Monday, December 4, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብረታ ብረት ኮርፖሬሽን ተርባይን ማምረቻ ፋብሪካ ሊገነባ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  በ350 ሚሊዮን ብር ያስገነባውን ትራንስፎርመር ፋብሪካ አስመርቋል

በግዙፉ መንግሥታዊ የኢንዱስትሪ ተቋም የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ሥር የሚገኘው የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ፣ የተርባይን ፋብሪካ ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ፡፡

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጀመሪያ ላይ ማለትም በ2008 ዓ.ም. የመጀመሪያ ወራት የተርባይንና የጄኔሬተሮች ማምረቻ ፋብሪካ ለመገንባት በዝግጅት ላይ መሆኑን፣ የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጂነሪንግ የኢንዱስትሪ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሻለቃ አሰፋ ዮሐንስ ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢንዱስትሪው ለኃይድሮ ፓወር ማመንጫነት የሚያገለግሉ ተርባይኖችና ጄኔሬተሮች ዲዛይን የማድረግ አቅም መፍጠሩን የገለጹት ሻለቃ አሰፋ፣ በቀጣዩ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን መርሐ ግብር መጀመሪያ ላይ የተፈጠረውን አቅም ወደ ማምረት፣ መትከልና ሥራ ማስጀመር ይቀየራል ብለዋል፡፡

ፋብሪካውን ለማቋቋም ምን ያህል ወጪ ያስፈልጋል የሚለውና ሌሎች የአዋጭነት ጥናቶች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን በ2002 ዓ.ም. በአሥር ቢሊዮን ብር ካፒታል ሲመሠረት፣ የ200 ሺሕ ብር መንቀሳቀሻ ካፒታል ተፈቅዶለት በኮርፖሬሽኑ ሥር የተደራጀው የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ በአሁኑ ወቅት ከ1.3 ቢሊዮን ብር በላይ ካፒታል እንደሚያንቀሳቅስና በሥሩም ሰባት ፋብሪካዎች መቋቋማቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

በቅርቡ በ350 ሚሊዮን ብር ካፒታል ከአዲስ አበባ በ20 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ታጠቅ የኢንዱስትሪ ዞን ያስገነባውን የትራንስፎርመር ፋብሪካ ግንቦት 9 ቀን 2007 ዓ.ም. አስመርቋል፡፡

የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ይህንን ፋብሪካ ከመገንባቱ ቀደም ብሎ የተለያዩ ትራንስፎርመሮችን ምርትና ዕድሳት በማድረግ፣ ለኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ያቀርብ የነበረ መሆኑ ይታወሳል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ መጠን ያላቸው ትራንስፎርመሮችን ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ማቅረቡን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ነገር ግን ቀደም ሲል የሚያመርትበት ወርክሾፕና የአገሪቱ የትራንስፎርመር ፍላጎት መጨመር ራሱን የቻለ ፋብሪካ እንዲያቋቁም አስገድዶታል፡፡ በመሆኑም በቡራዩ ታጠቅ የኢንዱስትሪ መንደር በ28 ሔክታር ላይ ያረፈ ፋብሪካ በቻይናው ፖሊ ግሩፕ አማካሪነት ገንብቶ በይፋ አስመርቋል፡፡

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ አስተባባሪና የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል የአገሪቱ የትራንስፎርመር ፍላጎት በዚህ ፋብሪካ እንደሚሸፈን ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያውያን አይችሉትም›› የሚል አስተሳሰብ የነበራቸው ወዳጅ አገሮችን ያሳመኑ ፕሮጀክቶችን የኢትዮጵያ ብረታ ብረት ኮርፖሬሽን ማረጋገጡን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ፓወር ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ከትራንስፎርመር ማምረቻ ፋብሪካው በተጨማሪ በ300 ሚሊዮን ብር ካፒታል ያስገነባው የኬብልና ዋየር ማምረቻ፣ የፓወር ፋክተር ኮሬክተርና የኮምፓክት ሰብስቴሽን ማምረቻ፣ በ350 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተገነባ የኢንጂን ማምረቻ ፋብሪካ፣ በ300 ሚሊዮን ብር ካፒታል የተገነባ የሶላር ፓናል ማምረቻ ፋብሪካ፣ በ200 ሺሕ ብር የተገነባ የሞተርና ጄኔሬተር ፋብሪካ በሥሩ ይገኛሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች