Sunday, June 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርብርቱና ጠንካራ በመሆን መቀጠል የምንችለው ብሔራዊ አንድነታችን ሲጠናከር ነው

ብርቱና ጠንካራ በመሆን መቀጠል የምንችለው ብሔራዊ አንድነታችን ሲጠናከር ነው

ቀን:

በልዑል ዘሩ

ዓባይ ስለሚባለው የአገራችን ታዋቂ ወንዝም ሆነ ‹‹የህዳሴው ግድብ›› ስለሚባለው ግዙፉ ፕሮጀክት፣ በዚሁ በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ የተለያዩ ጽሑፎችን ሳቀርብላችሁ ከርሜያለሁ፡፡ በእርግጥም ጉዳዩ ለኢትዮጵያዊያን ካለው ኢኮኖሚ ፋይዳ በላይ የብሔራዊ መግባባትና የዲሞክራሲያዊ አንድነት መሠረት ከመሆኑ አንፃር ደጋግሞ መነጋገሪያ መሆኑ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ደግሞ ዓባይ (ናይል) ወንዝም ሆነ ይኼው ግድብ ለአገራችን አዲስ የገጽታ ግንባታ አያበረከተ ያለውን አስተዋጽኦ መዳስስ ፈልጊያለሁና ወደዚያው ላምራ፡፡

ናይል ከዓለማችን ረዥሙና ከ6,650 ኪሎ ሜትር በላይ የሚጓዝ በመሆኑ ታዋቂ አልነበረም ሊባል አይችልም፡፡ የወንዙ ፍሰቱም ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛኒያ፣ ብሩንዲ፣ ዴሞክራቲክ ሪፕብሊክ ኮንጎ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ኤርትራና ግብፅን የሚያካትት መሆኑ ብቻ ሳይሆን በቆዳ ስፋት ረገድም 3.5 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር መሸፈኑ ዋነኛው መገለጫው ነው፡፡ ከወንዙ ዓመታዊ ፍሰት ሦስት ገባር ወንዞች የሚነሱት ከኢትዮጵያ ጥቁር ዓባይ ሲሆን፣ 86 በመቶ ውኃና 95 በመቶ ለም አፈር ይዞ መንጎዱ ግን ‹‹እየታወቀ የተዘነጋ›› እውነታ ነበር፡፡

ኢትዮጵያ የወንዙ ዋነኛ ምንጭ ብትሆንም ለዘመናት ከተፈጥሮ ሀብቷ አለመጠቀሟም ሌላውን ዓለም ቅንጣት ያህል የሚያሳስበው አልነበረም፡፡ እነ ግብፅና ሱዳን በቅኝ ግዛት ‹‹ስምምነት›› ከራሳቸው በማይመነጭ ውኃ ባለቤት ሆነው ለዓመታት ሲጠቀሙ ከመኖራቸውም ባሻገር፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የላይኛው ተፋሰስ አገሮች በድርቅና በረሃብ መመታትም የገጽታ ማጠልሻ ሆኖ ከመጠቀሱ በቀር የሌሎች ጭንቀት አልነበረም፡፡ ናይልም እንበለው ዓባይ የዓለም ሕዝብ በተለይም የተፅዕኖ ፈጣሪው መገናኛ ብዙኃን ትኩረትን የሳበው ከመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም. ወዲህ ነበር፡፡ ይኼውም የኢትዮጵያ መንግሥት በዓባይ ወንዝ ላይ 6,000 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚያመነጭ የአፍሪካ ግዙፍ ግድብ ሊገነባ በመሆኑ ነው፡፡ እዚህ ላይ ቀድሞ የተሠራው የናይል ተፋሰስ አገሮች (NBI) ውይይትም ሆነ የናይል የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት (Cooperative Framework Agreement) የተካሄደበት ሒደትና ያሳለፈው ውሳኔ ብዙም ትኩረት እንዳልሳበ መገመት ይቻላል፡፡ በተለይ ግብፅና ሱዳን ስምምነቱን በባለመቀበላቸው ሒደቱ ከተለመደው ግንዘቤ አልፎ ከክርክር ያለፈ እንዳልነበረ ትንታኔ የሰጡ ብዙዎች ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያ ወደ ተግባር መግባትና ያንን ተከትሎ በርከት ያሉት የተፋሰሱ አገሮች የስምምነቱ ማዕቀፉን በየምክር ቤቶቻቸው ማፅደቅ መጀመራቸው ግን አጀንዳውን ለኮሰው፡፡

አጀንዳው በየመገናኛ ብዙኃኑ እየተጋጋመ የመጣው ደግሞ በኢትዮጵያ በኩል ‹‹በተፈጥሮ ሀብታችን ምክንያታዊና ፍትሐዊ በሆነ አግባብ የመጠቀም መብታችን ዕውን ይሆናል›› የሚል ፅኑ አቋም በመያዙ ነው፡፡ በተቃኒው የግብፅ መሪዎች ታላቋ ብሪታኒያ ፍሰቱን ለመቆጣጠር ያደረገችውን እ.ኤ.ኤ. 1906፣ 1929 እና 1959 የቅኝ ግዛት ስምምነት ሕጋዊ የማድረግ ሙከራ እየተካረረ በመስተዋሉ ነበር፡፡

ግብፃዊያን ለዘመናት የውስጥ ትኩሳታቸውን የሚያበርዱ የናይል ፖለቲካ መሆኑ ቢታወቅም፣ በውስጥ የአብዮት ትኩሳት በታመሱበት ባለፉት አራት ዓመታት ውስጥም ከዚሁ አስተሳሰብ አልተነጠሉም ነበር፡፡ እ.ኤ.እ. በ2008 የናይል ቢዚን ኢንሼቲቭ የአራት ዓመት ዕቅድን በመተግበር የኃይል ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽን (NRBC) ለመሸጋገር የተደረገውን ጥረትም ወደ መዘንጋት ገብተዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ስምምነቱ በተወሰኑ አገሮች ከተፈረመ በኋላ ሒደቱ ወደፊት እንዳይቀጥል ለማደናቀፍ ብዙ ጥረቶች አድርገዋል፡፡

በኢትዮጵያ በኩል በተፈጥሮ ሀብቷ ለመጠቀም የተጀመረው ጥረትም ከፍተኛ ዘመቻ ተካሂዶበታል፡፡ ከብድር ክልከላ አንስቶ፣ የተለያዩ አገሮች በአማላጅነትና በተፅዕኖ እንዲገቡበት ለማድረግ፣ እንዲሁም በፕሮፓጋንዳና በሥነ ልቦና ጦርነት ለማስፈራራት (የመሐመድ ሙርሲን ሁኔታ ያስታውሷል) ተሞክሯል፡፡ እነዚህ ውዝግቦች ታዲያ ዓባይና ታላቋ የህዳሴ ግድብ አጀንዳነታቸው ተጠናክሮ ቀጠለ፡፡

የኢትዮጵያ ገጽታም በሌላ አዲስ ግድል እየደመቀ መጣ፡፡ በተለይ የአገሪቱ በግድቡ ግንባታ ሒደት ላይ ለአንድም ደቂቃ ላለማቆም የተያዘው አቋም፣ ሕዝቡ በስፋት ያሳየው ተሳትፎና ኅብረት እንደ ሱዳን ያሉ አገሮች የግድቡን ግንባታ መቀበላቸው በስፋት ተዘገበ፡፡ ከሁሉም በላይ በቢሊዮን ዶላሮች የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ተግባራዊ መደረጉ መነጋገርያ ሆነ፡፡

ፕሮጀክቱ አገሪቱ ያላትን የኃይል ዕምቅ ምንጭ ያሳየና የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ተምሳሌት ሆኖ መምጣቱም፣ በአገር ደረጃ ለዓመታት ሲቀነቀን በቆየው ሀቅ ላይ የተመሠረተ ሆነ፡፡

እነ አልጄዚራ፣ ፕሬስ ቲቪ፣ ቢቢሲና ሲሲቲቪ በአንድ ወገን የግብፅና የኢትዮጵያ ፍጥጫን፣ በሌላ በኩል የፕሮጀክቱን ትልቅነትና ዘርፈ ብዙ ፋይዳ ከኢትዮጵያ የማደግ ተስፋ ጋር አሰናስለው በዶክመንተሪ መልክ ሳይቀር ተረኩ፡፡ እንደ ሱዳን ትሪቡን፣ አልሃራም ኦንላይን፣ ዶቼቬሌ ኦንላይን (ሬዲዮ)፣ የቪኦኤ ኦንላይን (ሬዲዮ) የአሜሪካው ናሽናል ፐብሊክ ሬዲዮና ድረ ገጽ፣ እንዲሁም ታዋቂ የዓለም ሚዲያዎች እንደ ዘገባቸው ዕይታቸው ጉዳዩን ማስተጋባት ቀጠሉበት፡፡

ባሳለፍነው ወርና ከቅርብ ሳምንታት ወዲህም ናይል (ዓባይ) የመገናኛ ብዙኃኑ ትኩረትነቱ በሌላ ገጽታ ተመልሶ መጥቷል፡፡ የኢትዮጵያችን ገጽታም በዓባይ ከመድመቁ በላይ የአሸናፊነት ካባን እየተላበሰ ነው፡፡ አሁን ዋነኛ የአትኩሮት ማዕከላቻው ውዝግብና ፍጥጫ አይደለም፡፡ የአሸናፊና የተሸናፊ ንትርክም ሊሆን አይችልም፡፡ ይልቁንም በታዳጊው ዓለም ብዙም በአጭር ጊዜ ይፈጸማል የማይባለው ስምምነትና መቀራረብ ሆኗል፡፡

‹‹አንዳንዶች ግብፅ ተጎድታለች፣ ኢትዮጵያ ህልሟን አሳክታለች፤›› ቢሉም፣ ሌሎችም ዳግሞ ግብፅ ዘላቂ የናይል ጥቅሟን አስጠብቃለች፣ ኢትዮጵያም ከቀደመው የከረረ አቋሟ ለዘብ ብላ መስማማትን መርጣለች በማለት ቢደመድሙም፣ በብዙ መሥፈርት ሦስቱም አሸናፊ የሆኑበት (ሱዳንን ጨምሮ) መቀራረብ ተፈጥሯል፡፡

ከሳምንታት በፊት ‹‹የስምምነት መርሆ አንዳንድ ተጠየቆች›› በሚል ርዕስ ባቀረብኩት ጽሑፍ በግል ዕምነቴ የተሰማኝን ክፍተት ብዳስስም፣ አሁንም የሁሉም ድል የተባለው ስምምነት የዓለም ትኩረት ሆኗል ማለት ይቻላል፡፡

አንዳንዶቹን ለመጠቃቀስ ያህል ዴይሊ ኒውስ የተባለው ታዋቂ የጉዳዩን ተንታኝ ላስቀድም፡፡ ዘገባው የሦስቱን አገሮች የስምምነቱ ማዕቀፍ አብራርቶ ከ30 ዓመታት በኋላ የግብፅ ፕሬዚዳንት ኢትዮጵያን በኦፊሴላዊ ጉብኝት ማየቱን አድንቋል፡፡ በተለይ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ በኢትዮጵያ ፓርላማ ተገኝተው የተናገሩት ቁም ነገር በግልጽ መቀራረብን ያመላከተ እንደሆነ አትቷል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያዊያን ግብፃዊያንን መጠራጠር የለባቸውም፡፡ ሁላችንም በጋራ የምንጠቀምበትን ሥርዓት ማበጀት የምንሻ፣ በሰላምም ሆነ በልማት መደጋገፍን የመረጥን ነን፤›› ማለታቸው፣ ኢትዮጵያዊያን በሐሳብም ሆነ አመለካከት ከመከፋፈል አንድነትና ኅብረትን መምረጥ እንዳለባቸው መክረዋል ብሏል፡፡

