Sunday, June 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግር በሲሚንቶ ገበያ ውስጥ ችግር ፈጥሯል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በገበያ ውስጥ ለተከሰተው የሲሚንቶ እጥረት ዋነኛ ምክንያት መሆኑ ታወቀ፡፡ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጡ የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ሦስተኛውን መስመር ከጥቅም ውጪ ሲያደርግ፣ ደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ፋብሪካን ደግሞ የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረቱ የማምረት አቅሙን እንዳይጠቀም እንዳደረገበት ተገልጿል፡፡

ሁለቱ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች በሙሉ አቅም ማምረት ባለመቻላቸው፣ የሲሚንቶ አቅርቦት ጫና በዋነኛነት መሰቦና ናሽናል ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ላይ ማረፉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ከሳምንታት በፊት በዓመት 1.2 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ማምረት የሚያስችለው መስመር ቁጥር ሦስት መቆጣጠርያ መሣሪያ ተቃጥሎበታል፡፡ ይኼንን መሣሪያ ከውጭ ለማስገባት ልዩ ፈቃድ የሚያስፈልግ በመሆኑ፣ በአፋጣኝ ማስገባትና ፋብሪካውን ሥራ ማስጀመር አልተቻለም ተብሏል፡፡

የኬሚካልና የኮንስትራክሽን ግብዓት ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ሀላላ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጡ የሙገር ሲሚንቶ ፋብሪካ ሦስተኛውን መስመር ከጥቅሙ ውጪ ቢያደርገውም፣ ከአንድ ሳምንት በኋላ ሙገር የሚፈልገው መሣሪያ አገር ውስጥ የሚገባ በመሆኑ የፋብሪካው ቁጥር ሦስት መስመር ሥራ ይጀምራል፡፡

ደርባ ሚድሮክ ደግሞ የገጠመው ችግር የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ነው፡፡ የደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ደርባ ሚድሮክ ሲሚንቶ ፋብሪካ በመሉ አቅሙ ለማምረት 45 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ይፈልጋል፡፡ ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ፋብሪካው እያገኘ ያለው ከስድስት ሜጋ ዋት አይበልጥም ብለዋል፡፡

‹‹የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረቱ በሙሉ አቅማችን ሥራ እንዳንሠራ አድርጎናል፤›› በማለት አቶ ኃይሌ የችግሩን ክብደት ይናገራሉ፡፡

የእነዚህ ሁለት ፋብሪካዎች ችግር ውስጥ መግባት የሲሚንቶ ገበያውን ችግር ውስጥ ከቶታል፡፡ በእርግጥ በሥራ ላይ ያሉት የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የመሸጫ ዋጋቸው ላይ ጭማሪ ባያደርጉም ነጋዴዎች ግን በመሸጫ ዋጋ ላይ ጭማሪ አድርገዋል፡፡

መሰቦ ሲሚንቶ ሦስት ዓይነት ሲሚንቶዎች ለገበያ ያቀርባል፡፡ የሲሚንቶ መሸጫ ዋጋውም በኩንታል 250 ብር፣ 190 ብርና 165 ብር ነው፡፡ ነገር ግን በገበያ ውስጥ የመሰቦ ሲሚንቶ አንድ ኩንታል ከ350 ብር በላይ እየተሸጠ ነው፡፡

በሲሚንቶ ንግድ የተሰማሩ ነጋዴዎች እንደሚሉት፣ ማንኛውም ሰው ከፋብሪካው የፈለገውን መጠን ሲሚንቶ መግዛት ይችላል፡፡ በተለይ ደላሎች ክፍያ ተፈጽሞ ሲሚንቶውን ለማግኘት እስከ ሦስት ወራት የሚወስድ በመሆኑ ወረፋቸውን በመሸጥ ብቻ ከአንድ ኩንታል እስከ አንድ መቶ ብር እያተረፉ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በአሁኑ ጊዜ ፕሮጀክት ላለውና ንግድ ፈቃድ ላለው ቅድሚያ የሚሰጥ ባለመሆኑ የሲሚንቶ ገበያው ከፍተኛ ችግር ውስጥ እየገባ መሆኑን እየተናገሩ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት የሲሚንቶ ዋጋ በኩንታል ከ350 ብር እስከ 410 ብር ድረስ እየናረ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የመሰቦ ሲሚንቶ ፕሮሞሽን ክፍል ኃላፊ አቶ ኢሳያስ ሐጎስ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በሙገርና በደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካዎች ችግር የገበያው ጫና ወደ መሰቦ ዞሯል፡፡ መሰቦ ይህ ነው የሚባል ችግር የገጠመው ባለመሆኑ ከሰባት ሺሕ እስከ ስምንት ሺሕ ሜትሪክ ቶን ሲሚንቶ በቀን ለገበያ እያቀረበ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የሲሚንቶ ፋብሪካዎች የማምረት አቅም፣ ካለው ፍላጎት ከአምስት ሚሊዮን ቶን በላይ ትርፍ መሆኑ ይነገራል፡፡ ነገር ግን ፋብሪካዎቹ በተለያዩ ችግሮች ምክንያት የማምረት አቅማቸውን ሙሉ በመሉ መጠቀም ባለመቻላቸው ችግር እየተፈጠረ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

በሲሚንቶ ዘርፍ ያለውን ችግር ለመፍታት ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ስብሰባ ጠርቷል፡፡ በዋንኛነት በዘርፉ ያለው የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ችግርን ለመፍታት የተመከረ ሲሆን፣ በተለይ የደርባ ሲሚንቶ ፋብሪካን ችግር ለመፍታት በገፈርሳ ኃይል ማመንጫ የማሻሻያ ሥራዎች እየተከናወኑ በመሆናቸው፣ በአጭር ጊዜ ችግሩ እንደሚፈታ መግባባት ላይ ተደርሷል ሲሉ አቶ ሳሙኤል ተናግረዋል፡፡

ከወራት በፊት በአገሪቱ ለተከሰተው የሲሚንቶ ገበያ ችግር የትራንስፖርት እጥረት በምክንያትነት ይቀርብ ነበር፡፡ ይኼም የሆነበት ትራንስፖርት ባለሥልጣን በአገሪቱ የሚገኙ የደረቅ ጭነት ተሽከርካሪዎች በጂቡቲ ወደብ የተራገፉ መሠረታዊ ሸቀጦችን እንዲያነሱ በግዳጅ በማሰማራቱ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት የትራንስፖርት ችግሩ የተቃለለ ቢሆንም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ዋነኛ ምክንያት ሆኖ ቀርቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች