Tuesday, July 23, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የቻይናው ኮንትራክተር የኅብረት ባንክን ሕንፃ ግንባታ ተረከበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኅብረት ባንክ የወደፊቱ የፋይናንስ ተቋማት መንደር ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው ሠንጋተራ አካባቢ ለሚያስገነባው ባለ32 ወለል ሕንፃ ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል ከተባለ የቻይና ኩባንያ ጋር ተፈራረመ፡፡

ግንቦት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል በኅብረት ባንክና በቻይናው ኩባንያ መካከል የተፈረመው ስምምነት እንደሚያመለክተው፣ ጂያንግሱ ግንባታውን በሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ያስረክባል፡፡

የኅብረት ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ታዬ ዲበኩሉ፣ ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል ግንባታውን ከሦስት ዓመታት ተኩል በፊት ሊያጠናቅቀው እንደሚችል መግለጹንም ተናግረዋል፡፡ የጂያንግሱ ቀደም ያሉ ታሪኮች የሚያሳዩት በእጁ ያሉትን ፕሮጀክቶች በወቅቱ ገንብቶ የሚያጠናቅቅ በመሆኑ፣ የኅብረት ባንክ ሕንፃንም ቃል በገባው መሠረት እንደሚፈጽም እምነት አለኝ ብለዋል፡፡

ኅብረት ባንክ የዋና መሥሪያ ቤቱን ሕንፃ ግንባታ ለቻይናው ኩባንያ የሰጠው ግንባታውን ለማካሄድ ባንኩ አውጥቶት በነበረው ጨረታ ተሳትፎ በማሸነፉ ነው፡፡ ሆኖም ጂያንግሱ ኢንተርናሽናል አሸናፊ የሆነበት ዋጋ የግንባታ ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት አልተገለጸም፡፡

ኮንትራክተሩ አሸናፊ የሆነበት ዋጋ ለምን እንዳልተገለጸ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ታዬ ሲመልሱ፣ ‹‹ዋጋውን መግለጽ ያልተፈለገው በሁለቱ ኩባንያዎች መካከል ቀደም ብሎ በተደረሰ ስምምነት መሠረት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ኮንትራክተሩ በሌሎች ተመሳሳይ የግንባታ ጨረታዎች ላይ በመሳተፍ መወዳደሪያ ዋጋውን ያቀረበ በመሆኑ፣ የኅብረት ባንክ ሕንፃን ለመገንባት በጨረታ ያሸነፈበትን ዋጋ መግለጹ ችግር ይፈጥርብኛል በማለቱ ለጊዜው ዋጋውን ላለመግለጽ ታስቦ የተደረገ ስለመሆኑም ከማብራሪያው መገንዘብ ተችሏል፡፡ ሆኖም ኮንትራክተሩ ያሸነፈበት ዋጋ የማይገለጸው ለተወሰነ ጊዜ እንጂ ወደፊት መገለጹ እንደማይቀር አቶ ታዬ ጨምረው ገልጸዋል፡፡

የጂያንግሱ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ዙ ጃን ኩባንያቸው አሸናፊ የሆነበትን ዋጋ ከመግለጽ ተቆጥበው፣ አሸናፊ የሆነበትን ዋጋ ላለመግለጽ የሰጡት ምክንያት ደግሞ አቶ ታዬ ከሰጡት ጋር ተመሳሳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም የኅብረት ባንክን ሕንፃ ለመገንባት የሰጡት ዋጋ አነስተኛ የሚባል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የግንባታ ዋጋውን ሁለቱም ተዋዋዮች ከመናገር ቢቆጠቡም፣ ከአንድ ዓመት በፊት ኅብረት ባንክ ለሚያስገነባው ሕንፃ ዲዛይን ሲመረጥ ግንባታው ከ800 ሚሊዮን ብር እስከ አንድ ቢሊዮን ብር ሊፈጅ ይችላል ተብሎ እንደነበር ይታወሳል፡፡

የኅብረት ባንክን ሕንፃ ለመገንባት ከቻይናው ኩባንያ ሌላ ሁለት ኮንትራክተሮች ለመጨረሻ ውድድር ቀርበው ነበር፡፡ ሁለቱም የውጭ ኮንትራክተሮች ሲሆኑ፣ አንዱ የቻይና ሌላኛው ደግሞ የህንድ ኩባንያ እንደነበሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡

የባንኩን ሕንፃ ለመገንባት ለመጨረሻው ውድድር ቀርበው ነበር ከተባሉት ሦስቱ የውጭ ኮንትራክተሮች ሌላ ከአሥር በላይ የአገር ውስጥና የውጭ ኮንትራክተሮች ሕንፃውን ለመገንባት ፍላጎት አሳይተው ነበር ተብሏል፡፡ ሆኖም ለመጨረሻ ውድድር ከቀረቡት ሦስት ኮንትራክተሮች በተጨማሪ የነበሩት ተወዳዳሪዎች፣ በጨረታ ሰነዱ ላይ ተጠቅሰው የነበሩ መስፈርቶችን ማሟላት ባለመቻላቸው በየደረጃው ከውድድሩ ውጭ ስለመሆናቸውም ከባንኩ ያገኘነው መረጃ ያስረዳል፡፡

ጂያንግሱ በኢትዮጵያ ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ ካሉ የቻይና ዓለም አቀፍ ኮንትራክተሮች መካከል አንዱ ሲሆን፣ በመላው ዓለም በ46 አገሮች ቅርንጫፎች እንዳሉት ኢንጅነር ዙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ እስካሁን በኢትዮጵያ በሰባት የተለያዩ ፕሮጀክቶች ተሳታፊ ሆኗል፡፡

ከሰባቱ ፕሮጀክቶች ውስጥ ግንባታቸውን አጠናቅቆ ካስረከባቸው ፕሮጀክቶች መካከል ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውለው የባህር ዳር የስብሰባ ማዕከል ሕንፃና የጅማ ጤና ትምህርት ሆስፒታል ይገኝበታል፡፡ በሚድሮክ ደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካ የግንባታ ሒደት ውስጥ ተሳታፊ እንደነበር ያስታወሱት ኢንጂነር ዙ፣ በአዲስ አበባ ደግሞ በሁለት ቦታዎች በቻይና መንግሥት የገንዘብ ድጋፍ በ9.6 ሚሊዮን ዶላር ሁለት የቻይና አፍሪካ ፍሬንድሺፕ ትምህርት ቤቶች ግንባታ እያካሄደ ነው ብለዋል፡፡

ለባንኩ ዋና መሥሪያ ቤት የሚሆነው ይህ ሕንፃ 119 ሜትር ርዝማኔ ይኖረዋል፡፡ ሕንፃው የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የማሠልጠኛ ክፍሎች፣ የሠራተኞች መዝናኛ ማዕከሎች፣ እስከ 200 ተሽከርካሪዎችን በአንድ ጊዜ ሊያስተናግድ የሚችልና ከሕንፃው ሥር በአራት ደርዝ የሚገነባ የመኪና ማቆያ ይኖረዋል፡፡

ከዋናው ሕንፃ ጎን በስተግራ ተይዞ የሚገነባው ባለአራት ወለል ሕንፃ ደግሞ ለገበያ ማዕከል፣ ለሱቆች፣ ለካፍቴሪያና ለሌሎች አገልግሎት የሚውል ነው ተብሏል፡፡

የባንኩን ሕንፃ ዲዛይን የሠራው እስክንድር አርክቴክትስ ሲሆን፣ ከአንድ ዓመት በፊት ተካሂዶ በነበረ የዲዛይን ሥራ ጨረታ 40 የሚሆኑ ተፎካካሪዎች ቀርበው እንደነበር ይታወሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከኅብረት ባንክ ሌላ የአገሪቱ ፋይናንስ ተቋማት መንደር ይሆናል ተብሎ በሚጠበቀው ሠንጋተራ አካባቢ ወደ ሰባት የሚሆኑ ባንኮችና ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ትልልቅ የሚባሉ ሕንፃዎች ለመገንባት ቦታ መረከባቸው ይታወቃል፡፡ አብዛኛዎቹም የሚገነቡትን የሕንፃ ዲዛይን ይፋ በማድረግ የቅድመ ግንባታ ሥራዎችን እየሠሩ ናቸው፡፡ ከ30 ወለል በላይ የሆኑትን ሕንፃዎች ለማስገንባት በጨረታ ሒደቱ ላይ የቻይና ኩባንያዎች ተሳትፎ ጎላ ብሎ እየታየ መሆኑ እየተነገረ ነው፡፡

ከዚህ ቀደምም ወጋገን ባንክ የዋና መሥሪያ ቤቱን ሕንፃ ለማስገንባት በጨረታ የመረጠው ኮንትራክተር የቻይና ኩባንያ ነው፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ረዥሙ ሕንፃ ይሆናል የተባለውን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ባለ46 ወለል ሕንፃ እንዲገነባ የተወዋለውም ኩባንያ የቻይና ነው፡፡ ይህም የቻይና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ትላልቅ በሚባሉ ሕንፃ ግንባታዎች ላይ ለመሳተፍ ያላቸውን ፍላጎት እያመለከተ እንደሆነ ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች