Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርከቅርቃር ውስጥ የወጣ ወይስ ቅርቃር ውስጥ የገባ?

ከቅርቃር ውስጥ የወጣ ወይስ ቅርቃር ውስጥ የገባ?

ቀን:

በሕዝብ እንባ ጠበቂ ተቋም

ይህ ጽሑፍ በሪፖርተር ጋዜጣ ‹‹እኔ ምለው›› በሚል ዓምድ ሥር እሑድ ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. ‹‹ቅርቃር ውስጥ የገባው መረጃ መብት›› በሚል ርዕስ በአቶ ዘለዓለም ጉተማ በተጻፈው መጣጥፍ ላይ ጥቂት ነጥቦችን ለማለት ተፈልጐ የቀረበ ነው፡፡

ጸሐፊው ሐሳባቸውን ያቀረቡት በሁለት ንዑሳን ርዕሶች ከፍለው ሲሆን፣ ‹‹የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የዝግጁነት ደረጃ›› በሚል ሐተታ ውስጥ የእንባ ጠባቂ ተቋም ያስገኘው ውጤት እዚህ ግባ የሚባል አይደለም በማለት የተቋሙን ውጤት አልባነት አጉልቶ ለማሳየት ዳድተዋል፡፡ እንዲህ ዓይነት ድምዳሜ ላይ ለመድረስና የሰላ ትችት ለማቅረብ የተቻለው ከምን መነሻ እንደሆነ ባይገባንም ሁለት ነገሮችን መገመት ይቻላል፡፡ አንደኛው ከግንዛቤ እጥረት ነው፡፡ ሌላኛው ጨለምተኝነት ነው፡፡ መረጃ የማግኘት መብት ቅርቃር ውስጥ ገባ የሚያስብል የጭንገፋ ወሬ ከዚህ የዘለለ ምክንያት ሊኖረው እንደማይችል ይገመታል፡፡

የግንዛቤ እጥረት ከሆነ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ክፍል ሦስት እንዲያስፈጽም ሥልጣንና ተግባር የተሰጠውን የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋምን በማግኘት ዝርዝር መረጃ መውሰድና ትክክለኛውን ነገር በመረዳት በተረዱት ልክና በመረጃ በተደገፈ ሐሳብ መተቸት ተገቢና ገንቢ ስለሚሆን የምንማማርበት ይሆናል፡፡ የጨለምተኝነት መንፈስ ከሆነ ግን የክፋት ስለሆነ የብርሃን አምላክ እንዲያበራላቸው ከመለመን ውጪ ሌላ ምን ይደረጋል?

ለመንደርደሪያ ያህል ይህን ካልን ለትክክለኛ ግንዛቤ ይረዳን ዘንድ ተቋሙ በመረጃ ነፃነት ዙሪያ ካከናወናቸው በርካታ ተግባራት መካከል ጥቂት ነጥቦችን ለማንሳት እንሞክራለን፡፡

አሁን ያለንበት ዘመነ ‹‹አይሲቲ›› መረጃ ሕይወት ነው፣ መረጃ ሀብት ነው፣ ወዘተ እየተባለ የሚታወቅበትና መረጃ በዓለም ዙሪያ ተፈላጊነቱና ጠቀሜታው እየጐላ የመጣበት ወቅት ነው፡፡ ቀደም ባሉት ዘመናትም ቢሆን ባደጉ አገሮች ዘንድ መረጃ የነበረው ሥፍራ ቀላል ግምት የሚሰጠው አልነበረም፡፡ የመረጃ ነፃነት ጉዳይ ዓለም አቀፋዊ ትኩረት የነበረውና አሁንም በተሻለ ሁኔታ ግንዛቤው እየሰፋ የመጣ አንገብጋቢና ወሳኝ አጀንዳ ነው፡፡ ይልቁንም ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን በሚከተሉ አገሮች!

በዚህ ዓይነት የመረጃ ነፃነት ሕግ በዜጐች መካከል የሚደረገውን ነፃ የሐሳብና የመረጃ ልውውጥ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን የአሠራር ነፃነት ላይ መሰናክል የሚፈጥሩ ተቋማዊና መዋቅራዊ ችግሮችን በማስወገድ፣ በነፃ ሐሳብን የመግለጽ ባህል ለማዳበር በእጅጉ እንደሚረዳ ይታመናል፡፡

አገራችን በርካታ ታዳጊ አገሮች ያልደፈሩትን የመረጃ ነፃነት ሕግ በማውጣት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ቆራጥ ዕርምጃ መውሰዷ እሰየው እንበርታ እንበራታ የሚያስብል እንጂ፣ ውጤት አልባ ተግባር ተደርጎ መወሰዱ ለወገንም የማይጠቅም በመሆኑ የተጀመሩትን በጐ አፈጻጸሞች በማጠናከርና በሒደቱ ላይ በጋራ በመንቀሳቀስ የተፈለገውን ውጤት ለመጨበጥ መትጋት ይጠበቅብናል፡፡

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 29 ያለማንም ጣልቃ ገብነት የመሰላቸውን አመለካከት የመያዝና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት እንዳላቸው በግልጽ ደንግጓል፡፡ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ከሚረጋገጥባቸው መንገዶች አንዱ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት የተለያዩ አመለካከቶችን ማስተናገድ ሲቻል በመሆኑ፣ በዚህ አንቀጽ ላይ እንደተመለከተው የመገናኛ ብዙኃን ነፃነትም ተረጋግጧል፡፡ በዚህ እውነታ ላይ ተንተርሶ የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነትን የሚደነግግ አዋጅ 590/2000 ወጥቶ ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩ የሚታወቅ ሲሆን፣ የአዋጁ ክፍል ሦስት ማለትም መረጃ የማግኘት መብትን በተመለከተ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ኃላፊነት ተሰጥቶት በኅዳር ወር 2004 ዓ.ም. በይፋ ሥራ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ አዋጁ ማንኛውም ሰው ከማንኛውም መንግሥታዊ አካል መረጃ የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብቱ የተጠበቀ እንደሆነና ተነፃፃሪ የሕዝብና የግለሰቦችን ጥቅም ለማስጠበቅ ሲባል ብቻ የተጣለ ጠባብ ክልከላ መኖሩን ይደነግጋል፡፡

የመረጃ ነፃነት ሕጉ ተግባራዊ መደረግ በአገራችን በመገንባት ላይ ያለውን የዴሞክራሲ ሥርዓት ከጊዜ ወደ ጊዜ ሥር እየሰደደና እየተጠናከረ እንዲሄድ ከማድረግ ባሻገር፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 ላይ ለተጠቀሰው ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ሕጋዊ ጥበቃ ለማድረግ የወጣ አዋጅ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የመረጃ ነፃነት የማስከበር ሥልጣንና ተግባሩን ለመወጣትና አዋጁን ወጥነት ባለው መልኩ በአገር አቀፍ ደረጃ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችሉ የሕግ ማዕቀፎችን፣ የሥልጠና ማኑዋሎችንና የተለያዩ መመርያዎችን በአገር አቀፍ ደረጃ በተዋቀረ ግብረ ኃይል አማካይነት በማዘጋጀት ነበር የመጀመሪያዎቹን ዓመታት ያሳለፈው፡፡

ከዚያ በኋላ ደግሞ ማንኛውም የመንግሥት አካል ሕጉ በሚያዘውና በሚፈቅደው መሠረት ለመረጃ ጠያቂ መረጃ የመስጠት ግዴታውን እንዲወጣ በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችና የሥልጠና መድረኮች የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራትን አከናውኗል፡፡ በተለይም የመገናኛ ብዙኃንና የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀጽ 31 እና 32 ላይ በዝርዝር ከተመለከተውና ለሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋሙ ከተሰጠው ሥልጣን ውስጥ፣ በመረጃ ነፃነት ላይ ይግባኝ እንዲያስተናግድና በተቀላጠፈ ሁኔታ የመረጃ ልውውጥ የሚካሄድበትን ሁኔታ እንዲያመቻች ማድረግ የሚለው ትኩረት ተሰጥቶታል፡፡ በዚህ መሠረት የመረጃ ነፃነት የቅሬታ ማስተናገጃ የአፈጻጸም መመርያ አዘጋጅቶ ተግባራዊ አድርጓል፡፡ ማንኛውም ሰው መረጃ ጠይቄ መስተናገድ ባለብኝ ጊዜ አልተስተናገድኩም፣ መረጃ በጠየቅኩት መጠንና ጥራት አልተሰጠኝም፣ ማግኘት የነበረብኝን መረጃ በሙሉ ወይም በከፊል ተከልክያለሁ ካለና ቅሬታውን ለመሥሪያ ቤቱ የበላይ ኃላፊ በማቅረብ ተገቢውን ምላሽ ካላገኘ፣ ወይም በምላሹ ካልረካ ለሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም ይግባኝ የማቅረብ መብት አለው፡፡ በዚህ መሠረት በርካታ ቁጥር ያላቸው የይግባኝ አቤቱታዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ቀርበው የተስተናገዱበትና እየተስተናገዱም ባሉበት ሁኔታ ተቋሙ ግዴታውን እንዳልተወጣ ተደርጐ መቅረቡ ተገቢ አለመሆኑን አንባቢያንና ጸሐፊው ግንዛቤ ይኖራቸው ዘንድ ጥቂት መረጃዎችን ለአብነት መጥቀሱ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

 • በመረጃ ነፃነት አዋጅ 36 ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት የእያንዳንዱ መንግሥታዊ አካል የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የዚህ አዋጅ ክፍል ሦስት ለማስፈጸም ያከናወናቸውን ተግባራት በዓመታዊ ሪፖርት ከግንቦት 30 በፊት ለሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም ማቅረብ እንዳለበት በሚደነግገው መሠረት፣ 6,171,793 የመረጃ ጥያቄዎች ከተለያዩ የፌዴራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ቀርበው ተስተናግደዋል፡፡
 • የተለያዩ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች የመረጃ ጥያቄዎች በአዋጁ መሠረት አልተስተናገደም ብለው ሲያምኑና ቅሬታ ሲኖራቸው ለተቋሙ የበላይ ኃላፊ የሚያቀርቡበት ሥርዓት ተዘርግቷል፡፡ ለዚህ አፈጻጸም ይረዳ ዘንድ ደግሞ ተገቢ የሆኑ መመርያዎችና ቅጻቅጾች ተዘጋጅተው ለእያንዳንዱ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እንዲደርሱ ተደርጓል፡፡ በተጨማሪም አዋጁን እንዲያስፈጽሙ ከፍተኛ ኃላፊነት የተሰጣቸው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በቂ ግንዛቤና ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ በዚህ መልኩ የተለያዩ መረጃ ጠያቂዎች ቅሬታቸውን በይግባኝ ለተቋሙ ሲያቀርቡና በአዋጁ ላይ በተቀመጠው ስታንዳርድ መሠረት በወቅቱ ምላሽ ሲያገኙ ቆይተዋል፡፡ ዋና እንባ ጠባቂ በሰጡት ምላሽ ቅሬታ ያለው አካል ጉዳዩን ለሚመለከተው ፍርድ ቤት በማቅረብ መፍትሔ ማግኘት እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ይህ የሚያሳየው የመረጃ ጥያቄ ሲቀርብ በእኛ በጐ ፈቃድ የምንሰጠው ሳይሆን፣ የዜጐች ሕገ መንግሥታዊ መብት በመሆኑና ለሕገ መንግሥትም መገዛት ግዴታ በመሆኑም ጭምር ነው፡፡
 • የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ለተቋሙ ዓመታዊ ሪፖርት እየላኩ እንዳልሆነ ተደርጐ በጸሐፊው የቀረበው ሐሳብ የተሳሳተና በመረጃ ያልተደገፈ መሆኑን ለአብነት ያህል ለማቅረብ እንወዳለን፡፡ አብዛኞቹ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች ሪፖርታቸውን እየላኩ መሆናቸውንና ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ቀጥሎ የተመለከተው ዳታ ያሳያል፡፡
  • በ2004 ዓ.ም. 68፣
  • በ2005 ዓ.ም. 68፣
  • በ2006 ዓ.ም. 71፣
  • በ2007 ዓ.ም. 78 የፌዴራል ተቋማት በመረጃ ነፃነት ሕጉ ያከናወኗቸውን ተግባራት በዝርዝር ልከዋል፡፡ ተቋሙም ይህንኑ አጠናቅሮ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዓመታዊ ሪፖርቱ አካል በማድረግ ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ ተቋሙ በአዋጁ መሠረት ሪፖርት ያላቀረቡ የፌዴራል መሥሪያ ቤቶችን በመለየት ለምክር ቤቱ የሚያቀርብ ሲሆን፣ ምክር ቤቱም የእያንዳንዱ የመንግሥት አካል አፈጻጸም በቋሚ ኮሚቴዎች አማካይነት ቁጥጥር ሲያደርግ የመረጃ ነፃነት አዋጅ ትግበራን እንደ አንድ የዕቅዱ አካል ወስዶ በመገምገም አፈጻጸሙን ይከታተላል፡፡

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነው ሌላው ጉዳይም ‹‹… በዚህ ሚናው ያከናወነው ተግባር ጐልቶ አልታየም ብቻ ሳይሆን የለም›› በሚል የቀረበው ጽሑፍ ከመረጃ እጥረት ከሆነ እነሆ ብለናል፡፡ ውንጀላ ከሆነ ለማንም አይጠቅምም፡፡     

 • በተጨማሪም ጸሐፊው የግል አስተያየቴ ነው በማለት ተቋሙ በመረጃ ነፃነት ሕግ መሠረት በአንቀጽ 13 ሥር የተደነገገውን ግዴታ እየተወጣ እንዳልሆነ አድርገው ላቀረቡት ደካማ ግምገማ፣ ቀጥሎ የተመለከተውን ተጨባጭ መረጃ መመልከቱ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ አትሞ ከመወጣት ግዴታን ከመወጣት አንፃር ከ2004 እስከ 2007 ዓ.ም. ድረስ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም የሰበሰበው ሪፖርት የሚያሳየው ከአንድ ሚሊዮን በላይ የተለያዩ የመረጃ ሕትመቶች የወጡ ሲሆን፣ በርካታ ኮፒዎች ታትመው የተሰራጩ መሆኑን መገንዘቡ ተገቢ ይሆናል፡፡ አፈጻጸሙም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣት ላይ ነው፡፡
 • በሌላ በኩል ደግሞ ከእያንዳንዱ የመንግሥት ተቋም የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊዎች የሪፖርት አሰባሰብ ሥርዓት ለማሳለጥና በአገር ደረጃ ወጥነት እንዲኖረው ለማድረግ ትልቅ ሚና እንደሚኖረው የሚታሰበው በመረጃ መረብ የሪፖርት አቀራረብ ሥርዓት (Online Reporting System) በውጭ አማካሪ ድርጅት እንዲሠራ ተደርጐ፣ በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ የንድፍ ሥራው የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ሞዴል ተቋማት ተመርጠው ወደ ትግበራ በመግባት ላይ እንደምንገኝ ማወቁ ጠቃሚ ይሆናል፡፡

በዚህ መልኩ እስካሁን ያለው እንቅስቃሴና ውጤቱ ጥሩ ጅምር ነው፣ በርቱ ተበራቱ የሚያስብል እንጂ ተስፋ አስቆራጭ አለመሆኑን መረዳቱ ተገቢ ነው፡፡

የመረጃ ነፃነት ሕጉ ተግባራዊ እንዲሆን መረጃ ሰጪዎች፣ መረጃ ጠያቂዎችና የቅሬታ ሰሚዎች በመረጃ አያያዝ አጠባበቅና አሰጣጥ ላይ መብትና ግዴታቸውን አውቀው ለተግባራዊነቱ እንዲንቀሳቀሱ የግድ ይላል፡፡

በዚህ አጋጣሚ ግልጽ ሊሆን የሚገባው ጉዳይ መረጃ የመጠየቅ፣ የማግኘትና የማስተላለፍ መብት በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆን መንግሥት በቁርጠኝነት እየሠራ መሆኑን ነው፡፡ ለዚህ ነው በፌዴራል የሚገኙ የመንግሥት አካላት የሕዝብ ግንኙነት መዋቅሩ የመረጃ ነፃነት ሕጉን የማስፈጸም አቅሙ እንዲጐለብት የመዋቅር ማሻሻያ በፌዴራል መንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ተቀርጾ ተግባር ላይ እንዲውል እየተደረገ ያለው፡፡

በመሆኑም ማንኛውም ሰው በመንግሥት አካላት ቁጥጥር ሥር ያሉ መረጃዎችን በተቻለ ፍጥነትና በዝቅተኛ ወጪ ሳይደክሙ የሚያገኙበትን የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋትና በተሟላ ሁኔታ ተፈጻሚ እንዲሆን፣ ብሎም የሕዝቡን የሥልጣን ባለቤትነት ለማረጋገጥ እንዲሁም የግልጽነትና ተጠያቂነት ሥርዓት የሰፈነበት አሠራር የማጠናከር ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ የሌሎች አገሮች ተሞክሮ እንደሚያሳየው የመረጃ ነፃነት ሕጉን ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ለማድረግ በርካታ ዓመታትን የሚወስድ ጉዳይ ነው፡፡ በአንፃራዊነት የእኛ በፍጥነት ወደ ትግበራ የገባና የማይናቅ ውጤት በማስመዝገብ ላይ ያለ አዋጅ መሆኑን ጤናማ አመለካከት ያለው ሰው የሚረዳው ጉዳይ ነው፡፡ የሕጉ አፈጻጸም ደግሞ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሥር እየሰደደና እየተሻሻለ መምጣቱ በግልጽ የሚታይ ሲሆን፣ የዜጐች የግንዛቤ ደረጃ እያደገና የኅብረተሰቡ የቆየ የሚስጥራዊነት ባህል እየተሰበረ ሲሄድ የተፈለገው የአፈጻጸም ደረጃ ላይ እንደሚደርስ ይታመናል፡፡ ኅብረተሰቡ መረጃ መጠየቅና የማግኘት መብቱ እንደሆነ እየተረዳ የመጣበት ወቅት ላይ ለመሆኑ ባለፉት ዓመታት የቀረበው የመረጃ ጥያቄ ብዛት በጉልህ የሚያሳይ ነው፡፡

ቅርቃር ውስጥ የገባው መረጃ የማግኘት መብት በማለት ቅሬታቸውን የሰነዘሩት አቶ ዘለዓለም ጉተማም የዚሁ የመረጃ ነፃነት አዋጁ የፈጠረው ግንዛቤ ውጤት መሆናቸው አያጠያይቅም፡፡ ምክንያቱም በቀደሙት ጊዜያት ማለትም የመረጃ ነፃነት ጉዳይ ጨርሶ በማይታሰብበትና ቅርቃር ውስጥ በነበረበት ወቅት፣ ለዚያውም ጋዜጠኞች ብቻ ለመረጃ ጥያቄ የመንግሥትን በሮች በሚያንኳኩበትና መረጃ ለመስጠት የመንግሥት ኃላፊው በጐ ፈቃደኝነትን እንጂ አስገዳጅ ሁኔታ ባልነበረበት ሥርዓት ውስጥ አልፈን፣ ዛሬ ለመረጃ ነፃነት ተቆርቋሪነትና ግምገማ መብቃት ከጤናማ አስተሳሰብ የመነጨ ነው ብለን ከወሰድን፣ የመረጃ ነፃነት ሕጉና የተሰጠው ግንዛቤ የፈጠረው እንጂ ሌላ ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡ ስለሆነም ቅርቃር ውስጥ የነበረው መረጃ የማግኘት መብት ዛሬ ከቅርቃር ውስጥ ወጥቶ በመብቀል ላይ ያለ፣ ለጋና ከሁለንተናዊ ዕድገታችን ጋር ደረጃ በደረጃ አብሮ የሚያድግና ለፍሬ የሚያበቃ መሆኑ በዜጐች ዘንድ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡ 

            

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...