Sunday, April 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ሳዑዲ ስታር አንድ መቶ ሺሕ ሔክታር መሬት ጠየቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  በካሩቱሪ ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ከኤጀንሲው አቅም በላይ ሆኗል

ሳዑዲ ስታር ግብርና ልማት ኩባንያ አንድ መቶ ሺሕ ሔክታር መሬት እንዲሰጠው፣ ለግብርና ሚኒስቴር አዲስ ጥያቄ ማቅረቡን መረጃዎች አመለከቱ፡፡

ሳዑዲ ስታር የመሬት ጥያቄውን ከሦስት ዓመት በፊት ያቀረበ ቢሆንም፣ ሚኒስቴሩ ቀደም ብሎ የወሰደውን መሬት ማልማት ባለመቻሉ፣ በፍጥነት ወደ ልማት እንዲገባ ማሳሰቢያ በመስጠት ጥያቄውን አልተቀበለም ነበር፡፡ ነገር ግን ሳዑዲ ስታር በዚህ የበጀት ዓመት ቀደም ሲል ከተሰጠው አሥር ሺሕ ሔክታር መሬት ሰባት ሺሕ ሔክታሩን በማልማቱ፣ የተጨማሪ መሬት ጥያቄውን በድጋሚ ማቅረቡን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

የሼክ መሐመድ ሁሴን አል አሙዲ ግዙፍ የእርሻ ኩባንያ የሆነው ሳዑዲ ስታር፣ በጋምቤላ ክልላዊ መንግሥት አሥር ሺሕ ሔክታር መሬት የተረከበው የሩዝ ልማት ለማካሄድ እንደነበረ ይታወቃል፡፡ የኩባንያው የረጅም ጊዜ ዕቅድ በጋምቤላ፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝና በአማራ ክልሎች እስከ 500 ሺሕ ሔክታር መሬት ድረስ ማልማት ነው፡፡

ኩባንያው ከዕቅዱ ውስጥ በአብዛኛው ልማት በጋምቤላ ክልል ማካሄድ እንደሚፈልግ የኩባንያው መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ዕቅድ መሠረት አሥር ሺሕ ሔክታር መሬት በመረከብ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡

ሰፋፊ የገጠር መሬቶችን ከክልሎች በውክልና እየተረከበ የሚያስተዳድረው የኢትዮጵያ የግብርና ኢንቨስትመንትና መሬት አስተዳደር ኤጀንሲ የሚመሩት አቶ አበራ ሙላት ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሳዑዲ ስታር በዚህ የበጀት ዓመት የተሻለ የሥራ አፈጻጸም አሳይቷል፡፡ ‹‹ከዚህ ቀደም የተሰጠውን አሥር ሺሕ ሔክታር መሬት ሳያለማ ተጨማሪ መሬት በመጠየቁ የቦታ ጥያቄው አልተስተናገደም፡፡ ነገር ግን ዘንድሮ ሰባት ሺሕ ሔክታር መሬት በማልማቱ የሳዑዲ ስታር ተጨማሪ መሬት ጥያቄ ሊታይ ይችላል፤›› በማለት አቶ አበራ ኩባንያው የጠየቀው መሬት ሊሰጠው እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡

በ500 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተቋቋመው ሳዑዲ ስታር፣ ከሦስት እስከ አምስት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስት በማድረግ በአሥር ዓመት ውስጥ በ500 ሺሕ ሔክታር መሬት ላይ ሩዝን ጨምሮ የተለያዩ ሰብሎችን የማልማት ዕቅድ እንዳለው ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ነገር ግን በተሰጠው መሬት ላይ የሚፈለገውን ልማት ባለማካሄዱ ምክንያት ዕቅዱ የይስሙላ ነው ተብሎ ሲተች ነበር፡፡

የሚያመርተውን ምርት ለአገር ውስጥ ገበያ ከማቅረብ ባሻገር በተለይ ለሳዑዲ ዓረቢያ ገበያ በስፋት እንደሚያቀርብ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡ 80 ሚሊዮን ዶላር ወጭ በማድረግ ዘመናዊ የእርሻ መሣሪያዎች ገዝቶ ወደ ሥራ የገባው ሳዑዲ ስታር በቅርቡ የጠየቀው መሬት ሊሰጠው እንደሚችል የግብርና ሚኒስቴር ምንጮች ያስረዳሉ፡፡

በኢትዮጵያ ሰፋፊ እርሻ ውስጥ በመግባታቸው ድጋፍና ውግዘት ካስተናገዱ ኩባንያዎች መካከል ሳዑዲ ስታርና ካሩቱሪ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አቶ አበራ እንዳሉት ሳዑዲ ስታርና ሌሎች የህንድ ኩባንያዎች አሁን በጥሩ ሁኔታ  ላይ የሚገኙ ቢሆንም፣ ካሩቱሪ ግን በችግር ውስጥ ይገኛል፡፡

አንድ መቶ ሺሕ ሔክታር መሬት ተረክቦ ወደ ሥራ የገባው ካሩቱሪ እስካሁን ማልማት የቻለው 1,340 ሔክታር መሬት ብቻ መሆኑን አቶ አበራ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኩባንያው የውስጥ ችግር ያለበት በመሆኑ መሬቱን ያለማል ብለን አንጠብቅም፡፡ መሬቱን በመንጠቅ ለሚያለማ አካል ማስተላለፍ ቢኖርብንም፣ በእኛ ደረጃ ዕርምጃ መውሰድ አንችልም፤›› በማለት የሚናገሩት አቶ አበራ ጉዳዩ በመንግሥት ደረጃ በሚወሰድ አቋም የሚፈታ ነው ብለዋል፡፡

ካሩቱሪ ከአምስት ዓመት በፊት ከጋምቤላ ክልል 300 ሺሕ ሔክታር መሬት ተረክቦ ነበር፡፡ የክልሎችን ሰፋፊ መሬት የፌዴራል መንግሥት በውክልና ተረክቦ ማስተዳደር ሲጀምር ካሩቱሪ ይዞት ከነበረው መሬት ሁለት መቶ ሺሕ ሔክታር ተነጥቆ፣ አንድ መቶ ሺሕ ሔክታሩን እንዲያለማ ተወስኖ ነበር፡፡

ነገር ግን ከአንድ መቶ ሺሕ ሔክታር መሬቱም ቢሆን ማልማት የቻለው 1,340 ሔክታር ብቻ በመሆኑ፣ ለግብርና ሚኒስቴር ባለሥልጣናት ተስፋ አስቆራጭ ሆኗል፡፡

ግብርና ሚኒስቴር ለ86 የአገር ውስጥና የውጭ ኩባንያዎች 2.3 ሚሊዮን ሔክታር መሬት ሰጥቷል፡፡ ነገር ግን መልማት የቻለው 840 ሺሕ ሔክታር ብቻ በመሆኑ በዝቅተኛ የሥራ አፈጻጸም ተመዝግቧል፡፡  

ነገር ግን በቅርቡ በግብርና ፖሊሲ ላይ የፖለቲካ ፓርቲዎች ባደረጉት የቴሌቪዥን ክርክር በውጭ ባለሀብቶች የግብርና ልማት ላይ የተጠየቁት የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ተፈራ ደርበው፣ ‹‹የውጭ ባለሀብቶች የካፒታል እጥረታችንን በሚያቃልል፣ ቴክኖሎጂ በሚያሸጋግር፣ የገበያ ትስስር በሚፈጥር መንገድ እስከ 300,000 ሔክታር የሚደርስ መሬት ይዘው ለማልማት ጥረት እያደረጉ ነው፡፡ 50 ሚሊዮን ሔክታር ገና የሚለማ መሬት አለን፤›› ብለዋል፡፡ በአገር ውስጥ ባለሀብቶች 2.2 ሚሊዮን ሔክታር መልማቱንም አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች