Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

“ማወቁንስ እናውቃለን…”

እነሆ መንገድ! ከሽሮ ሜዳ ወደ አራት ኪሎ ልንጓዝ ነው። ነቀፋ አንሶላው፣ ትችት ብርድ ልብሱ በሆነው ጎዳና ላይ እንራመዳለን። “እኔ ምለው ባቡሩ ተመረቀ አልተባለም እንዴ? ምነው ሥራ ጀምሮ ይኼንን ሠልፍ ተግ ቢያደርገው?” ትላለች መደበቂያ እንዳጣች ድንቢጥ ተወትፋ የቆመች ታክሲ ናፋቂ እንስት። “አንቺ ደግሞ! እኔ ይኼው ተመርቄ ሥራ መቼ ጀመርኩ፤” ወዳጁዋ በጥያቄዋ ያለቅጥ በግኗል። ልጅት ስሜቱን አጢና ልታለዝበው፣ “አይዞህ ትንሽ ቀን ነው። አንድ ‘ቪትዝ’ መግዛታችን መቼም አይቀርም፤” አለችው። ልጁ ሳቀ። “አንድ ሚኪያቶ ለሁለት መጠጣት ሳናቆም ጭራሽ ቪትዝ? ቆይ እንዴት ነው የምታስቢው?” ሳቁ አልበረደም። “ቪትስ እኮ ነዳጅ አትበላም ሲሉ ስለሰማሁ ነው፤” ግራ ገባት። “በቃ! በቃ! ደህና በቀናነትሽ የበላሽውን አንጀቴን እንዳትቆርጪው ዝም ብትይ ጥሩ ነው፤”  ቱግ አለ ልጁ። የባሰው ብሶት? በሁለት ነፍስ መሠረታዊ ፍላጎት የተወጠረው ወጣት ፊቱን ዘፈዘፈው።

ከእነሱ ቀጥለው በጉያቸው ክንድ የሚረዝም ነገር በፌስታል ጠቅልለው ካቀፉ ሠልፈኞች አንደኛው፣ “ተመልከታቸው እስኪ። እሷ አንድ ፍሬ፣ እሱ የአርበኞቻችን እኩያ። ምነው ሰው ግን ብጤውን አልመርጥ አለ?” ሲል የወዲያኛው፣ “የራሷ ሲያርባት የሰው ታማስላለች’ በሴት ተተረተ እንጂ አማሳዩስ አንተ ነበርክ። ይልቅ ዞር ዞር እያልክ ራስህ ቢጤህን ብትፈልግ ይሻልሃል። ከተሳፈሩ ወዲያ ተመልሰው የማይመጡ ምርጫዎችህን አትቁጠርና የሰው ተመልከት። ለምሳሌ እይ እዚያ ጋ ቁመናና እርጋታ አይታይህም?” ብሎ ወዳጁ ጨዋታውን በመልሶ ማጥቃት ይቀለብስበታል። አንዳንዶች በተጣማሪዎች ጥምረት ከንፈር ሲመጡ፣ ተጣማሪዎች ከጥምረታቸው አልፈው ስለነጋቸው ውሎ በሐሳብ ሲዋዥቁ ለሚታዘብ ፍላጎት ገደብ እስከሌለው ድረስ፣ በምርጫና በአማራጭ ግንባር መዝመት ሰው የመባል ግዳጅ መሆኑን ያምናል። እናም ዘምተናል!

ተራችን እንደተጠበቀ ተረኛ ታክሲ ውስጥ እንሳፈራለን። “ቀስ በሉ እንጂ ምንድነው የምትወዘውዟት? አልገለበጥ አለቻችሁ?” መልኩ እንደ ቁራ የጠቆረ፣ ቁመቱ እንደ አጠና የተመዘዘው ወያላ ያንባርቅብናል። “ሰላማዊና የተረጋጋ አገባብ የምትገቡ ከሆነ ግቡ። አለበለዚያ ግን …” ሳይጨርሰው ሳንቲም ሊዘረዝር ጥሎን ሮጠ። “ምንድነው የሚቀባጥረው? ምናችንን መዝኖ ነው ደግሞ ታክሲውን ያወዛወዝነው?” የሱሪ አስተጣጠቁ ግራ የሚያጋባ ልጅ እግር ግራ ‘ገባኝ ብሎ’ ከሾፌሩ ጀርባ እየተመቻቸ ይጠይቃል። “ዝም በለው እባክህ። ሲሉ ሰምቶ ተናግሮ ሊያናግረን ፈልጎ ነው፤” ትላለች አጠገቡ የምትንሸራሸር ቀልጠፍጠፍ ያለች ወጣት። “እነዚህ ወያሎች ዘንድሮ ባቡር ባቡር አላችሁ ብለው ዓይናቸው ቀልቷል። በምርጫችንና በፍላጎታችን ምን አገባቸው?” መሀል መቀመጫ የአለባበስ ፕሮቶኮሏ ፍፁም የተጠበቀ ወይዘሮ ሐሳብ ይዟት ስትጠይቀኝ፣ “እንጃ! ከተራ አስከባሪዎቹ ጎን ለጎን የምርጫ አስከባሪ ኮሚቴ ካላቋቋምን የምንችላቸው አልመሰለኝም። በዚያውም ለሥራ አጥ ዜጎቻችን አንድ የሥራ ዕድል እንፈጥራለን። አይመስላችሁም? እንዲህ እርስ በርስ እንረዳዳ እንጂ የሚረዳን ያለ አይመስልም፤” ይላል ከጀርባችን አናቱ የታክሲዋን ኮርኒስ የሚታከክ ጎልማሳ።

ወዲያው ወያላችን ተመልሶ መጣና በሩን ዘጋ። መለስ ብሎ እያንዳንዱን ተሳፋሪ በዓይኑ አበጠረ። “ኧረ ዛሬስ የጤና ያድርግልን። ይኼ ወያላ ምን ሊለን ነው እናንተ?” ትላለች አሁንም ከፍቅረኛዋ ጉያ ተሸሽጋ የምትተሻሸው ወጣት ከወደ መጨረሻ ወንበር። “እሺ የቦታ ሽግሽግ ማድረግ ይኖርብኛል። እስኪ አንተ በዚያ በኩል ተቀመጥና እሳቸውን በዚህ አድርጋቸው…” አለ ወደ እኔ እየጠቆመ። “እኮ ለምን?” ወደ እኔ መቀመጫ እንዲዛወሩ ከወያላው ቀጭን ትዕዛዝ የተላለፈባቸው ወይዘሮ ጮሁ። “በዚያ በኩል ከኋላ የገጠምነው ተቀያሪውን ጎማ ስለሆነ ክብደት ያለችሁ ተሳፋሪዎች የጋቢናውን መስመር ያዙ። በኋላ በእናንተ ምክንያት ጎማዬ ሲፈነዳ የእኔ ስብ የሚቀልጥበት ምክንያት አይኖርም፤” ወያላው አመረረ። እንደ ሰንጋ ከበድ ከበድ ያሉት ከግራ ወደ ቀኝ አቅጣጫ እስኪዘዋወሩ ደቂቃዎች ነጎዱ። “ስንሞግግ መከራ ስንሰባ መከራ!” አንዱ ተሳፋሪ ይነጫነጫል። የንጭንጭ ዘመን!

ጉዟችን መጀመር ከነበረበት ዘግየት ብሎ ተጀምሯል። ሾፌራችን ሳይንቀዠቀዥ ተረጋግቶ ያሽከረክራል። አጠገቡ ያሉት ወጣቶች ስለመጪው የእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ዓመት መተንበይ ይዘው ከጣራ በላይ ይጮሃሉ። መለስ ብለው ደግሞ፣ “ስቲቨን ዤራርድ ሊቨርፑልን አሁን መልቀቅ ነበረበት? እ? ንገረኝ እስኪ ነበረበት?” እርስ በርስ ይፋጠጣሉ። መጨረሻ ወንበር ጥጋቸውን ይዘው የተቀመጡ አዛውንት፣ “ወይ ጉድ። እሱ በቃኝ ብሎ አስቦ አውጥቶ አውርዶ ክለቡን ለቋል። እነዚህ ደግሞ ምን አገባቸው በእሱ ምርጫ?” ይላሉ። ጎልማሳው ትከሻውን በምንቸገረኝ እየሰበቀ፣ “አዞብን! በሰው ምርጫ፣ በሰው እንጀራ፣ በሰው መንገድ፣ በሰው ላብ እንደ እርጎ ዝንብ ጥልቅ ስትሉ ኑሩ ብሎ አዞብን እንጂ ሌላ ምክንያት የለን። በምናልፍ በምናገድምበት ምን ይሉኝን የምንፈራውን ያህል ተራችንን ምን እንበላቸው ስንል ትንሽ ቁንጥጥ የሚያደርገን ስሜት የሌለንም ለዚህ ነው። ዙሪያችን ያሉ ሰዎች በማያገባቸውና በማይገባቸው ሲገቡ እንደ ማስቆም ራሳችን በመረጥነው ባሰመርነው መስመር እንድንጓዝ፣ እነሱም እንዲያ እንዲጓዙ አልናገር እያልን ነገራችን ይመሰቃቀልና ተራችንን እኛም በማያገባንና በማይገባን እንደሚያዩን ዘው ስንል እንኖራለን። ለምን? አዞብን!” ይላል ጎልማሳው።

ጋቢና የተቀመጡት ወጣቶች ግን በስሜት ጦፈው ሲነጋገሩ ድምፃቸውን እንኳ አይቆጣጠሩም። “ቱ! በሚቀጥለው ‘ሲዝን’ ደጋፊው አርሴን ቬንገርን ካላባረረ እውነት እንግሊዝ ጀግና አልወለደችም!” ሲባባሉ ብንሰማ አላስችል ስላለን ቀስ እያለ የሚቀጥል የሳቅ ትንታ ጀመረን። “አንዳንዴ እኮ ‘ያልበላንን ማከክ’፣ አለፍ ሲልም ‘መጥነን መደቆስ አቅቶን ማልቀስ’፣ ባስ ሲልም ‘የራሳችን እያረረ የሰው ማማሰል’፣ ሲከፋ ‘በሰው ቁስል እንጨት መስደድ’…” እያለ አንዱ ሲመረር ይሰማል፡፡ “ነገራችን ሁሉ ወዲያና ወዲህ እየሆነ ለስኬት ካልበጀን ብናወራው ሆድ ይቆርጣል…” የሚል ድምፅም ይሰማል፡፡ እግዚኦ!

ቀጥለናል። ወያላው ሒሳቡን ቶሎ ሰብስቦ ፊቱን ወደኛ አዞረና ሞተሩ ላይ ተቀመጠ። ቀነጣጥቦ ኪሱ ያቆያትን ዳማከሴውን እየጎረሰ ከተለጣጠፉት ጥቅሶች ወዳንዱ ጠቆመን። “የወያላውን ምርቃና መስበር ምርጫ ቦርድን ከማብጠልጠል ተለይቶ አይቆጠርም፤” ይላል። አንብበን መጨረሳችንን እንደገመተ፣ “አይ ካላችሁ . . .  መልስ ሳይመለስላችሁ መሀል መንገድ ላይ ዱብ ለማለት ተዘጋጁ፤” ብሎ ጆሮውን በ‘ኤርፎን’ ጠረቀመ። “እንዴት ያለ ወንበዴ ወያላ ጣለብን ደግሞ ዛሬ?” አዛውንቱ አጉተመተሙ። “አይዞዎት! ላይሰማ ስለማለ ጮክ ብለው ያውሩ። የዘንድሮ ፖለቲከኞች ዕድሜ ለቴክኖሎጂ ሰምቶ እንዳልሰማ ከመሆን ጭራሹኑ የሚባሉትን የማያዳምጡበት ጊዜ ላይ ናቸው፤” ወይዘሮዋ ነፍራለች። “እሱስ የባሰው በጭፍራው ነው።

ይኼ ዕውቀት አመጣሽ ሳይንሳዊ ቁሳቁስ ዓይንና ጆሮ ሊሆነን ሲገባ ሊያሰክነን፣ ሊያረጋጋን፣ ከመናገራችን በፊት ሁለቴ ሦስቴ እንድናስብ ሊያደርገን ሲገባ ቸኩሎ እያቻኮለ ጉድ የሰራውማ ጭፍራውን ነው፤” አሉ አዛውንቱ። “ምን ይደረግ ማስተዋል በ‘ብሉቱዝ’ የሚላክ ቢሆን እናንተ እናንተ ትረጥቡን ነበር። እህ ‘ብሉቱዙ’ የሚሠራው ለበርበሬና ለሚጥሚጣ ማስተላለፊያ ብቻ ሆነ። ሰው ለዕውቀት የሚበጀውን መርምሮ እንዳይመርጥ ኑሮ ‘ብሮድባንድ’ ሆኖ ቀልብ ነሳን፤” አላቸው ፈቅረኛውን እያሻሸ በሙቀት የታፈነው ወጣት። ይኼኔ አዛውንቱ፣ “እስኪ ለማንኛውም ብዙ አትጠጋጉ። ደግሞ ይኼ ወያላ ‘ከወያላው በቀር ታክሲ ውስጥ መተቃቀፍ ክልክል ነው’ የሚል አዋጅ እንዳይለጥፍ፤” ብለው በዘዴ ምቾት የነሳቸውን የወጣቶቹን ሙቀት አሳስቀው ያቀዘቅዙታል። እንዲህ እንደ አዛውንቱ አሳስቆ የልቡን በሚያደርስ ወያላ ታክሲ እስክንሳፈር፣ በዚህኛው ወያላችን ደረቅ አስተዳደር ልባችን ይቆስላል። ዳሩ መንገድ ነውና ችለነዋል።

ወደ መዳረሻች ልንቃረብ ነው። መጨረሻ ረድፍ ከአዛውንቱ በስተግራ የተቀመጠች ወጣት ስልክ ይዛለች። “ቅዳሜ ልደቴ  መሆኑን አውቀሻል?!  . . .  በቃ ተዘጋጂ። በሕይወትሽ ዘመን እንደ መጪው ቅዳሜ ስለማትጠጪ ራስሽን እየጠገንሽ ሰንብቺ፤” ትላለች። “አይ እነትዬ አልሰሜ። በመጪው ሰንበት ሕዝብ የድምፁን ልደት ሊያከብር እየተሰናዳ አንቺ ለአስረሽ ምቺው ቀጠሮ ትይዢያለሽ?” ጎልማሳው በለሆሳስ ሲናገር ካጠገቤ የተቀመጡት ወይዘሮ ዶሮ ካልጮኸ ቤቷ ስለማትገባው ልጃቸው በምሬት ያጫውቱኝ ይጀምራሉ። “በልቼ ልሙት አንድ ነገር ነው። ጠጠቼ ልሙት ጥጋብ ካልሆነ ምን የሚሉት ቋንቋ ነው አንተዬ? ‘አላበዛሽውም?’ ስላት፣ ‘ተይኝ ጠጥቼ ልሙት’ አትለኝ መሰለህ? ኧረ ዘንድሮስ ፈራሁ፤” ከአቅማቸው በላይ ቢሆን ለእኔ እንደሚያወሩት ገብቶኝ ራሴን ባዘኔታ እነቀንቃለሁ። አዛውንቱ በበኩላቸው የስልክ ወሬዋን ወዳበቃቺው ወጣት ዘወር ብለው፣ “ኋላ ፕሮግራምሽ እንዳይበላሽ እስኪ መጀመሪያ አጣሪ። የፊታችን ቅዳሜ ሰዓት እላፊ ሳይታወጅም አይቀርም፤” ሲሏት ከጎልማሳው አጠገብ የተቀመጠው ዝምታ የሚጫነው ወጣት “አለዚያማ ማን ተቀስቅሶ ሊሰማ፤” ይላል።

“እኮ ልደቴን እንዳሻኝ ላላከብር? ቤቴ ውዬ ቤቴ ላድር?” ስትል ወጣቷ፣ “ላንቺም ግልግል ነው በአምስት ዓመት አንዴ ቢዘልሽ ምንድነው?” ይላታል። “አንተ ደግሞ ምናለበት እነዚያን 364 ቀናት በአንዷ ተወዳጅ የልደት ቀኔ ባካክሳቸው? አንድ የልደቴን ቀን ‘እንኳን መጣሁ፣ ተፈጠርኩ’ ብል ነውር አለው?” ልጅት ከፍቷታል። “ተረጋጊ እንጂ የእኔ ልጅ። ለሁኔታዎች መመቻቸት ዜጎች የየዕለት ሠልፋቸውን ለመቀነስ የአምስት ዓመቱን ታላቅ ሠልፍ ሲሠለፉ እንዳይሳነፉና እንዳይደክሙ፣ የሚጠልፋቸውና የሚያዝላቸው እንዳይበዛ የአገር ጉዳይ ነውና መጪዋ ቅዳሜ ሰኞን ሁና ውላ ልታድር ትችላለች ከሚል ነው፤” አሉዋት፡፡ አክለውም፣ “ደግሞ ለአንቺም ድርብ ልደት ነው። ሕዝብሽ የሚመራውን መንግሥት በድምፅ በሚወስንበት ዋዜማ በመወለድሽ ደስ ይበልሽ። አራት ጊዜ 364 ቀናት ሲያነጫንጩሽ ከነበር እንዲያውም በአሁኑ ልደትሽን ማክበር የሚገባሽ መሸታ ቤት ሳይሆን ምርጫ ጣቢያ ነው፤” ሲሏት አዛውንቱ ከልባቸው ተሳፋሪዎች በሳቅ ፈነዱ። ምን እንዳሳቀን፣ ሳቃችን ለምን የነጎድጓድ ድምፅ እንደመሰለ የሚያውቅ ያውቀዋል። ‘ኩሉ መርምሩ ወ ዘ ሰናየ አፅኑ’ ያለው ማን ነበር? እያልኩ በሐሳብ ስናውዝ፣ አንድ ወፈፍ ያደረገው የሚመስል ተሳፋሪ ደግሞ፣ “እውነት እውነት እላችኋለሁ ‘ሁሉን መርምሩ የተሻለውን ያዙ’ እንዲሉ በአፈ ጮሌዎች እንዳትታለሉ…” አለ፡፡ ይኼኔ አዛውንቱ፣ “ማወቁንስ እናውቃለን…” ከማለታቸው ወያላው “መጨረሻ” ብሎን ወርደን በየፊናችን ተበታተንን። መልካም ጉዞ!  

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት