በአገራችን በሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ውስጥ ተሳታፊ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ሊወደሱ ይገባቸዋል፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል የሚጠይቀውን ፅናትና ቁርጠኝነት ተላብሰው በኢትዮጵያ ምድር ዴሞክራሲ እንዲሰፍን የሚያደርጉት አስተዋጽኦ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል እንደ ስሙ ሳይሆን፣ በጣም የከበደ ኃላፊነትና ተልዕኮ ያለው በመሆኑ በፅናትና በቁርጠኝነት የሚደረገው ትግል ሸክሙ የከበደ ነው፡፡ ለዘመናት የዘለቀው ሥር የሰደደ የአምባገነንነት አስተሳሰብ የተፀናወተው የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ መሳተፍ በራሱ ከባድ ነው፡፡ ነገር ግን ቁርጠኝነት ከሌለ ልፋቱ በሙሉ መና ይቀራል፡፡
ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ በአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ሊያመጣ የሚችለው፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወጥ የሆነ ርዕዮተ ዓለም ሲያራምዱና በተደራጀ ሁኔታ የተዘጋጀ የዓላማ ማስፈጸሚያ ፕሮግራም ሲኖራቸው ነው፡፡ መነሻውንና መድረሻውን በቅጡ መርምሮ ዓላማውን ከዳር ለማድረስ የተዘጋጀ ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲ፣ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ በቁርጠኝነት ትግሉን የመምራት ብቃት ይኖረዋል፡፡ ከዚህ አንፃር የአገራችንን የፖለቲካ ፓርቲዎች ስንገመግማቸው በርካታ ውስጣዊና ውጪያዊ ችግሮች ቢኖሩባቸውም፣ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ላላቸው ቁርጠኝነትና ፅናት ምሥጋና ይገባቸዋል፡፡ ቁርጠኝነት በፅናት በቀጠለ ቁጥር ዴሞክራሲን አለማምዶ የህልውና መሠረት ለማድረግ የሚደረገው ጥረት ጊዜ ቢወስድም ተግባራዊ መሆኑ አይቀርም፡፡
ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ በተጠናከረና የፖለቲካ ፓርቲዎች ልምድ በጨመረ ቁጥር፣ ዴሞክራሲ በኢትዮጵያ ምርጡ የመንግሥት መመሥረቻ ዘዴ ይሆናል፡፡ በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚፈጠር መንግሥት ሁልጊዜም በራሳቸው የሚተማመኑና ነፃነት ያላቸው ዜጎችን ያፈራል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብትን ተግባራዊ ያደርጋል፡፡ የዜጎች ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ይስከብራል፡፡ ዜጎች በነፃነት የፈለጉትን ይመርጣሉ፡፡ የሕግ የበላይነት ይኖራል፡፡ የመረጡትን መንግሥት በነፃነት ይተቻሉ፡፡ በፖሊሲዎች አወጣጥ ላይ ተፅዕኖ ያሳድራሉ፡፡ በአገር ብሔራዊ ጉዳዮች ቀጥታ ተሳትፎ ስላላቸው ለሰላምና ለመረጋጋት አስተዋጽኦ ያደርጋሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹ ነፃነቶች ተግባራዊ ሆነው መታየት የሚችሉት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ስኬታማ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ በአመፅና በብጥብጥ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት ይቅርና በሰላም ወጥቶ መግባት ይቸግራል፡፡
ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ፅናትና ቁርጠኝነት ያስፈልገዋል ሲባል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላቶቻቸውንና ደጋፊዎቻቸውን ከማናቸውም ሕገወጥ ተግባራት ሲያቅቡና ሲቆጣጠሩ፣ ዓላማዎቻቸውን በሚገባ በማስረፅ ሕዝቡን የሚያማልሉ የፖሊሲ አማራጮችን ሲያቀርቡ፣ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲፈጠሩና እንዲያብቡ አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ፣ ለነፃ ሐሳብና ውይይት በራቸውን ክፍት ሲያደርጉ፣ ከጥላቻና ኢዴሞክራቲክ ከሆኑ አስተሳሰቦች ራሳቸውን በማላቀቅ የሕዝብን ፍላጎት ማስተጋባት ሲችሉ፣ በተጠናና በተደራጀ መንገድ የሰሉ ትችቶችን ሲያቀርቡ፣ ለሚፈጠሩ ችግሮች መፍትሔ አመንጪ መሆን ሲችሉና መሰል ጠቃሚ ተግባራትን ሲያከናውኑ ነው፡፡ እነዚህን ተግባራት ለማከናወን ደግሞ በምርጫ ወቅት የሚደረጉ ቅስቀሳዎች ወይም ክርክሮች ብቻ ሳይሆኑ የሁልጊዜ ሥራቸው መሆናቸውን ማወቅ ይኖርባቸዋል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ግብ ሥልጣን በመያዝ አገር ማስተዳደር እንደመሆኑ መጠን፣ ለዚህ ግብ ስኬት ደግሞ ዋነኛው ቁልፍ በዴሞክራሲያዊ ምርጫ የሕዝቡን ድምፅ አግኝቶ ማሸነፍ ነው፡፡ ይህንን ድል ለመቀዳጅት በሚደረገው ትግል በርካታ መሰናክሎች ይኖራሉ፡፡ ሥልጣን በያዘው ገዥ ፓርቲና በሚያስተዳድረው የመንግሥት መዋቅሮች የሚደርሱ ፈተናዎች አሉ፡፡ ፓርቲዎች እርስ በርስ በሚያደርጓቸው ግንኙነቶች የሚፈጠሩ ችግሮች ይኖራሉ፡፡ በራሳቸው በፓርቲዎች ውስጥ አለመግባባቶች ይፈጠራሉ፡፡ ፓርቲዎችን በገንዘብና በተለያዩ ቁሳቁሶች የሚደግፉ አካላት ተፅዕኖዎች ሳይቀሩ መሰናክሎች ናቸው፡፡ ምርጫ ከሚያስፈጽመው አካል ጋር በሚደረግ ግንኙነት አለመስማማቶች ወይም ቅሬታዎች ይፈጠራሉ፡፡ እነዚህ ከላይ የተጠቀሱት መሰናክሎች በአገራችን የሰላማዊ ፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ በብዛት የሚታዩ ችግሮች ናቸው፡፡ እነዚህን ችግሮች በብቃት ተቋቁሞ ህልውናን ማስጠበቅ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡
የፖለቲካ ፓርቲዎች ህልውና እጅግ አዳጋች በሆኑ ችግሮች ውስጥ ሲገባ ከማንም በላይ ለመፍትሔው መሯሯጥ ያለባቸው የፓርቲ አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው፡፡ ለመፍትሔ የሚደረገው እንቅስቃሴ በተጠና ዘዴ የማይከናወን ከሆነ ችግሩ ይሰፋል፡፡ ከቁጥጥር በላይ ይሆናል፡፡ የፓርቲዎች ህልውና አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ ስህተትን በስህተት የማረም ሙከራ ከተደረገ ውጤቱ አስከፊ ነው፡፡ የተለመዱ ስህተቶችን መድገምም አደገኛ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የተጓዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሲበተኑ ወይም ሲፈርሱ በተደጋጋሚ ታይተዋል፡፡ እንኳን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እገዛ ሊያደርጉ ራሳቸውም ከስመዋል፡፡ ይህ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግር አሁንም ድረስ አለ፡፡ ቁርጠኝነትና ፅናት እየጠፋ የመከኑ ብዙ ናቸው፡፡
ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል አንዳንዶቹ እንደሚሉት ቀላል ወይም መስዋዕትነት የማይከፈልበት አይደለም፡፡ ይልቁኑም በኢንተርኔት የጦርነት ከበሮ እየደለቁ ‹‹ጦርነት አውጀናል›› ከሚሉት የተለየ ነው፡፡ የበለጠ መከራ የሚታይበትም ነው፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል መስመሩን እየሳተ ሕጋዊና ሕገወጡን መቀላቀል ሲጀምር ደግሞ መስዋዕትነቱ የከፋ ከመሆንም በላይ ይሆናል፡፡ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል በዴሞክራቲክ አስተሳሰብ የሚያምኑ፣ ለሰብዓዊና ለዴሞክራሲያዊ መብት መከበር የሚታገሉ፣ አገር ከአምባገነናዊ አስተሳሰብ ተላቃ ሁሉም ዜጎች በሰላምና በፍቅር የሚኖሩባት እንድትሆን በፅናት መስዋዕትነት የሚከፍሉ ዜጎች የሚሳተፉበት ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ትግል እናደርጋለን የሚሉ ግን ሲጀመር የሰው ልጆችን ነፃነት አያከብሩም፡፡ የሐሳብ ልዩነትን አይቀበሉም፡፡ የሚቃወማቸውን በጅምላ ፈርጀው ማንነቱን ሳይቀር እየተሳደቡ ጥላቻ ይዘራሉ፡፡ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከትና በመሳሰሉት ልዩነቶች ሳይቀር የሚቃወሙዋቸውን ይሳደባሉ፡፡ የአገር ብሔራዊ ደኅንነትንና የሕዝቡን የጋራ ጥቅም ለአደጋ ያጋልጣሉ፡፡ ከጠባብ የቡድን ፍላጎታቸው ውጪ የአገር ጉዳይ ለእነሱ ምንም አይደለም፡፡ ሥልጣን ቢይዙ እንኳ የሰው መብት ከመጣስ አይመለሱም፡፡ ዴሞክራትነት ተፈጥሮአቸው አይደለምና፡፡
