Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

ሰኞ ግንቦት 10 ቀን 2007 ዓ.ም. ከየመን የተመለሱ ኢትዮጵያውያን ቁጥር 260 ነው

ትኩስ ፅሁፎች

ባለ አደራ

የገደል ማሚቶ መጣች፣

በዘመን ጭራ ታስራ፡፡

የአእላፍ ሙታን ድምፅ፣

      ቋጥራ፡፡

      አደራ፡፡

ሕዝብ ፊት ቀርባ ጮኸች፣

አገልግሏን ከፍታ ተማፀነች፣

‹‹ታከተኝ – ተቀበሉኝ፣›› አለች፡፡

ግማሾቹ የቻሉትን ወሰዱላት፣

ያልቻሉትን መለሱላት፡፡

ሌሎቹ ሌላ ነገር አኖሩላት፣

ካንቺ ሌላ ሌላ አናምንም እያሏት፡፡

– ደበበ ሰይፉ “ለራስ የተጻፈ ደብዳቤ” (1992)

                        *******

አሁን አርጅቻለሁ

እኔ ሽማግሌ ውሻ ነኝና የምጠቅም አይደለሁም፡፡ ቢሆንም ገና ጎበዝ ሳለሁ ከሙሉ ልቤ እንዳገለገልሁት ያውቃልና ጌታዬ ይወደኛል፡፡

ጌታዬ ገና ጎበዝ ልጅ ሳለ አብረን በመስኩ ላይ እንደምንጫወት በሜዳውም ላይ ብዙ እሽቅድምድም እናደርግ እንደ ነበርን አውቃለሁ፡፡ ሁልጊዜ ያዝንልኝ ነበር እንጂ ከቶ አይመታኝም ነበር፡፡ ጌታዬ ይፈልገው የነበረውን ሁሉ ለማድረግ የተዘጋጀሁ ነኝና መመታት እንደማይገባኝ እርሱ ያውቃል፡፡

ማናቸውንም ነገር ባስተማረኝ ጊዜ ያቅሜን ያህል ለማወቅ ተጣጣርሁ፡፡ ጌታዬ ሊያደርገው፣ ከኔ የሚፈልገውን እንደምችለው ያህል ሞከርሁ፡፡ አንድ ጊዜም ካወቅሁ በኋላ ከቶ አልረሳውም፡፡ ከርሱ ጋራም ወደ ተማሪ ቤት እሄድና በሩጫ ወደ ቤት እመለሳለሁ፡፡ አሁን እርሱ ትልቅ ልጅ ሆኗል፡፡ ነገር ግን ሲመጣ ባየሁት ጊዜ እንዴት ሩጨ እንደምቀበለው ያውቃል ለማለት እደፍራለሁ፡፡

በርሱ ፈንታም እንድሸከም አንዳንድ ጊዜ የመጽሐፉን ኮሮጆ ይሰጠኛል፣ መንገዱንም ሁሉ በጥንቃቄ ተሸክሜ በጎን በጎኑ ስሄድ እጅግ እኮራለሁ፡፡ ለጌታዬ ለወልደ ጊዮርጊስ፣ ተስፋዬ የምትባል እህት ነበረችው፡፡ አንድ ቀን በሳሩ ላይ ተቀምጣ በእጅዋ ብስኩት ይዛ ነበረ፡፡ አንድ ራብተኛ ውሻ አያትና የያዘችውን ብስኩት ለመንጠቅ ወደርሷ እየሮጠ መጣ፡፡ በተስፋዬ አቅራቢያ ከቁጥቋጦው በኋላ ተጋድሜ ነበርና እንግዳው ውሻ ሲመጣ ባየሁት ጊዜ እርሷን ለማስጣል ዘለልሁ፡፡

ወደ ተስፋዬም በረረና ብስኩቱን ለመንጠቅ ሞከረ፣ ግን አንገቱን ይዤ ጎተትሁት፡፡ በብርቱም ታገልን በመጨረሻውም አሸነፍሁት፡፡ በተስፋዬም ጩኸት እናቲቱ ፈጥና መጣች፡፡ ትንሽቱንም ልጅዋን ከጉዳት እንዳዳንኋት ባየች ጊዜ በጣም ደስ አላት፡፡

ጌታዬ ወልደ ጊዮርጊስ ከተማሪ ቤት በተመለሰ ጊዜ የነገሩን ሁኔታ ነገረችውና ከድሮው ይልቅ አብልጦ ወደደኝ ከዚህ ቀን ጀምሮ ከጌታዬ ጋራ ብዙ የደስታ ዓመት ነበረኝ፡፡ ነገር ግን እኔ እንግዲህ ሽማግሌ ነኝና አደርገው እንደነበረ ላገለግለው አልችልም፡፡ ለወልደ ጊዮርጊስ የኔ ሥዕል አለው፡፡ በቤቱም ክፍል ተንጠልጥሏል ጎበዝ በነበርሁ ጊዜ እንደ ምን እታይ እንደ ነበርከሁ ያን ጊዜ አይተኸኝ እንኳ ብትሆን ዛሬ አታውቀኝም፡፡

እንደዚህ ያለ ጌታ ስለነበረኝ ላመሰግን ይገባኛል፡፡ የኔን ጌታ የሚመስሉ ብዙ ጌቶች ቢኖሩ መልካም ነበር፡፡ እንደኔ ያለ ሽማግሌ የታመነ አገልጋይ ምንም እንኳ ውሻ ቢሆን ከቶ አይረሳም፡፡

