Tuesday, April 16, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከንፋስ ኃይል ማመንጨት የተቻለው 324 ሜጋ ዋት ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

– በርካታ የውጭ ኩባንያዎች ከንፋስ ኃይል ለማመንጨት ፍላጎት አሳዩ

በሰኔ 2007 ዓ.ም. መጨረሻ በሚጠናቀቀው የአምስት ዓመቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን፣ ከንፋስ ከሚገኝ የኤሌክትሪክ ኃይል 894 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ለማመንጨት ቢታሰብም፣ ማሳካት የተቻለው 324 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻ መሆኑ ተገለጸ፡፡

ይህ 324 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ሊገኝ የቻለው ከአዳማ አንድ 51 ሜጋ ዋት፣ ከአሸጎዳ 120 ሜጋ ዋትና ግንቦት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ከተመረቀው አዳማ ሁለት 153 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ድምር ነው፡፡

ሌሎች ፕሮጀክቶች በሚፈለገው ፍጥነት መሄድ ባለመቻላቸው ዕቅዱ ወደሚቀጥለው አምስት ዓመት መሸጋገር ግድ ሆኖበታል፡፡ በዕቅድ ዘመኑ ግንባታቸው ተጀምሮ ይጠናቀቃሉ ተብሎ ይጠበቁ የነበሩት አይሻ 300 ሜጋ ዋት፣ መሶቦ-ሐረና 42 ሜጋ ዋት፣ አሰላ 100 ሜጋ ዋትና ደብረ ብርሃን 100 ሜጋ ዋት የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ናቸው፡፡

እነዚህ ፕሮጀክቶች ግን እስካሁን ፋይናንስም ሆነ ኮንትራክተር አላገኙም፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፣ እነዚህን የንፋስ ኃይል ኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክቶችን ለማግኘት በርካታ ኩባንያዎች ፍላጎት እያሳዩ ነው፡፡

ምንጮች እንደገለጹት የአይሻን ፕሮጀክት የቻይናው ዲዶንግ ፎንግና የጀርመኑ ላፍቶ ኩባንያዎች ለማልማት ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ከእነዚህ ኩባንያዎች በተጨማሪ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን የፕሮጀክቱ ተሳታፊ እንዲሆን መንግሥት ፍላጎት አሳይቶ በድርድር ሒደት ላይ ይገኛል፡፡

አዳማ ሁለትን የገነቡት ኃይድሮ ቻይናና ሲጂሲ ኦቨርሲስ አሰላ ላይ ይገነባል ተብሎ የሚጠበቀውን የንፋስ ኃይል ፕሮጀክት በአዳማ ሦስት ስም ለመረከብ ድርድር እያካሄዱ ነው፡፡

ነገር ግን የአሜሪካው ዲሴንቴ ኩባንያን ጨምሮ የቱርክ፣ የቻይናና የአውሮፓ ኩባንያዎች የንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ለማግኘት ፍላጎት እያሳዩ በመሆናቸው ውድድሩ መካረሩን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

እነዚህ የውጭ ኩባንያዎች ይዘው የመጡት በዓለም አቀፍ ደረጃ የወቅቱ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ከመሆኑም ባሻገር፣ አንድ ተርባይን ያለው የማመንጨት አቅም አሁን ካለው 1.5 ሜጋ ዋት የበለጠ በመሆኑ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ድርጅት በሩን ለድርድር እንዲከፍት እንዳደረገው ታውቋል፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ 95 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተገነባው አዳማ ሁለት ንፋስ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት በተመረቀበት ወቅት የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ አቶ ዓለማየሁ ተገኑ እንደተናገሩት፣ የአዳማ ሁለት ፕሮጀክት ሥራ መጀመር በአገሪቱ ከንፋስ ኃይል ይመረት የነበረውን 171 ሜጋ ዋት ኤሌክትሪክ ወደ 324 ሜጋ ዋት አሸጋግሮታል፡፡

‹‹እነዚህ የንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከውኃ ማመንጫ ጣቢያዎች ጋር የተጣጣመ የኃይል ስብጥር ለመፍጠር ጠቀሜታ አላቸው፤›› ያሉት አቶ ዓለማየሁ፣ ‹‹የዝናብ እጥረት በሚያጋጥምበት ወቅት የንፋስ ኃይል የሚጨምር በመሆኑ፣ አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት ከመዘርጋት አንፃር ጉልህ ሚና ይጫወታል፤›› በማለትም የፕሮጀክቱን ጠቀሜታ አብራርተዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከውኃና ከንፋስ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች 2,368 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት መቻሉን፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል መረጃ ያመለክታል፡፡

ኢትዮጵያ ከውኃ 50 ሺሕ ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ 1.3 ሚሊዮን ሜጋ ዋት፣ ከእንፋሎት ከአሥር ሺሕ ሜጋ ዋት በላይ የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም እንዳላት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

በሰኔ 2005 ዓ.ም. ተጀምሮ በግንቦት 2007 ዓ.ም. የተጠናቀቀው አዳማ ሁለት 102 ተርባይኖች አሉት፡፡ አንዱ ተርባይን 1.5 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው፡፡ ይህ ፕሮጀክት 345 ሚሊዮን ዶላር ሲወጣበት፣ 85 በመቶ በቻይናው ኤግዚም ባንክ፣ ቀሪው 15 በመቶ ደግሞ በኢትዮጵያ መንግሥት የተሸፈነ መሆኑ ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች