Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የሆላንድ ካር ባለቤት ኩባንያቸውን ለመታደግ ወደ አገር ቤት ተመለሱ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  የኩባንያው ንብረት እንዳይሸጥ በድጋሚ ታገደ

በሆላንድ ካር የመኪና መገጣጠሚያ ኩባንያ በተፈጠረ ቀውስ ከሦስት ዓመት በፊት ኪሳራ በማሳወጅ አገር ጥለው የተሰደዱት ኢንጂነር ታደሰ ተሰማ፣ ኩባንያቸውን ለመታደግ ግንቦት 4 ቀን 2007 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ፡፡

ኢንጂነር ታደሰ ግንቦት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ኩባንያውን ለመታደግ የሚያስችል ዕቅድ ነድፈውና ለመንግሥት አቅርበው ተቀባይነት በማግኘታቸው የሕግ ከለላ ተሰጥቷቸው ወደ አገር ቤት መመለሳቸውን ተናግረዋል፡፡

ከ200 በላይ የሚሆኑ ደንበኞች መኪና ለመግዛት ለሆላንድ ካር ክፍያ ፈጽመው ኩባንያው መኪኖቻቸውን ለማስረከብ ሳይችል መቅረቱ ይታወሳል፡፡ ለኩባንያው ብድር የሰጠው ዘመን ባንክ በመያዣነት የያዛቸውን የኩባንያውን ንብረቶች ለመሸጥ ጥረት ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ መኪኖቻቸውን ያልተረከቡት ደንበኞችም በፍርድ ቤት ሲሟገቱ ቆይተዋል፡፡

በሆላንድ ካር መክሰር ምክንያት የኩባንያው ባለቤትና ዋና ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ታደሰ በ2004 ዓ.ም. ወደ ኔዘርላንድ ተሰደዋል፡፡ ኩባንያው በየካቲት 2005 ዓ.ም. በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መክሰሩ በይፋ ታውጇል፡፡

አቶ ታደሰ ኩባንያቸው ወደ ኪሳራ ሊገባ የቻለው በመሥሪያ ካፒታል እጥረት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ከሦስት ዓመት በፊት አገሬን ለቅቄ ወጥቼ ነበር፡፡ የወጣሁበት ምክንያት ሆላንድ ካር ውስጥ በተፈጠረ ችግር ምክንያት ሥራ መሥራት ስላልተቻለ ነው፡፡ ለገጠሙን ችግሮች መፍትሔ ማግኘት ስላልቻልኩኝ ምናልባት ለጊዜው ዞር ማለት ይሻላል በማለት ወጥቼ ነበር፤›› ብለዋል፡፡

ከአገር ከወጡ በኋላ የተቋረጠውን የኩባንያውን ሥራ ለማስቀጠል በተለይ መኪና የገዙ ደንበኞች ንብረታቸውን የሚያገኙበት ዘዴ ከመፈለግ ወደኋላ እንዳላሉ አስረድተዋል፡፡ ‹‹ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ፕሮፖዛሎች አስገብቻለሁ፤›› ያሉት ኢንጂነር ታደሰ፣ በመጨረሻ ለመንግሥት ያስገቡት ፕሮፖዛል በቤልጂየም የኢትዮጵያ ኤምባሲ በኩል ቀርቦ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና በፍትሕ ሚኒስቴር በተደረገላቸው ድጋፍ የሕግ ከለላ ተሰጥቷቸው አገራቸው ገብተው እንዲሠሩ መደረጉን ተናግረዋል፡፡

ሆላንድ ካር የከሰረበት ምክንያት ንብረት በማጣት እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡ ኢንጂነር ታደሰ አበዳሪያቸውን ዘመን ባንክን ወቅሰዋል፡፡ ‹‹በዚያን ጊዜ ባንኩ የኩባንያውን ንብረቶች የመሸጥ አቋም ነበረው፡፡ ያ ቢሆን የአንድ ቡድን ጥቅም ብቻ ነው የሚጠበቀው፡፡ ባንኩ ንብረቶቹን ሽጦ ገንዘቡን ይወስዳል፡፡ የቀሩት ደንበኞች ምንም የሚያገኙት ነገር አይኖርም፡፡ ከባንኩ ጋር ስንነጋገር የነበረው ወደ ሐራጅ ከተገባ ደንበኞች ስለሚጎዱ ወደዚያ አንግባ ብዬ ብዙ ተከራክሬያለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ዘመን ባንክ በሠራው የፋይናንስ ዕቅድ ኩባንያውን ለመታደግ በወቅቱ ለሦስት ወራት 17 ሚሊዮን ብር ያስፈልግ እንደነበር ጠቁሞ፣ ከሦስት ወራት በኋላ ያለ ዕዳ መንቀሳቀስ ይችላል የሚል ነበር፡፡ ‹‹ነገር ግን ባንኩ ቶሎ ብሎ ወደ ሐራጅ ማውጣት ስለፈለገ ያንን ለመከላከል የምችለው ኪሳራ በማወጅ ብቻ ነው፡፡ ወደ ኪሳራ በማስገባበት ጊዜ ባንኩ እንደ ሌሎች ደንበኞች ተሰልፎ ይጠብቃል፡፡ እኔ ብቻ ሸጬ ልውሰድ የሚለው አይኖርም፡፡ ይህን ደግመን ደጋግመን ተናግረናል፡፡ እዚያ ውስጥ አንግባ በሚል ተነጋግረናል፡፡ እስከ መጨረሻው ቀን ጠብቄ ወደ ኪሳራ እንዲገባ አድርጌያለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ሪፖርተር ዘመን ባንክን ለማነጋገር ተደጋጋሚ ጥረት ያደረገ ቢሆንም፣ ማኔጅመንቱ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡ ‹‹አስተያየት የለንም፤›› ብለዋል አንድ የባንኩ ከፍተኛ ኃላፊ፡፡

ሆላንድ ካር የዘመን ባንክ 34 ሚሊዮን ብር ዕዳ አለበት፡፡ ባንኩ የኩባንያውን ንብረቶች በ83 ሚሊዮን ብር የመነሻ ዋጋ ለጨረታ አቅርቧል፡፡ ሞጆ ከተማ የሚገኘው በ20,000 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ያረፈው የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ፣ መጋዘንና የቢሮ ሕንፃ 22.3 ሚሊዮን ብር የተገመተ ሲሆን፣ 236 ያልተገጣጠሙና 70 የተገጣጠሙ መኪኖች 51.7 ሚሊዮን ብር ተተምነዋል፡፡

ዘመን ባንክ የጨረታ ማስታወቂያውን ባለፈው ሳምንት በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ያስነገረ ሲሆን፣ የጨረታ መዝጊያው ግንቦት 8 ቀን 2007 ዓ.ም. ነበር፡፡ ኢንጂነር ታደሰ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ግንቦት 7 ቀን 2007 ዓ.ም. የኩባንያው ንብረቶች እንዳይሸጡ አግዷል፡፡ እንደ ኢንጂነር ታደሰ ገለጻ ኩባንያው ያለበት የባንክ፣ የደንበኞችና የመንግሥት (ግብር) ዕዳ በአጠቃላይ 63 ሚሊዮን ብር ሲሆን፣ የኩባንያው ጠቅላላ ንብረት ግምት 180 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ኢንጂነር ታደሰ በአውሮፓ ቆይታቸው የገንዘብ ምንጭ ሲያፈላልጉ እንደነበር ገልጸው፣ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት በቤልጂየም ከኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ተሾመ ቶጋ ጋር ረዥም ጊዜ ሲወያዩ እንደነበር፣ አምባሳደር ተሾመ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ተናግረዋል፡፡

አዲስ የነደፉትን ሆላንድ ካርን ካለበት ችግር አውጥቶ ወደፊት ሊያስኬድ የሚያስችል ያሉትን ዕቅድ፣ ቤልጂየም ለሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ አቅርበው ኤምባሲው ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ማቅረቡን፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽንና የፍትሕ ሚኒስቴር አስተያየት እንዲሰጡበት ተጠይቀው ዕቅዱ ተቀባይነት በማግኘቱ፣ አስፈላጊው የሕግ ከለላ ተደርጎላቸው ወደ አገር ቤት ተመልሰው ችግሮቹን በውይይት እንዲፈቱ እንደተፈቀደላቸው አስረድተዋል፡፡

ኢንጂነር ታደሰ ያቀረቡት ዕቅድ በመጀመርያ በፋብሪካ ውስጥ የሚገኙትን መኪኖች ገጣጥሞ ክፍያ ለፈጸሙ ደንበኞች ማቅረብ፣ በመቀጠል የተቀሩትን መኪኖች ገጣጥሞ በመሸጥ ኩባንያው ያለበትን የባንክ ዕዳ መክፈል የሚል ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት 150 ያልተገጣጠሙ መኪኖች በፋብሪካው ውስጥ እንደሚገኙ ጠቅሰው፣ እነዚህን መኪኖች ለመገጣጠም አምስት ሚሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ስድስት ሚሊዮን ብር ከአውሮፓ የገንዘብ ምንጮች ይዘው እንደመጡ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ሆላንድ ካር ከገባበት ማጥ ውስጥ ለማውጣት አንድ ዓመት እንደሚፈጅም ተናግረዋል፡፡ ‹‹ያልተገጣጠመ መኪና ብረት ነው፡፡ አይሸጥም፡፡ ገጣጥመን እሴት ጨምረን ብንሸጠው ሁሉም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ ደንበኞች ንብረታቸውን ያገኛሉ፡፡ ከዚያም ተርፎ ድርጅቱ መቀጠል የሚችልበት ሁኔታ ይኖራል፤›› ብለዋል፡፡

ኢንጂነር ታደሰ 115 ደንበኞች ክፍያ ፈጽመው መኪኖቻቸውን አለመረከባቸውን፣ 40 ያህል ደግሞ ቀረጥ ከፍለው መኪኖቹን መውሰዳቸውን አረጋግጠዋል፡፡ የጀመሩት ጥረት ከሰመረ ወደ ሌሎች ኢንቨስትመንቶች ለመግባት ዕቅድ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

 ከሆላንድ ካር መኪና ከገዙ ግለሰቦች መካከል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉ አንዱ ናቸው፡፡ በሆላንድ ካር ቀውስ ከተፈጠረ በኋላ መኪናቸውን የተረከቡ የመጀመርያው ደንበኛ መሆናቸውን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹መኪናዬን ከተረከብኩ በኋላ ሌሎች ግለሰቦች መኪናቸውን እንዲያገኙ ጊዜዬንና ገንዘቤን በመሰዋት ብዙ ጥረት አድርጌያለሁ፡፡ ሆኖም እጃችን አመድ አፋሽ ሆነና ባልሠራነው ኃጢያት ተከሰን ጠበቃ ቀጥረን ተከራክረን ነፃ ወጥተናል፤›› በማለት በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ አስታውሰዋል፡፡ ‹‹አሁን ባለሀብቱ ያሉትን ችግሮች ፈትቼ ከባንኩ ጋር ተነጋግሬ ለደንበኞች መኪኖቹን አስረክባለሁ ካሉ በእውነቱ ይህ መልካም ዜና ነው፡፡ የሚደገፍ ተግባር ነው፤›› ብለዋል አቶ ግርማ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች