በአሰላ አረንጓዴው ስታዲየም ከግንቦት 5 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ አራት ቀን የተከናወነው የኢትዮጵያ ታዳጊ ወጣቶች ሻምፒዮና ‹‹አሳፋሪ›› የሆነ የዕድሜ ማጭበርበር የታየበት መሆኑ ተገለጸ፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በተጨባጭ ማስረጃ የደረሰባቸው ከ73 በላይ አትሌቶች ከሻምፒዮናው እንዲሰረዙ መደረጉም ተነግሯል፡፡
በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ስለሽ ብስራት፣ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ በተከናወነው የታዳጊ ወጣቶች ሻምፒዮና ላይ፣ ከኢትዮጵያ ሱማሌ ክልል በስተቀር ስምንቱ ክልሎች፣ ሁለቱ የከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች እንዲሁም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ለመጀመርያ ጊዜ ተሳታፊ እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ በሌላ በኩል ሻምፒዮናው የታዳጊ ወጣቶች ሻምፒዮና እንደሆነ ቢታመንም በተጨባጭና በተግባር መሬት የታየው ግን ክለቦችና ክልሎች ይዘዋቸው የቀረቡት ተወዳዳሪዎች በአብዛኛው ዕድሜያቸው ያለፈ በመሆኑ ሻምፒዮናው በወጪ ደረጃ ካልሆነ ከዓላማው አኳያ ትርጉም እንደማይሰጥ የዩኒቨርሲቲ ተወካዮች ትዝብታቸውን ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ የፌዴሬሽኑ ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያም በቀረበው አስተያየትና ትችት እንደሚስማሙ ገልጸው፣ ለሻምፒዮናው ተገቢ ያልሆኑ ተወዳዳሪዎች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ጎልቶ መታየቱን አምነዋል፡፡
ውድድሩ ከ15 እስከ 17 የዕድሜ ክልል የሚገኙ ታዳጊ ወጣቶች የሚሳተፉበት መሆኑ ከታወቀና ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም የዕድሜ ችግር መኖሩን ካረጋገጠ ዕርምጃ ለምን አልተወሰደም በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ስለሽ፣ ‹‹ተቋሙ ባለው መረጃ መሠረት ለምሳሌ በአንደኛውና በሁለተኛው የኢትዮጵያ ታዳጊ ወጣቶች ሻምፒዮና ላይ ተሳትፈው በወቅቱም ዕድሜና ውጤታቸው በትክክል ተመዝግቦ የተገኙ ከ73 በላይ ተወዳዳሪዎች በውድድሩ እንዳይሳተፉ አግዷል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የታዳጊ ወጣቶች ሻምፒዮና የሚዘጋጀው ሜዳሊያና መሰል ጥቅማ ጥቅሞችን ለመሰብሰብ ሳይሆን፣ የነገዎቹን ተረካቢ ታዳጊዎች ለማግኘት መሆኑ ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በበለጠ የሚያውቁት የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ለወደፊቱም ቢሆን ይኼው ችግር ሊፈታ የሚችለው ሁሉም ባለድርሻ አካላት አምና አሰላ ከተማ ላይ በተደረገው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን 18ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ በተላለፈው ውሳኔ መሠረት የአዋቂ፣ የወጣትና የታዳጊ ቡድኖችን እንዴትና በምን አግባብ ማዘጋጀት እንደሚገባ ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ስምምነቱን መነሻ በማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት መሥራትና መዘጋጀት ካልቻሉ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ብቻውን የሚያደርገው ቁጥጥርና ክትትል መፍትሔ ሊሆን አይችልም፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ለክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች በተለይ ከዕድሜ ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለማስወገድ በጋራ በመነጋገር የክለብ ማቋቋሚያና መመሥረቻ መመርያ ተዘጋጅቶ ለሁሉም ባለድርሻ የተላለፈ መሆኑን የሚናገሩት ባለሙያው፣ ለአትሌቲክሱ ስፖርት ትልቅ እንቅፋት እየሆነ የመጣው የዕድሜ ችግር እስከወዲያኛው ማስቀረት የሚቻለው ፌዴሬሽኑ፣ ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮችና ክለቦች በተቀመጠው መመርያ መሠረት የተወዳዳሪዎቻቸውን ዕድሜ የሚቆጣሩበት ትክክለኛ መረጃ ይዘው መንቀሳቀስ ሲችሉ መሆኑን ጭምር አስረድተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድኑ ዋና አሠልጣኝ ዶ/ር ይልማ በርታ ዘንድሮ ለሦስተኛ ጊዜ የተከናወነውን የታዳጊ ወጣቶች ሻምፒዮና ከፍተኛ የዕድሜ ማጭበርበር የታየበት መሆኑ እንደሚያሳስባቸው ይገልጻሉ፡፡ ዋና አሠልጣኙ ሻምፒዮናው በአጠቃላይ ከዓላማው አኳያ መሬት ላይ የታየው እጅግ በጣም አሳፋሪ እንደነበርም ጠቁመዋል፡፡ የውድድሩ ዓላማ ለታዳጊ ወጣቶች የውድድር ዕድል ማመቻቸት፣ ተተኪ ወጣቶችን በብቃትና በጥራት ማግኘት መሆኑ ግምት ውስጥ ሊገባ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
‹‹የታዳጊ ወጣቶች ሻምፒዮና ከአዋቂዎች በብዙ መልኩ ይለያል፡፡ ለምሳሌ የሜዳ ተግባራት ከሆነው አንዱ የአሎሎ ውርወራ ይጠቀሳል፡፡ ለዚህ ውድድር ለአዋቂዎች ስድስት ኪሎ ግራም ሲሆን፣ ለታዳጊዎች ደግሞ ሦስት ኪሎ ግራም ነው፡፡ አሁን ግን በዚህ በታዳጊዎች ሻምፒዮና የተመለከትነው የአዋቂዎችን ኪሎ ግራም መወርወር የሚገባቸው ታዳጊዎች ሦስት ኪሎ ግራም በመወርወር አሸናፊ ተደርገው የሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆኑ ነው፡፡ ይኼ ተተኪዎችን ከማፍራት አኳያ ሲታይ ምንም ትርጉም አይሰጥም፡፡ ውድድሩን ለመምራት ብሔራዊ ፌዴረሽኑ ከፍተኛ ወጪ አውጥቷል፡፡ እንደ ባለሙያ ደግሞ እኔና እኔን መሰል ሙያተኞች በየዓመቱ ተመሳሳይና የማይሻሻል ሻምፒዮና ለመምራት እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ እውነቱን ለመናገር ይኼ ለሞራልም ደስ አይልም፡፡ መሥራት ካለብን ትክክለኛውንና የአትሌቲክሱን ዕድገት ሊያስቀጥል የሚችል ቢሆን ነው የሚበጀው፤›› በማለት ዶ/ር ይልማ ሜዳሊያን ታሳቢ ያደረገ የይስሙላው ሻምፒዮና መፍትሔ ሊበጅለት እንደሚገባ ጠይቀዋል፡፡
የታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዋናነት በሐምሌ ወር በኮሎምቢያ በሚካሄደው የዓለም ታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና አገሪቱን የሚወክሉ ወጣቶችን ለመመልመል መሆኑ ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡ ፌዴሬሽኑ ለአሰላው ታዳጊ ወጣቶች ሻምፒዮና 779,000 ብር ወጪ ማድረጉም ተገልጿል፡፡