Friday, April 19, 2024

የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ የሱዳን ጉዞ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ቅድመ ዝግጅት – በሱዳን የተከናወኑ ተግባራት – የተገኙ ውጤቶችና ቀጣይ አቅጣጫ

ከወራት በፊት ወደ ግብፅ ተጉዞ የነበረው የኢትዮጵያ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን፣ ከዚያ ያገኘውን ትምህርት በመቅሰምና በማጠናከር፣ ሁለተኛ ጉዞውን ከሚያዝያ 30 እስከ ግንቦት 5 ቀን 2007 ዓ.ም. በሱዳን አከናውኖ ተመልሷል፡፡

ቅድመ ዝግጅቱ ምን ይመስል ነበር?

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ከመነሻው ከሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል የተውጣጣ ቢሆንም፣ ከግብፅ ጉዞ ተሞክሮ በመቅሰም በሱዳኑ ጉዞ ከዩኒቨርሲቲ ምሁራን፣ ከሴቶችና ከአርሶ አደሮች ተጨማሪ አባላትን አካቷል፡፡ ተገቢ መሆኑም ታምኖበታል፡፡ ወደ ሱዳን የተጓዘው የልዑካን ቡድን አባላት ቁጥር 92 ነበር፡፡

ቡድኑ በሱዳን በሚቆይባቸው ጊዜያት ከአገሪቱ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ከሃይማኖት መሪዎች፣ ከንግዱ ማኅበረሰብ፣ ከምሁራንና ከምርምር ተቋማት፣ ከወጣቶችና ከሴቶች ማኅበራት፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮች፣ በሱዳን ከሚገኙ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አባላት ጋር እንደሚገናኝ ፕሮግራም ተይዞ ነበር፡፡ በተጨማሪ በሱዳን የመረዌ ግድብ፣ ታሪካዊ ቦታዎች፣ የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ከተማ የተባለው ጭምር አባላቱ እንደሚጎበኙ አስቀድሞ በፕሮግራም ተይዞ ነበር፡፡ የኢትዮጵያና የሱዳን ባህላዊ የሙዚቃ ዝግጅቶችም ቀደም ብሎ ዝግጅት የተደረገባቸው ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዓላማና ግብ በትክክል የሱዳን ሕዝብ ሊገነዘበው እንዲችልም፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን በቂ ጥናት አካሂደው ከቡድኑ አባላት ጋር በሚገባ ተወያይተው ነበር ወደ ሱዳን የተጓዙት፡፡ ሊነሱ ከሚችሉ ጥያቄዎች መካከል የግድቡ ዲዛይንና ኢንጂነሪግ፣ የግንባታው አስፈላጊነትና ማንንም እንደማይጎዳ፣ እንዲሁም ለዘመናት የዘለቀውን የኢትዮ-ሱዳን ግንኙነት በተመለከተ በቂ ምሁራዊ ጥናትና ምርምር ተደርጎበት የተዘጋጀ ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ከመሄዱ በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ጋር ውይይት አካሂዷል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩም በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል 11 የተለያዩ ስምምነቶች እንደተፈረሙና ያለው ግንኙነት በዓባይ ግድብ ዙሪያ ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚ ውህደት፣ በፖለቲካ መቀራረብ፣ አብሮ መሥራትና ለሰላም አብሮ በመንቀሳቀስ ላይ ያተኮረ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያና ሱዳን በመኪና መንገድ የተገናኙ መሆናቸውንና በአምስት ዓመታት ውስጥም የባቡር መስመር እንደሚያገናኛቸው ገልጸዋል፡፡ በፖርት ሱዳንም ኢትዮጵያ ከፍተኛ የወደብ አገልግሎት ለማግኘት የማስፋፊያ ግንባታ እያካሄደች መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን በማግኘት መደረግ ያለበትን የመተጋገዝ፣ ድንበር አሻጋሪ ደላሎችን የማውገዝና የማስወገድ፣ ዜጎች ወደ አገራቸው ተመልሰው እንዲኖሩ ጥረት መደረግ እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አስረድተው ነበር፡፡ ይህ ሁሉ ዝግጅት ከተከናወነ በኋላም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአየር ትኬቱንና የቪዛውን ሥራ የማቀላጠፍ ኃላፊነቱን ተወጥቶ በታቀደው መሠረት ወደ ሱዳን ጉዞ ተደርጓል፡፡

