Tuesday, July 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ልማት ለማምጣት የምንታገል በመሆናችን የትኛው ብሔር የትኛው ወንበር ላይ ተቀመጠ የሚለው አያሳስበንም››

አቶ ዓለምነው መኮንን፣ የብአዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል

አቶ ዓለምነው መኮንን የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) ጽሕፈት ቤት ኃላፊና የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ አቶ ዓለምነው ከ18 ዓመታቸው ጀምሮ ብአዴን (ኢሕዴን)ን በታጋይነትና በተለያዩ የሥራ ኃላፊነቶች አገልግለዋል፡፡ ሰለሞን ጐሹ በብአዴን ጽሕፈት ቤት በመገኘት አቶ ዓለምነውን በብአዴን፣ በአማራ ክልልና በአማራ ብሔር ላይ በሚነሱ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የጽሕፈት ቤታችሁ ሕንፃ ላይ የኢሕዴን የትግል ዘመናትን የሚያሳዩ በርካታ ፎቶዎች ይታያሉ፡፡ በኢሕዴንና በብአዴን መካከል መሠረታዊ የሚባል ልዩነት አለ? ብአዴን ከኢሕዴን የወረሳቸውና የለወጣቸው ነገሮችስ ምንድን ናቸው?

አቶ ዓለምነው፡- የያኔው ኢሕዴን አምባገነኖችን ታግሎ ማሸነፍ ተራራን በገመድ መጎተት ነው ተብሎ ይታመን በነበረበት አስቸጋሪ ወቅት ነው የተፈጠረው፡፡ ትክክለኛ ዓላማ እስካነገብን፣ ሕዝባዊ ወገንተኝነት እስከተላበስን፣ ፅናት እስከጨበጥን ድረስ የደርግ የበላይነት ጊዜያዊ ነው ብሎ የተቋቋመ ነበር፡፡ ያኔ ሁሉም በመሰለው መንገድ ደርግን የሚታገልበት ወቅት ነበር፡፡ ብሔራዊና ኅብረ ብሔራዊ መልክ ይዞ ነው የተንቀሳቀሰው፡፡ በወቅቱ ኅብረ ብሔራዊ መልክ ይዘው መታገል ለሚፈልጉ የለውጥ ታጋዮች ሁነኛ የመታገያ መድረክና ድርጅት ሆኖ አገልግሏል፡፡ ኢሕዴን ከሌላው ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲ ከኢሕአፓ ተነጥሎ የወጣ ፓርቲ ነበር፡፡

ኢሕዴን በወቅቱ መሠረታዊ ዓላማና ፕሮግራሞች ነበሩት፡፡ አንደኛ በኢትዮጵያ የሕዝቡ አንገብጋቢ ጥያቄ በነበሩ ጉዳዮች ላይ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ነው፡፡ ይህ የዴሞክራሲ፣ የሕዝባዊ መንግሥት ምሥረታ፣ የመሬት ተጠቃሚነት፣ የብሔርና ብሔረሰቦች የራስን ዕድል በራስ የመወሰንና የማንነት፣ የሃይማኖትና የፆታ እኩልነት ጥያቄዎችን ያካትታል፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች እንዳይመለሱ እንቅፋት የሆነው አምባገነን ሥርዓት መወገድ አለበት የሚል አቋም ነበረው፡፡ በዚህም የትጥቅ ትግሉ ውስጥ ለአሥር ዓመታት ቆይቷል (ከ1973 – 1983)፡፡ በሒደት ደግሞ የመስመርና የዓላማ አጋር ከሆነው ሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጋር የጋራ ግንባር ፈጥሯል፡፡ ግንባሩ የተፈጠረው በድንገት ሳይሆን በሒደት በተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎችና መተማመን ነው፡፡ በ1981 ዓ.ም. የጋራ ግንባር የሆነውን ኢሕአዴግን ፈጥረናል፡፡

በኋላ ግን ኢሕዴን ውስጥ የነበሩ የሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አባላት ወይም ተወላጆች በብሔራዊ ማንነታቸው የመደራጀት ጥያቄ እየጎላ መጣ፡፡ ለምሳሌ ከኦሕዴድ መሥራች አባላት መካከል የኢሕዴን ታጋዮች ይገኙበታል፡፡ የአማራ ክልል ተወላጆችና ነዋሪዎች ብቻ እየቀሩ መጡ፡፡ ስለዚህ ብሔራዊ መልክ መያዝ ነበረበት፡፡ ስለሆነም ወደ ብአዴን ራሱን ለወጠ፡፡

የብአዴንም ሆነ የኢሕዴን ሥር መታገያ ሥልቶች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ የሕዝባዊ መንግሥትን ምሥረታ በተመለከተ በአማራ ክልል ከቀበሌ እስከ ተወካዮች ምክር ቤት ሕዝብ የመረጣቸው ምክር ቤቶች እንዲቋቋሙ ተደርጓል፡፡ የብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የራስን ዕድለ በራስ የመወሰን መብትን በተመለከተም የአማራ ክልል ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት እንዲለመልም ሰፊ ሥራ በመሥራት ላይ ነው የሚገኘው፡፡ ዜጎች የመሬታቸውና የጉልበታቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሠርቷል፡፡ ይኼን በትጥቅ ትግሉ ዘመንም ነፃ ባወጣቸው አካባቢዎች መሬት እየከፋፈለ አርሶ አደሩ የመሬቱና የምርቱ ተጠቃሚ እንዲሆን ጥረት አድርጓል፡፡ ከድል በኋላም መሬት ባልተከፋፈለባቸው ቦታዎች በማከፋፈል፣ በተለይ ሴቶች በወቅቱ እስከ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ መሬት እንዲያገኙ አድርጓል፡፡ አሁን ዜጎች በክልላችን መሬታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ካፒታላቸውንና ብልሃታቸውን አቀናጅተው እንዲያለሙ ሁኔታዎች ተመቻችተውላቸዋል፡፡ እንደ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ያሉ የተሻሉ አሠራሮችና ቴክኖሎጂዎች፣ የተሻሉ የማምረቻ መሣሪያዎች፣ የመስኖ ቴክኖሎጂ እንዲስፋፋ አድርገናል፡፡ በኢሕዴን በሐሳብ የተጠነሰሰው በብአዴን በተግባር ተተርጉሟል፡፡ ዕድገትና ለውጥም እያመጣ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ብአዴን በአማራ ብሔራዊ ክልል ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ከመፍጠር አኳያ ምን ያህል ስኬታማ ነው?

አቶ ዓለምነው፡- ብዝኃነት ባለበት ሁኔታ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ይኖራል፡፡ እንዲሁም ደግሞ ትምክህተኛና ጠባብ ብሔርተኝነት ይኖራል፡፡ በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ዴሞክራሲያዊ አንድነት ለመገንባት ትምክህተኛና ጠባብ ብሔርተኝነትን መታገል ያስፈልጋል፡፡ የትምክህተኛና የጠባብ ብሔርተኝነት መነሻ ሕገወጥ ተጠቃሚነትና አላግባብ ለመክበር የሚነሳ የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ ነው፡፡ ሽፋን የሚያደርገው ግን ዘርን ነው፡፡ በአጠቃላይ የጦር መሣሪያንና ሃይማኖትንም እንደ ሽፋን በመጠቀም መግዛትና የሕዝብን ሀብት ለራሳቸው መጠቀም ነው ፍላጎታቸው፡፡ ትምክህተኝነት የተገፉ የብዙኃኑ ሕዝቦች መለያ አይደለም፡፡ ነገር ግን የጥቂቶቹ ባህሪ ምልዓተ ሕዝቡን ቀስ በቀስ ሊገዛው ይችላል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ሳናሰርፅ አንድ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ማኅበረሰብ ልንፈጥር አንችልም፡፡

የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ለማጠናከር ብአዴን በርካታ ሥራዎችን ሠርቷል፡፡ የቀድሞ ገዥዎች እኮ አማራ የሚባል ብሔር ሳይሆን በደጋ የሚኖር ሕዝብ ነው ያለው ብለው ነበር፡፡ ኢሕዴንም ሆነ ብአዴን ይኼን አልተቀበሉም፡፡ ብአዴን ቀደም ብለው እነ ዋለልኝ መኮንን በ1960ዎቹ ይሉት እንደነበረው አማራ የሚባል ብሔር አለ ብሎ ነው የሚያምነው፡፡ ብአዴን የአማራ ብሔር ከሌሎች ብሔሮች ጋር ተባብሮ እንዲኖር ነው የሠራው፡፡ በቅድሚያ ለሕዝብ ያስረዳነው የዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትን ምንነት ነው፡፡ በመቀጠል ትምክህተኛና ጠባብ ብሔርተኝነትን በማስረዳት እንዲያነፃፅር ነው ያደረግነው፡፡ አካባቢውን እንዲያለማና በአካባቢው ልማት እንዲኮራም አድርገናል፡፡ በሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነት ላይ የደረሰውን በደል በማስረዳት የቆየውን መከፋት እንዲረዳውና በመከባበር ላይ የተመሠረተ አንድነት እንዲገነባ አድርገናል፡፡ በደቡብና በኦሮሚያ ስለ አማራው የነበረው ምሥል የተለየ ነው የነበረው፡፡ ብአዴን የአማራው ሕዝብ ትክክለኛ ምሥል እንዲታይ አድርጓል፡፡ ይኼማ እንደኛው የተገፋ አይደለም እንዴ እንዲሉ አድርጓል፡፡

ሪፖርተር፡- በአንድ በኩል የአማራ ብሔርተኝነትን ከኢትዮጵያ የአንድነት ኃይሎች ጋር አጣምረው የሚያዩ አሉ፡፡ በሌላ በኩል የአማራ ብሔር ከዚህ ቀደም የነበሩት ገዥዎች የወጡበት በመሆኑ ለጥቃት የተጋለጠ ሆኗል ብለው የሚከራከሩ አሉ፡፡ በእነዚህ ሁለት ፅንፍ የያዙ ዕይታዎች መካከል ብአዴን ከሰፊው የአማራ ሕዝብ ጋር ጥብቅ ግንኙነት ፈጥሯል ማለት ይቻላል? ለአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ማበብ ማሳያ ተደርገው የሚወስዱትስ ምንድን ናቸው?

አቶ ዓለምነው፡- የአማራ ብሔር ከሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ጋር በመልካም ግብረ ገብነት እየኖረ ይገኛል፡፡ በክልሉ ውስጥ ብቻ የአዊ፣ የህምራ፣ የኦሮሞ፣ የአርጎባና የቅማንት ብሔርና ማኅበረሰቦች አሉ፡፡ ባለፉት 24 ዓመታት ሕዝቡ ከብአዴን ጋር ነው እየሠራ ያለው፡፡ ሕዝቡ ድጋፉን የሚያረጋግጥባቸው መድረኮች አሉ፡፡ አንዱ የምርጫ መድረክ ነው፡፡ ሕዝቡ በተከታታይ ብአዴንን መርጧል፡፡ ይህ ማለት የዴሞክራሲ ብሔርተኝነት አስተሳሰብና ተግባር የሚያራምደውን ብአዴንን መርጧል ማለት ነው፡፡ የአማራ ሕዝብ በፊትም ሌላውን ብሔር ተጭኖ የመኖር ፍላጎት የለውም፡፡ የአማራ ብሔር በሌሎች ብሔሮች ላይ ተፅዕኖ የማድረግ ፍላጎት አለው ብለው የሚረዱ ኃይሎች መሠረት የላቸውም፡፡ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ማለት አንዱ ከፍ ሌላው ዝቅ የማይልበት የእኩልዮሽ ሥርዓት ነው፡፡ የአማራው ብሔር እንደሌሎች ብሔሮች በእኩልነት መኖር አለበት ብለው በቅድሚያ የታገሉት ከአብራኩ የወጡት እነ ዋለልኝ መኮንን ናቸው፡፡

ነገር ግን አንዳንድ ኃይሎች በዚህ ጉዳይ ላይ ግራ የሚያጋባ አቋም ይይዛሉ፡፡ አንዳንድ ምሁራን ብሔረ አማራ ማለት የአማራ ሕዝብን ማሳነስ ነው ብለው ይከራከራሉ፡፡ በሌላ በኩል የአማራ ብሔር እየተገፋ ነው የሚሉም አሉ፡፡ እንዳነሰ የሚቆጥሩ ኃይሎች በአማራ ብሔር ስም የበላይ ሆነው ለመውጣት የሚፈልጉ ናቸው፡፡ ይኼ ግን የግለሰቦቹ ትንተና እንጂ የአማራ ሕዝብን የሚወክል አመለካከት አይደለም፡፡ የአማራ ሕዝብ እየተገፋ ነው የሚሉ ኃይሎች ደግሞ መሥፈርትና ማስረጃ የላቸውም፡፡ እኛ እየተገፋ አይደለም ስንል መሥፈርቶች አሉን፡፡ ሕገ መንግሥቱ የራሱን መልከዓ ምድራዊ ሁኔታ ከልሎ አስቀምጦለታል፡፡ የራሱ ክልላዊ ሕገ መንግሥት አለው፡፡ በአገር አቀፍ መድረኮችም ተዋጽኦውን ጠብቆ ይሳተፋል፡፡ ከሁሉም በላይ ክልሉ ለረጅም ጊዜ ሕዝብ የኖረበት በመሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ ተራቁቶ ነበር፡፡ አሁን የተፈጥሮ ሀብቱ እየለማ ነው፡፡ ከተሞች እያበቡ ነው፡፡ ማንነቱን፣ ቋንቋውንና ወጉን እያስፋፋ ነው፡፡

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕዝቦች ከአማራ ክልል ወጥተው በመላ አገሪቱ ይኖራሉ፡፡ እነዚህ ሕዝቦች ሕገ መንግሥቱ በፈጠረላቸው ምቹ ሁኔታ ራሳቸውንና አካባቢያቸውን እያለሙ ነው፡፡ አልፎ አልፎ የሚኖሩ ግጭቶች ይኖራሉ፡፡ በአማራ ክልል ውስጥም ድንበር ገፋኸኝ ብሎ የሚጋጭ አለ፡፡ ግጭት መኖር የለበትም፡፡ ችግሩ ለዘለቄታው ሊፈታ የሚችለው ድህነትና ኋላቀርነት ሲወገዱ ነው፡፡ ስለዚህ በዚሁ ላይ እየሠራን ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትንም ለማጠናከር እንደ ኦሕዴድ፣ ደኢሕዴን፣ ቤጉዴፓ ካሉ ዴሞክራሲያዊ ድርጅቶች ጋር በጣምራና በመልካም ግንኙነት እየሠራን ነው፡፡ ነገር ግን መለስተኛ ግጭቶችን እያጋነኑ የአማራ ብሔር እንደተገፋ አድርጎ መቀስቀስ ለማንም አይበጅም፡፡        

ሪፖርተር፡- የአማራ ብሔር ለጥቃት ተጋልጧል ብለው የሚከራከሩ አካላት የሚያቀርቡት ማስረጃ በአብዛኛው በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱና የተለያዩ ዝርዝር ሕጎች ከአካባቢ አካባቢ በነፃነት ተንቀሳቅሶ የመኖርና የመሥራት መብትን ያረጋግጣሉ፡፡ የአተገባበሩ ክፍተት በተለይ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝና በኦሮሚያ ክልሎች የክልሉ ተወላጆች ለማያባራ የመብት ጥሰት እንዲጋለጡ አድርጓል በማለት አብነቶችን ይጠቅሳሉ፡፡ በእናንተ በኩል ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ምን ዓይነት ዕርምጃዎችን ወስዳችኋል?

አቶ ዓለምነው፡- ባለፉት ሦስትና አራት ዓመታት በተፈጠሩ አለመግባባቶች ይታዩ የነበሩ መፈናቀሎች አሁን ቀርተዋል፡፡ ለምሳሌ የዛሬ ሁለት ዓመት ቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ የደን መሬት አላግባብ ጨፍጭፋችኋልና ትወጣላችሁ ብለው ያፈናቀሉ አመራሮች ወደ ፍርድ ቀርበው ተጠይቀዋል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ አርሶ አደሩ መሥፈርም ከፈለገ በሕጋዊና በታቀደ መንገድ እንጂ ደን ያላግባብ ማውደም እንደማይገባም አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡ አሁን ችግሩ ተፈቷል፡፡ አምና ወለጋ አካባቢ አንድ ክስተት አጋጥሟል፡፡ በአካባቢው በቡና ልማት የተሰማሩ የአማራ ክልል ተወላጆች አሉ፡፡ በኋላ እንደተረጋገጠው ኦነግ አማሮች ጥሩ ኑሮ እየኖሩ እናንተ ሥራ አጥ ሆናችኋል ብሎ ወጣቶችን ቀሰቀሰ፡፡ በዚህ ምክንያት ይኼ የእኛ መሬት ስለሆነ ከቀያችን ውጡልን በሚል ግጭት ተቀሰቀሰ፡፡ ይኼን በቅድሚያ የተፋለመው ራሱ የኦሮሞ ሕዝብ ነው፡፡ ጥቃቱንም ቀድሞ የተቀበለው ራሱ ነው፡፡ ሁኔታው እስኪረጋጋ ወደ አማራ ክልል መጥተው የነበሩ እነዚህ ዜጎች አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎና መግባባት ላይ ተደርሶ ሲመለሱም ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡

ተቃዋሚዎች የችግሩ መነሻ አድርገው የሚያቀርቡት የፌዴራላዊ አወቃቀሩን ነው፡፡ ድህነትና ኋላቀርነት እስካለ ድረስ በሀብት ለመጋጨት የተለያዩ ብሔሮች አባል መሆን አይጠይቅም፡፡ መፍትሔ አድርገው የሚያስቀምጡት ደግሞ የተሳሳተ ነው፡፡ የሚሉት ብአዴን የአማራ ብሔር ተወካይ ነኝ ካለ በመላው ኢትዮጵያ ተንቀሳቅሶ ፖሊስና የፀጥታ ኃይል አሰልፎ ጥብቅና መቆም አለበት ነው፡፡ ይኼ አመለካከት ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን የናደ ነው፡፡ እኛ የምናምነው ለአማራ ሕዝቦችም ሆነ ለሌሎች ብሔሮች ዋናው ዋስትናቸው ሕገ መንግሥቱና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ እንደሆነ ነው፡፡ የሁሉም ክልሎች ፕሬዚዳንቶች የአማራ ብሔርም ወኪሎች ናቸው ብለን ነው የምናምነው፡፡ አስተዳደራዊ ችግሮች በየክልሎቹ ቢያጋጥሙ ደግሞ ብአዴን በየክልሉ ጽሕፈት ቤት አለው፡፡ የጽሕፈት ቤቶቹ ዓላማ ለአማራ ብሔር ተወላጆች ጥብቅና መቆም አይደለም፡፡ ክልላቸውን ለመደገፍ ተደራጅተው እንዲንቀሳቀሱ ማስቻልና ትምክህተኝነትን እንዲዋጉ መርዳት ነው ዓላማው፡፡      

ሪፖርተር፡- ብአዴን ኢሕአዴግ ውስጥ ስላለው ቦታ ጥያቄ የሚያነሱ አካላት አሉ፡፡ የአማራ ብሔር ከዚህ ቀደም የነበረው የበላይነት ግምት ውስጥ እየገባ ለተለያዩ ቦታዎች እኩል ዕድል አይሰጡትም በማለት ይከራከራሉ፡፡ ለአብነትም የጠቅላይ ሚኒስትርነትን ቦታ በቅርብ ዓመታት ለብአዴን መስጠት አደጋ አለው ይላሉ፡፡ የእርስዎ አመለካከት ምንድን ነው?

አቶ ዓለምነው፡- ሕዝቦች ሕገ መንግሥቱ ባስቀመጠው መሠረት የሚገባቸውን ውክልና ማግኘት አለባቸው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ወንበርን ጨምሮ አገር የመምራት ብቃት ላለው ክፍት ናቸው፡፡ ቁጥር አንድ መሥፈርቱ ብቃት ነው፡፡ ድህነትንና ኋላቀርነትን በማስወገድ ልማት ለማምጣት የምንታገል በመሆናችን የትኛው ብሔር የትኛው ወንበር ላይ ተቀመጠ የሚለው አያሳስበንም፡፡ ሥራውን በብቃት ለመምራት ይችላል ወይ የሚለው ነው ዋናው ነገር፡፡ ቀጥሎ ደግሞ የብሔር ውክልና ግምት ውስጥ ይገባል፡፡ በተወካዮች ምክር ቤት፣ በፌዴሬሽን ምክር ቤት፣ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ቦታ ያለው ውክልና የብሔር ውክልናን ከግምት ውስጥ ያስገባል፡፡ ነገር ግን ቁልፍ የማስፈጸሚያ ቦታዎች ላይ ብቃት ቁጥር አንድ ነው፡፡ ሁሉም የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶች ቁልፍ ሚና የሚጫወቱ ሰዎችን ሊቀመንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር፣ ሥራ አስፈጻሚና ማዕከላዊ ኮሚቴ አድርገው ይመርጣሉ፡፡ የኢሕአዴግም አመራሮች ከእነዚሁ ነው የሚመረጡት፡፡ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበሮች ጠቅላይ ሚኒስትርና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ፡፡ ብአዴን የሥልጣን ክፍፍልን የሚያየው ከመሠረታዊ ለውጥ አኳያ ነው፡፡ የተለያዩ የሥልጣን ቦታዎች በድምሩ አገሪቱን መምሰል መቻል አለባቸው፡፡ ይኼ ማለት ከ80 በላይ ብሔር፣ ብሔረሰብና ሕዝብ ስላለ በዚያው ልክ የሥልጣን ወንበሮች ይኖራሉ ማለት አይደለም፡፡ አቅም ያለው ሰው ከየትኛውም ብሔር ወጥቶ መሪ መሆን ይችላል፡፡ ከአሁን ቀደም መርተሃልና ማዕቀብ ተጥሎብሃል የሚባለው ጉዳይ መሠረት የሌለው ተረት ተረት ነው፡፡ በኢሕአዴግ ውስጥ ጣምራ አመራር ነው ያለው፡፡ ማንም ጠቅላይ ሚኒስትር ቢሆን የሚተገብረው የኢሕአዴግን ፖሊሲ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- በአገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ በርካታ ኅብረ ብሔራዊ ፓርቲዎች በአማራ ክልል ጠንካራ የድጋፍ መሠረት አለን ይላሉ፡፡ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ምሁራንም በክልሉ ላይ መሠረት ያደረጉ በአብዛኛው አሉታዊ የሆኑ የጥናት ውጤቶችን ያወጣሉ፡፡ ከእነዚህ አካላት የሚያገኘው እውነተኛ ወይም እውነት የሚመስል መረጃ የብአዴንና የሕዝቡን ግንኙነት ምን ያህል ያውካል?

አቶ ዓለምነው፡- ትምክህተኛና ጠባብ ብሔርተኝነትን ስትታገል የሚጠይቅህ የሐሳብ ከፍታና የትግል ደረጃ በአንፃራዊነት ላቅ ያለ ነው፡፡ ብአዴን ባለፉት ዓመታት በዋነኛነት ለአርሶ አደሩ ከዚያም አለፍ ብሎ ለከተማው ንዑስ አምራች፣ ለምሁራኑም የሠራቸው በርካታ ሥራዎች አሉ፡፡ ከዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት በተቃራኒ ያለው አስተሳሰብ የሚያስከትላቸውን ጉዳቶች አስረድተናል፡፡ ይኼም ሆኖ ግን አሁንም ከምሁራኑ ጋር በቂ መግባባት ላይ አልደረስንም፡፡ ቀላል ያልሆነ ቁጥር ያለው ምሁር በዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነት ላይ ገና ጥያቄዎች አሉት፡፡ ሒደት ያስተምራቸዋል ብለን እናምናለን፡፡ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ የፖለቲካዊና የባህላዊ ልማት እየመጣ ሲሄድ በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለመደማመጥ አስቻይ ሁኔታዎች እየተፈጠሩ ይመጣሉ፡፡ በዚያው ትይዩ ሁኔታዎች እየጠሩ ይመጣሉ፡፡ ሒደት ይፈታዋል ብለን ደግሞ ዝም አንልም፡፡ የአስተሳሰብ ግንባታ መፍጠር አለብን፡፡ ከታች ጀምሮ አስተሳሰቦች እየተቀረፁ እንዲመጡ እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች አሉ፡፡ ተቃውሞዎች ከዚህም በላይ ጠንክረን እንድንሠራ ያደርጉናል፡፡ የፈለገውን ያህል ብንሠራ ደግሞ የማንቀይረው ኃይል እንዳለ እንገነዘባለን፡፡ በአማራ ክልል የመጣው ለውጥ በምሁራን ተሳትፎ የተገኘ እንደሆነም መታወቅ አለበት፡፡ ጥያቄ ያላቸው ምሁራን ጭምር በገባቸው ትይዩ የሠሩት ሥራ ውጤት ነው፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በይበልጥ ከምሁራን ጋር በቅርበት እንወያያለን፡፡ በዕውቀት ላይ የተመረኮዘ የሐሳብ ልውውጥ ለማድረግ ጥረት እናደርጋለን፡፡  

ሪፖርተር፡- ለመጪው ጠቅላላ ምርጫና ክልላዊ ምርጫ የብአዴን ዝግጅት ምን ይመስላል?

አቶ ዓለምነው፡- ምርጫው ሰላማዊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ፍትሐዊ፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ ያልተለየው፣ በሒደቱም ሕዝቡ ያመነበት እንዲሆን አቅደን ነው የሠራነው፡፡ ማቀድ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ እንዲያውቀውም አድርገናል፡፡ በምርጫ ሥነ ምግባሩ ላይ ብቻ 5.5 ሚሊዮን ሕዝብ እንዲወያይበት አድርገናል፡፡ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ እንዲመርጥ ጥረት አድርገናል፡፡ 8.1 ሚሊዮን ሕዝብ እንዲመርጥ ነበር ያቀድነው፡፡ የዚህ 97 በመቶ የሚሆኑ መራጮች የምርጫ ካርድ ወስደዋል፡፡ ሕዝቡን በምርጫ ቅስቀሳ መድረኮች አሳትፈናል፡፡ ብአዴን ባለፉት 24 ዓመታት የሠራቸውን ሥራዎች፣ ያጋጠሙትን ተግዳሮቶች፣ የፈታባቸውን አግባቦች በዝርዝር በመድረኮቹ ላይ አቅርቧል፡፡ ሕዝቡ ለተሠሩ ሥራዎች ዕውቅና ይሰጣል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የሕዝቡን ፍላጎት የሚመጥን ሥራ ከመሥራት ጋር የልማትና የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም ለይቶ አመልክቷል፡፡ ዓላማችንን ለማሳካት በምርጫ ማቸነፍ እንፈልጋለን፡፡ የህዳሴው መስመር ሊሳካ የሚችለው በንዑስ ምዕራፎች በተከታታይ እየተመረጥን ዓላማችን መሳካት ከቻለ ብቻ ነው፡፡ የምርጫ ቅስቀሳውን ግን የፈለግነው ከዚህ ለላቀ ዓላማ ነው፡፡ የዴሞክራሲ አስተሳሰብ እንዲበለፅግ፣ ሞጋች ኅብረተሰብ እንዲፈጠርና ሕዝቡ በካርዱ እንዲተማመን የሚረዳ ነው፡፡ አሁን መንገድ ስላልሠራህልኝ አልመርጥህም የሚል ኅብረተሰብ እየተፈጠረ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ብአዴን ባለፉት አምስት ዓመታት ያከናወናቸው አንኳር ተግባራት ምንድን ናቸው? በምርጫው አሸንፎ ቢቀጥል በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ምን ዓይነት ለውጦችን ለማድረግ አቅዷል?

አቶ ዓለምነው፡- ባለፉት አምስት ዓመታት ምርጥ አርሶ አደሮች የደረሱበት የምርታማነት ደረጃ መበራከት ትልቅ ስኬት ነበር፡፡ ምርጥ ተሞክሮዎችን ማስፋፋትም ችለናል፡፡ ባሰብነው ደረጃ ባይሆንም የግብርና ምርት በመኸርም በሰብልም ማሳደግ ችለናል፡፡ በትምህርት ልማት ተሳትፎንና ጥራትን ለማስፋፋት አቅደን ተሳትፎን በጥሩ ሁኔታ አሳክተናል፡፡ ጥራትን በተመለከተ ተመሳሳይ ስኬት አስመዝግበናል፡፡ ጤናን በተመለከተ መከላከልን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ አቅደን ነበር፡፡ ከዚያ አልፎ ሲመጣ ብቻ የማከም ነገር እንዲኖር ነበር የታቀደው፡፡ 96 በመቶ በሚሆኑ ቦታዎች የጤና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ተመድበዋል፡፡ በማኅበራዊና በኢኮኖሚ መስኮችም ጥሩ ውጤቶች ተመዝግበዋል፡፡ ይኼ እንደተጠበቀ ሆኖ እንደ እጥረት የምናየው በኢንዱስትሪ ልማት መስክ በተለይ ደግሞ በጥቃቅንና አነስተኛ ላይ ተመሥርቶ በመሥራት በኩል ለውጦች ቢኖሩም ባሰብነው መልኩ አለመሄዳችንን ነው፡፡ መልካም አስተዳደርም ላይ ድክመቶች አሉብን፡፡ ሞጋች ኅብረተሰብ ከመፈጠሩም ጋር ተያይዞ ባሰብነው ትይዩ የኅብረተሰቡን እርካታ አላረጋገጥንም፡፡ በተለይ በገጠር የወል መሬቶችን በሕገወጥ ሁኔታ አስፍቶ ማረስ አሁንም አለ፡፡ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ግብርና፣ ጤና፣ ትምህርትና ኢንዱስትሪ ላይ አተኩረን እንሠራለን፡፡ የመልካም አስተዳደር ጉድለቶች ምንጮችን ፈልፍለን በማውጣት መፍትሔ ለመስጠት ትኩረት እናደርጋለን፡፡

ባለፉት አምስት ዓመታት የተገኘውን ውጤት በአጠቃላይ ባለፉት 24 ዓመታት ከተገኘው ውጤት ጋር እያስተያዩ ማየትም አስፈላጊ ነው፡፡ ለምሳሌ ማዕከላዊ ስታጽስቲክስ ባለሥልጣን በ1986 ዓ.ም. ባወጣው መረጃ የአማራ ክልል የሰብል ምርታማነት 28 ሚሊዮን ኩንታል በድምር፣ በሔክታር ደግሞ ምርታማነቱ ዘጠኝ ኩንታል ነው የነበረው፡፡ በ2006/2007 ዓ.ም. 87 ሚሊዮን ኩንታል የመኸር የሰብል ምርት ብቻ ሲደርስ፣ በሔክታር ደግሞ 21 ኩንታል ደርሷል፡፡ ይኼ ማለት የአማራ ክልል ሕዝቦች 20 ሚሊዮን በመሆናቸውና በአማካይ የአንድ ሰው ፍጆታ ሦስት ኩንታል በመሆኑ በትርፍ ከአንድ ኩንታል በላይ ለግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ፋብሪካዎች የሚሆን ምርት በነፍስ ወከፍ ማምረት ችሏል፡፡ በተመሳሳይ በ1986 ዓ.ም. ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱ ሕፃናት በአገር ደረጃ ከ100 ሕፃናት 17 ብቻ ነበሩ፡፡ አማራ ክልል ለስሙ የገዥዎች ትውልድ ቦታ ነው ቢባልም 13 ልጆች ብቻ ነበሩ ወደ ትምህርት ቤት የሚሄዱት፡፡ ከአገር አቀፉ አማካይም በታች ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከ100 ሕፃናት ውስጥ 96 ወደ ትምህርት ቤት ይሄዳሉ፡፡ አራቱም ሕፃናት ወደ ትምህርት ቤት የማይሄዱት ትምህርት ቤት ስለሌለ አይደለም፡፡ አርሶ አደሩ በተለያዩ ችግሮች የልጆቹን ጉልበት በመፈለግ ስለማይልካቸው ነው፡፡   

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች ሥራቸውን በነፃነት ሳይፈሩና ሳይሸማቀቁ እንዲያከናውኑ ዋስትና የሚሰጣቸው ሕግ የለም›› አቶ አመሐ መኮንን፣ የሕግ ባለሙያና የመብት ተሟጋች

ለበርካታ የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በፍርድ ቤት በመሟገት የሚታወቁት የሕግ ባለሙያ፣ ጠበቃና የመብት ተሟጋቹ አቶ አመሐ መኮንን የፈረንሣይና  የጀርመን መንግሥታት በጋራ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር የላቀ...

‹‹የአጎራባች ክልሎች የሰላም ዕጦት በእኛ ላይ ሸክምና ጫና ፈጥሮብናል›› ከአቶ ባበከር ሀሊፋ፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የግብርና ቢሮ ኃላፊ

አቶ ባበከር ሀሊፋ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ወንዶ ገነት ኮሌጅ በፎረስትሪ ሠርተዋል። ሁለተኛ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምረው አጠናቀዋል። ከ2002 ዓ.ም. እስከ 2003 ዓ.ም....

‹‹ሥራችን ተከብሮ እየሠራን ነው ብዬ አስባለሁ›› ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ የፌዴራል ዋና ኦዲተር

ቀደም ሲል በተለያዩ ተቋማት በኃላፊነቶች ሲሠሩ የቆዩትና በ2014 ዓ.ም. የፌደራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤትን በዋና ኦዲተርነት እንዲመሩ የተሾሙት  ወ/ሮ መሠረት ዳምጤ፣ በኦዲት ክፍተቶች ላይ...