ዘ ኢስት አፍሪካን የተሰኘ ድረ ገጽ 50 የሚሆኑ በከፍተኛ ሁኔታ የታጠቁ የኢትዮጵያ ወታደሮች የኬንያን ድንበር በማቋረጣቸው ምክንያት፣ የኬንያ የፀጥታ አካላት በከፍተኛ ተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን ዘገበ፡፡ መንግሥት ግን አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል፡፡
በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ተወልደ ሙሉጌታ ‹‹ብዙም የተጠናከረ መረጃ የለኝም፤›› በማለት ለሪፖርተር ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በኬንያ ሰሜናዊ ሁር ግዛት የሚገኘውን ኢለሬት ፖሊስ ጣቢያን የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የተቆጣጠሩት የሁለቱ አገሮች ድንበር ለማካለል የቅየሳ ሥራ ከተጠናቀቀ ከአንድ ሳምንት በኋላ እንደሆነ፣ የኬንያ ፖሊስን ጠቅሶ ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
ክላሺንኮቭ መሣሪያዎችን የታጠቁ የኢትዮጵያ ወታደሮች በአሥር ተሽከርካሪዎች ተጭነው የኬንያን ድንበር 16 ኪሎ ሜትሮችን ያህል አቋርጠው በመግባት ገዥ ቦታዎችን በመያዝ፣ የፖሊስ ጣቢያውን የከበቡ መሆናቸውና በአካባቢው ቅኝት ማድረጋቸውን፣ እንዲሁም ፎቶግራፎችን ማንሳታቸውንም እንዲሁ ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
በድረ ገጹ ዘገባ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ሥፍራውን እንደሚለቁ ቃል መግባታቸውን ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ሠራዊት ድንበሩን ያቋረጠበትን ምክንያት ያልጠቀሰው ድረ ገጹ፣ የኢትዮጵያ ጦር ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ የኬንያን ድንበር ማቋረጡን አስታውሶ ዘግቧል፡፡
የኬንያ መከላከያ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኮሎኔል ዴቪድ ኦቦነዬ ስለክስተቱ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸው፣ ‹‹ኢትዮጵያና ኬንያ ዘለግ ያለ ዕድሜ ያስቆጠረ ግንኙነት ያላቸውና ወዳጆች ከመሆናቸው አንፃር ኢትዮጵያውያኑ የከፋ ነገር ያደርሳሉ የሚል እምነት የለኝም፤›› በማለት መግለጻቸውን ድረ ገጹ አስነብቧል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ በማኅበራዊ ድረ ገጾች አስተያየታቸውን ያሰፈሩ ሰዎች፣ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የኬንያን ድንበር በማለፍ የገባው በመጪው እሑድ የሚካሄደው ምርጫ ያለምንም የፀጥታ ሥጋት እንዲካሄድ አስተማማኝ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡ በተለይ አልሸባብን የመሳሰሉ ሰርጎ ገቦች የፀጥታ ሥጋት እንዳይሆኑ ለማድረግ የተከናወነ ድርጊት መሆኑንም አክለዋል፡፡