Thursday, September 21, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኢትዮጵያ የመጀመርያውን የብረት ማዕድን ለማውጣት ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ኃላፊነቱን ተረከበ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽ በኢትዮጵያ የመጀመርያውን የብረት ማዕድን ማውጫና ማቅለጫ ፋብሪካ ሊገነባ ነው፡፡ ፋብሪካው የሚገነባው በምሥራቅ ወለጋ ዞን ነቀምት ከተማ ሲሆን፣ የብረት ክምችቱም በምዕራብ ወለጋ ዞን ቢቅላል አካባቢ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

ለዚህ ግዙፍና ለአገሪቱ የመጀመርያ ለሆነው ፋብሪካና የብረት ማዕድን ማውጪያ ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚደረግ፣ ግንቦት 6 ቀን 2007 ዓ.ም. የፋብሪካው የመሠረት ድንጋይ በነቀምት ከተማ በተቀመጠበት ወቅት ተገልጿል፡፡

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ብርጋዴር ጄኔራል ጠና ቁሩንዴ እንደተናገሩት፣ የሚገነባው የብረታ ብረት ፋብሪካ በዓመት ከሦስት መቶ ሺሕ ሜትሪክ ቶን በላይ የተለያዩ ብረቶችን ማምረት ያስችላል፡፡

በቀድሞው ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ባለቤትነት በኢትዮጵያ መሠረታዊ ለውጥ ማምጣት ያስችላሉ የተባሉትን የድንጋይ ከሰልና የብረት ማዕድን መገኛ ለማወቅ ጥናት ተካሂዶ ነበር፡፡ በሚኒስቴሩ በተቋቋመው ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትና የቻይና ኩባንያዎች በተሳተፉበት ጥናት፣ በምዕራብ ኢትዮጵያ ኢሉአባቦራ ዞን ያዩ አካባቢ ከፍተኛ የድንጋይ ከሰል መኖሩን፣ በዚሁ ቀጣና ውስጥ ምዕራብ ወለጋ ቢቅላል አካባቢ ደግሞ የብረት ማዕድን ክምችት (አይረን ኦር) ከሌሎች ማዕድናት ጋር መኖሩን አመልክቷል፡፡

በወቅቱ እነዚህን ማዕድናት ማውጣትና ማምረት የሚያስችል ፋብሪካ ለማቋቋም የሚፈለገው ካፒታል ከፍተኛ በመሆኑ ሳይሞከር እንደቀረ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ነገር ግን ከመከላከያ ተገንጥሎ በኢትዮጵያ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ለውጥ እንዲያመጣ የተቋቋመው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ በሒደት በሁለቱም ዘርፎች በጥልቀት መግባት ችሏል፡፡

ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ወቅት ያዩ አካባቢ የሚገኘውን የድንጋይ ከሰል በማውጣት ማዳበሪያ ፋብሪካ ለመገንባት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከጀመረ ዓመት አስቆጥሯል፡፡ ባለፈው ሳምንት አጋማሽ ደግሞ የብረት ማዕድን አውጥቶ የሚያቀልጥበት ፋብሪካ ለመገንባት የመሠረት ድንጋይ አስቀምጧል፡፡

በብረታ ብረት ኢንዱስትሪ ዘርፍ ግዙፍ ኩባንያ የሆነው ስቲሊ አርኤምአይ  የኦፕሬሽንና የፖሊሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ተፈራ ለማ የፋብሪካውን መገንባት አስመልክተው ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ ከውጭ ይገባ የነበረው ቢሌት (ጥቅል ፌሮ ብረት) አገር ውስጥ ማምረት መቻል ትልቅ ትርጉም አለው፡፡

አቶ ተፈራ ጨምረው እንደገለጹት፣ አገር ውስጥ ሲመረት የቆየው ብረት ከወዳደቁ ብረታ ብረት (ስክራፕ) እና ከውጭ በሚገባ ቢሌት ነው፡፡ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ወደዚህ ዘርፍ ከገባ ዩክሬን፣ ቻይናና አውስትራሊያ የሚታወቁበት የብረት ምርት በኢትዮጵያ እንዲመረት ያስችላል፡፡

‹‹ይህ ለአገሪቱ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ ነው፤›› በማለት አቶ ተፈራ የፕሮጀክቱን ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አብራርተዋል፡፡

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ይኼን አዲስ ፕሮጀክት በሁለተኛው የአምስት ዓመት የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውስጥ ያካተተ ሲሆን፣ ፕሮጀክቱ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል፡፡

የፕሮጀክቱ ዕውን መሆን ለምዕራብ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ከመፍጠሩም ባሻገር፣ በሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ይፈጥራልም ተብሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች