Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምምርጫና ፍጥጫ በብሩንዲ

ምርጫና ፍጥጫ በብሩንዲ

ቀን:

ለ12 ዓመታት ያህል ከዘለቀው የእርስ በርስ ጦርነት እፎይ ብላ ያለፈውን አሥር ዓመት በተነፃፃሪ ሰላም ያሳለፈችው ብሩንዲ፣ ዳግም ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊያስገባት ይችላል ወደተባለው አለመረጋጋት ከገባች ቀናት ተቆጥረዋል፡፡ ዋና ከተማዋን ቡጁምቡራን ጨምሮ የተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች በብጥብጥ እየታመሱ ነው፡፡ በቡጅምቡራ አብዛኞቹ የንግድ እንቅስቃሴዎች ተቋርጠዋል፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች ከሥራ ይልቅ ተቃውሞን መርጠዋል፡፡ ‹‹ፕሬዚዳንታችን በሕገ መንግሥቱ የተሰጣቸው የሥልጣን ጊዜ አልቋል፡፡ ዳግም ለምርጫ መምጣት የለባቸውም፤›› ሲሉም የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ለሦስተኛ ጊዜ መወዳደር እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡

ዳግም የእርስ በርስ ጦርነት ሰለባ ላለመሆን የመረጡ ዜጐች ወደ ጐረቤት አገሮች እየተሰደዱ ሲሆን፣ በአገራቸው ተቃውሞውን ለመቀጠል የወሰኑ የፕሬዚዳንቱ ተቃዋሚዎች ደግሞ ጐዳና ወጥተዋል፡፡ የብሩንዲ ዜጐች ለተቃውሞ ወደ ጐዳና የወጡትና ከወታደሮች ጋር የተጋጩት፣ ሕገ መንግሥቱ መከበር አለበት ብለው ከመንግሥት ጋር የተፋጠጡት፣ በሚቀጥለው ወር በሚካሄደው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ምክንያት ነው፡፡

የብሩንዲ ፕሬዚዳንት ፒዩር ንኩሩንዚዛ በአገሪቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ሜጀር ጄነራል ጎድፍሮይድ ኒዮምባሬ የከሸፈ መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ባለፈው ሳምንት ሲካሄድባቸው፣ ታንዛኒያ ነበሩ፡፡ የወታደሩ መከፋፈል የታደጋቸው ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ፣ ከታንዛኒያ መልስ መግለጫ ቢሰጡም ስለመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ያወሱት ነገር የለም፡፡ ሆኖም ሦስት ሚኒስትሮቻቸውን ከሥልጣን አንስተዋል፡፡ ለብጥብጡና ለመፈንቅለ መንግሥቱ መነሻ በሆነው የአገሪቱ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫም እንደሚሳተፉ ዳግም አሳውቀዋል፡፡

በብሩንዲ ሕገ መንግሥት መሠረት ለአምስት ዓመት በሚዘልቀው ፕሬዚዳንታዊ ሥልጣን፣ አንድ ፕሬዚዳንት ከሁለት ተከታታይ ጊዜ በላይ መመረጥ አይችልም፡፡ ሆኖም እ.ኤ.አ. ከ2005 ጀምሮ አገሪቱን ሲመሩ የቆዩት ፕሬዚዳንቱ፣ በሚቀጥለው ወር በሚካሄደው ምርጫ ለሦስተኛ ጊዜ እንደሚወዳደሩ ማሳወቃቸው፣ የብጥብጡና የመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ መንስዔ ነው፡፡ የፕሬዚዳንቱ ተቃዋሚዎች የፕሬዚዳንቱ አካሄድ ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ሲሉ፣ ፕሬዚዳንቱ ደግሞ አንድ ጊዜ በፓርላማው፣ አንድ ጊዜ በሕዝብ መመረጣቸውን በማውሳት ሁለት ጊዜ የመመረጥ መብት እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡

ፕሬዚዳንቱ በድንበር አካባቢ ባሉ የሰላም ማስከበር ሥራዎች ላይ ለመምከር ታንዛኒያ በነበሩበት ባለፈው ሳምንት ረቡዕ፣ በሜጀር ጄኔራል ኒዮምባሬ የተሰጠውና በሁለት ሬዲዮ ጣቢያዎች የተላለፈው መግለጫ የአገሪቱ ዜጐች ጐዳና እንዲወጡ፣ ከፖሊስ ጋር እንዲጋጩና 22 ያህሉ እንዲሞቱ ምክንያት ሆኗል፡፡

‹‹ፕሬዚዳንት ፒዬር ንኩሩንዚዛ ከሥልጣን ተወግደዋል፡፡ መንግሥት ፈርሷል፡፡ የአገራችን ዜጎች የሰዎች ሕይወትና ንብረት እንዳይጠፋ ጠብቁ፤›› የሚለው የሜጀር ጄኔራሉ መልዕክት አቅጣጫውን ስቶ በአገሪቱ ቀውስ ፈጥሯል፡፡

ከመፈንቅለ መንግሥቱ ሙከራ ሁለት ሳምንታት በፊት ጀምሮ በፕሬዚዳንቱ ዳግም ለፕሬዚዳንትነት የመወዳደር ውሳኔ ቁጣውን አፍኖ የነበረውን ሕዝብ ጐዳና እንዲወጣ አድርጓል፡፡ ምንም እንኳን መፈንቅለ መንግሥቱ ባይሳካም፣ በሕዝቡና በወታደሮች መካከል ግጭት ተፈጥሯል፡፡ ብሩንዲ ዳግም ሰላሟን አጥታለች፡፡ ዜጐቿ ከወታደሮች ጋር መጋፈጣቸውን አላቆሙም፡፡ ከቡጁምቡራ ውጪ ባሉ ከተሞችም ተቃውሞው ተስፋፍቷል፡፡ ተቃውሞ አድራጊዎች እየታሰሩና እየሞቱ ነው፡፡ ጋዜጠኞችም ለእስር ተዳርገዋል፡፡ በብሩንዲ ቡጁምቡራን ጨምሮ በተለያዩ ከተሞች የተቃውሞ ሠልፍ እየተደረገ ቢሆንም፣ ጋዜጠኞች የተቃውሞ ሠልፉን ለመቅረፅ መከልከላቸውን አልጄዚራ ዘግቧል፡፡

በድህነቷ ከዓለም ከመጀመሪያዎቹ አገሮች በሁለተኛነት ደረጃ የምትገኘው ብሩንዲ፣ የሚያንኮታኩታትና ዳግም ወደ እርስ በርስ ጦርነት የሚያስገባት ደረጃ ላይ ደርሳለች፡፡

ከዓመታት በፊት የሁቱና የቱትሲ ዝርያ አባላት የሆኑትና 10.4 ሚሊዮን የሚገመቱት ዜጐቿ በጐሳ በመከፋፈል ለ12 ዓመታት ባደረጉት የእርስ በርስ ጦርነት 300 ሺሕ ዜጐች መሞታቸው ይታወሳል፡፡ በጐረቤት ሩዋንዳ ለአንድ ሚሊዮን ዜጐች ሕልፈት ምክንያት የሆነው የሁቱና የቱትሲ ጅምላ ጭፍጨፋ በብሩንዲ እንዳይከሰትም ሥጋት አለ፡፡ የአገሪቱ ወታደሮች ያልተሳካውን መፈንቅለ መንግሥት በሚደግፉና በማይደግፉ የፕሬዚዳንቱ ታማኞች ተከፋፍለዋል፡፡ በሌላ በኩል የመከላከያ፣ የውጭ ጉዳይና የንግድ ሚኒስትሮች ከመፈንቅለ መንግሥት ሙከራው በኋላ ከሥልጣን መወገዳቸው ተጨማሪ ውጥረት ፈጥሯል፡፡

ቢቢሲ እንደ ዘገበው፣ በተለይ መከላከያ ሚኒስትር ከመሆናቸው በፊት ወታደር የነበሩት ተሰናባቹ የመከላከያ ሚኒስትር ፖንቴን ጋሲዩቡዋንጅ በርካታ ተከታዮች አሏቸው፡፡ በመሆኑም የእሳቸው ከሥልጣን መሰናበት ሌላ ቀውስ ሊያስነሳ ይችላል ተብሎ ተሰግቷል፡፡

የተቃውሞ ሠልፍ አድራጊዎች፣ ‹‹ፕሬዚዳንቱ ለሦስተኛ ዙር እንደማይወዳደሩ ካላሳወቁ የተቃውሞ ሠልፉን እንቀጥላለን፤›› ማለታቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ‹‹መፈንቅለ መንግሥት አንፈልግም፡፡ ፕሬዚዳንቱ ለሦስተኛ ዙር እንዲወዳደሩም አንፈልግም፤›› የሚሉ ባነሮች ይዘው ወጥተዋል፡፡

በብሩንዲ ያለው ሁኔታ እንደ ሩዋንዳው የእርስ በርስ ግጭት እንዳያስነሳ ፍርኃት አለ፡፡ በተያዘው ሳምንት መጀመርያ ላይ መግለጫ የሰጡት የኬንያው ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ የምርጫውን ጊዜ ማራዘም እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ ማክሰኞ ዕለት በአንጐላ በተካሄደ ጉባዔ ላይ ቡሩንዲ በሚቀጥለው ወር የሚካሄደው ምርጫ መራዘም እንዳለበት ተናግረዋል፡፡

ኬንያታ እንዳሉት፣ በብሩንዲ በፕሬዚዳንቱና በተቃዋሚዎች መካከል በአፋጣኝ ውይይት መጀመር አለበት፡፡ ልዩነቶችን በውይይት መፍታት ካልተቻለ የምርጫው ሒደት ሰላምን ሳይሆን ግጭትን ያባብሳል፡፡ ይህም ለብሩንዲ ብቻ ሳይሆን ለምሥራቅ አፍሪካ አገሮች በሙሉ ሥጋት ነው፡፡

ከሳምንታት በፊት በብሩንዲ በተቀሰቀሰው ግጭት ሳቢያ ከአንድ መቶ ሺሕ በላይ ዜጐች ወደ ሩዋንዳና ሌሎች አጐራባች አገሮች መሰደዳቸውን፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ኤጀንሲ አስታውቋል፡፡

ፕሬዚዳንት ንኩሩንዚዛ በሰጡት መግለጫ፣ ስለመፈንቅለ መንግሥት ሙከራውም ሆነ ብጥብጡ ያነሱት ነገር የለም፡፡ ሆኖም አልሸባብ በብሩንዲ ላይ ሥጋት እየፈጠረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የብሩንዲ ወታደሮች በሶማሊያ ካለው የአፍሪካ ኅብረት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች ጐን መቆሙን በማስመልከት፣ አልሸባብ በአገራቸው ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑን ቢናገሩም፣ የአልሻባብ ቃል አቀባይ ሼክ አሊ መሐሙድ ‹‹ፕሬዚዳንቱ የዓለምን ትኩረት ለመሳብ ሆን ብለው የሰነዘሩት ውንጀላ ነው፤›› ሲሉ አጣጥለውታል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የምርጫውን ነገር ተወት አድርገውት አገሪቱን በማረጋጋት፣ ሰላም እንዲሰፍን የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ እየተወተወቱ ነው፡፡

           

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...