የናይል ውኃ የጋራ ተጠቃሚነት ማዕቀፍ ላይ ግብፅ፣ ኢትዮጵያና ሱዳን የፈረሙት የመጀመሪያው ስምምነት ዋሽንግተንን ያስደሰታት መሆኑን የዘገበውና ከዚያም ወዲህ ገንቢ አስተያየቶችን እያስተናገደ ያለው ሌላው ድረ ገጽ ደግሞ ‹‹ኢጂፕት ኢንዲፐንዴንት›› ነው፡፡ በተለይ የአሜሪካው ስቴት ዲፓርትመንት ቃል አቀባይ ጄን ሳኪን ጠቅሶ እንደገለጸው፣ አሜሪካ ስምምነቱን ይበልጥ ለማጠናከር ከአገሮቹ ጋር እንደምትሠራ መግለጿንና የዓባይ ልማት ለሁሉም የተፋሰሱ አገሮች ጥቅም እንዲውል መመኘቷን አስረድተዋል፡፡ ይኼ እውነት በዲፕሎማሲያዊም ሆነ በኢኮኖሚያዊ ትርፍ ሲታይ ለኢትዮጵያ ትልቅ ድል ተደርጎም ይወሰዳል፡፡

‹‹ዘ ኒው ታይምስ ኦፍ ኪጋሊ›› በጻፈው ርዕሰ አንቀጽ ደግሞ የሦስት አገሮች መሪዎች የተፈራረሙት ኢትዮጵያ በ4.2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በሆነ ወጪ ለመገንባት የጀመረችውን ግድብ ለማቀላጠፍ እንደሚያግዝ ተንትኗል፡፡ ስምምነቱ በሦስቱ አገሮች ብቻ የተወደደ ሳይሆን፣ የናይልን ውኃ የሚጋራ አገሮችን ሁሉ የሚያስደስትና ብዙዎቹ ለሕዝባቸው ለሚሠሩት ፕሮጀክቶች በር የሚከፍት ነው ብሎታል፡፡

የአሜሪካው ናሽናል ፐብሊክ ሬዲዮ ድረ ገጽ (NPR News) እ.ኤ.አ. ማርች 26 2015 ይዞት የወጣው ዘገባም ለጉዳዩ ትኩረት የነፈገ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ በታሪክ ውስጥ እንደ አንድ የጀግንነት ገድል በመሆን ተመዝግቦ እንዲቀመጥ ፍላጎት አላት ብሏል፡፡

ግድቡ ሲጠናቀቅ በአፍሪካ ትልቁ የኤሌክትሪክ ማመንጫ ፕሮጀክት እንደሆነ አትቷል፡፡ ከሰው ሠራሹ ሐይቅ አንፃር ግን ከአስዋን ግድብ የናስር ሐይቅ በግማሽ ያነሰ ብሎታል፡፡ ከዚህም በላይ ኢትዮጵያ ከአሜሪካም ሆነ ከምዕራበ አገሮች አንዳች ዕርዳታ ሳታገኝ እየተገነባ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ግድብ ‹‹ህዳሴ›› የተባለው አፍሪካ በራስዋ አቅምና ተዝቆ በማያልቀው ሀብቷ ማደግ አንደምትችል የ70 ዓመት ራዕይዋን ያደሰ ነው በማለት አኅጉራዊ አንድምታ አላብሶ ተንትኖታል፡፡ የጨለማው አኅጉር እየተባለ በሚጠራው ምድር በነፃነትና በራስ መተማመን በኤሌክትሪክ ኃይል መስክ ይበልጥ እውን ሊሆን መሆኑን ከረዥምና ብሩህ ተስፋ አስደግፎ አስቀምጦታል፡፡

ትንተናው በአሜሪካ የኦሪገን ስቴት ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ ፕሮፌሰርና በውኃ ምክንያት የሚነሱ ግጭቶች ላይ ታዋቂ አደራዳሪ የሆኑት አሮን ዎልፍን ሐሳብ አካቷል፡፡ የግድቡ ውኃ ማጠራቀሚያ አንድ ጊዜ ከሞላ በኋላ ግድቡ በግብፅ ላይ ምንም የሚያደርሰው ተፅዕኖ እንደሌለው ማስገንዘባቸው፣ ለአገራችን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እንደተጨማሪ ድል ይቆጠራል፡፡

የመርሆ ስምምነቱን በአንፃራዊነት በበጎ ያልተመለከተው (ከኢትዮጵያ አንፃር) አልሃራም ኦንላይን ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ ሚዲያ በተለይ ባለፉት ሦስት ዓመታት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሲያዥጎደጉዳቸው ከከረሙት ፀረ ዓባይ ልማትና የኢትዮጵያ እንቅስቃሴ አንፃር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መሻሻል አሳይቶ ነበር፡፡ ከሰሞኑ ግን አደናጋሪ የሚመሰል ሐሳብ አንሸራሽሯል፡፡

‹‹ግብፅ የህዳሴው ግድብ ግንባታን በመርህ ደረጃ ዕውቅና እንዳልሰጠችው›› ጠቅሷል፡፡ አንዳንድ የአገራቸው ኤክስፐርቶች ግብፅ የኢትዮጵያን የህዳሴ ግድብ አስመልክቶ ከኢትዮጵያና ከሱዳን ጋር ያደረገችው ስምምነት የዓባይን ውኃ በእኩልነት የመካፈል ዕድልዋን እንደገደበባት መግለጻቸውንም ምንጭ አጣቅሶ አስነብቧል፡፡ በዚህ ላይ የግድቡን ሕጋዊነት ለመቀበል አስቸጋሪ እንደሆነ ከከፍተኛ ባለሥልጣኑ መካከል የመስኖ ሚኒስቴርና መሥሪያ ቤቱን በመጥቀስ፣ በተለይ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የዓባይ ውኃ ሀብት ክፍፍል ዋና ኃላፊ አህመድ በሐኤልዲን የስምምነቱ አጠቃላይ ይዘት ግድቡ የሚይዘውን የውኃ መጠን ወይም በዓባይ ውኃ ላይ ግብፅ ላላት አጠቃላይ ዕውቅና መስጠትዋን የሚያረጋግጥ አይደለም ማለታቸው ተወስቷል፡፡

በእርግጥ ‹‹ዴይሊ ኒውስ ኢጂፕት›› የተባለው የካይሮ ታዋቂ ድረ ገጽ የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ የኢትዮ-ግብፅ ትብብር በአፍሪካ አገሮች የመልካም ግንኙት ተምሳሌት ከመሆኑ ባሻገር በታላቁ ህዳሴ ግድብ ትግበራ ላይ ለመነጋገር መሠረት የሚጥል ነው ማለታቸውን ዘግቧል፡፡ በዚህም ከውዝግብና ከንትርክ ይልቅ ሰላማዊ መነጋገርን የሚፈጥር፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ላይ የተመሠረተና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው ማለቱ የአልሃራም ኦንላይንን ሐሳብ እንዳጣጣለ መገንዘብ ይቻላል፡፡

የሦስት አገሮችን የመርሆ ስምምነት ተከትሎ አልጄዚራ ቴሌቪዥን ረዥም ጊዜ ሰጥቶ ያወያየው የቀጥታ ሥርጭት ይጠቀሳል፡፡ ከአሜሪካ፣ ከግብፅና ከኢትዮጵያ የውኃ ፖለቲካ ተንታኞችን በማሳተፍ ሰፊና ገንቢ የሚባል ሽፋን ለጉዳዩ ሰጥቶታል፡፡ ‹‹ግብፅ፣ ሱዳንና ኢትዮጵያ ካልተገባ ውዝግብ ወጥተው በናይል ውኃ በጋራ ለመጠቀም ተስማሙ›› በሚል መሪ ሐሳብ ስለግብፅ እንኳን በጎ መዘገብ የተወው አልጄዚራ የስምምነቱን ፍሬ ነገር በምሑራን አንደበት አስረግጧል፡፡ በተመሳሳይ እነቢቢሲ፣ ሲኤንኤንና ሲሲቲቪ የስምምነቱን የፊርማ ሥርዓትም ሆነ የግብፅ ፕሬዚዳንት የኢትዮጵያ ጉብኝት በቂ በሚባል ደረጃ የዜና ሽፋን ሰጥተውታል፡፡ በተለይ የቢቢሲው ‹‹አፍሪካ ፎከስ›› ፕሮግራም ዳሰሳ የአገራችን ገጽታ ይበልጥ የገነባና የማንመለስበት ጠንካራ ዕርምጃ ወስጥ መገኘታችንን ያረጋገጠ ነበር፡፡

የግብፅ፣ የሱዳንም ሆነ የኢትዮጵያ የግልና የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሽፋን በድምሩ ሲታይ የመርሆ ስምምነቱን በበጎ የወሰደ ነው፡፡ ምንም እንኳን በአገራችን ያለው የግል ሚዲያ መዳከምና አሁንም አንዳንዱ በጎ ሁነትን የመዘገብ ውስንነት ባለመቀረፉ ሽፋኑ እንደሌሎቹ አገሮች ጎልቶ ባይታይም፣ የተለያዩ ዕውቅናን ያተረፉ ጋዜጦች፣ ብሎጎችና ማኅበራዊ ሚዲያዎች ድርሻም የሚናቅ አይደለም፡፡ ጉዳዮ የማኅበራዊ ድረ ገጽ የትኩረት ንጥብ ሆኖ መሰንበቱም ሲታይ ታላቁ የህዳሴ ግድብ የገጽታ ግንባታውም ሆነ የብሔራዊ መግባባት ሒደቱ ፈርጥ ሆኗል ለማለት ያስደፍራል፡፡

የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይና ብሔራዊ ደኅንነት ፖሊሲ ዋነኛ ማጠንጠኛና ራዕይ ያደገች ዲሞክራሲያዊ አገር ለመገንባት ምቹ አካባቢ መፍጠር የሚል ነው፡፡ ይኼን ለማድረግ ዓለም አቀፍ ሕግጋትና ስምምነቶችን መሠረት ያደረጉ ፕሮጀክቶችን መተግበርና ልማቱን ማፋጠን የግድ ነው፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን አገራችን በሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው የጠለሸ ስም እንዳይኖራትና መደነቃቀፍ እንዳይፈጠር መትጋት ያስፈልጋል፡፡

ታላቅ ግድብም ሠራን፣ ሰፊ የነዳጅ ሀብት ወጣ፣ ወይም የባቡርና የመንገድ ልማት አከናወንን፣ እንደ አገር ብርቱና ጠንካራ በመሆን መቀጠል የምንችለው ብሔራዊ አንድነታችን ይበልጥ ሲጠነክር ነው፡፡ አንድነታችንም ንፋስ የማይወዘውዘውና ዜጎች የሚከበሩና የሚዋሀዱ ሲሆን ነው፡፡ በዚህ ረገድ በውስጥ የሚቀሩን የቤት ሥራዎች እንዳሉ መዘንጋት የለበትም፡፡ በተለይ በጠባብነት መንፈስ የብሔር ባንዲራን ብቻ በማውለብለብ ትልቁን የኢትዮጵያን ምሥል ደጋግሞ መዘንጋት ዋጋ ያስከፍላል፡፡ እኔ ብቻ ዋነኛ መሪ ካልሆንኩ ማለትም ጅልነት ነው፡፡

በአጠቃላይ ዓባይ አዲስ የኢትዮጵያ ገጽታ መዘውር ሆኗል፡፡ ይኼን መልካም ተስፋ ይበልጥ በማሳደግ አገራችን ከድህነት እንድትወጣም ሆነ ገጽታችን ይበልጥ እንዲፈካ ሁላችንም ትኩረት እንስጥ ለማለት እወዳለሁ፡፡ ይህ ጥረትም በብሔራዊ መግባባት ይጠናከር፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...