በሬ የገዛውን ዐወቀ አህያም የጌታውን ጋጥ፡፡

እስራኤል ግን አላወቀም ሕዝቤም አላስተዋለም፡፡

  • ከበደ ሚካኤል “ታሪክና ምሳሌ” (1999)                      

 

*******

የማግለል ቅጣት በኾንሶ

በኾንሶ ብሔረሰብ የባህል ሕግ ውስጥ የተለያዩ የቅጣት አይነቶች አሉ፡፡ የገንዘብ፣ የአይነት፣ የጉልበት፣ የግርፋትና የማግለል ቅጣቶች የሚጠቀሱም ናቸው፡፡

በኾንሶ የማግለል ቅጣት የሚጣለው የማኅበረሰቡን እሴቶችና ውሳኔዎች የማይቀበል ሰው ከማኅበረሰቡ ማግኘት የሚገባውንና የሚችለውን ጥቅምና አገልግሎት እንዳያገኝ በማድረግ ነው፡፡ ሰላምታን ከመንፈግ ጀምሮ እሳት እንዳይሰጠው፣ ችግሮች ቢደርሱበት እርዳታና እገዛ እንዳይደረግለት ይደረጋል፡፡ የኼላው (ኼላ ማለት በየዘጠኝ ዓመቱ የሥልጣን ሽግግር የሚካሄድበት የወጣቱ ትውልድ የቡድን ስም ነው) መሪዎች ይህንን የማግለል ቅጣት በመቆጣጠር ተግባራዊ ያደርጉታል፡፡ ጥፋተኛ የተባለው ሰው ተጸጽቶ ሲመለስም የመቅጣትና የማንጻት ሥነ ሥርዓት ተካሂዶለት ወደ መደበኛው የማኅበረሰቡ ሕይወት ሊመለስ ይችላል፡፡

የማግለል ቅጣቱ በኻውዳ (የተለያዩ ሥራዎችን የሚሠሩ ሰዎች ወይም ነጋዴዎች) ሥርዓቱም ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን ማናቸውም ግብይቶች ከሱ ጋር እንዳይደረጉ፣ ንግድ መንገድ እንዳይችል፣ መስመር ላይ ችግር ቢደርስበት እርዳታና እገዛ እንዳይሰጠው ለነጋዴው ክፍል መልዕክቱ ተላልፎ ክልከላ ይጣልበታል፡፡ ‹‹የእገሌን ንብረት ወስዶ አልሰጥም በማለቱ በመካዱ (የተረጋገጠ ከሆነ) የማይገባ ተግባር ስለፈጸመ የንግድ ማኅበረሰቡን በድሏል፣ አጭበርብሯል ተብሎ ውሳኔው ይጣልበታል፡፡ የአንድን ሰው ንብረት አላግባብ ከወሰደ የአጠቃላይ የነጋዴውን ማኅበረሰብ ንብረት እንደወሰደ ይቆጠርበታል፡፡ ነገ በሁሉም ላይ ተመሳሳዩን ተግባር ሊፈጽም እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ፡፡ ይህ ሰው በሥራው ተጸጽቶ ሲመለስ ደግሞ ቅጣትና ከእርክሰቱ የማንጻት ሥራ ተሠርቶለት ከነጋዴው ማኅበረሰብ ጋር እንዲቀላቀል ይደረጋል፡፡ የተቀጣውም ቅጣት በየደረጃው ለሚገኙ የኻውዳው መሪዎች መከፋፈልና መድረስ ይኖርበታል፡፡ ይህ የሚሆነው ቅጣቱ ብዙና የሚጠቅም ሆኖ ሳይሆን አንድ ብር፣ ሃምሳ ሳንቲምም ትሁን ሊደርሰው ይገባል በሚል መንፈስ ነው፡፡ ዋናው ጉዳይ ከቅጣቱ የሚገኘው ብር ሳይሆን ጉዳዩ በየደረጃው መሰማትና ባለድርሻ አካላት የሚገባቸውን ዕውቅና ከመስጠት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምክንያቱም ቅጣቱን ተግባራዊ የሚያደርጉት በየደረጃው የሚገኙት አካላት ናቸውና ነው፡፡

  • አብዱልፈታህ አብደላህ “ሴራ አታ ኾንሶ” (2006)

*******

የውኃ ውስጥ ‹‹ባር›› በሜክሲኮ

በዓለም የመጀመሪያ የሆነው የውኃ ውስጥ ባር በሜክሲኮ ኮዙሜል ደሴት ሥራ መጀመሩን ዘ ቴሌግራፍ ዘግቧል፡፡ ተገልጋዮች ወደ ባሩ ሲመጡ በቤት ውስጥ እንደሚሰጠው አገልግሎት የሚቀመጡበትን ቦታ ቀድመው ማስያዝ አይጠበቅባቸውም፡፡ ይልቁንም ከ59 ሺህ ጋሎን በላይ ውኃ እንዲያቁር ተደርጎ በተሰራው ቤት መሳይ ገንዳ ውስጥ ለመግባት ለሚያስፈልጋቸው ኦክስጅን የሚያስተላልፍ ሄልሜት መክፈል ብቻ ነው፡፡ በውኃ ውስጥ የሚስተናገዱ ሰዎች የሚያገኙት ኦክስጅን በመልካም መዓዛ (በሽቶ) የተቃኘም ነው፡፡  

እንደ ዘገባው ከሆነ፣ ተገልጋዮች በውኃ ውስጥ በተሠራው ባር የተለያዩ ስፖርታዊ ጨዋታዎችን ማድረግ ይችላሉ፡፡ የታሸጉ ትኩስና ቀዝቃዛ መጠጦችንም ይጠቀማሉ፡፡

- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች