ሰኞ ግንቦት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. በስዊዘርላንድ ጄኔቫ በተካሄደው 68ኛው የዓለም የጤና ጉባዔ ከፍተኛ ችግር የሚያስከትሉና በዓለም አቀፍ ደረጃ የጤና ሥጋት ሊሆኑ የሚችሉ እንደ ኢቦላ ያሉ ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ዓለም አቀፍ ስትራቴጂ እንደሚያስፈልግ የዓለም የጤና ድርጅት መግለጫ አስታውቋል፡፡
ጉባዔውን በንግግር የከፈቱት የጀርመኗ መራሔተ መንግሥት አንጄላ ሜርከል እንደገለጹት፣ በምዕራብ አፍሪካ ተቀስቅሶ የነበረው የኢቦላ ወረርሽኝ በዓለም አቀፍ ደረጃ አዲስ ስትራቴጂ ማስፈለጉን ይህም በአፋጣኝ መሆን ያለበት እንደሆነ ያሳየ ነው፡፡
‹‹ሁኔታው በዓለም አቀፍ ደረጃ ጤናማነትን ማረጋገጥ የሚያስችል የተቀናጀና ጠንካራ ሥርዓት በአፋጣኝ መዘርጋት ወሳኝ እንደሆነ የታየበት ነው፤›› ብለዋል፡፡
በጀርመን የመሪነት ዘመን ቡድን ሰባት (G7) አገሮች፣ የመድኃኒት መላመድና ትሮፒካል በሽታዎች ላይ በትኩረት እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ዶክተር ማርጋሬት ቻንም የዚህ ወጥ የሆነ ዓለም አቀፍ የአፋጣኝ የጤና ቀውስ ምላሽ ሥርዓት ዝርጋታ እንዴት ዕውን እንደሚሆን ማብራራታቸው በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ ‹‹ዓለም ከእኛ እንደሚጠብቅ አድምጫለሁ፣ እኛም ይህን ዕውን እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡
ይህ አዲስ ፕሮግራም ተጠሪነቱ ለዳይሬክተር ጄኔራሉ የሚሆን ሲሆን የራሱ የሥራ አፈጻጸምና አሠራር እንደሚኖረውም ተመልክቷል፡፡