልተገላገለ ድረስ ዴሞክራሲን የመገንባትና ልማትን የማምጣት፣ ሙስናን የመዋጋት ሚና ሊጫወት አይችልም፡፡ ዛሬ ብዙም አይሰማም እንጂ ዱሮ ኢሕአዴግ በየመድረኩ ነጋ ጠባ እንደሚለው ዴሞክራሲ በአንድ ድርጅት በጎ ፈቃድ ላይ የሚንጠላጠል ጧት ሰጥቶ ከሰዓት ሊከለከለው የሚችለው መሆን የለበትም፡፡ በአንድ ወቅት (እነሆ ስለ ኢሕአዴግ ሲናወራ ከዕለታት አንድ ቀን ማለት ጀመርን) የኢሕአዴግ መሪ በ1994 ዓ.ም. ክረምት ውስጥ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ከምሁራን ጋር ባደረጉት ውይይት እንደተናገሩትም፣ የኢሕአዴግ ወደ ፍፁማዊ አገዛዝ (አውቶክራሲ) መውረድ ለድርጅቱም ለአገሪቱም በእሳት ተበልቶ የመጥፋት አደጋ መሆኑ አሁንም እውነት ነው፡፡ ምክንያቱም ህልውናችን ከኢሕአዴግ ጋር ስለተጣበቀ፣ ከኢሕአዴግ በጎ ፈቃድ የወጣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እስካሁን ሊደራጅ ባለመቻሉ ነው፡፡ መፍራት ይህንን ነው፡፡

አቶ መለስ በአንድ ወቅት የተናገሩለት የዚያ “ፍፁማዊ አገዛዝ” አደጋ እንዳፈጠጠ መቆየቱ፣ ጠንቶና ተጠናክሮ የሚቆይበት ሌላም አስፈሪ ሁኔታ አለ፡፡ ይህንን አፍረጥርጦ መግለጽና መነጋገር ያስፈልጋል፡፡ የኢሕአዴግ አባላት የድርጅቱ የገደል ማሚቴዎች ናቸው፡፡ የድርጅቱ አቋምና አካሄድ ፈታይ የድርጅቱ ቁንጮ አመራር ነው፡፡ የድርጅቱ ቁንጮ አመራር ደግሞ የመንግሥታዊ ሥልጣኑም ቁንጮ ነው፡፡ ሕግ የማውጣት፣ አስፈጻሚውን የመንግሥት የሥልጣን አካል የመመርመርና የመጠየቅ፣ ሕግ ተርጓሚውን የመሾምና መንግሥታዊ የመገናኛ ብዙኃንን የመምራት ሥልጣን በሕግ አለው የሚባለውና በኢሕአዴግ ተመራጮች የተሞላው ፓርላማ ዞሮ ዞሮ በፓርቲው የበላይ አመራር መዳፍ ውስጥ ነው፡፡ ኢሕአዴግን የሚመሩት የአመራር አባላት የመንግሥቱን ሥራ አስፈጻሚ የሥልጣን አካል ይመራሉ፡፡ በኢሕአዴግ የእትብት ቧንቧ አማካይነት ደግሞ በፓርላማው ውስጥ ያሉትን ተወካዮች ያዛሉ፡፡ መናገር፣ መደገፍና መቃወም ያለባቸውን ይሰፍሩላቸዋል፡፡ በአጭሩ ሥራ የማስፈጸሙም፣ ሥራ አስፈጻሚውን የመመርመርና የመጠየቅ፣ ሕግ የማውጣትና ዳኛ የመሾሙ ሥራ ሁሉ በአንድ ቡድን እጅ ውስጥ ነው ማለት ነው፡፡ በዚህ ምክንያትና ይህ እስከቀጠለ ድረስ የተባለው አደጋ እንዳንዣበበና እንደተጠመደ ይቆያል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን የመበስበስ/የመሰንጠቅ ችግሩ የራሱ የፓርቲው ችግር ብቻ ሆኖ የሚቀርበት ሁኔታ እስካልተፈጠረ፣ ማለትም ፀረ ዴሞክራሲን የማስፈን ሙከራ ሲታይ ወይም የገዢው ፓርቲ ፍላጎት ከሕዝብ ሲቃረን፣ ሕዝብ ሳያሸማቀቅ የሚቃወምበትና አውርዶ ዘጭ የሚያደርግበት፣ ገዢው በእንቢተኝነት ሊቆይ የማይችልበት (የመከላከያውንና የፀጥታውን ኃይል የቡድናዊ ፖለቲካው ተቀጥላ አድርጎ መጠቀም የማይችልበት) ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር እስካልተገነባ ድረስ የገዢው ፓርቲ ዳፋ የአገር ዕዳ መሆኑ አይቀርም፡፡

ኢሕአዴግ መንግሥትን በኃይል የመጣልና የመተካት ታሪክ መቆም አለበት ባይ ነው፡፡ እውነትም ነው፡፡ ትክክልም ነው፡፡ የመከላከያ ኃይልን ለመንግሥት ግልበጣ ማገልገል መፈቀድ እንደሌለበት ሁሉ ሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት አደጋ ላይ ነው በማለት የጨነቀው ገዢ የሚያካሂደውን ሕገወጥነት ነቅቶ መጠበቅና ማቆምም በተመሳሳይ ስም የሚጠራ ኢሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡ የኢሕአዴግ አገራዊ መግባባት የመፍጠር ሙከራው “እኔ በገነባሁት ሥርዓት ውስጥ በምርጫ እንጂ በጉልበት ልትጥሉኝ አትሞክሩ” ዓይነት መሆኑ ችግር አይደለም፡፡ ያለውን ሕገ መንግሥትና የምርጫ ሥርዓት ሁሉም የእኔ ብሎ እንዲቀበለው የማድረግ ዘመቻም አለው፡፡

በአሁኑ ወቅት ያለው ችግር ግን ሕገ መንግሥቱን የመቀበልና ያለመቀበል ጉዳይ ሳይሆን፣ ሕገ መንግሥቱን የተቀበለም ሆነ መለወጡን የሚፈልግ ሁሉ ፍላጎቴን ይዞ ለመታገልና ለመወዳደር ያስችለዋል ብሎ የሚያምንበት ዴሞክራሲያዊ ሁኔታ የመኖርና ያለመኖር ጉዳይ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ፣ እስከዛሬ ድረስ ሁሌም የሚነሳውና የሚባለው ግልጽ ጉዳይ ነፃ ምርጫ እየተካሄደ አይደለም፣ ምርጫ ቦርድ በቀጥታም ሆነ በእጅ አዙር በኢሕአዴግ ቁጥጥር ሥር ነው፣ የመንግሥት የመገናኛ ዘዴዎች አጠቃቀም በኢሕአዴግ የተዋጠ ነው፣ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና ዕጩ ተወዳዳሪዎች እንግልት ይደርስባቸዋል፣ ወዘተ. ነው፡፡

ለስሞታውና ለክሱ ምንጭ የሆነውን ምክንያት ከሥር መንቀል ካልተቻለ የመንግሥት ተቃዋሚዎችን ሙልጭ ባለ ውሸት ማሳጣትና “በስም ማጥፋት ወንጀል” ማስፈራራት መፍትሔ አይደለም፡፡ ሐሜቱንና ስሞታውን ከሥር ከመሠረቱ ማስወገድ እንኳንስ የሕጋዊዎቹን ተቃዋሚዎች ሠልፍ ለማስተካከል ጥይት የሚተኩሱትንም ወደ ሰላማዊው መድረክ ይስባል፣ ወይም ወደ ክስመት ይመራል፡፡ “አገራዊ መግባባታችን” ይህን ቆራጥ ማሻሻያ መጎናፀፍ አቅቶታል፡፡ ኢሕአዴግ ተቃዋሚዎችን የማመናመንም ሆነ ተባባሪዎቹ የማድረግ አስተዋይነት በጭራሽ አልታየበትም፡፡ ይልቁንም ተቃዋሚዎች ተመርረውና ተማረው ወደ ስደትና ወደ ጫካ ቢሄዱ እንደተገላገላቸው ቆጥሮ ደስ የሚለው ይመስላል፡፡ ተቃዋሚዎች የፖለቲካ ስህተት ፈጽመው በሕገወጥነት አዋርዶና አግዶ ለማወራረድና በተለያየ ሥልት ከፋፍሎ አንዱን በሌላው ለመምታትም የሚተጋ ይመስላል፡፡

ኢትዮጵያ ምርጫ በደገሰች ቁጥር በተለይም ከምርጫ 97 በኋላ የሚታየው “የወዳጅ ዘመዱ” የመሰናዶ ግርግርና ሥጋት ከሚገባው በላይ፣ ምናልባትም የማይገባውን እንዲያውም የሌለውን ትኩረት ካላገኘሁ ሞቼ እገኛለሁ ሲል ይታያል፡፡

እሑድ ግንቦት 9 ቀን 2007 ዓ.ም. “ስለድምፅ አሰጣጡ ሒደት ለመራጮች የአንድ ቀን ገለጻ በየቀበሌው የሚሰጥበት ዕለት” በመሆኑ ማንኛቸውም ዓይነት ይህን ፕሮግራም ሊያደናቅፍ የሚችል ሠልፍ ማካሄድም ሆነ ስብሰባ መጥራት እንደማይቻል ምርጫ ቦርድ ማስታወቁን ሪፖርተር (ግንቦት 2) ዘግቦ አይተናል፡፡ የምርጫ ቦርዱ ሊቀመንበርም መንግሥት ክልከላውን ተግባራዊ በማድረግ የገዛ ራሱን ሕግ እንዲያስከብር በቴሌቪዥን ሲያስጠነቅቁ ሰምተናል፡፡ ለምርጫ 2007 ግንቦት 9 ማለት የምርጫ 97 ሚያዝያ 29 እና ሚያዝያ 30 ማለት ነው፡፡ እነዚህ ቀናት ምን እንደነበሩ ገና የአሥር ዓመት የቅርብ ጊዜ ትዝታዎች ናቸው፡፡

በዚህ ዓይነት ዕርምጃ አማካይነት ቅድመ ምርጫ እንቅስቃሴዎችን ሰላማዊ ሠልፍና ሕዝባዊ ስብሰባ ሲፈሩና ሲጠረጥሩ እያየን ነው? ይህ ምናልባት አሉባልታና ተራ ጥርጣሬ ነው ይባል ይሆናል፡፡

ቅድመ ምርጫ ሪፖርቶች፣ ቅስቀሳዎችና መግለጫዎች የኢሕአዴግን “ፍርኃት” ሲያሳብቁ አያለሁ፡፡ ኢሕአዴግ መፍራት ካወቀ መፍራት ያለበት ተቃዋሚዎች ወንበር ይሻሙኛል፣ አብላጫ ድምፅ ይከለክሉኛል በጭራሽ ብሎ አይደለም፡፡ ፓርላማ ውስጥ በገዛ እጁ “አጫዋች” እንኳ አጣለሁ ብሎም አይደለም መፍራት ያለበት ብቻውን እንዳያሸንፍ ነው፡፡

የኢሕአዴግን ብቻውን ማሸነፍ ኢሕአዴግ መፍራት ያለበት የኢሕአዴግ ዳፋ የአገርም አደጋ ስለሆነ ነው፡፡ የዚህ ምክንያት ህልውናችን ከኢሕአዴግ ጋር ስለተጣበቀ ከኢሕአዴግ በጎ ፈቃድ የወጣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እስካሁን ሊደራጅ አለመቻሉ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...