ሌላው ቀርቶ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ውስጥ በፅናት እየታገሉ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ‹‹ፈሪ፣ አድርባይ፣ የገዢው ፓርቲ አጃቢ፣ ወዘተ›› እያሉ በመጥራት ሰላማዊውን የፖለቲካ ትግል ለማኮላሸት ይፈልጋሉ፡፡ በሌላ በኩል ሰላማዊው የፖለቲካ ትግል ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዳይከናወን ከገዢው ፓርቲ በኩል የሚታዩ አላስፈላጊ የሆኑ ወከባዎች፣ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውን እየተፈታተኑ ናቸው፡፡ ምርጫ በደረሰ ቁጥር ማዋከብ፣ ማሰርና የመሳሰሉት ችግሮች በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች መድረሳቸው በተለያዩ ጊዜያት ይነገራል፡፡ ይህ ዓይነቱ ተደጋጋሚ ፀረ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል እንቅስቃሴ ለሰላምና መረጋጋት እንቅፋት መሆኑ አይቀርም፡፡ ሕገወጥ ተግባራት ይፈጸማሉ ተብሎ ቢታመን እንኳን የፖለቲካ ፓርቲዎቹ መጠየቅ ያለባቸው በሕጋዊ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ ያሉ የኃይል ተግባራት ተቀባይነት የላቸውም፡፡ ለአገሪቱም አይጠቅሟትም፡፡ ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው ሲባል የአገሪቱ ዘለቄታዊ ህልውና ነው መቅደም ያለበት፡፡
የሰላማዊ ፖለቲካ ትግሉ ፋይዳ በፖለቲካ ፓርቲዎች ፅናትና ቁርጠኝነት ይለካል ሲባል፣ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሕገወጥ ተግባራት በመራቅ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ እየሠሩ መሆናቸውን ማረጋገጥ መቻል ተገቢ ነው፡፡ ከሕግ የበላይነት በማፈንገጥና ሕገወጥ ተግባራትን በማበረታታት ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ማካሄድ በፍፁም አይቻልም፡፡ ሕዝብ ነፃነት ኖሮኝ በአገሬ ሠርቼ እኖራለሁ ብሎ ሲያስብ በሕግ የበላይነት ተማምኖ ነው፡፡ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ማፅናትም ያለባቸው ሕጋዊነትን ነው፡፡ በኃይል የፖለቲካ ሥልጣን ለመያዝ የሚደረገው ፍላጎት ጊዜ ያለፈበት በመሆኑ፣ ለሰላማዊና ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ ቅድሚያ ይሰጥ፡፡ ዜጎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ናቸው እንደሚባለው ሁሉ፣ ሁሉም ሰላማዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕግ ፊት እኩል ይሁኑ፡፡ ሕገወጥ ተግባራትን በማውገዝና ሕጋዊ በመሆን ራሳቸውን በተግባር ያሳዩ፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የሚያደርጉት ሰላማዊ ትግል በሕገወጦች የሚታዘዝ አለመሆኑን በተግባር ያረጋግጡ፡፡ ሕጋዊነትንና ሕገወጥነትን አይቀላቅሉ፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች የአኩራፊዎችና የተበሳጩ ግለሰቦች መሰባሰቢያ እንዳልሆኑ፣ በሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ያረጋግጡ፡፡ የሕዝብን ስሜት ያዳምጡ፡፡ የሕዝብን ውሳኔ ያክብሩ፡፡ ለሰላማዊ የፖለቲካ ትግሉ ቁርጠኝነታቸውንና ፅናታቸውን ያሳዩ!