የፐብሊክ ዲፕሎማሲው ተጨባጭ የሱዳን እንቅስቃሴና ሒደት ምን ይመስል ነበር?

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ሱዳን ሲደርስ፣ እዚያም ወደ ተለያዩ ሥፍራዎች ሲሄድና ሲመለስ፣ በመጨረሻም ተልዕኮውን አጠናቆ ሲሰናበት ከፍተኛ የሕዝብ አቀባበልና አሸኛኘት ተደርጎለት ነበር፡፡ የሱዳን ባለሥልጣናትም ከቡድኑ ጎን ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እንደ ተቋም፣ አምባሳደር አባዲ ዘሙ እንደ አምባሳደር ከልዑካን ቡድኑ አልተለዩም፡፡ በአጠቃላይ መስተንግዶው ልዑካኑን ከልብ ያስደሰተና ከተጠበቀው በላይ መሆኑን አባላቱን ያስማማ ነው፡፡

በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ያከናወናቸው ዋና ዋና ተግባራት ሲዳሰሱ፣

 1. ከውኃና ከኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ጋር የነበረው ውይይት

ከውኃና ከኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ከሙታዝ ሙሳ ጋር የነበረው የጋራ ውይይት ለቡድኑ አባላት እጅግ አመርቂ ነበር፡፡ ሚኒስትሩ በማያወላውልና በማያሻማ መንገድ ኢትዮጵያ ዓባይን የመገደብ ሙሉ መብት አላት ብለው ተናግረዋል፡፡ “ግድቡ ሌሎችን እንዳይጎዳ ነው ማሰብ ያለብን እንጂ፣ ኢትዮጵያ ለምን ተጠቀመች የሚል ሥጋት የለንም፤” ብለዋል፡፡ “በግድቡሁላችንም እንጠቀማለን እንጂ አንጎዳም፤” ብለዋል፡፡ እንዲያውም የህዳሴ ግድቡ በኢትዮጵያ፣ በሱዳንና በግብፅ መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጠናክር ይሆናል ብለው በአፅንኦት ገልጸዋል፡፡ አንዳንድ ሥጋቶች ተቃውሞችም ይረግባል በማለት ተናግረዋል፡፡ ሱዳን መረዌ ግድብን ስትገድብም መጀመሪያ ግብፅ ተቃውሞ አሰምታ እንደነበር ጠቅሰዋል፡፡ የሱዳኑ ሚኒስትር በአፅንኦት በገለጹት አቋም የልዑካን ቡድኑን አባላት የተደሰቱበትና ከጠበቁት በላይም ሆኖላቸው ነበር፡፡

 1. ከሱዳን የፓርላማ አፈ ጉባዔ ጋር የነበረው ቆይታ

የኢትዮጵያ የልዑካን ቡድን የተመራው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በአቶ አባዱላ ገመዳ ነበር፡፡ የሱዳን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ዶክተር አልፋታህ ኢዘዲን ቡድኑ ሱዳን ሲደርስ በአውሮፕላን ማረፊያ አቀባበል አድርገዋል፡፡ ግሪን ፓርክ በተባለ ቦታ የሙዚቃ ዝግጅት ሲደረግም ንግግር አድርገዋል፡፡ በንግግራቸው የህዳሴ ግድቡ ግንባታ እንደሚጧጧፍና ለልማት ጠቃሚ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ የሁለቱም አገሮች ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል አድርገዋል ያሉዋቸውን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሚና አድንቀዋል፡፡

የህዳሴ ግድቡን ግንባታ ከመደገፍ ባሻገርም በሊቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸመውን አረመኔያዊ ግድያ አውግዘዋል፡፡ የትኛውንም ሃይማኖት እንደማይወክልም ገልጸዋል፡፡ ይህ በፐብሊክ ዲፕሎማቲክ ቡድኑ አባላት ላይ ከፍተኛ መተማመን የፈጠረ ነበር፡፡  

 1. የ“ኢንተርናሽናል ሲቲ ኦፍ አፍሪካ” የምርምርና የጥናት ተቋም ጉብኝት

ሱዳን “ኢንተርናሽናል ሲቲ ኦፍ አፍሪካ” የሚባል የቴክኖሎጂ ምርምርና ጥናት ማዕከል መሥርታለች፡፡ በሱዳን ደረጃ ለማመን የሚያስቸግር እመርታ ያሳየችበት ይመስላል፡፡ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑን እጅግ ያስደሰተና ያስገረመ የቴክኖሎጂ ምርምርና ውጤት የታየበት ነበር፡፡ ይህ በጭራሽ ያልተጠበቀም ነበር፡፡ ሱዳን በዚህ ዙሪያ በአፍሪካ እንቅስቃሴ መጀመርዋና ከኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመሥራት መፈለጓም ልዑካኑን ያረካ እንደነበር ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

 1. ከሃይማኖት መሪዎችና ተቋማት ጋር የተደረገው ውይይት

ይህ መድረክ በልዑካኑ ቡድን ላይ የደስታና የመተማመን መንፈስ የፈጠረ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ ልዑካን ውስጥ የተለያዩ የሃይማኖት አባቶች አሉ፡፡ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፣ ከካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን፣ ከፕሮቴስታንትና ከሙስሊም ቤተ እምነቶች የተወከሉ አሉበት፡፡ ሁሉም አርዓያነት ያለው መቀራረብና መወያየት ከማድረጋቸውም በላይ በስምምነት ሲንቀሳቀሱ ይታዩ ነበሩ፡፡

ሱዳን ውስጥም እንደዚሁ የእስልምናና የኮፕቲክ ሃይማኖት መሪዎች ልዩ መቀራረብና ፍቅር ሲያንፀባርቁ ነበር፡፡ ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት መቻቻል አለ እያሉ ይኮራሉ፡፡ በዚህም ኩራት እንደሚሰማቸው በግልጽ ይናገራሉ፡፡ ሱዳን ውስጥ የታየው ደግሞ ከዚህም በላይ ነበር፡፡ በኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስብሰባ ሲካሄድና መዝሙር ሲዘመር ሙስሊሞችም አብረው ነበሩ ብቻ ሳይሆን፣ በቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ ይሰግዳሉ፡፡ ይህ በዚያን ቀን ብቻ የታየ ሳይሆን፣ ሌላ ጊዜም ሙስሊሞች ቤተ ክርስቲያን ግቢ ውስጥ እንደሚሰግዱ የሃይማኖት አባቶቹ በይፋ በግልጽ ተናግረዋል፡፡ የሚገርምና ልዩ የመቻቻል ማሳያ ነበር፡፡

ከኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን በተጨማሪም የልዑካን ቡድኑ አባላት በኡምዱርማን አካባቢ የሚገኘው የሼክ ካሊድ አባስ አልሰይም የእስልምና የትምህርት ተቋም ጎብኝተው ነበር፡፡ በሼኩ ደጋፊዎችና በቅዱስ ቁርዓን ተማሪዎች ሞቅ ያለ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ የታየውም ፍቅር በግልጽ የተንፀባረቀ እንደነበር ልዑካኑን አግባብቷል፡፡

 1. የመረዌ ግድብ ጉብኝት

የመረዌ ግድብ ከተጠበቀው በላይ ትልቅ ነው፡፡ ሱዳናዊያን፣ “እኛ ይህን ከገነባን ኢትዮጵያ አትገንባ ማለት አንችልም፤” ብለዋል፡፡ የሱዳን የተቃዋሚ ፓርቲ አባልና የውኃና የኤሌክትሪክ ምክትል ሚኒስትሯ ለኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሙሉ ድጋፍ እንዳላቸው ገልጸዋል፡፡ የመረዌ ግድብንም አስጎብኝተዋል፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲ አባል ቢሆኑም በግድብና በልማት ዙሪያ ከመንግሥትና ከፕሬዚዳንት አማር ሐሰን አልበሽር ፓርቲ ጋር ቅራኔ እንደሌላቸው አስረድተዋል፡፡ ሌሎች ተቃዋሚዎች ሊማሩበት የሚገባ ጉዳይ መሆኑንም አሳይተዋል፡፡

 1. የመረዌ ታሪካዊ አካባቢና የሙዚየም ጉብኝት

ይህ ጉብኝት በራሱ በልዑካን ቡድኑ አባላት ላይ ልዩ መንፈስ የፈጠረ ነበር፡፡ በታሪካዊ ቦታዎች አካባቢ ሱዳን አራት ፒራሚዶች አሉዋት፡፡ ፒራሚድ ግብፅ ውስጥ እንጂ ሱዳን ውስጥ እንዳለ አይታወቅም ነበር፡፡ እንዲያውም ከግብፅ ፒራሚድ በፊት የተገነባው ይህ የሱዳን ፒራሚድ ነው ተብሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የሙዚየም ጉብኝት ነበር፡፡ መረዌ ሙሁያም ይባላል፡፡ ከካርቱም በስተሰሜን 600 ኪሎ ሜትር በሚርቅ አካባቢ እንደዚህ ዓይነት ሙዚየም ማግኘት ያልተጠበቀ ነበር፡፡ የሚገርመው ግን ሱዳናውያን በመረዌና በኑቢያ አካባቢ ታሪካቸው የእስልምናና የክርስትና ነው፡፡ ራሳቸውን ከዓለም ሥልጣኔ ጋር ያያይዛሉ፡፡ እነሱም ንግሥተ ሳባ አለቻቸው፡፡ “በዚህም ኢትዮጵያና ሱዳን በእጅጉ የተቀራረብን አንድ ዓይነት ሕዝብ ነን፤” ይላሉ፡፡ የሚሉትንም ታሪካቸውና ሙዚየሙ ይመሰክራሉ፡፡ ስለሱዳን ብዙ የማይታወቅ ነገር እንዳለ ትምህርት የሰጠ ጉብኝት ነበር፡፡

 1. ከሊቢያ ከመጡ ሱዳን ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ጋር

ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ግብፅና ሊቢያ በመተባበር ባደረጉት ጥረት 45 ያህል ኢትዮጵያውያን ከሊቢያ ወደ አገራቸው ተመልሰዋል፡፡ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በካይሮ አውሮፕላን ማረፊያ ኢትዮጵያውያንን አግኝተዋል፡፡ ሱዳንም ቪዛና ፓስፖርት ሳይኖራቸው ከግብፅ እንዲገቡና ወደ ኢትዮጵያ እንዲያልፉ አድርጋለች፡፡ ሱዳን ያለው የኢትዮጵያ ኤምባሲም ትልቅ ሥራ ሠርቷል፡፡ ከሌሊቱ ዘጠኝ ሰዓት  ካርቱም አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባላትና ሌሎች እዚያው ድረስ ሂደው አግኝተዋቸዋል፡፡ ሱዳን ትልቅ ትብብር ማድረጓ ለልዑካኑም ለስደተኞችም የሚያስደስት ስሜት ፈጥሮ ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባዘጋጀው መድረክ ላይ ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ከልዑካኑ ቡድን ጋር ተገናኝተዋል፡፡ ልብ የሚነካ ስብሰባ ነበር የተደረገው፡፡ ስደተኞቹም የልባቸውን ተናግረዋል፡፡ ኑሯቸው የሚሻሻል መስሏቸው የተሰደዱ እንጂ፣ ኢትዮጵያን እንደሚወዱና መመለስ እንደሚፈልጉ ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን “ድጋፍ ይደረግልን” በማለት በጋራ ጠይቀዋል፡፡ መሬት የማግኘትና አገራቸው የመመለስ ድጋፍ ይደረግ ከማለት አልፈውም መንግሥት በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ላይ ጥብቅ ዕርምጃ እንዲወስድ አሳስበዋል፡፡ “ደርግን ለመደምሰስ የቻለ መንግሥት ደላላን ለመቆጣጠርና ለመግታት እንዴት እንዳልቻለ ግራ ገብቶናል፤” ብለዋል፡፡ ኃይለኛና ልብ የሚነኩ በርካታ ንግግሮች ተደምጠዋል፡፡ በወቅቱ አፈ ጉባዔ አባዱላና አምባሳደር አባዲም ነበሩ፡፡ ለስደተኞቹ ጥያቄዎች ተገቢ ነው ያሉትን መልስም ሰጥተዋል፡፡ አሁንም ጥረት እየተደረገ እንደሆነና ወደፊትም እንደሚደረግ አስረድተዋል፡፡ ቃል ገብተዋል፡፡

ሱዳን የሚኖሩ የኢትዮጵያ ስደተኞች በጋራ ማኅበር መሥርተው በኤምባሲው ግቢ የቢሮ ሕንፃ የሚገነቡ ታታሪዎች መሆናቸው ተነግሯል፡፡ ይህም በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ላይ ልዩ ስሜት ሲፈጥር መታዘብ ይቻል ነበር፡፡ በስብሰባው ወቅት 500 የሚሆኑ ስደተኞች ተገኝተው ነበር፡፡

 1. የኢትዮጵያና የሱዳን ምሁራን ግድቡንና ቢዝነስን በተመለከተ ያቀረቧቸው ጥልቅ ጥናቶች

የህዳሴውን ግድብ በሚመለከት በኢትዮጵያና በሱዳን ምሁራን ጥናቶች ቀርበው፣ ሁለቱ አገሮች እንዴት መተባበር እንዳለባቸው ሰፊ ውይይት ተካሂዷል፡፡ በጋራ መሥራት ለጋራ ዕድገት ፋይዳ እንደሚኖረውም ሁለቱም ወገኖች ገልጸዋል፡፡

የንግዱ ኅብረተሰብ በኢንቨስትመንት እንዲገናኝም ጥልቅ ጥናታዊ ጹሑፎች ቀርበዋል፡፡ በጥያቄና መልስም ዳብረዋል፡፡ በዚህ ሲምፖዚየም የቀረቡት የግድቡና የቢዝነስ ጥናቶች በይበልጥ ከመረዳዳትና መቀራረብ ከመፍጠር አልፎ፣ ለኢንቨስትመንት ትልቅ ቅስቀሳና መነሳሳት ትኩረት የሰጡ ናቸው፡፡

 1. ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የተደረገው ውይይት

በኢትዮጵያ ልዑካን ቡድን ውስጥ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትና አመራሮች አሉ፡፡ የሱዳን ተቃዋሚ ፓርቲዎችና የገዥው ፓርቲ አባላት በጋራ የተገኙበት ስብሰባ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ በኩል ተቃዋሚዎች በህዳሴ ግድቡ ላይ ከገዥው ፓርቲ ጋር የጋራ አቋም አላቸው፡፡ የሱዳን ተቃዋሚዎች ደግሞ በራሳቸው ግድብና ልማት፣ በኢትዮጵያ ግድብና ግንኙነት ላይ የጋራ አመለካከት አላቸው፡፡ በውይይቱ ላይ የተንፀባረቀውም ተቃዋሚ መሆን ጭፍንና ጽንፈኛ መሆን ሳይሆን፣ በሚያገናኘው አንድ እየተሆነ በሚለያየው ደግሞ መቃወም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ለልማት፣ ለሰላምና ለደኅንነት እየተቃወሙም አንድ መሆን እንደሚቻልና ተገቢ መሆኑ የታየበት ግልጽ መድረክ ነበር፡፡

ከወጣቶች፣ ከሴቶችና ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይቶች ተካሂደዋል፡፡ ከስብሰባዎቹ በተጨማሪም በተናጠል ኢንቨስተሮችን፣ አርቲስቶችን፣ ስፖርተኞችን፣ ዲፕሎማቶችን፣ ወዘተ ለማግኘትና ለመወያየት ተችሏል፡፡ ፕሬዚዳንት አል በሽር ልዑካኑን ለማግኘት ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላቸው ቢታወቅም፣ ባልታሰበ የጤና ችግር ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

ከሱዳን ጉዞ ምን ውጤት ተገኘ?

በሱዳን የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ጉብኝት በርካታ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡ ዋና ዋናዎቹም ይህንን ይመስላሉ፡፡

 1. የህዳሴ ግድብ ለልማትና ለጋራ ጥቅም መሆኑን በማመን ድጋፍ መገኘቱ ተረጋግጧል

በባለሥልጣናትም፣ በንግዱ ኅብረተሰብም፣ በፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ በሴቶችና በወጣቶችም፣ በፓርላማ አባላትም የህዳሴ ግድቡ ሱዳንን እንደማይጎዳ፣ እንዲያውም ይበልጥ ለእርሻ እንደሚጠቀምና ኃይል ለማመንጨትም ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው መተማመን ተፈጥሯል፡፡ በዚህም የተረጋጋ ሁኔታ ታይቷል፡፡ እንዲያውም ሱዳኖች በተከዜ ግድብ መጠቀማቸውንና ከዓባይ ግድብ ደግሞ ይበልጥ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በትኩረት እየጠበቁ ናቸው፡፡ የግንባታው ጥንካሬና አስተማማኝነት ትኩረት እንዲሰጠው ብቻ መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ትልቁ ድል ይህ ድጋፍና አመኔታ ነበር፡፡

 1. የኢኮኖሚ ትስስሩ ይጠናከር የሚለው መልዕክት ከሱዳን መንግሥትና ከቢዝነስ ዘርፍ እየቀረበ ነው

ግንኙነቱና ውይይቱ ከዓባይ በላይ ይሁን የሚል ይፋዊ ጥያቄ እየቀረበ ነው፡፡ የኢኮኖሚ ትስስር ይፈጠር የሚል ከፍተኛ ጥያቄ ቀርቧል፡፡ በፖርት ሱዳን ግንኙነት እየተፈጠረ ነው፡፡ በመኪና መንገድ ከካርቱም አዲስ አበባ መግባት ይቻላል፡፡ የባቡር መስመር ለመዘርጋት ዕቅድ ተይዟል፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል ግብይት ሊደረግ ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት የባቡር፣ የመንገድ ትራንስፖርት፣ የኤሌክትሪክ ሕጎች ተሻሽለው ወደ ኢኮኖሚ ውህደት በማምራት ቀስ በቀስ ወደ ፖለቲካዊ ውህደት እንጓዝ የሚል ጥያቄም አለ፡፡ ይህንን ኢትዮጵያም ታምንበታለች ተብሏል፡፡ ይህ ከፍተኛ ውጤት ነው፡፡ ከወዲሁም በርካታ የሱዳን ኢንቨስተሮች ወደ ኢትዮጵያ ለመግባት መዘጋጀታቸው ተሰምቷል፡፡

 1. ታሪካዊው አንድነት ጎልቶ እየወጣ ነው

የሱዳን ምሁራን ሲናገሩ የመረዌና የኑቢያ ሥልጣኔ ከአክሱም ሥልጣኔ ጋር የተያያዘ ነው ይላሉ፡፡ የእስልምና ታሪክ ብቻ ሳይሆን የክርስትና ታሪክም አለን ይላሉ፡፡ የንግሥት ሳባ ታሪክ አለን ይላሉ፡፡ ግብፅን ለመውረር ጠላቶች ሲመጡ ንጉሥ ካሌብ መረዌ ድረስ ዘምተው አግዘውናል ይላሉ፡፡ እነሱ ታሪካቸውን እንደ አዲስ እየተመራመሩበት እያጠኑ ናቸው፡፡ የትምህርት ቤታቸውን የታሪክ ካሪኩለም ለመቀየርም እየተዘጋጁ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የታሪክ ተመራማሪዎችም ይህንን ግንኙነት እንደገና እንዲያጠኑት ጠይቀዋል፡፡

 1. ለኢኮኖሚና ለፖለቲካዊ ትስስርና ውህደት፣ ለፀረ ሽብርተኝነት ትግልና ለሰላም ዕውንነት በጋራ ሞዴል ስለመሆን

በትክክል ከተሠራና ዕድሉ እንዳያመልጥ ጥረት ከተደረገ በአፍሪካ ቀንድና በኢጋድ አገሮች ዕውን እንዲሆን ለሚፈልገው ትስስርና ውህደት፣ ኢትዮጵያና ሱዳን አርዓያ መሆን ይችላሉ እየተባለ ነው፡፡ የሃይማኖት አክራሪነቶች በሁለቱም አገሮች ጎልተው አለመታየታቸውና የኢኮኖሚ ዕድገት በሁለቱም አገሮች መታየቱ ይጠቀሳል፡፡ ይህን ዕውን የሚያደርጉ በርካታ ስምምነቶች ተፈርመዋል፡፡ ፍላጎቱም በመንግሥትና በፖለቲከኞችም፣ በፓርላማ አባላትም፣ በቢዝነስ ሰዎችም ይፋ ሆኗል፡፡ “ስለዚህ ወደ ተግባር ቶሎ ገብተን በአፍሪካ ሞዴል እንሁን፡፡ የሃይማኖት ልዩነት ፀጋ እንጂ እንቅፋት እንደማይሆን ለዓለም እናሳይ፡፡ ዕድሉ ተከፍቷል፡፡ አያምልጠን፤” የሚል መንፈስ ታይቷል፡፡

የፐብሊክ ዲፕሎማሲው ቀጣይ አቅጣጫና ጉዞ ምን ይሁን?

በፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን የግብፅና የሱዳን ጉዞ ለወደፊት እንዴት መንቀሳቀስና ምን መሠራት እንዳለበት የሚያሳዩ ዕውቀትና ልምዶች ተገኝተዋል፡፡ ከግብፅና ከሱዳን ጉዞ በኋላም ቡድኑ በጋራ ተሰብስቦ ተወይይቷል፡፡ ቀጣይ አቅጣጫዎችንም ጠቁሟል፡፡ በርካታ ተግባራት መከናወን ያለባቸው ቢሆንም፣ በቀጣይ ጉዞው የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ የሚከተሉትን ዋና ዋና ሥራዎች መሥራት እንዳለበት እምነት አለ፡፡

 1. የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራ በተቋም (Institution) ይዘትና መልክ መዋቅርና መቋቋም አለበት፡፡ ተቋሙ መንግሥትና ሕግ በሚደግፈው፣ ነገር ግን  የሕዝብ ዲፕሎማሲ ባህርይውን ተጠብቆለት መዋቀርና መቆም አለበት፡፡ የራሱ ማኔጅመንት፣ ሴክሪታሪያት፣ በጀት፣ ቢሮ፣ ወዘተ ሊኖረው ይገባል፡፡ የራሱ ዌብ ሳይትም ሊኖረውም ይገባል፡፡ ወደ አንድ አገር መሄድ ሲፈለግ ተደዋውሎ ተገናኝቶ የሚንቀሳቀስ ሳይሆን፣ በቋሚ አሠራር አደረጃጀት ኖሮት እያንዳንዱ የቡድኑ አባል ስለፐብሊክ ዲፕሎማሲ የሚያስብ፣ የሚያጠናና የሚሠራ መሆን አለበት፡፡ ይህ ተቋም በአስቸኳይ መዋቀር እንዳለበት ነው፡፡
 2. እንደ ተቋም የማዋቀሩ እንዳለ ሆኖ ይህ ተግባራዊ እስኪሆን ባይጠበቅም፣ የፐብሊክ ዲፕሎማሲው ቡድን ያገኘውን ትምህርት ለሕዝብ ማስተላለፍ አለበት፡፡ የውይይት መድረኮች እየተዘጋጁ፣ ጥናቶች እየቀረቡ፣ ውይይቶችና ክርክሮች ለሕዝብ በቀጥታ መድረስ አለባቸው፡፡
 3. የጥናት ጽሑፎች በመጽሐፍ መልክ መታተም አለባቸው፡፡ በሱዳንና በኢትዮጵያዊያን ምሁራን የቀረቡ ጥናቶችና ሌሎች በመጽሐፍ መልክ ሊቀርቡ ይገባል፡፡ የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ ራሱም የራሱ ወርኃዊ መጽሔት ሊኖረው ይገባል፡፡
 4. የዳያስፖራና የስደተኛ ኢትዮጵያዊያንን ጉዳይ የሚያጠኑና መፍትሔ የሚያቀርቡ ልዩ የውይይት መድረኮች በአስቸኳይ መደራጀት ይኖርባቸዋል፡፡ ሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ያቀረቡት ሐሳብ አለ፡፡ እነሱን መነሻ በማድረግ ሌላው ስደተኛ፣ ሌላው ዲያስፖራስ ምን ይላል የሚል ሐሳብ የሚንሸራሸርበት መድረክ በአስቸኳይ ተከፍቶ ዘላቂ የሆነ የመፍትሔ ስትራቴጂ መቀየስ ይኖርበታል፡፡
 5. የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ሥራው መከናወን ያለበት ከዓባይ አጎራባች አገሮች ጋር ብቻ አይደለም፡፡ ለኢንቨስትመንት በሚፈለጉ አገሮች የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድኑ መንቀሳቀስ አለበት፡፡ ሌሎች የዓባይ ተፋሰስ አገሮችም ከኢትዮጵያ ጎን የቆሙና የትብብር ማዕቀፍ ስምምነቱን የፈረሙ ስለሆኑ፣ ግብፅና ሱዳን ብቻ መሄድ እነሱን መርሳት ወይም ችላ ማለት አለመሆኑን ማሳየትና ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ ይህም ጥያቄ እያስነሳ ነው፡፡ ቢቻል በመጓዝ ካልተቻለ ዲፕሎማቶቻቸውን በመጋበዝ፡፡
 6. የፐብሊክ ዲፕሎማሲ ቡድን አባላት የተሠለፉበትን ዓላማ ግዳጅ እንዲወጡ የሚያደርግ የሥነ ምግባር ደንብና የዓላማ ፅናት ማረጋገጫ ሰነድ የመንደፍና የመፈረም ተገቢነቱ ይታመንበታል፡፡

የፐብሊክ ዲፕሎማሲ አባል መሆን በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ግዳጅ የለበትም፡፡ ነገር ግን የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ስለሆነ አንድ ዜጋ አባል ለመሆን ፈቃደኝነቱን ከገለጸ፣ አባል ሆኖ መሥራትና መንቀሳቀስ ለሚጠይቀው ፅናት የሥነ ምግባር ደንብ (Code of Conduct) የግድ ሊኖር ይገባል፡፡ አባል መሆን በፍላጎት ቢሆንም ውጤት ለማግኘት ደግሞ ኃላፊነት፣ ታማኝነት፣ ፅናትና ብቃት አስፈላጊነቱ ታምኖበታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -